ወደ አምላክ ቅረብ
‘የአምላኩን በጎነት ፈለገ’
ከልጅነቱ ጀምሮ የተማረውን የአምላክ የጽድቅ መሥፈርት ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ የነበረ አንድ ሰው “ፈጽሞ እንደማልረባ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። ሕይወቱን ለማስተካከል እርምጃ መውሰድ ሲጀምር አምላክ ፈጽሞ ይቅር አይለኝም የሚል ፍርሃት አድሮበት ነበር። ይሁንና ከኃጢአቱ ንስሐ የገባው ይህ ግለሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 2 ዜና መዋዕል 33:1-17 ላይ ከሚገኘው የምናሴ ታሪክ ማጽናኛ ማግኘት ችሏል። አንተም ከዚህ በፊት በፈጸምካቸው ኃጢአቶች ምክንያት ምንም የማትጠቅም እንደሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ከምናሴ ተሞክሮ ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ።
ምናሴ ያደገው ፈሪሃ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቱ ሕዝቅያስ ጥሩ ከሆኑ የይሁዳ ነገሥታት መካከል አንዱ ነበር። ምናሴ የተወለደው አምላክ የአባቱ ሕይወት ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲራዘም ካደረገ ከሦስት ዓመት በኋላ ነበር። (2 ነገሥት 20:1-11) ሕዝቅያስ ይህን ልጅ በአምላክ ምሕረት የተገኘ ስጦታ አድርጎ እንደተመለከተውና ለንጹሑ አምልኮ ፍቅር እንዲኖረው አድርጎ ለማሳደግ የተቻለውን ያህል እንደጣረ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ፈሪሃ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች በሙሉ የወላጆቻቸውን ፈለግ ይከተላሉ ማለት አይደለም። የምናሴ ሁኔታ ይህን ሐቅ ያረጋግጣል።
ምናሴ አባቱን በሞት ሲያጣ ዕድሜው ከ12 ዓመት አይበልጥም ነበር። የሚያሳዝነው ምናሴ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።” (ቁጥር 1, 2) ለእውነተኛው አምልኮ ምንም ደንታ ያልነበራቸው አማካሪዎች በወጣቱ ንጉሥ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድረውበት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይልም። ከዚህ ይልቅ ምናሴ በጣዖት አምልኮ ውስጥ እንደተዘፈቀና በርካታ የጭካኔ ድርጊቶችን እንደፈጸመ የአምላክ ቃል ይናገራል። ምናሴ ለሐሰት አማልክት መሠዊያዎችን ሠርቷል፣ የገዛ ልጆቹን ሠውቷል፣ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል እንዲሁም በኢየሩሳሌም ባለው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የአሼራ ምስሎችን አቁሟል። አንገተ ደንዳና የነበረው ምናሴ የአባቱን ሕይወት በተአምራዊ ሁኔታ በማራዘም እሱ እንዲወለድ አጋጣሚ የፈጠረው ይሖዋ አምላክ፣ በተደጋጋሚ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት አሻፈረኝ ብሏል።—ቁጥር 3-10
በመጨረሻም ይሖዋ፣ ምናሴ በሰንሰለት ታስሮ ወደ ባቢሎን እንዲወሰድ ፈቀደ። ምናሴ በግዞት እያለ ከዚያ ቀደም ያሳለፈውን ሕይወት መለስ ብሎ እንዲያስብ የሚያስችለውን አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ያመልካቸው የነበሩት አቅመ ቢስና በድን የሆኑ ጣዖታት እሱን መጠበቅ እንዳልቻሉ ተገንዝቦ ይሆን? ፈሪሃ አምላክ የነበረው አባቱ ልጅ ሳለ ያስተማረውን ነገሮች መልስ ብሎ አስታውሶ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የምናሴ ልብ ተለውጧል። ዘገባው “የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ . . . ራሱን እጅግ አዋረደ። ወደ እርሱም [ጸለየ]” ይላል። (ቁጥር 12, 13) ይሁንና አምላክ እንዲህ ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን የፈጸመን ሰው ይቅር ሊል ይችላል?
ምናሴ ልባዊ ንስሐ በመግባቱ ይሖዋ በጣም ተደሰተ። በመሆኑም ምሕረት ለማግኘት ያቀረበውን ልመና ሰምቶ “ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው።” (ቁጥር 13) ምናሴ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት ሲል የጣዖት አምልኮን ከይሁዳ በማስወገድና ሕዝቡ “እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ” በማሳሰብ ስህተቱን ለማረም የተቻለውን አድርጓል።—ቁጥር 15-17
አንተም ከዚህ በፊት በፈጸምካቸው ኃጢአቶች የተነሳ የአምላክን ይቅርታ ማግኘት እንደማትችል ከተሰማህ ከምናሴ ተሞክሮ ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ። አምላክ ስለ ምናሴ የሚናገረውን ዘገባ በመንፈሱ መሪነት በቃሉ ውስጥ እንዲካተት አድርጓል። (ሮም 15:4) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ “ይቅር ባይ” አምላክ መሆኑን እንድናውቅ ይፈልጋል። (መዝሙር 86:5) ይሖዋ ትኩረት የሚያደርገው አንድ ሰው በፈጸመው ኃጢአት ላይ ሳይሆን በግለሰቡ የልብ ዝንባሌ ላይ ነው። ኃጢአት የፈጸመ አንድ ሰው ከልብ መጸጸቱን በጸሎት ከገለጸ፣ መጥፎ አካሄዱን እርግፍ አድርጎ ከተወና ትክክል የሆነውን ለማድረግ ከልቡ የሚጥር ከሆነ እንደ ምናሴ ‘የአምላክን በጎነት’ ሊያገኝ ይችላል።—ኢሳይያስ 1:18፤ 55:6, 7
በጥር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
◼ ከ2 ዜና መዋዕል 29 እስከ ዕዝራ 10