የአንባቢያን ጥያቄዎች
ክርስቲያኖች ለመንግሥት ሠራተኞች ስጦታ ወይም ጉርሻ መስጠት ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ምን ሊረዳቸው ይችላል?
ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገባን በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከሁሉ በፊት ክርስቲያኖች ሐቀኞች መሆን አለባቸው። ከይሖዋ ሕግ ጋር የማይጋጭ እስከሆነ ድረስ ያሉበትን አገር ሕግ የመታዘዝ ኃላፊነት አለባቸው። (ማቴ. 22:21፤ ሮም 13:1, 2፤ ዕብ. 13:18) ከዚህም ሌላ የአካባቢውን ባሕልና ልማድ ለማክበር እንዲሁም ‘ባልንጀሮቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ለመውደድ’ ይጥራሉ። (ማቴ. 22:39፤ ሮም 12:17, 18፤ 1 ተሰ. 4:11, 12) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ክርስቲያኖች፣ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋላቸው ስጦታና ጉርሻ ስለመስጠት ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
በብዙ አገሮች አንድ የማኅበረሰቡ አባል፣ መብቱ የሆነውን ነገር ለማግኘት ሲል ለመንግሥት ሠራተኞች ምንም ነገር መስጠት አያስፈልገውም። የመንግሥት ሠራተኞች ለሚሰጡት አገልግሎት መንግሥት ስለሚከፍላቸው ከመደበኛ ደሞዛቸው ሌላ ምንም ነገር ለማግኘት አይጠይቁም ወይም አይጠብቁም። በብዙ አገሮች ውስጥ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ሲሰጥ ስጦታ ወይም ጉርሻ ቢቀበል አሊያም አንድ ነገር እንዲደረግለት ቢጠይቅ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ነው። እንዲህ ያለው ድርጊት ባለሥልጣኑ በሚወስደው እርምጃ ላይ ለውጥ የማያመጣ ቢሆንም እንኳ እንደ ጉቦ ይቆጠራል። በመሆኑም እንዲህ ባሉ አገሮች የሚኖር አንድ ክርስቲያን ለመንግሥት ሠራተኞች ስጦታ ወይም ጉርሻ መስጠት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጉዳይ ምንም አያሻማም። በአጭሩ እንዲህ ያለ ስጦታ መስጠት ተገቢ አይደለም።
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሕግ በሌለባቸው ወይም ሕጉ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በማይሆንባቸው አገሮች ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያላቸው አመለካከት የተለየ ነው። በአንዳንድ አገሮች ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙበት ሲሆን ሊያገለግሉት ከሚገባው ሕዝብ ገንዘብ ወይም ሌላ ስጦታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲያውም ስጦታ ካልተቀበሉ ምንም ነገር ለመሥራት ፈቃደኞች አይደሉም። በመሆኑም ጋብቻን ሕጋዊ የሚያደርጉ፣ ተገቢውን የገቢ ግብር የሚሰበስቡ፣ ከግንባታ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚያስፈጽሙና እነዚህን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባለሥልጣናት ጉርሻ ይጠይቃሉ። ባለሥልጣናቱ ጉርሻ ካላገኙ፣ ዜጎች ሕጋዊ መብታቸውን እንዳያገኙ ሁኔታውን በጣም ሊያወሳስቡት ወይም አገልግሎቱን ጭራሽ ማግኘት እንዳይቻል ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲያውም በአንድ አገር ውስጥ፣ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያለባቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንኳ በቅድሚያ ጠቀም ያለ ጉርሻ ካልተሰጣቸው እሳቱን ማጥፋት እንደማይጀምሩ ሪፖርት ተደርጓል።
ጉርሻ እጅግ በተስፋፋባቸው እንዲህ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች፣ ጉርሻ መስጠት ግድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ጉርሻን ሕጋዊ አገልግሎት ለማግኘት ሲባል እንደሚጠበቅበት ተጨማሪ ክፍያ አድርጎ ይመለከተው ይሆናል። ይሁን እንጂ ሙስና በተስፋፋበት አካባቢ የሚኖር አንድ ክርስቲያን፣ ከአምላክ አመለካከት አንጻር ተቀባይነት ባለውና ተቀባይነት በሌለው ጉርሻ መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሊሆንለት ይገባል። መብታችን የሆነን ነገር ለማግኘት ስንል ጉርሻ በመስጠትና ሕጋዊ ያልሆነ ነገር ለማግኘት ስንል ጉርሻ በመስጠት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ሙስና በተንሰራፋበት አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች፣ መብታቸው ያልሆነውን አገልግሎት ለማግኘት ሲሉ ለመንግሥት ባለሥልጣን ጉቦ ይሰጣሉ፤ አሊያም የተጣለባቸውን ተገቢ ቅጣት ላለመክፈል ሲሉ ለፖሊስ ወይም ለመንግሥት ባለሥልጣን “ጉርሻ” ይሰጣሉ። እንዲህ ያለ “ስጦታ” መስጠት ትክክል እንዳልሆነ ሁሉ እንዲህ ያለውን “ስጦታ” መቀበልም ስህተት ነው። ሁለቱም ድርጊቶች ፍትሕ እንዲዛባ ያደርጋሉ።—ዘፀ. 23:8፤ ዘዳ. 16:19፤ ምሳሌ 17:23
አብዛኞቹ የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ ባለሥልጣናት የሚጠይቁትን ጉርሻ ለመስጠት በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናቸው አይፈቅድላቸውም። እንዲህ ማድረግ ሙስናን በቸልታ ማለፍ ወይም ማበረታታት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ስጦታ ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም።
የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሕጋዊ ያልሆነ ነገር ለማግኘት ስጦታ መስጠት ጉቦ የመስጠት ያህል እንደሆነ ይገነዘባሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን በአካባቢው ካለው ሁኔታ አንጻር፣ መብታቸው የሆነን አገልግሎት ለማግኘት ወይም አላስፈላጊ የሆነ መጓተትን ለማስቀረት ሲሉ የተወሰነ ጉርሻ ይሰጡ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ የመንግሥት ሆስፒታል ነፃ ሕክምና ካገኙ በኋላ አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ ለሐኪሞቹና ለነርሶቹ ስጦታ ይሰጣሉ። ስጦታውን የሚሰጡት ሕክምና ከማድረጋቸው በፊት ሳይሆን ከሕክምናው በኋላ በመሆኑ ይህን ማድረግ ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል፤ ስለሆነም ስጦታው፣ የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ብለው እንደሰጡት ጉቦ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም።
በእያንዳንዱ አገር ያለውን ሁኔታ አንድ በአንድ እያነሱ መወያየት አይቻልም። በመሆኑም በአካባቢው ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ክርስቲያኖች አንድ ነገር ለማድረግ ሲወስኑ ሕሊናቸውን የሚያቆሽሽ ነገር እንዳያደርጉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ሮም 14:1-6) ሕጋዊ ካልሆኑ ተግባሮች መራቅ አለባቸው። (ሮም 13:1-7) በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ከሚያስከትል ወይም ሌሎችን ከሚያሰናክል ማንኛውም ድርጊት መቆጠብ ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 6:9፤ 1 ቆሮ. 10:32) እንዲሁም የሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ለባልንጀራቸው ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል።—ማር. 12:31
አንድ ሰው ከውገዳ እንደተመለሰ ማስታወቂያ ሲነገር ጉባኤው ደስታውን መግለጽ የሚችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ 100 በጎች ስላሉት ሰው የሚገልጽ ግሩም ምሳሌ በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ ተናግሯል። ሰውየው አንዷ በግ ስትጠፋበት 99ኙን በምድረ በዳ ትቶ “የጠፋችውን እስኪያገኝ ድረስ” መፈለግ ጀመረ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በሚያገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ላይ ይሸከማታል። ቤት ሲደርስም ጓደኞቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋችውን በጌን ስላገኘኋት የደስታዬ ተካፋዮች ሁኑ’ ይላቸዋል።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ንስሐ መግባት ከማያስፈልጋቸው 99 ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል።”—ሉቃስ 15:4-7
በዙሪያው ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው፣ ‘የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ ብለው ይተቹት የነበሩትን የጸሐፍትንና የፈሪሳውያንን አመለካከት ለማረም ነው። (ሉቃስ 15:1-3) ኢየሱስ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ በሰማይ ደስታ እንደሚሆን ተናግሯል። እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘አንድ ኃጢአተኛ አካሄዱን ለውጦ ንስሐ ሲገባና ለእግሩ ቀና መንገድ ሲያበጅ በሰማይ ደስታ የሚኖር ከሆነ በምድርስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊኖር አይገባም?’—ዕብ. 12:13
አንድ የተወገደ ሰው ወደ ጉባኤው ሲመለስ እንድንደሰት የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት አለን። እርግጥ ግለሰቡ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለሱን መቀጠል አለበት፤ ሆኖም ከውገዳ የተመለሰው ንስሐ ስለገባ ነው፤ ይህን ማድረጉም ያስደስተናል። በመሆኑም ሽማግሌዎች አንድ ሰው እንደተመለሰ ማስታወቂያ በሚናገሩበት ጊዜ ስሜታችን ፈንቅሎን ብናጨበጭብ ስህተት አይደለም ማለት ነው።
በኢየሩሳሌም በሚገኘው የቤተዛታ የውኃ ገንዳ ውስጥ ያለውን ‘ውኃ እንዲናወጥ’ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ በቤተዛታ የውኃ ገንዳ ውስጥ ያለው ውኃ “በሚናወጥበት ጊዜ” የታመሙ ሰዎችን እንደሚፈውስ ያስቡ ነበር። (ዮሐ. 5:1-7) በመሆኑም ለመፈወስ የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ አካባቢ ይሰበሰባሉ።
የቤተዛታ የውኃ ገንዳ፣ አይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት ለማካሄድ የሚታጠቡበት እንደሆነ ይታመናል። ውኃ ወደ ገንዳው የሚገባው በአቅራቢያው ካለ የውኃ ማጠራቀሚያ ሲሆን ገንዳውና ማጠራቀሚያው የሚገኙት በአንድ አካባቢ ነው። በቦታው ላይ የተደረገው ምርምር እንደሚጠቁመው በገንዳውና በውኃ ማጠራቀሚያው መካከል ግድብ አለ። ይህ ግድብ፣ ውኃ ለማሳለፍ የሚያስችል በር ያለው ሲሆን ይህን በር በመክፈት ከውኃ ማጠራቀሚያው ወደ ገንዳው ውኃ እንዲፈስ ማድረግ ይቻላል፤ ውኃው ወደ ገንዳው የሚገባው ከታች በኩል በተሠራ ቦይ አማካኝነት ነው። የግድቡ በር ተከፍቶ ውኃ ወደ ገንዳው ሲገባ የሚኖረው ኃይለኛ ግፊት የገንዳውን ውኃ እንደሚያናውጠው ግልጽ ነው።
አንድ መልአክ ውኃውን እንደሚያናውጠው የሚናገረው በዮሐንስ 5:4 ላይ የሚገኘው ዘገባ፣ ትልቅ ግምት በሚሰጣቸው ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎች (ለምሳሌ በአራተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀው ኮዴክስ ሲናይቲከስ) ውስጥ አይገኝም። ሆኖም በቤተዛታ ኢየሱስ ለ38 ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረን አንድ ሰው ፈውሷል። ሰውየው ገንዳው ውስጥ መግባት ሳያስፈልገው በቅጽበት ተፈውሷል።