እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
1 ሁሉም ክርስቲያኖች ሌሎችን ስለ እውነት የማስተማርና “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግብ ሊኖራቸው ይገባል። (ሥራ 13:48 አዓት፤ ማቴ. 28:19, 20) የይሖዋ ድርጅት ይህን ለማድረግ የሚያስችል ግሩም መሣሪያ አዘጋጅቶልናል፤ ይህም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ነው። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ብቻውን እውነተኛ አምላክ ስለ ሆነው ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት በመቅሰማችን ላይ በመሆኑ የመጽሐፉ ርዕስ ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን አስፈላጊነት አጉልቶ ያሳያል።— ዮሐ. 17:3
2 በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት የሚያገለግለው ዋነኛው የማኅበሩ ጽሑፍ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ነው። ይህን መጽሐፍ በመጠቀም እውነትን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስተማር እንችላለን። ይህም የሚማሩትን ሰዎች ልብ ለመንካት ያስችላል። (ሉቃስ 24:32) እርግጥ፣ አስጠኚው ጥሩ የማስተማር ዘዴ መጠቀም ይኖርበታል። ይህንንም ማድረግ እንዲችል ውጤታማ ሆነው የተገኙ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በሚመለከት አንዳንድ ሐሳቦችንና ማሳሰቢያዎችን የያዘው ይህ አባሪ ጽሑፍ ተዘጋጅቷል። ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹን ወይም ሁሉንም ማስተዋል በተሞላበት መንገድና እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ቀስ በቀስ ልትሠሩባቸው ትችሉ ይሆናል። ይህን አባሪ ጽሑፍ ጥሩ ቦታ አስቀምጠህ በየጊዜው ተጠቀምበት። በውስጡ የተጠቀሱት የተለያዩ ነጥቦች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሊረዱህ ይችላሉ።
3 እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ምሩ፦ ተማሪው ወደፊት ክርስቲያን ደቀ መዝሙርና መንፈሳዊ ወንድም ወይም እህት እንደሚሆን በማሰብ በግልህ ከልብ የመነጨ አሳቢነት አሳየው። ሞቅ ያለ የፍቅር ስሜት፣ የመግባባት መንፈስና ግለት ይኑርህ። ጥሩ አዳማጭ ከሆንክ ስለ ግለሰቡ አስተዳደግና የኑሮ ሁኔታ ማወቅ ትችላለህ፤ ይህም እርሱን በተሻለ መልኩ በመንፈሳዊ መርዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድትገነዘብ ይረዳሃል። ተማሪውን በሚያስፈልገው ሁሉ ለመርዳት ራስህን በፈቃደኛነት አቅርብ።— 1 ተሰ. 2:8
4 አንድ ጊዜ ጥናት ከተጀመረ በኋላ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ምዕራፎች በቅደም ተከተላቸው ማጥናቱ የተሻለ ይሆናል። መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስ መወያያ ርዕሶችን ምክንያታዊ በሆነ ቅደም ተከተል ስለሚያስቀምጥ በዚህ መንገድ ማጥናቱ ተማሪው ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድ እውቀት እንዲያገኝ ያስችለዋል። ጥናቱ ሕያውና ቀጣይ እንዲሆን ቀላልና አስደሳች አድርገው። (ሮሜ 12:11) እንደ ተማሪው ሁኔታና ችሎታ በአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሳትጣደፉ አንድ ምዕራፍ መጨረስ ትችሉ ይሆናል። አስተማሪውም ሆነ ተማሪው በየሳምንቱ የጥናት ፕሮግራማቸውን አክብረው ሲገኙ ተማሪዎች የተሻለ እድገት ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ብዙ ሰዎች የመጽሐፉን 19 ምዕራፎች በስድስት ወር ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሊጨርሱ ይችሉ ይሆናል።
5 በእያንዳንዱ ጥናት መጀመሪያ ላይ ለትምህርቱ ፍላጎቱን የሚያሳድር አጭር የመግቢያ ሐሳብ ተናገር። ሊጎላ የሚገባው ጭብጥ ራሱ የምዕራፉ ርዕስ እንደሆነ ሳታስተውል አትቀርም። እያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ አንድ ዋና ነጥብ ብቻ የያዘ በመሆኑ በምዕራፉ ጭብጥ ላይ ለማተኮር ይረዳሃል። ብዙ ላለመናገር ተጠንቀቅ። ከዚያ ይልቅ ተማሪው ሐሳቡን እንዲገልጽ ለማድረግ ሞክር። ቀደም ሲል በሚያውቃቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ቀጥተኛ መሪ ጥያቄዎችን መጠየቅ ተማሪው እንዲያመዛዝንና ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ይረዳዋል። (ማቴ. 17:24-26፤ ሉቃስ 10:25-37፤ ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 51 አንቀጽ 10ን ተመልከት።) እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሠፈረውን ትምህርት በጥብቅ ተከተል። ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ማቅረብ ከዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ሊያስወጣችሁ ወይም ነጥቦቹ እንዲድበሰበሱ ሊያደርግ ከመቻሉም በላይ የጥናቱን ጊዜ ያራዝማል። (ዮሐ. 16:12) ከሚጠናው ርዕስ ጋር ግንኙነት የሌለው ጥያቄ ከተነሣ በአብዛኛው በጥናቱ መጨረሻ ልትመልስለት ትችላለህ። ይህም ወደሌላ ጉዳይ ሳትሄዱ የሣምንቱን ትምህርት ለመሸፈን ያስችላችኋል። ተማሪው የሚያነሣቸው አብዛኞቹ ጥያቄዎች በጥናቱ ወቅት ደረጃ በደረጃ እንደሚመለሱ አስረዳው።— ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 94 አንቀጽ 14ን ተመልከት።
6 ተማሪው በሥላሴ፣ በነፍስ አለመሞት፣ በሲኦል እሳት ወይም ይህን በመሰሉ ሌሎች የሐሰት ትምህርቶች አጥብቆ የሚያምን ከሆነና እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያለው ነገር ካላረካው ማመራመር፣ ለዘላለም መኖር፣ ብሮሹር ወይም ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ የሚያወሳ ሌላ ጽሑፍ ልትሰጠው ትችላለህ። ባነበበው ነገር ላይ ካሰበበት በኋላ እንደምትወያዩበት ንገረው።
7 የይሖዋን አመራርና በረከት ለማግኘት ፕሮግራሙን በጸሎት ጀምሮ በጸሎት መደምደም ጥናቱ ሥርዓታማ በሆነና አክብሮት በተሞላበት መንፈስ እንዲካሄድ ከማስቻሉም በላይ ዋነኛው አስተማሪ ይሖዋ መሆኑ እንዲተኮርበት ያደርጋል። (ዮሐ. 6:45) ተማሪው ገና ከሲጋራ ሱሱ ያልተላቀቀ ከሆነ በጥናቱ ወቅት ማጤሱን እንዲያቆም ቀስ ብለህ አንድ ቀን ልትጠይቀው ትችላለህ።— ሥራ 24:16፤ ያዕ. 4:3
8 በጥቅሶቹ፣ በምሳሌዎቹና በክለሳ ጥያቄዎቹ አማካኝነት ውጤታማ በሆነ መንገድ አስተምሩ፦ ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ አንድን ርዕስ ምንም ያህል ጊዜ ደጋግሞ ቢያጠናው የተማሪውን ሁኔታ በአእምሮው ይዞ እያንዳንዱን ምዕራፍ እንደገና ይከልሳል። ይህም ተማሪው ሊያነሳቸው የሚችላቸውን ጥያቄዎች በጉጉት እንዲጠብቅ ያደርገዋል። ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር በምዕራፉ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ለመረዳት ጣር። ጥቅሶቹ ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማገናዘብ እያወጣህ ካነበብህ በኋላ በጥናቱ ወቅት መነበብ የሚገባቸው ጥቅሶች የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድመህ ወስን። ምሳሌዎቹንና በየምዕራፉ መጨረሻ ላይ የሚገኙትን የክለሳ ጥያቄዎች ተጠቅመህ እንዴት ማስተማር እንደምትችል አስብ።
9 ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ተማሪው በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና እንዳለ እንዲገነዘብ ልትረዳው ትችላለህ። (ሥራ 17:11) እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 14 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስህን በደንብ ተጠቀምበት” የሚለውን ሣጥን ተጠቅመህ ጥቅስ እንዴት ማውጣት እንደሚቻል አስተምረው። በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ የሚገኙትን ጥቅሶች ለይቶ ማወቅ የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሳየው። ጊዜ በፈቀደልህ መጠን ሐሳባቸው ሳይገለጽ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተህ አንብብ። በአንቀጹ ውስጥ የተገለጸውንም ሐሳብ የሚደግፉት ወይም ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ እንዲናገር አድርግ። ጥቅሱ የቀረቡትን ዋና ዋና ነጥቦች እንዴት እንደሚደግፍ መረዳት እንዲችል የጥቅሱን ቁልፍ ክፍል ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። (ነህ. 8:8) አብዛኛውን ጊዜ አስተማሪው መጽሐፉ ውስጥ ከተሰጡት ውጭ ሌሎች ጥቅሶችን መጨመር አያስፈልገውም። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ስምና ቅደም ተከተል ማወቅ ያለውን ጠቀሜታ ግለጽለት። ተማሪው ሰኔ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 27-30 ያለውን ሐሳብ ማንበቡ ሊጠቅመው ይችላል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአዲሱ ዓለም ትርጉም እንዲጠቀም አበረታታው። የኅዳግ ማጣቀሻውንና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫውን የመሳሰሉትን የትርጉሙን የተለያዩ ገጽታዎች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ደረጃ በደረጃ ልታሳየው ትችላለህ።
10 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ጥናት 34 ላይ ምሳሌዎች አእምሮን በማመራመር አዳዲስ ሐሳቦችን በቀላሉ ለመጨበጥ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል። አእምሮን ያሳምናሉ፤ ስሜትንም ይነካሉ። ይህም በመሆኑ መልእክቱ በበለጠ ኃይል ወደ አእምሮ ይተላለፋል። ነገሩን በቀጥታ መግለጹ የዚህን ያህል ኃይል አይኖረውም። (ማቴ. 13:34) የእውቀት መጽሐፍ ቀላል የሆኑና ኃይለኛ መልእክት የሚያስተላልፉ በርካታ ምሳሌዎች ይዟል። ለምሳሌ ያህል በምዕራፍ 17 ውስጥ የተሠራበት ምሳሌ ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ ያለንን አድናቆት የሚገነባ ነው። እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን የሚያማምሩ ሥዕላዊ መግለጫዎችም የሰዎችን ስሜት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቀስቀስ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ተማሪው በገጽ 185 ላይ ከሚገኘው “አስደሳቹ ትንሣኤ” ከሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን አንቀጽ 18ን ከተመለከተ በኋላ ወደ ገጽ 86 ተመልሶ ሥዕሉን እንዲያይ ማድረጋችን ቀደም ሲል ያገኘውን የአንቀጹን መልእክት ይበልጥ ያጠናክርለታል። ይህ ደግሞ ትንሣኤ በአምላክ መንግሥት ግዛት እውን እንደሚሆን እንዲያስብ ሊያንቀሳቅሰው ይችላል።
11 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከእያንዳንዱ ትምህርት በኋላ መንፈሳዊ መሻሻል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ በሚገኘው “እውቀትህን ፈትሽ” በሚለው ሣጥን ውስጥ ያሉትን የክለሳ ጥያቄዎች መጠየቅ አትርሳ። የተጠናውን ትምህርት ትክክለኛ መልስ በመስማትህ ብቻ አትርካ። ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ብዙዎቹ ተማሪው በልቡ ውስጥ ያለውን የራሱን አመለካከት እንዲገልጽ ለማድረግ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በገጽ 31 ላይ “አንተን በተለይ የሚማርኩህ የትኞቹ የአምላክ ባሕርያት ናቸው?” በሚል የቀረበበትን ጥያቄ ተመልከት።— 2 ቆሮ. 13:5
12 ተማሪዎችን ለጥናቱ እንዲዘጋጁ አሰልጥኗቸው፦ ትምህርቱን አስቀድሞ የሚያነብ፣ መልሶቹ ላይ ምልክት የሚያደርግና በራሱ አባባል እንዴት እንደሚመልስ አስቦ የሚመጣ ተማሪ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ያደርጋል። ራስህ ምሳሌ በመሆንና በማበረታታት ለጥናቱ እንዲዘጋጅ ልታሰለጥነው ትችላለህ። ቁልፍ በሆኑት ቃላትና ሐረጎች ላይ ያሰመርህበትን የራስህን መጽሐፍ አሳየው። ለጥያቄዎቹ ቀጥተኛ መልስ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አስረዳው። አንድ ምዕራፍ አብራችሁ መዘጋጀታችሁ ተማሪውን ሊጠቅመው ይችላል። የተረዳውን ነገር በራሱ አገላለጽ እንዲናገር አበረታታው። ትምህርቱ ገብቶት እንደሆነና እንዳልሆነ መረዳት የሚቻለው በራሱ አገላለጽ ሲናገር ነው። ከመጽሐፉ ላይ እያነበበ የሚመልስ ከሆነ ይህን ነጥብ በራሱ አባባል ለሌላ ሰው እንዴት ሊያስረዳ እንደሚችል በመጠየቅ አእምሮውን እንዲያሠራ ልታደርግ ትችላለህ።
13 በጥናቱ ወቅት ሁሉንም ጥቅሶች ለማንበብ ጊዜ ላይበቃ ስለሚችል ተማሪው በሳምንቱ መሃል ሲዘጋጅ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሰውን ጥቅሶች እያወጣ እንዲያነብ አበረታታው። ለትምህርቱ ስለሚያሳየው ትጋት አመስግነው። (2 ጴጥ. 1:5፤ ጥናቱ ውጤታማ እንዲሆን አስተማሪውም ሆነ ተማሪው ምን ማድረግ እንደሚችሉ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የነሐሴ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-14ን ተመልከት።) በዚህ መንገድ ተማሪው ለጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀትና ትርጉም ያለው ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችለውን ሥልጠና ያገኛል። እውቀት በተባለው መጽሐፍ የሚደረገው ጥናት ካበቃ በኋላ በእውነት ውስጥ እድገት እያደረገ እንዲቀጥል የሚያስችለውን ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እንዴት ማዳበር እንደሚችል ይማራል።— 1 ጢሞ. 4:15፤ 1 ጴጥ. 2:2
14 ተማሪዎችን በይሖዋ ድርጅት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ፦ ተማሪው በይሖዋ ድርጅት ላይ እንዲያተኩር የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ደቀ መዝሙር አድራጊው ነው። ተማሪው ከድርጅቱ ጋር ከተዋወቀና አድናቆት ካደረበት እንዲሁም የድርጅቱ ክፍል የመሆንን አስፈላጊነት ከተገነዘበ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና የበለጠ ፈጣን እድገት ያደርጋል። ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመተባበሩ እንዲደሰትና ከክርስቲያን ጉባኤ የሚገኘውን መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ ሊያገኝ ወደሚችልበት የመንግሥት አዳራሽ የመምጣት ጉጉት እንዲያድርበት እንፈልጋለን።— 1 ጢሞ. 3:15
15 በዓለም ዙሪያ እንደ አንድ አካል ሆነው የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው ዛሬ ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ከሚጠቀምበት ብቸኛው ምድራዊ ድርጅት ጋር ሰዎችን ለማስተዋወቅ ታስቦ ነው። ጥናት ከተጀመረ በኋላ ለተማሪው ለምን አንድ ቅጂ አትሰጠውም? ከመጀመሪያ አንስቶ ተማሪው በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ከመጋበዝ ወደኋላ አትበል። ስብሰባዎቹ እንዴት እንደሚካሄዱ አስረዳው። በሚቀጥለው ጊዜ የሚቀርበውን የሕዝብ ንግግር ርዕስ ልትነግረው ወይም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት የሚጠናውን ርዕስ ልታሳየው ትችላለህ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ ቦታ በመሄዱ ሊፈጠርበት የሚችለውን ጭንቀት ለማቃለል ስብሰባ በሌለበት ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሹ ወስደህ ልታሳየው ትችላለህ። ወደ ስብሰባው አብሮህ በመኪና እንዲሄድ ልታደርግ ትችል ይሆናል። በዚያም ሲገኝ ዘና እንዲልና እንግድነት እንዳይሰማው አድርግ። (ማቴ. 7:12) ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከሌሎች ምሥክሮች ጋር አስተዋውቀው። ጉባኤውን እንደ መንፈሳዊ ቤተሰቡ አድርጎ መመልከት እንደሚጀምር አያጠራጥርም። (ማቴ. 12:49, 50፤ ማር. 10:29, 30) በሳምንት ቢያንስ በአንድ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ግብ ልታወጣለትና ከዚያም ቀስ እያልክ ግቡን ልታሳድገው ትችል ይሆናል።— ዕብ. 10:24, 25
16 እውቀት በተባለው መጽሐፍ በሚያደርገው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየገፋ ሲሄድ አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከጉባኤው ጋር የመተባበሩን አስፈላጊነት የሚያጎሉትን ክፍሎች ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። በተለይ ገጽ 52, 115, 137-9, 159 እና ምዕራፍ 17ን ተመልከት። ለይሖዋ ድርጅት ያለህን ጥልቅ አድናቆት ንገረው። (ማቴ. 24:45-47) ስላለህበት ጉባኤና በስብሰባዎቹ ላይ ስለምትማራቸው ነገሮች አዎንታዊ ነገር ተናገር። (መዝ. 84:10፤ 133:1-3) ተማሪው የይሖዋ ምሥክሮች— ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት ከሚለው አንሥቶ ማኅበሩ ያዘጋጃቸውን የቪዲዮ ክሮች በሙሉ ቢመለከት ጥሩ ነው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በድርጅቱ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 11-105 ገጽ 7-9 እንዲሁም የሚያዝያ 1993 መንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ጽሑፍ ተመልከት።
17 ተማሪዎች ለሌሎች እንዲመሠክሩ አበረታቷቸው፦ ከሰዎች ጋር የምናጠናበት ዓላማ ለይሖዋ የሚመሠክሩ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ነው። (ኢሳ. 43:10-12) ይህም ማለት ተማሪው ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማራቸውን ነገሮች ለሌሎች ሰዎች እንዲያካፍል አስተማሪው ሊያበረታታው ይገባል ማለት ነው። “ይህን እውነት ለቤተሰቦችህ እንዴት አድርገህ ታስረዳቸዋለህ?” ወይም “ይህን ነገር ለጓደኛህ ለማስረዳት በየትኛው ጥቅስ ትጠቀማለህ” የሚሉትን የመሰሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ብቻ ለሌሎች እንዲናገር ማበረታታት ይቻላል። እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ለሌሎች መመሥከርን የሚያበረታቱ ሐሳቦች የሚገኙባቸውን እንደ ገጽ 22, 93-5, 105-6, እንዲሁም እንደ ምዕራፍ 18 ባሉት ቁልፍ ቦታዎች ላይ ስትደርስ ጠበቅ አድርገህ ግለጽለት። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተማሪው ለሌሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት ለመስጠት እንዲጠቀምባቸው ጥቂት ትራክቶች ልትሰጠው ትችላለህ። የቤተሰቡን አባላት በጥናቱ ላይ እንዲገኙ እንዲጋብዛቸው ሐሳብ አቅርብለት። ማጥናት የሚፈልጉ ጓደኞች አሉትን? ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እንዲጠቁምህ ጠይቀው።
18 ዕጩው ደቀ መዝሙር በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ ላይ በመገኘቱ የምሥራቹ አስፋፊ እንዲሆን የሚያስችለውን ተጨማሪ ሥልጠናና ማነቃቂያ ያገኛል። በትምህርት ቤቱ ለመመዝገብ ወይም ደግሞ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል እንደሚፈልግ ሲገልጽ ጥያቄው አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ገጽ 98 እና 99 ላይ በተዘረዘሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት ይታያል። ለዚህ እንዳይበቃ የሚያግደው የሕይወቱ ዘርፍ ካለ ስለዚያ ጉዳይ የሚያብራሩትን የማኅበሩን ጽሑፎች ፈልገህ ትምህርቱን ልታካፍለው ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል አንድ ተማሪ ከሲጋራ ወይም ሌላ ዓይነት የዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ተቸግሮ ይሆናል። ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ጎጂ ልማዶች መላቀቅ የሚገባቸው ለምን እንደሆነ የሚገልጹ ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶችን ካቀረበ በኋላ በገጽ 112 ላይ ሰዎች ከእነዚህ ሱሶች እንዲላቀቁ በመርዳት በኩል ውጤታማ ሆነው የተገኙ ዘዴዎችን ይዘረዝራል። ስለጉዳዩ ከእርሱ ጋር ሆነህ ጸልይ፤ እርዳታ ለማግኘት በይሖዋ ላይ መታመንን እንዴት ማዳበር እንደሚችል አስተምረው።— ያዕ. 4:8
19 አንድ ሰው ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ለመካፈል ብቁ መሆንና አለመሆኑን ለመወሰን ልንከተለው የሚገባን አሠራር በጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 አንቀጽ 6 ላይ ሠፍሮ ይገኛል። ተማሪው ብቁ ሆኖ ሲገኝ ለመጀመሪያ ወደ መስክ አገልግሎት ከመውጣቱ በፊት ልምምድ የምታደርጉበት ፕሮግራም ማውጣታችሁ ጠቃሚ ነው። በአገልግሎት ክልላችሁ ውስጥ ስለ ተለመዱት የሰዎች ምላሽና ተቃውሞዎች አዎንታዊ በሆነ መንገድ አወያየው። በተቻለ መጠን በመጀመሪያ ከቤት ወደ ቤት ይዘኸው ሂድ፤ በሌሎቹ የአገልግሎት ዘርፎችም ቀስ በቀስ ታሠለጥነዋለህ። አቀራረብህ አጭርና ቀላል ከሆነ በቀላሉ ሊቀዳው ይችላል። የአንተን መንፈስ እንዲኮርጅና እንዲያንጸባርቅ የምታንጽና የምታበረታታ ሁን፤ በአገልግሎት እንደምትደሰትም በግልጽ ይታይ። (ሥራ 18:25) አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር አዘውታሪና ቀናተኛ የምሥራቹ አስፋፊ የመሆን ግብ ሊኖረው ይገባል። ለአገልግሎት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም በማውጣት በኩል ልትረዳው ትችል ይሆናል። ለሌሎች የመመሥከር ብቃቱን ለማሻሻል እንዲችል የነሐሴ 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15-25፤ 14-109 ገጽ 10-26፤ ጥር 15, 1991 ገጽ 15-20 እንዲሁም ጥር 1, 1994 ገጽ 20-5ን እንዲያነብ ሐሳብ ልታቀርብለት ትችላለህ።
20 ተማሪዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት እንዲደርሱ አበረታቷቸው፦ አንድ ቅን ልብ ያለው ተማሪ እውቀት በተባለው መጽሐፍ የሚያደርገው ጥናት ራሱን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያበቃው መሆን ይኖርበታል። (ከሥራ 8:27-39ና ከ16:25-34 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ለመወሰን ከመነሣቱ በፊት ለይሖዋ የማደርን ባሕርይ በውስጡ መኮትኮት ያስፈልገዋል። (መዝ. 73:25-28) በጥናቱ ወቅት ለይሖዋ ባሕርያት ያለውን አድናቆት ለመገንባት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ለማግኘት ሞክር። ስለ አምላክ የሚሰማህን የራስህን ውስጣዊ ስሜት ንገረው። ተማሪው ከይሖዋ ጋር ሞቅ ያለ የግል ዝምድና ስለ መመሥረት እንዲያስብ እርዳው። ለአምላክ ያደሩ መሆን በግለሰብ ደረጃ ስለ ይሖዋ ከሚሰማን ስሜት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተማሪው አምላክን ለማወቅና ለመውደድ ከቻለ በታማኝነት ያገለግለዋል።— 1 ጢሞ. 4:7, 8 አዓት፤ ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 76 አንቀጽ 11ን ተመልከት።
21 የተማሪውን ልብ ለመንካት ጣር። (መዝ. 119:11፤ ሥራ 16:14፤ ሮሜ 10:10) ተማሪው እውነት በግሉ እንዴት እንደሚነካው ማስተዋልና በተማረው መሠረት ምን ማድረግ እንደሚኖርበት መወሰን ያስፈልገዋል። (ሮሜ 12:2) በየሳምንቱ የሚማረውን እውነት በእርግጥ ያምንበታልን? (1 ተሰ. 2:13) ይህንንም ለማድረግ እንደሚከተሉት ያሉትን አንዳንድ ማስተዋል የተሞላባቸው የአመለካከት ጥያቄዎች በመጠየቅ ስሜቱን እንዲገልጽ ማድረግ ትችላለህ:- ስለዚህ ጉዳይ አንተ ምን ይሰማሃል? ይህንን ነገር በሕይወትህ ውስጥ ልትሠራበት የምትችለው እንዴት ነው? ተማሪው ከሚሰጣቸው አስተያየቶች ልቡን ለመንካት ይበልጥ በምን በኩል እርዳታ እንደሚያስፈልገው ለማስተዋል ትችል ይሆናል። (ሉቃስ 8:15 ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ገጽ 51 አንቀጽ 11ን ተመልከት።) እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 172 እና 174 ላይ የሚገኙት ስዕሎች መግለጫዎች እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎች ያቀርባሉ:- “ራስህን መወሰንህን ለአምላክ በጸሎት አስታውቀሃልን?”፣ “እንዳትጠመቅ የሚከለክልህ ምንድን ነው?” እነዚህ ጥያቄዎች ተማሪውን ለድርጊት ሊያንቀሳቅሱት ይችላሉ።
22 አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ መጠመቅ ሲፈልግ የምንከተለው አሠራር በጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17 አንቀጽ 9 ላይ ሠፍሯል። እውቀት የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው አንድ ሰው ሽማግሌዎች ከእርሱ ጋር የሚከልሷቸውን አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ተጨማሪ ክፍል ላይ የሚገኙትን ‘ለመጠመቅ ለሚፈልጉ የሚቀርቡትን’ ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረዳው ታስቦ ነው። እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡትን ጥያቄዎች መልስ በግልጽ ካስረዳኸው ተማሪው ለጥምቀት ሲዘጋጅ ከሽማግሌዎች ጋር ለሚወያይባቸው ጥያቄዎች በሚገባ የተዘጋጀ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
23 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጨረሱትን እርዷቸው፦ አንድ ሰው እውቀት በተባለው መጽሐፍ ጥናቱን ሲያጠናቅቅ አምላክን ለማገልገል የሚኖረው ልባዊ ፍላጎትና ጥልቅ ምኞት በግልጽ መታየቱ የሚጠበቅ ነገር ነው። (ማቴ. 13:23) የመጽሐፉ የመጨረሻ ንዑስ ርዕስ “ምን ለማድረግ ታስባለህ?” የሚል ጥያቄ የሚያቀርበው ለዚህ ነው። የመደምደሚያዎቹ አንቀጾች ተማሪው ከአምላክ ጋር ስለ መሠረተው ዝምድና፣ ያገኘውን እውቀት በሥራ ላይ ማዋሉ አስፈላጊ ስለመሆኑና ለይሖዋ ያለውን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት እንዲያስብ ያበረታቱታል። የእውቀት መጽሐፍ ከጨረሱ ሰዎች ጋር ተጨማሪ ጽሑፎች ለማጥናት የተደረገ ዝግጅት የለም። ለአምላክ እውቀት ምላሽ መስጠት የተሳነው ተማሪ ካለ በመንፈሳዊ ለማደግ ምን ማድረግ እንዳለበት በደግነትና ግልጽ በሆነ መንገድ አስረዳው። አልፎ አልፎ እየሄድክ በማነጋገር የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን እርምጃ እንዲወስድ በሩን ክፍት ልታደርግለት ትችላለህ።— መክ. 12:13
24 አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር እውነትን መያዙን ግልጽ ካደረገና ከተጠመቀ በኋላ በእምነት ሙሉ በሙሉ እንዲጸና በእውቀትና በማስተዋል ገና ብዙ ማደግ ይኖርበታል። (ቆላ. 2:6, 7 አዓት) እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አጥንታችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ከመቀጠል ይልቅ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርስ የሚያስፈልገውን እርዳታ በግል ለመስጠት ራስህን ፈቃደኛ አድርገህ ልታቀርብ ትችላለህ። (ገላ. 6:10፤ ዕብ. 6:1) እርሱም በበኩሉ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ መጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ የሚያወጣቸውን ጽሑፎች በግሉ በማጥናት፣ ለስብሰባ በመዘጋጀትና ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም ከመሰል አማኞች ጋር ስለ እውነት በመወያየት እውቀቱን ማስፋት ይችላል። (ማቴ. 24:45-47፤ መዝ. 1:2፤ ሥራ 2:41, 42፤ ቆላ. 1:9, 10) አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ማንበቡና ከዚያ ያገኘውን ነገር ተግባራዊ ማድረጉ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተደራጀ እንዲሆን ትልቅ ሚና ይጫወታል።— 2 ጢሞ. 2:2፤ 4:5
25 የማስተማር ችሎታችሁን አዳብሩ፦ ሰዎችን ‘እያስተማርን ደቀ መዛሙርት የማድረግ’ ተልእኮ ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) የማስተማር ችሎታና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የማይነጣጠሉ ነገሮች በመሆናቸው የአስተማሪነት ችሎታችንን ለማሻሻል መጣጣር ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 4:16፤ 2 ጢሞ. 4:2) የማስተማር ችሎታን ማዳበር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚከተሉትን ጽሑፎች ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል:- “የማስተማርን ችሎታ ማዳበር” እና “የአድማጮችህን ልብ መንካት” ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ጥናት 10 እና 15፤ “አስተማሪ፣ ትምህርት” [“Teacher, Teaching”] ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2፤ እንዲሁም ከመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች:- “እሳትን በሚቋቋሙ ነገሮች መገንባት” እና “ስታስተምር ልቡን ለመንካት ሞክር” 8-105፤ “ማሳመን እንደምትችል አድርገህ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀስህ ታስረዳለህን?” 3-107 እና “ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?” የካቲት 15, 1996
26 እውቀት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅመህ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስትጥር ‘የሚያሳድገው’ ይሖዋ በመንግሥቱ ምሥራች የሰዎችን ልብ ለመንካት የምታደርገውን ጥረት እንዲባርክልህ ዘወትር ጸልይ። (1 ቆሮ. 3:5-7) ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ፣ እንዲያደንቁና ካገኙት እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለሱ በማስተማር ደስታ እንድታገኝ እንመኝልሃለን!