በማንኛውም ቦታ ምሥራቹን ስበኩ
1 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በማንኛውም ቦታ ምሥራቹን ይሰብኩ ነበር። ከነበራቸው ከፍተኛ ቅንዓት የተነሣ ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ በነበሩት 30 ዓመታት ውስጥ የመንግሥቱን መልእክት “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረታት ሁሉ ዘንድ” ማዳረስ ችለው ነበር።— ቆላ. 1:23
2 ዛሬ ያሉትም የይሖዋ ቀናተኛ አገልጋዮች ዓላማቸው በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ሰው የመንግሥቱን ምሥራች ማድረስ ነው። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? የሙሉ ቀን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ስለመጣ ብዙውን ጊዜ ቤታቸው ስንሄድ ሰዎቹን ሳናገኛቸው እንቀራለን። ሥራ በማይኖራቸው ጊዜ ደግሞ ወደሌላ ከተማ ይሄዳሉ፣ ገበያ ይወጣሉ ወይም ደግሞ ወደ መዝናኛ ሥፍራዎች ይሄዳሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ለሚገባቸው የመንግሥቱን መልእክት ማድረስ የሚቻለው እንዴት ነው?— ማቴ. 10:11
3 አንዳንዶቹ በሥራ ቦታቸው ምሥራቹ ይደርሳቸዋል። በትናንሽ ከተሞች እንኳ ቀኑን ሙሉ ሰው የማይጠፋባቸው የንግድ ማዕከሎች አሉ። በትላልቅ ከተሞች ውስጥ በኢንዱስትሪ ክልሎች ወይም በትላልቅ የመሥሪያ ቤት ሕንፃዎች ውስጥ የሚሠሩና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው አፓርተማዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ምሥራቹ እየደረሳቸው ሲሆን ብዙዎቹ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ መስማታቸው ነው። ቅዳሜና እሁድ በመናፈሻዎችና በመዝናኛ ቦታዎች ሲንሸራሸሩ ወይም በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ወይም በገበያ ቦታዎች የተገኙት አንዳንዶቹ ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ አመለካከት አሳይተዋል።
4 በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አስፋፊዎች ሰዎች በሚገኙባቸው የተለያዩ ሥፍራዎች ሁሉ ለመመሥከር ልዩ ጥረት እያደረጉ ነው። እነዚህ ምሥክሮች መጀመሪያ አካባቢ የማመንታትና የፍርሃት ስሜት አድሮባቸው ነበር። ሌሎች ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እንደማገልገል በመሰለው መደበኛ መንገድ መሥራት አልተለማመዱም ነበር። አንዳንዶች የተለያዩ የስብከት ዘርፎችን ከሞከሩ በኋላ እንዴት ተሰምቷቸዋል?
5 አንድ የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያለው ወንድም “አገልግሎቴ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል” ብሏል። ሌላ ወንድም ደግሞ “በአገልግሎቴ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል” ሲል ተናግሯል። አንድ በዕድሜ የገፋ አቅኚ “አእምሮን፣ አካልንና መንፈስን የሚያድስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ . . . አሁንም ገና እድገት በማድረግ ላይ ነኝ!” ሲል ገልጿል። አንድ አስፋፊ ከአሁን በፊት ጨርሶ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተነጋግረው የማያውቁ ብዙ ሰዎች እያገኘ እንዳለ ተናግሯል። ወጣቶችም በዚህ አስደሳች ሥራ ውስጥ በግለት እየተካፈሉ ነው። አንድ ወጣት “ብዙ ሰዎች ማነጋገር ስለሚያስችል በጣም ደስ ያሰኛል!” በማለት የተሰማውን ገልጿል። ሌላ ወጣት ደግሞ “እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ያህል ጽሑፍ አበርክቼ አላውቅም!” ብሏል።
6 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ግንባር ቀደም ሆነዋል፦ ማኅበሩ “የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ” መሆኑን በመገንዘብ ምሥራቹን የተቻለውን ያህል ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ይቻል ዘንድ ተጓዠ የበላይ ተመልካቾች የመስክ አገልግሎት ፕሮግራማቸውን በየሳምንቱ እንዲያስተካክሉ ሐሳብ አቅርቧል። (1 ቆሮ. 7:31 አዓት) ለብዙ ዓመታት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በሳምንቱ የሥራ ቀናት በሙሉ ጠዋት ጠዋት ከቤት ወደ ቤት ለመሥራትና ከሰዓት በኋላ ደግሞ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና ጥናት ለመምራት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ፕሮግራም አሁንም ተግባራዊ ሊሆን ይችል ይሆናል። በሌሎቹ አካባቢዎች ደግሞ ጠዋት ከሱቅ ወደ ሱቅ ወይም በመንገድ ላይ ምሥክርነት መሠማራት ጥሩ እንደሆነ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ሊወስን ይችላል። ወይም ደግሞ ትናንሽ ቡድኖች በመሥሪያ ቤት ሕንጻዎች፣ በገበያ አካባቢ፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች አለዚያም በሌሎች የሕዝብ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተሠማርተው እንዲያገለግሉ ዝግጅት ሊያደርግ ይችል ይሆናል። አስፋፊዎች ለአገልግሎት የመደቡትን ጊዜ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሲጠቀሙበት ብዙ ሰዎችን ማነጋገር ይችላሉ።
7 ይህ ማስተካከያ በተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ሆነ በአስፋፊዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እንዳገኘ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በርካታ የሽማግሌዎች አካላት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤው ትኩረት ሊሰጠው በሚገባው መስክ ጥቂት ወንድሞችን እንዲያሰለጥኑላቸው ግብዣ አቅርበዋል። እነዚህ አስፋፊዎች ከተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ጋር በእነዚህ ዘርፎች አብረው ማገልገላቸው ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። እነርሱም በተራቸው ሌሎችን ማሠልጠን ችለዋል። (2 ጢሞ. 2:2) በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ምሥራቹ እየደረሳቸው ነው።
8 እርግጥ ከእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች በአንዱ ለመሳተፍ ስትፈልግ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ አለብህ ማለት አይደለም። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን አንዳንድ ሐሳቦች በአንተም የአገልግሎት ክልል ተግባራዊ ሆነው ታገኛቸው ይሆናል:-
9 የመንገድ ላይ ምሥክርነት፦ መጽሔቶችን ይዞ አንድ ቦታ ከመቆም ይልቅ ወደ ሰዎች ቀረብ ብሎ ወዳጃዊ ውይይት መጀመሩ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። ለሚያልፈው ሰው ሁሉ መመሥከር አለብን ማለት አይደለም። እንዲሁ እየዞሩ ገበያ የሚያዩ ሰዎችን፣ በቆመ መኪና ውስጥ የተቀመጡትን ወይም ትራንስፖርት የሚጠብቁትንና የመሳሰሉትን የማይቸኩሉ ሰዎች አነጋግር። በመጀመሪያ ወዳጃዊ ሰላምታ ካቀረብህ በኋላ ምላሽ እስኪሰጥህ ድረስ ጠብቅ። ሰውየው ለመነጋገር ፈቃደኛ ከሆነ ፍላጎቱን ይቀሰቅሳል ብለህ ባሰብከው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት ጠይቀው።
10 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አንድ ጉባኤ ሲጎበኝ ስድስት አስፋፊዎች ከእርሱና ከባለቤቱ ጋር በመንገድ ላይ በሚደረገው የምሥክርነት ሥራ አብረዋቸው እንዲካፈሉ ጋበዛቸው። ተግተው በመሥራታቸው ብዙ ሰዎችን አነጋግረው ነበር። ምን ውጤት አገኙ? እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በጣም ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍን። ሰማንያ መጽሔቶችንና ብዙ ትራክቶችን አበርክተናል። በርካታ የሚያነቃቁ ውይይቶችንም አድርገናል። ከአስፋፊዎቹ መካከል አንዱ በመንገድ ላይ ምሥክርነት ሲሰማራ የመጀመሪያው ጊዜ ሲሆን ‘ለበርካታ ዓመታት እውነት ውስጥ ስኖር ይህን የመሰለ ነገር እንዳመለጠኝ አልተገነዘብኩም ነበር’! ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በጉባኤ ውስጥ ተከማችቶ የነበረው መጽሔት ሁሉ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተሟጥጧል።”
11 ፍላጎት ያለው ሰው ሲያጋጥምህ የሰውዬውን ስም፣ አድራሻና የስልክ ቁጥር ለማግኘት ሞክር። አድራሻውን እንዲሰጥህ ቀጥታ ከመጠየቅ ይልቅ እንደሚከተለው ለማለት ትችል ይሆናል:- “ዛሬ ያደረግነው ውይይት በጣም አስደስቶኛል። ይህን ውይይት ሌላ ጊዜ መቀጠል የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?” ወይም “ቤትዎ መጥቼ ልጠይቅዎ የምችልበት መንገድ ይኖራል?” ብለህ ጠይቀው። በዚህ መንገድ የተገኙ ብዙ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግላቸው ፈቃደኞች ሆነዋል።
12 በሌላ ጉባኤ የአገልግሎት ክልል ውስጥ የሚኖር ፍላጎት ያለው ሰው ካገኘህ እዚያ ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞች ፍላጎቱ ሳይጠፋ በፊት ተከታትለው ሊረዱት እንዲችሉ መረጃዎቹን ማስተላለፍ ይኖርብሃል። በእናንተ አካባቢ ምሥራቹን ለማስፋፋት የመንገድ ላይ ምሥክርነት ውጤታማ ሆኖ ይገኝ ይሆን? ከሆነ በሐምሌ 1994 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ “ውጤታማ በሆነ የመንገድ ላይ ምሥክርነት ፍላጎት ያላቸውን ማግኘት” በሚል ርዕስ የወጣውን ሐሳብ ከልስ።
13 በሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ መመሥከር፦ አንድ ቀን ጠዋት ጥቂት አቅኚዎች በክልላቸው ውስጥ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ አቅራቢያ ቆመው አውቶቡስ ለሚጠብቁት ሰዎች ለመመሥከር ወሰኑ። አንዳንድ አስደሳች ውይይቶችን ማድረግ ቢችሉም ችግር ገጠማቸው። ውይይቱ ሞቅ ብሎ እያለ አውቶቡሷ ትመጣና ለጀመሩት ውይይት መቋጫ ሳያበጁለት ይቋረጣል። አቅኚዎቹ ከተማውን አቋርጣ በምትሄደው አውቶቡስ ተሳፍረው ለታሳፋሪዎቹ መመሥከራቸውን በመቀጠል ለችግሩ መላ አበጁለት። አቅኚዎቹ የአውቶቡሱ ማዞሪያ ላይ ሲደርሱም በሄዱበት አኳኃን እየመሠከሩ ይመለሳሉ። እንዲህ እየተመላለሱ በርካታ ጉዞዎችን ካደረጉ በኋላ የጥረታቸው ውጤት አንድ ላይ ሲደመር ከ200 በላይ መጽሔቶችን ከማበርከታቸውም ሌላ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ችለው ነበር! አንዳንዶቹ መንገደኞች ወንድሞች እቤታቸው ሄደው እንዲጠይቋቸው ሲሉ አድራሻቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን ሰጥተዋቸዋል። በሚቀጥለውም ሳምንት አቅኚዎቹ እንደገና ወደ አውቶቡስ ማቆሚያው በመሄድ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቀሙ። በዚህ ወቅት 164 መጽሔቶችን ለማበርከትና አንድ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ችለዋል!
14 ብዙ አስፋፊዎች በአውቶቡስ፣ በባቡር ወይም በአውሮፕላን ሲጓዙ ውጤታማ ምሥክርነት ይሰጣሉ። አጠገብህ ከተቀመጠው ተሳፋሪ ጋር ውይይት መጀመር የምትችለው እንዴት ነው? አንድ የ12 ዓመት ዕድሜ ያለው አስፋፊ አውቶቡስ ውስጥ አጠገቡ የተቀመጠችው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ጉጉት ያድርባት ይሆናል ብሎ በማሰብ ንቁ! መጽሔቱን አውጥቶ ማንበብ ይጀምራል። ያሰበው ነገር ተሳካለት! ልጅቷ ምን እንደሚያነብ ስትጠይቀው ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መወጣት እንደሚችሉ የሚገልጽ ጽሑፍ መሆኑን ይነግራታል። አክሎም ከዚህ ርዕስ ብዙ እንደተጠቀመና እርሷንም ይጠቅማታል ብሎ እንደሚያምን ገለጸላት። ደስ ብሏት መጽሔቱን ወሰደች። ሌሎች ደግሞ አጠገባቸው ላለው ሰው አንድ የሚነበብ ነገር አውጥተው ይሰጡታል።
15 በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች መመሥከር፦ የአየሩ ጠባይ አመቺ በሚሆንበት ጊዜ በመናፈሻዎችና በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች መመሥከር ሰዎችን ለማግኘት የሚያስችል በጣም ግሩም ዘዴ ነው። በገበያ ማዕከሎች የመኪና ማቆሚያ ቦታ ለመመሥከር ሞክረህ ታውቃለህን? የማይቸኩል ወይም መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ ሰው የሚጠብቅ ሰው ፈልገህ በወዳጅነት መንፈስ ውይይት ለመጀመርና የመንግሥቱን መልእክት ለመናገር ሞክር። አብሮህ ያለው አስፋፊ ከቦታው ሳይርቅ ለየብቻ ሆናችሁ ለመሥራት ሞክሩ። አስተዋይ ሁኑ። በአንድ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ጥቂት ጊዜ ብቻ ከሠሩ በኋላ ወደሌላው መሸጋገሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሰውዬው ለመወያየት የማይፈልግ ሆኖ ካገኘኸው በትሕትና ተለያይተህ ሌላ ሰው ፈልግ። አንድ ወንድም እነዚህን ዘዴዎች ተጠቅሞ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ሲያገለግል በአንድ ወር ውስጥ 90 መጽሔቶችን አበርክቷል!
16 ከሱቅ ወደ ሱቅ ማገልገል፦ በአንዳንድ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልል ውስጥ የንግድ አካባቢዎች ይገኛሉ። የአገልግሎት ክልሎችን የሚያዘጋጀው ወንድም በጣም የተጨናነቁ የንግድ ክልሎችን የሚያሳይ ልዩ የአገልግሎት ክልል ካርዶችን ሊያዘጋጅ ይችላል። በእነዚህ የተጨናነቁ የንግድ ክልሎች መካከል የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ያቀፈ ማንኛውም የአገልግሎት ክልል ካርታ ካርድ የንግድ ክልሎቹ ለብቻ የሚሸፈኑ መሆናቸውን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ሊኖረው ይገባል። በሌሎች የአገልግሎት ክልሎች የሚገኙ የንግድ ቤቶች ከመኖሪያ ቤቶች ጋር አብረው ሊሸፈኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ከሱቅ ወደ ሱቅ የማገልገሉ ሥራ ቸል እንዳይባል ሲሉ በንግድ ክልሎች ውስጥ እንዲሠሩ ብቃት ያላቸውን አስፋፊዎች ሊመድቡ ይችላሉ።
17 በዚህ የአገልግሎት መስክ እንድትካፈል ግብዣ ከቀረበልህና ልምዱ ከሌለህ በመጀመሪያ አነስ አነስ ያሉትን ጥቂት ሱቆች መሥራትና ይበልጥ የመተማመን ስሜት ስታገኝ ወደ ትላልቆቹ ሱቆች መሻገር ‘ድፍረት ለማግኘት የሚያስችል’ ጥሩ ዘዴ ነው። (1 ተሰ. 2:2) ከሱቅ ወደ ሱቅ ስታገለግል በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በስብሰባ ላይ ስትገኝ የሚኖርህን ዓይነት አለባበስ ይኑርህ። የሚቻል ከሆነ ለመስተናገድ የሚጠብቁ ደንበኞች በሌሉበት ጊዜ ብትገባ ጥሩ ነው። አስተዳዳሪውን ወይም ኃላፊነት ያለውን ሰው ለማነጋገር እንደምትፈልግ ግለጽ። ሞቅ ያለ ስሜት ይኑርህ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ነገር አታስረዝም። እንዳስቸገርካቸው ተሰምቶህ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልግህም። ብዙዎቹ የንግድ ሥራዎች ከብዙ ደንበኞች ጋር የሚያገናኙ በመሆናቸው ቀርበን ስናነጋግራቸው ሥራ እንዳስፈታናቸው ሆኖ አይሰማቸውም።
18 ከሻጩ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “በንግድ ሥራ የተሠማሩ ሰዎች ጊዜያቸው በሙሉ የተያዘ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ቤታቸው አናገኛቸውም፤ በዚህም ምክንያት አንድ አእምሮን የሚያመራምር ርዕስ እንዲያነቡ ስለፈለግን ሱቅዎ ድረስ መጥተናል።” ከዚያም በቅርቡ ከወጣ መጽሔት አንድ ወይም ሁለት ሐሳብ ጥቀስ።
19 ወይም ከአስተዳዳሪው ጋር ስትነጋገር የሚከተለውን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:- “በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ስለ ተለያዩ ነገሮች በቂ መረጃ ለማግኘት እንደሚጥሩ አስተውለናል። በቅርቡ የወጣው መጠበቂያ ግንብ (ወይም የንቁ!) መጽሔት ሁላችንንም በግል የሚነካ አንድ ርዕስ ይዞ ወጥቷል።” ይህ ርዕስ ምን እንደሆነ ከገለጽህ በኋላ “ይህን ርዕስ በማንበብዎ እንደሚደሰቱ እርግጠኞች ነን” በማለት ደምድም።
20 ሠራተኞች ካሉና አመቺ ሆኖ ካገኘኸው እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል:- “ለሠራተኞችዎ ተመሳሳይ የሆነ አጭር ሐሳብ እንዳካፍላቸው ይፈቅዱልኛል?” ከተፈቀደልህ ባጭሩ ለመናገር ቃል እንደገባህ አትዘንጋ፤ አስተዳዳሪውም ተስፋ የሚያደርገው ቃልህን ትጠብቃለህ ብሎ ነው። ረጅም ውይይት ማድረግ የሚፈልግ ሠራተኛ ካለ ቤቱ ሄዶ መነጋገሩ የተሻለ ይሆናል።
21 በቅርቡ በአንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ ጥቂት አስፋፊዎች ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጋር ከሱቅ ወደ ሱቅ በሚደረገው አገልግሎት ተሠማርተው ነበር። መጀመሪያ አካባቢ አንዳንዶቹ አስፋፊዎች ከአሁን በፊት በዚህ መስክ ሠርተው ስለማያውቁ ፍርሃት ተሰምቷቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ ወዲያው ጭንቀቱ ጠፋና ተረጋግተው በደስታ ማገልገል ጀመሩ። ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 37 ሰዎች ሲያነጋግሩ 24 መጽሔትና 4 ብሮሹር አበርክተዋል። አንድ ወንድም ብዙውን ጊዜ አንድ ወር ሙሉ ከቤት ወደ ቤት ቢሠራ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ከሱቅ ወደ ሱቅ በመሥራት ያገኛቸውን ያክል ብዙ ሰዎች እንደማያገኝ ተናግሯል።
22 ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር፦ ኢየሱስ የመመሥከር ተግባሩን በመደበኛ መንገድ በማከናወን ብቻ አልተወሰነም። አመቺ ሆኖ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን አሠራጭቷል። (ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 19:1-10፤ ዮሐ. 4:6-15) አንዳንድ አስፋፊዎች ለመስበክ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ እንዴት እንደሚፈጥሩ ልብ በል።
23 አንዳንዶች በትምህርት ቤቶች ወይም በመዋዕለ ሕፃናት መግቢያ አካባቢ ቆመው ልጆቻቸውን የሚጠብቁ ወላጆችን ማነጋገርን ልማድ አድርገውታል። ብዙ ወላጆች 20 ደቂቃ ገደማ ቀደም ብለው ስለሚደርሱ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ ርዕሶች ላይ ከእነርሱ ጋር ስሜት ቀስቃሽ ውይይት ለማድረግ በቂ ጊዜ ይኖራል። ሌሎች ደግሞ በገበያ ቦታዎች ይሰብካሉ።
24 ብዙ አቅኚዎች በመጽሔቶቻችን ላይ በወጣ አንድ የተወሰነ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለየት ያለ ፍላጎት ሊኖራቸው የሚችሉትን ሰዎች ለማነጋገር ንቁዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንዲት እህት በታኅሣስ 22, 1995 የእንግሊዝኛ ንቁ! ላይ የወጣውን “ትምህርት ቤቶች ያጋጠሟቸው ችግሮች” የሚለውን ርዕስ ይዛ በጉባኤዋ የአገልግሎት ክልል ውስጥ የሚገኙ ስድስት ትምህርት ቤቶችን በመጎብኘት ጥሩ ምላሽ አግኝታለች። በተጨማሪም ስለ ቤተሰብ ሕይወትና በልጆች ላይ ስለሚፈጸመው በደል የሚናገሩ መጽሔቶችን ተጠቅማለች፤ ወደፊትም ተመሳሳይ ርዕስ ያላቸው እትሞች ሲወጡ ይዛላቸው እንድትመጣ ጋብዘዋታል።
25 ከቤት ወደ ቤት፦ እርግጥ ነው ኢየሱስ ክርስቶስና የጥንት ደቀ መዛሙርቱ የሠሩበትና ባለፉት ረጅም ዘመናት ውጤታማነቱ የተረጋገጠው ሰዎችን በየቤታቸው ሄዶ የማነጋገሩ ዘዴ የአገልግሎታችን ቋሚ ክፍል ሊሆን ይገባል። የአገልግሎት ክልላችንን ያለ አድልዎ መሸፈን የምንችለውና ሌላ የትም ቦታ በቀላሉ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ሰዎች የምናገኘው በዚህ መንገድ ነው። ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች አድራሻ መያዝ ስለምንችል ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በር ይከፍታል። ብዙውን ጊዜም መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንደልብ መጠቀም እንችላለን። በዚህም መስክ ቢሆን በተቻለን መጠን ዘና ብለን በጭውውት መልክ ውይይት ማድረግ እንችላለን፤ ይህ ጥሩ ዘዴ ነው።— ሥራ 20:20፤ 5:42
26 በማንኛውም ቦታ ለመስበክ ጥረት አድርጉ፦ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ የተሰጠንን ሥራ ለመፈጸም የጥድፊያ ስሜት መያዝንም ይጨምራል። ሰዎችን ‘በማንኛውም መንገድ ለማዳን’ ለእነርሱ አመቺ በሆነው ወቅት ለማነጋገር የግል ምርጫችንን መተው ይኖርብናል። ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” ለማለት የሚችሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ።— 1 ቆሮ. 9:22, 23
27 ከዚህም በላይ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። . . . ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።” (2 ቆሮ. 12:9, 10) በሌላ አባባል ማንኛችንም ብንሆን ይህን ሥራ በራሳችን ኃይል ልናከናውን አንችልም። ይሖዋ ብርቱ ኃይል ያለውን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። አምላክ ብርታት እንዲሰጠን ከጸለይን ጸሎታችን መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ከዚያ በኋላ ለሰዎች ያለን ፍቅር በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን የምንሰብክበትን አጋጣሚ እንድንፈልግ ይገፋፋናል። በመጪው ሳምንት በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ለምን አትሞክራቸውም?