ይህን ያውቁ ኖሯል?
በጥንት ዘመን ሰዎች በዘፀአት መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰውን “ቀይ ማግ” የሚሠሩት እንዴት ነበር?
▪ በጥንቷ እስራኤል የአምልኮ ማዕከል በሆነው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ እንደ ግድግዳና መግቢያ የሚያገለግለው መጋረጃ “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና . . . በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፀአት 26:1፤ 38:18) ለካህናቱ የተዘጋጁት ‘የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችም’ ቢሆን ‘ከቀይ ማግ’ መሠራት ነበረባቸው።—ዘፀአት 28:1-6
ቀዩ ማግ የሚሠራበት ቀለም የሚገኘው ኮክሲዴ ከተባለው የነፍሳት ዝርያ ነበር፤ ቀለሙ የሚወሰደው ከእንስት ነፍሳት ነው። እነዚህ ክንፍ አልባ ነፍሳት የሚኖሩት በአብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅና በሜድትራንያን የባሕር ዳርቻ በሚበቅሉ የኦክ ዛፎች (ክዌርከስ ኮክሲፌራ) ላይ ነው። ቀዩ ቀለም የሚገኘው በእንስቷ ነፍሳት እንቁላል ውስጥ ነው። ይህች ነፍሳት እንቁላሏ በሰውነቷ ውስጥ እያለ ስትታይ ቅርጿና መጠኗ የአተር ፍሬ የሚመስል ሲሆን በኦክ ዛፍ ቅርንጫፍና ቅጠል ላይ ትጣበቃለች። ነፍሳቱ በእጅ ተለቅመው ከተጨፈለቁ በኋላ በውኃ የሚሟሟና ልብስ ለማቅለም የሚረዳ ደማቅ ቀይ ቀለም ያስገኛሉ። ትልቁ ፕሊኒ የተባለው የሮም የታሪክ ምሁር፣ ስለዚህ ቀይ ቀለም የጠቀሰ ሲሆን በዘመኑ ከነበሩት ተወዳጅ ቀለማት መካከል አንዱ እንደሆነም ተናግሯል።
ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች መካከል በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የነበሩት እነማን ናቸው?
▪ ይህን የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ከጻፉት ስምንት ሰዎች መካከል በበዓሉ ላይ የተገኙት ስድስቱ ሳይሆኑ አይቀሩም።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዘገባ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ከዚህ ይልቅ አብ . . . የገባውን . . . ቃል ፍጻሜ ተጠባበቁ።” (የሐዋርያት ሥራ 1:4) በመሆኑም በኋላ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆኑት ማቴዎስ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ በኢየሱስ ትእዛዝ መሠረት ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር “በአንድ ቦታ” ተሰብስበው እንደነበር ይኸው ዘገባ ይገልጻል። የኢየሱስ ወንድሞችም እዚያው ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 1:12-14፤ 2:1-4) ከወንድሞቹ መካከል ሁለቱ ማለትም ያዕቆብ እና ይሁዳ በስማቸው የተጠሩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ከጊዜ በኋላ ጽፈዋል።—ማቴዎስ 13:55፤ ያዕቆብ 1:1፤ ይሁዳ 1
ማርቆስ በወንጌል ዘገባው ላይ ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ስለ ሸሸ አንድ ወጣት ጽፏል። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ቀድሞውንም ቢሆን ኢየሱስን ትተውት ሸሽተው ስለነበር ማርቆስ የጻፈው ስለ ራሱ መሆን አለበት። (ማርቆስ 14:50-52) በመሆኑም ማርቆስ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል የነበረ ይመስላል፤ በጴንጤቆስጤ ዕለትም አብሯቸው ሳይሰበሰብ አልቀረም።
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈስ መሪነት ከጻፉት ሰዎች መካከል በጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ያልተገኙት ጳውሎስና ሉቃስ ናቸው። በ33 ዓ.ም. ጳውሎስ የክርስቶስ ተከታይ አልሆነም ነበር። (ገላትያ 1:17, 18) ሉቃስም ቢሆን በቦታው የነበረ አይመስልም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ከነበሩት “የዓይን ምሥክሮች” መካከል ራሱን አላካተተም።—ሉቃስ 1:1-3
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማቅለሚያ ለማዘጋጀት የሚረዱ ነፍሳት
[የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of SDC Colour Experience (www.sdc.org.uk)
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ንግግር ሲያቀርብ