‘በአሕዛብ ሁሉ የተጠሉ’
1 ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ስላገኟቸው አስደናቂ በረከቶች ስንሰማ ሁላችንም ተደስተናል። በማላዊ ከ26 ዓመታት ከባድ ጭቆና በኋላ ሥራችን ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘቱ በጣም አስደስቶናል። በምሥራቅ አውሮፓ አምላክ የለሹ ኮሚዩኒዝም ሲፈራርስና በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን ተጭኗቸው ከነበረው ጨቋኝ ቀንበር ሲላቀቁ በመመልከታችን እፎይ ብለናል። በግሪክ አገር የአምልኮ ነፃነታችን ሕጋዊ ስለመሆኑ ጥያቄ በተነሳ ጊዜ ተጨንቀን ነገሩን ስንከታተል ነበር። በኋላም በአውሮፓ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደረገው ሙግት አሸናፊ በመሆን ከፍተኛ ድል ስንቀዳጅ በደስታ ፈንድቀናል። የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋታቸው እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት መቻሉን የሚገልጹ ዘገባዎች ስንሰማ በጣም ደስ ብሎናል። በዩክሬን ውስጥ በኪየቭ ከተማ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ከ7,400 የሚበልጡ ሰዎች እንደተጠመቁ ስንሰማ በጣም ተደንቀን ነበር። አዎን፣ የመንግሥቱን ሥራ በማስፋፋቱ ረገድ የታዩት እነዚህ አስደናቂ ክንውኖች እጅግ አስደስተውናል!
2 ብዙ የምንደሰትባቸው ምክንያቶች ቢኖሩንም ከመጠን በላይ እንዳንፈነድቅ ልንጠነቀቅ ይገባናል። ጥሩ ጥሩ ሪፖርቶችን በተከታታይ ስንሰማ በምሥራቹ ላይ የነበረው ተቃውሞ አብቅቷል፤ የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት እያገኙ ነው ብለን እንድንደመድም ሊያደርጉን ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አታላይ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን አንዳንድ አስደሳች ድሎች ያገኘንና ጭማሪ እንዳናገኝ ያግዱን የነበሩ እንቅፋቶችን በተወሰነ መጠን የተወጣናቸው ቢሆንም ከዓለም ጋር ያለን መሠረታዊ ግንኙነት እንዳልተለወጠ መዘንጋት አይኖርብንም። የኢየሱስ ተከታዮች ስለሆንን ‘የዓለም ክፍል አይደለንም።’ በዚህም ምክንያት ‘በአሕዛብ ሁሉ የተጠላን’ እንደምንሆን እርግጠኞች ነን። (ዮሐ. 15:19፤ ማቴ. 24:9) ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” የሚለውን መሠረታዊ ሕግ ሊለውጠው የሚችል ነገር አይመጣም። — 2 ጢሞ. 3:12
3 ይህ ማስጠንቀቂያ እውነት መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል። የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ኃያል በነበሩ ገዢዎችና በዜጎቻቸው ፊት አስደናቂ ምስክርነት ቢሰጥም በየዕለቱ ይነቀፍና እርሱን ለመግደል ጥረት ይደረግ ነበር። ሐዋርያቱም ብዙ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ቢረዱም፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጻፍ ቢካፈሉና በተሰጣቸው የመንፈስ ስጦታ በመጠቀም ተዓምራት ቢፈጽሙም ይጠሉና ግፍ ይፈጸምባቸው ነበር። ጥሩ ጠባይ የነበራቸውና ጎረቤቶቻቸውን የሚወዱ ቢሆኑም ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖችን ‘በየቦታው ሰዎች የሚቃወሙት’ የተናቀ “ኑፋቄ” አባላት አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። (ሥራ 28:22) ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም በዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ በአስደናቂ መንገድ እየተጠቀመ ቢሆንም በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በሚገኙት የሥርዓቱ ክፍሎች የማያቋርጥ ተቃውሞ ይደርስበታል እንዲሁም መጥፎ ስም ተሰጥቶታል። ተቃውሞው ያቆማል ብለን የምንጠብቅበት ምንም ምክንያት የለንም።
4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰይጣን የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በተለያዩ መንገዶች አሳድዷቸዋል። ይጠሏቸው የነበሩ ተቃዋሚዎቻቸው ስለነሱ ፍጹም ውሸት የሆነ ነገር በመናገር መጥፎዎች ናቸው በማለት ይናገሩ ነበር። (ሥራ 14:2) እነሱን ለማስፈራራት ይዝቱባቸው ነበር። (ሥራ 4:17, 18) በቁጣ የነደዱ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው እነሱን ዝም ለማሰኘት ሞክረዋል። (ሥራ 19:29–34) ፍትሕ በጎደለው መንገድ ይታሰሩ ነበር። (ሥራ 12:4, 5) አብዛኛውን ጊዜ አሳዳጆቻቸው ይደበድቧቸው ነበር። (ሥራ 14:19) ንጹሐን ቢሆኑም ክርስቲያኖቹን ገድለዋቸዋል። (ሥራ 7:54–60) ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ይህ ሁሉ ግፍ ደርሶበት ጸንቷል። (2 ቆሮ. 11:23–27) ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራ ለማደናቀፍና እነዚህን ትጉህ ሠራተኞች ለማሠቃየት ማንኛውንም አጋጣሚ ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም ነበር።
5 ዛሬም ቢሆን ሰይጣን ተመሳሳይ ዘዴዎች እየተጠቀመ ነው። ስለ እኛ ሙሉ በሙሉ ውሸት የሆነ ነገር ይነገራል። የተሳሳቱ መናፍቃን ወይም የሃይማኖት ቡድን ናቸው ተብለን መጥፎ ስም ተሰጥቶናል። በአንዳንድ አገሮች ባለ ሥልጣኖች ጽሑፎቻችንን ሰዎችን የሚያበጣብጡ ናቸው በማለት አግደዋቸዋል። የደምን ቅድስና በማክበራችን ተቀልዶብናል እንዲሁም ፍርድ ቤት አስከስሶናል። በ1940ዎቹ ዓመታት ለባንዲራ ለምን ሰላምታ አትሰጡም በማለት በቁጣ የተነሳሱ ሰዎች ረብሻ ፈጥረው ወንድሞቻችንን በማጥቃት ጉዳት አድርሰውባቸዋል፣ ንብረታቸውንም አውድመዋል። ገለልተኞች በመሆናቸው ምክንያት በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች ወኅኒ ወርደዋል። አምባገነንናዊ አገዛዝ በሰፈነባቸው አገሮች ወንድሞቻችን ቀልባሾች ናችሁ ተብለው በሐሰት ተከሰዋል። ከዚህም የተነሣ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጭካኔ ተደብድበዋል፤ እንዲሁም በእሥር ቤት እና በእሥረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተገድለዋል። የሚደርስብን የማያቋርጥ ተጽዕኖ ያለ ምንም ምክንያት በሰዎች ዘንድ የምንጠላ መሆናችንን በግልጽ ያሳያል። — አዋጅ ነጋሪዎች የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 29 ተመልከቱ።
6 የወደፊቱ ጊዜ ምን ያመጣ ይሆን? የይሖዋ ሕዝቦች አልፎ አልፎ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያለ ተጽዕኖ የሚሠሩ ቢሆንም ጠቅላላው ሁኔታ ግን አልተለወጠም። ዲያብሎስ በ1914 ከተዋረደ ጀምሮ ቁጣው አልበረደለትም። የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ያውቃል። ታላቁ መከራ እየቀረበ ሲሄድ ቁጣው እየጨመረ እንደሚሄድ የተረጋገጠ ነው። በዙፋን ላይ የተቀመጠውን ንጉሡን ክርስቶስ ኢየሱስን ለመዋጋት ወስኗል፤ በውጊያውም እስከ መጨረሻው ለመቀጠል ቆርጧል። እሱና አጋንንቱ ቁጣቸውን መግለጽ የሚችሉት እዚህ ምድር ላይ ባሉት “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች” በታማኝነት ‘በሚጠብቁትና ለኢየሱስ በሚመሰክሩት’ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ ብቻ ነው። — ራእይ 12:12, 17 የ1980 ትርጉም
7 ስለዚህ የወደፊቱን ጊዜ ስንጠባበቅ ሊመጣ ስለሚችለው ነገር ከእውነታው ያልራቀ አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልገናል። ዲያብሎስ ተስፋ ቆርጦ ውጊያውን ያቆማል ብለን የምናስብበት ምንም ምክንያት የለም። ሰይጣን ዓለም እኛን እንዲጠላን አድርጓል። ይህ ጥላቻ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሊቀሰቀስ ይችላል። በብዙ አገሮች የመስበክ ነፃነት ያገኘነው ከረጅም ጊዜ ትግል በኋላ ነው። ይህ ነፃነት የተገኘው እኛን በሚደግፍ በጊዜው በሥልጣን ላይ ባለ ገዥ ወይም በሕዝብ ዘንድ ብዙም ተቀባይነት በሌለው ሕግ አማካኝነት ሊሆን ስለሚችል በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል። ነገሮች ሁሉ ባንድ ጀንበር ሊገለባበጡና ሰብዓዊ መብቶች የሚረገጡበት የተተረማመሰ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
8 አሁን በአንዳንድ አገሮች ያገኘነው ብልጽግናና ነፃነት በድንገት ሊጠፋና ወንድሞቻችን ባለፉት ጊዜያት ወዳሳለፏቸው ችግሮች ሊመለሱ ይችላሉ። ጠላቶቻችን ተሸንፈዋል ብለን በማሰብ ግዴለሾች በመሆን እንቅስቃሴያችንን ጋብ ለማድረግ አንደፍርም። ይህ ዓለም ለኛ ያለው ጥላቻ ሁልጊዜ በግልጽ አይታይ እንጂ በጣም ከፍተኛ ነው። የአምላክ ቃል መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ ከዓለም የሚመጣው ተቃውሞ እየቀነሰ ሳይሆን እየበረታ እንደሚሄድ ያሳያል። ስለዚህ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” በመሆን ሁልጊዜ ተጠንቅቀን መኖር አለብን። (ማቴ. 10:16) እስከመጨረሻው ድረስ ‘መጋደል’ እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባል። ለመዳን የሚያስችለን ቁልፍ ነገር ደግሞ መጽናት ነው። — ይሁዳ 3፤ ማቴ. 24:13
9 በጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል ውስጥ ተቃዋሚዎች ለሥራው ዕንቅፋት መሆናቸው ሳይታወቅ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ ‘የምንጨነቅበት ምክንያት አይታየንም’ በማለት እንድንጠራጠር ሊያደርገን ይችላል። ቢሆንም ሁልጊዜ ንቁዎች መሆን ያስፈልገናል። ሁኔታዎች በቶሎ ሊለዋወጡ ይችላሉ። ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ተቃዋሚዎች ጽሑፎቻችንን መርምረው ያገኙትን ነገር እኛን ለማጥቃት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ከሃዲዎች እኛን ሊከሱ የሚችሉበትን ሰበብ ለማግኘት ሁልጊዜ ይፈልጋሉ። ሥራችን አበሳጭቷቸው የተናደዱ ቄሶች በሕዝብ ፊት ሊያወግዙን ይችላሉ። የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ማቀዳችን የአካባቢውን ሰዎች የሚያስቆጣ ጭቅጭቅ ሊያስነሳ ይችል ይሆናል። ሰዎችን ለቁጣ የሚያነሳሱ አነጋገሮች ታትመው ሊወጡና በመጥፎ ዓይን እንድንታይ ሊያደርጉን ይችሉ ይሆናል። አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ሆን ብለው ሰዎች ስለ እኛ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነገር በመናገር በአካባቢያችን ወዳሉት ሰዎች ቤት ልንመሰክር ስንሄድ ተቃውሞ እንዲነሳብን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል። በቤታችን ውስጥ የሚኖሩ የምናፈቅራቸው ሰዎች ሳይቀሩ ሊጠሉንና ሊያሳድዱን ይችላሉ። ስለዚህ ዓለም ምንጊዜም ለኛ ጥላቻ እንዳለውና ይህ ጥላቻ በማንኛውም ጊዜ ሊገለጥ እንደሚችል ተገንዝበን ጠንቃቆች መሆን ያስፈ ልገናል።
10 ይህ እኛን እንዴት ሊነካን ይገባል? ይህ ሁሉ አስተሳሰባችንንና ስለ መጪው ጊዜ ያለንን አመለካከት በሚገባ ይነካዋል። በምን መንገድ? በጽናት ልንቋቋመው ስለሚገባን አስቸጋሪ ሁኔታ በማሰብ እንድንሰጋ ወይም እንድንፈራ ሊያደርገን ይገባልን? በአካባቢያችን ያሉ አንዳንድ ሰዎች ስለ ተረበሹ የስብከት ሥራችንን ቀዝቀዝ ማድረግ ይገባናልን? ስማችንን ያላግባብ ሲያክፋፉት የምንረበሽበት በቂ ምክንያት አለንን? ከባድ መከራ ቢደርስብን ይሖዋን በማገልገል የምናገኘውን ደስታችንን ያጠፋብናልን? ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያጠራጥር ነገር አለን? በፍጹም የለም! ለምን?
11 የምናውጀው መልዕክት እኛ ያመነጨነው ሳይሆን ከይሖዋ የመጣ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። (ኤር. 1:9) “ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ . . . በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ” በሚለውን ጥብቅ ማሳሰቢያ የመከተል ግዴታ አለብን። (ኢሳ. 12:4, 5) እርሱ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን መከራ የታገሠው ለአንድ የተለየ ዓላማ ሲል ይኸውም ‘ስሙ በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ’ ነው። (ዘጸ. 9:16) እየሠራን ያለነው ይሖዋ ያዘዘውን ሥራ ነው። ያለፍርሃት እንድንናገር ድፍረት የሚሰጠን እርሱ ነው። (ሥራ 4:29–31) ይህ ሥራ በነዚህ የአሮጌው ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚሠራ በጣም አስፈላጊ፣ ጠቃሚና አጣዳፊ ሥራ ነው።
12 ይህንን ማወቃችን ሰይጣንና ይህ ዓለም የሚያመጡብንን ቀጥተኛ ተቃውሞ ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቋም እንድንወስድ ድፍረት ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 5:8, 9) ይሖዋ ከእኛ ጋር መሆኑን ማወቃችን አሳዳጆቻችንን እንድንፈራ የሚያደርገንን ነገር ሁሉ አስወግደን “ደፋሮችና ጠንካሮች” እንድንሆን ያደርገናል። (ዘዳ. 31:6 አዓት ፤ ዕብ. 13:6) ተቃዋሚዎቻችን ስደት በሚያደርሱብን ጊዜ ሁሉ ዘዴኞች፣ ምክንያታውያንና ጥበበኞች ለመሆን ብንጥርም አምልኮታችንን የሚፈታተን ነገር ካጋጠመን ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ለመታዘዝ’ እንደቆረጥን በግልጽ እንነግራቸዋለን። (ሥራ 5:29) ስለራሳችን መከላከያ ማቅረብ የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ ካገኘን እንከራከራለን። (1 ጴጥ. 3:15) ይሁን እንጂ የእኛን ስም ለማጥፋት ከሚፈልጉ ግትር ተቃዋሚዎች ጋር በመከራከር ጊዜያችንን አናጠፋም። ከመበሳጨት ወይም ስማችንን ሲያጠፉ ወይም በሐሰት ሲወነጅሉን አጸፋውን ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ ‘ብንተዋቸው’ ይሻለናል። — ማቴ. 15:14
13 በመከራ መጽናታችን ይሖዋን ያስደስተዋል። (1 ጴጥ. 2:19) ተቀባይነት ያለውን ይህንን አቋም ለማግኘት ምን ዓይነት መሥዋዕትነት መክፈል አለብን? የተጠላንና ተቃውሞ የሚደርስብን ስለሆንን በምናገለግልበት ጊዜ ደስታ ልናጣ ይገባልን? በጭራሽ! ይሖዋ ለታዛዥነታችን “ደስታንና ሰላምን” በመስጠት እንደሚሸልመን ቃል ገብቶልናል። (ሮሜ 15:13) ኢየሱስ ከባድ መከራ ቢደርስበትም ደስተኛ የነበረው ‘በፊቱ ባለው ደስታ’ ምክንያት ነው። (ዕብ. 12:2) እኛም ልንደሰት እንችላለን። ለጽናታችን የምናገኘው ሽልማት በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ጽኑ መከራ ሲደርስብን ‘ደስ እንዲለንና ሐሤት እንድናደርግ’ እንገፋፋለን። (ማቴ. 5:11, 12) መከራ በሚደርስብን ጊዜ የሚኖረን ደስታ የመንግሥቱን መልዕክት በመደገፍ ለይሖዋ ምስጋናና ክብር እንድንሰጥ ያደርገናል።
14 በመጨረሻ ስለምናገኘው ነገር ተጠራጥረን ስጋት እንዲያድርብን ወይም ለምንወስደው እርምጃ ወሳኞች እንዳንሆን ምክንያት ሊሆነን ይገባልን? አይገባም። በይሖዋ ድርጅትና በሰይጣን ዓለም መካከል ያለው ግጭት የመጨረሻ ውጤት ከረጅም ጊዜ በፊት ተወስኗል። (1 ዮሐ. 2:15–17) ተቃውሞው ምንም ያህል ብርቱ ወይም ታላቅ ቢሆን ይሖዋ ድል ያቀዳጀናል። (ኢሳ. 54:17፤ ሮሜ 8:31, 37) ምንም እንኳን ብዙ ብንፈተንም ሽልማታችንን እንዳንቀበል የሚከለክለን ነገር ሊኖር አይችልም። ይሖዋ ለምናቀርብለት ምልጃ በምላሹ ሰላምን እንደሚሰጠን ስላረጋገጠልን ‘የምንጨነቅበት’ ምክንያት የለም። — ፊል. 4:6, 7
15 ስለዚህ ወንድሞቻችን ከስደት እንዴት እንደዳኑ ወይም በፊት ተከልክለው በነበሩባቸው ቦታዎች የመስበክ ነፃነት እንዳገኙ የሚገልጽ ሪፖርት በሰማን ቁጥር ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ሁኔታዎች ተለውጠው በሺህ የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት የሚሰሙባቸው አዳዲስ አጋጣሚዎች ሲገኙ ደስ ይለናል። ይሖዋ የሚጠሉን ተቃዋሚዎቻችንን እንድናሸንፍ በመፍቀዱ በጣም እናመሰግነዋለን። እውነተኛ አምልኮ የሚካሄድበትን ቤቱን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ከአሕዛብ ሁሉ “የተመረጡት” ወደ ቤቱ ለመምጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመስጠት አስፈላጊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ ሥራችንን እንደሚባርከውና እንደሚያሰፋው እናውቃለን። — ሐጌ 2:7፤ ኢሳ. 2:2–4
16 እንዲሁም ጠላታችን ሰይጣን በጣም ኃይለኛ መሆኑንና እስከ መጨረሻው ድረስ ባለው ኃይል ተጠቅሞ እንደሚዋጋንም በሚገባ እናውቃለን። ጥቃቱ ግልጽ ወይም ደግሞ ረቂቅና አታላይ ሊሆን ይችላል። በፊት ሰላም በነበረባቸው ቦታዎች በድንገት ስደት ሊነሣ ይችላል። ክፉ ተቃዋሚዎች በተንኮልና ፍትሕ በጎደለው ሁኔታ እኛን ለመጨቆን ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ሁሉ ‘በእርግጥ ከአምላክ ጋር እየተጣሉ’ እንዳሉ በጊዜው ግልጽ ይሆናል። እርሱም ጨርሶ ይደመስሳቸዋል። (ሥራ 5:38, 39፤ 2 ተሰ. 1:6–9) እስከዚያው ድረስ ምንም ነገር ቢደርስብን በታማኝነት ይሖዋን ከማገልገልና የመንግሥቱን መልዕክት ከመስበክ ፍንክች ላለማለት ቆርጠናል። እኛ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ደስተኞች ነን። ‘ከተፈተንን በኋላ የሕይወትን አክሊል እንደምንቀበል’ እናውቃለን። — ያዕቆብ 1:12