ከታሪክ ማኅደራችን
“ይሖዋ ወደ ፈረንሳይ ያመጣችሁ እውነትን እንድትማሩ ነው”
አንትዋን ስካሌትኪ፣ ልጅ ሳለ ምንጊዜም ከእሱ የማይለይ ድንክ ፈረስ ነበረው። አንትዋን ከመሬት በታች 500 ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ የማዕድን ማውጫ ውስጥ ድንግዝግዝ ባለ ዋሻ እያለፈ በፈረሱ ከሰል ያመላልስ ነበር። የአንትዋን አባት የማዕድን ማውጫ ሲደረመስ ጉዳት ስለደረሰበት ቤተሰቡ በዚህ ቦታ በቀን ለዘጠኝ ሰዓት ያህል አድካሚ የሆነውን ሥራ እንዲሠራ አንትዋንን ከመላክ ውጪ ምርጫ አልነበረውም። በአንድ ወቅት ዋሻው ከላይ በመደርመሱ አንትዋን ሕይወቱን ሊያጣ ነበር።
አንትዋን በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት ፈረንሳይ ውስጥ ከተወለዱ ፖላንዳውያን ወላጆች ያሏቸው በርካታ ልጆች አንዱ ነው። ይሁንና ፖላንዳውያን ወደ ፈረንሳይ የመጡት ለምንድን ነው? ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፖላንድ ነፃነቷን ስትቀዳጅ የሕዝብ ብዛት አሳሳቢ ችግር ሆኖባት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ፈረንሳይ በጦርነቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወንዶች አጥታ ስለነበር በከሰል ማዕድን ማውጫ የሚሠሩ ሰዎች ከፍተኛ እጥረት አጋጠማት። በዚህም ምክንያት ፖላንድ ዜጎቿን ወደ ፈረንሳይ እንድትልክ ሁለቱ መንግሥታት ስምምነት በማድረግ መስከረም 1919 ተፈራረሙ። በ1931 በፈረንሳይ የሚኖሩት ፖላንዳውያን 507,800 የደረሱ ሲሆን በርካታ ፖላንዳውያን በስተ ሰሜን በሚገኘው የማዕድ ማውጫ አካባቢ ይኖሩ ነበር።
ጠንካራ ሠራተኞች የሆኑት እነዚህ ፖላንዳውያን ይዘዋቸው ከመጡት ነገሮች መካከል ለየት ያለ ባሕላቸውና ሃይማኖተኛ መሆናቸው ይገኙበታል። አሁን 90 ዓመት የሆነው አንትዋን “አያቴ ጆሴፍ ለቅዱሳን መጻሕፍት ከፍተኛ አክብሮት ያለው ሲሆን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የቀረጸበት አባቱ እንደሆነ ይናገር ነበር” በማለት ያስታውሳል። በማዕድን ማውጫው ውስጥ የሚሠሩት ፖላንዳውያን ቤተሰቦች አገራቸው እያሉ እንደሚያደርጉት እሁድ እሁድ የክት ልብሳቸውን ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር፤ ለሃይማኖት ግድ የሌላቸው የአገሪቱ ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ ፈረንሳውያን በዚህ ምክንያት ይንቋቸዋል።
በርካታ ፖላንዳውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በኖር ፓ ደ ካሌ ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከ1904 ጀምሮ በዚህ ክልል በቅንዓት ሲሰብኩ ቆይተዋል። በ1915 መጠበቂያ ግንብ በፖላንድ ቋንቋ በየወሩ መታተም የጀመረ ሲሆን ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ! ይባላል) በዚህ ቋንቋ በ1925 መታተም ጀመረ። በርካታ ቤተሰቦች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት የያዙትን እነዚህን መጽሔቶች እንዲሁም በፖላንድ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአምላክ በገና የተባለውን መጽሐፍ በማግኘታቸው ደስተኞች ነበሩ።
የአንትዋን ቤተሰብ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያወቀው በአጎቱ አማካኝነት ነው፤ አጎቱ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ የተገኘው በ1924 ነበር። በዚያው ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በብሩየ አናርትዋ ከተማ በፖላንድ ቋንቋ የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ አደረጉ። ይህ ከሆነ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በዚሁ ከተማ በተደረገ ስብሰባ ላይ 2,000 ሰዎች ተገኙ፤ የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ የሆነው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በስብሰባው ላይ የሕዝብ ንግግር አቀረበ። ወንድም ራዘርፎርድ በስብሰባው ላይ ብዙ ሕዝብ መገኘቱ አስደስቶት ነበር፤ አብዛኞቹ ፖላንዳውያን በመሆናቸው እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ ወደ ፈረንሳይ ያመጣችሁ እውነትን እንድትማሩ ነው። አሁን እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ የፈረንሳይን ሕዝብ መርዳት ይኖርባችኋል! ገና መከናወን ያለበት ሰፊ የስብከት ሥራ አለ፤ ይሖዋ ደግሞ ለዚህ ሥራ አስፋፊዎችን ያስነሳል።”
ይሖዋ አምላክም ይህን አድርጓል! እነዚህ ፖላንዳውያን ክርስቲያኖች በማዕድን ማውጫ ውስጥ በትጋት ይሠሩ እንደነበረ ሁሉ ስብከቱንም በሙሉ ልብ አከናውነዋል! እንዲያውም አንዳንዶቹ የተማሩትን ውድ እውነት ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ የትውልድ አገራቸው ወደሆነችው ወደ ፖላንድ ተመልሰዋል። ከፈረንሳይ ወደ ፖላንድ ተመልሰው በብዙ ክልሎች ውስጥ ምሥራቹን ካሰራጩት ወንድሞች መካከል ቲኦፊል ፒያስኮፍስኪ፣ ሽቼፓን ኮሲያክ እና ያን ዛቡዳ ይገኙበታል።
የፖላንድ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ወንጌላውያን ደግሞ እዚያው ፈረንሳይ ቀርተው ከፈረንሳውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በቅንዓት መስበካቸውን ቀጠሉ። በ1926 በሲን ለ ኖብል በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ 1,000 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች በፖላንድ ቋንቋ፣ 300 የሚሆኑ ደግሞ በፈረንሳይኛ ስብሰባውን ተከታትለዋል። የ1929 የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) “በዚህ ዓመት 332 ፖላንዳውያን ወንድሞች ራሳቸውን መወሰናቸውን በጥምቀት አሳይተዋል” የሚል ሪፖርት ይዞ ወጥቷል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት በፈረንሳይ ከነበሩት 84 ጉባኤዎች መካከል 32ቱ በፖላንድ ቋንቋ የሚካሄዱ ነበሩ።
በ1947 የፖላንድ መንግሥት ዜጎቹ ወደ ፖላንድ እንዲመለሱ ያቀረበውን ግብዣ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ተቀበሉ። ይሁንና እነሱ ከሄዱም በኋላ የሥራቸው ፍሬ ታይቷል፤ በዚያ ዓመት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በ10 በመቶ መጨመሩ የእነሱም ሆነ በፈረንሳይ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጥረት ውጤት እንዳስገኘ ማስረጃ ይሆናል። ከዚያም ከ1948 እስከ 1950 ባሉት ዓመታት ውስጥ 20፣ 23 አልፎ ተርፎም 40 በመቶ ጭማሪ ተገኝቷል! የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ እነዚህን አዲስ አስፋፊዎች ለማሠልጠን በ1948 የመጀመሪያዎቹን የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሾመ። ለዚህ ሥራ ከተመረጡት አምስት ወንድሞች መካከል አራቱ ፖላንዳውያን ሲሆኑ ከእነሱ አንዱ አንትዋን ስካሌትኪ ነበር።
በፈረንሳይ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙዎቹ ከእነሱ በፊት በነበሩትና በማዕድን ማውጫዎቹም ሆነ በመስክ አገልግሎት በትጋት በሠሩት ፖላንዳውያን ዘመዶቻቸው የቤተሰብ ስም ይጠራሉ። በዛሬው ጊዜም ወደ ፈረንሳይ የሚመጡ በርካታ የሌላ አገር ዜጎች በዚህች አገር እውነትን እየተማሩ ነው። ከሌሎች አገሮች ከመጡት ወንጌላውያን አንዳንዶቹ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ሌሎቹ በዚያው በፈረንሳይ እየኖሩ ነው፤ ያም ሆነ ይህ ከእነሱ በፊት የነበሩትን ፖላንዳውያን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ምሳሌ በመከተል በቅንዓት መስበካቸውን ቀጥለዋል።—በፈረንሳይ ካለው የታሪክ ማኅደራችን