የአንባቢያን ጥያቄዎች
በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ላይ የተገለጸው የሁለቱ በትሮች አንድ ላይ መያያዝ ምን ትርጉም አለው?
ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ አንድ እንደሚሆኑ የሚገልጽ ተስፋ ያዘለ መልእክት በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት፣ በፍጻሜው ዘመን የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦችም አንድ እንደሚሆኑ ይጠቁማል።
ይሖዋ ለነቢዩ ሕዝቅኤል በሁለት በትሮች ላይ እንዲጽፍ ነግሮት ነበር። በአንዱ በትር ላይ “ለይሁዳና ከእሱ ጋር ላሉት የእስራኤል ሰዎች” በሌላው በትር ላይ ደግሞ “ለዮሴፍ ይኸውም ኤፍሬምን ለሚወክለው በትርና ከእሱ ጋር ላሉት የእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ” ብሎ እንዲጽፍ ነገረው። ከዚያም ሕዝቅኤል፣ ሁለቱ በትሮች “አንድ በትር” እንዲሆኑ በእጁ አያያዛቸው።—ሕዝ. 37:15-17
“ኤፍሬም” የሚለው ስያሜ ማንን ይወክላል? አሥሩን ነገድ ያቀፈውና በስተ ሰሜን የነበረው መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ፣ ኢዮርብዓም የተባለ ኤፍሬማዊ ሲሆን የኤፍሬም ነገድ ደግሞ ኃያል ነበር። (ዘዳ. 33:13, 17፤ 1 ነገ. 11:26) ይህ ነገድ የመጣው ከዮሴፍ ልጅ ከኤፍሬም ነው። (ዘኁ. 1:32, 33) ዮሴፍ ከአባቱ ከያዕቆብ ልዩ በረከት አግኝቶ ነበር። በመሆኑም አሥሩን ነገድ ያቀፈውን መንግሥት የሚያመለክተው በትር ‘ኤፍሬምን የሚወክለው በትር’ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነበር። አሦራውያን በ740 ዓ.ዓ. ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ድል በማድረግ ሕዝቡን በምርኮ ወስደው ነበር፤ ሕዝቅኤል ስለ ሁለቱ በትሮች የሚገልጸውን ትንቢት የጻፈው ይህ ከሆነ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። (2 ነገ. 17:6) ከዓመታት በኋላ የአሦራውያን አገዛዝ በባቢሎናውያን ተተካ፤ በመሆኑም ሕዝቅኤል ትንቢቱን በጻፈበት ወቅት፣ አሦራውያን በግዞት ከወሰዷቸው እስራኤላውያን አብዛኞቹ በባቢሎናውያን ግዛት ውስጥ ተበታትነው ይኖሩ ነበር።
በ607 ዓ.ዓ. ደግሞ ባቢሎናውያን ሁለት ነገዶችን ያቀፈውን ደቡባዊውን የይሁዳ መንግሥት ድል በማድረግ ሕዝቡን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዱ፤ ከሰሜናዊው መንግሥት የቀሩ ሰዎች ከነበሩ እነሱንም ማርከው ወስደዋቸው ሊሆን ይችላል። በደቡባዊው መንግሥት ላይ የሚገዙት፣ ከይሁዳ ነገድ የመጡ ነገሥታት ነበሩ፤ ካህናቱ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ያገለግሉ ስለነበር የሚኖሩት በይሁዳ ነበር። (2 ዜና 11:13, 14፤ 34:30) ስለዚህ ሁለቱን ነገዶች ያቀፈው መንግሥት “ለይሁዳ” በሚለው በትር መወከሉ ተገቢ ነበር።
እነዚህ ሁለት ምሳሌያዊ በትሮች አንድ ላይ የተያያዙት መቼ ነው? እስራኤላውያን ቤተ መቅደሱን በድጋሚ ለመሥራት በ537 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ጊዜ ነው። ሁለቱን ነገድ ካቀፈው መንግሥትና አሥሩን ነገድ ካቀፈው መንግሥት የተውጣጡ እስራኤላውያን አንድ ላይ ከምርኮ ተመልሰዋል። በመሆኑም በእስራኤል ልጆች መካከል የነበረው መከፋፈል ቀረ። (ሕዝ. 37:21, 22) እስራኤላውያን ይሖዋን እንደገና በአንድነት ማምለክ ጀመሩ። ነቢዩ ኢሳይያስና ኤርምያስም የእስራኤል ልጆች አንድ እንደሚሆኑ ትንቢት ተናግረው ነበር።—ኢሳ. 11:12, 13፤ ኤር. 31:1, 6, 31
ይህ ትንቢት፣ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ የትኛውን እውነታ ያጎላል? ይሖዋ፣ አምላኪዎቹን “አንድ” እንደሚያደርጋቸው ይጠቁማል። (ሕዝ. 37:18, 19) ታዲያ ስለ አንድነት የሚገልጸው ይህ ተስፋ በዘመናችን እውን ሆኗል? አዎ። ትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በ1919 የአምላክ ሕዝቦች ቀስ በቀስ እንደገና ሲደራጁና አንድ ሲሆኑ ነው። ሰይጣን እነሱን ለዘለቄታው ለመከፋፈል ያደረገው ሙከራ ከሽፏል።
እንደገና አንድ ከሆኑት ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ ነበራቸው። (ራእይ 20:6) እነዚህ ክርስቲያኖች ለይሁዳ ተብሎ እንደተጻፈበት በትር ነበሩ። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ከእነዚህ መንፈሳዊ አይሁዳውያን ጋር መተባበር ጀመሩ። (ዘካ. 8:23) እነዚህ ሰዎች ለዮሴፍ ተብሎ እንደተጻፈበት በትር ናቸው፤ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ የላቸውም።
በዛሬው ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች የይሖዋ ሕዝቦች ሆነው በአንድ ንጉሥ ሥር በአንድነት ያገለግላሉ፤ ንጉሣቸውም “አገልጋዬ ዳዊት” ተብሎ ትንቢት የተነገረለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሕዝ. 37:24, 25) ኢየሱስ ስለ ሁሉም ተከታዮቹ ባቀረበው ጸሎት ላይ ‘አባቱ ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለውና እሱም ከአባቱ ጋር አንድነት እንዳለው ሁሉ እነሱም አንድነት እንዲኖራቸው’ ጠይቋል።a (ዮሐ. 17:20, 21) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹን ያቀፈው ታናሽ መንጋ ‘ከሌሎች በጎች’ ጋር “አንድ መንጋ” እንደሚሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር። ሁሉም ‘አንድ እረኛ ይኖራቸዋል።’ (ዮሐ. 10:16) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ በዛሬው ጊዜ ባሉ የይሖዋ ሕዝቦች (ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን) መካከል ያለውን አንድነት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል!
a ኢየሱስ የመገኘቱ ምልክት ክፍል የሆኑትን ምሳሌዎች የተናገረበት ቅደም ተከተል ትኩረት የሚስብ ነው። በመጀመሪያ፣ ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይኸውም አመራር የሚሰጡ ቅቡዓን ወንድሞችን ስላቀፈው አነስተኛ ቡድን ተናገረ። (ማቴ. 24:45-47) ከዚያም ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች በሙሉ የሚመለከቱ ምሳሌዎች ተናገረ፤ እነዚህ ምሳሌዎች በዋነኝነት የተነገሩት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። (ማቴ. 25:1-30) በመጨረሻም የክርስቶስን ወንድሞች ስለሚደግፉ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ተናገረ። (ማቴ. 25:31-46) በተመሳሳይም የሕዝቅኤል ትንቢት በዘመናችን የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ሰማያዊ ተስፋ ባላቸው ክርስቲያኖች ላይ ነው። አሥሩን ነገድ ያቀፈው መንግሥት ብዙውን ጊዜ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ባያመለክትም በዚህ ትንቢት ላይ የተገለጸው አንድነት፣ ምድራዊ ተስፋ ባላቸውና ሰማያዊ ተስፋ ባላቸው ክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ያስታውሰናል።