ለልጆች ክፍት የሆነ የአገልግሎት መብት
1 በእውነት ቤት ውስጥ አድገው አሁን ወላጆች የሆኑ ብዙዎች በልጅነታቸው የመጽሔት ቀን እየተባለ በሚታወቀው ልዩ የአገልግሎት መብት መካፈል አስደሳች እንደነበረ ያስታውሳሉ። ይህ ሥራ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ የተጀመረው በ1949 ነበር። በሳምንት አንድ ቀን እያንዳንዱ ሰው ከመንገድ ወደ መንገድ፣ ከቤት ወደ ቤት፣ ከሱቅ ወደ ሱቅ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በማሰራጨቱ ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋል። በተለይ በዕድሜ አነስ ያሉ አስፋፊዎች በጉባኤው ውስጥ የሚገኙት ትልልቅ አስፋፊዎች በሚሠሩት ተመሳሳይ ሥራ የመካፈል አጋጣሚ ስለሚሰጣቸው በዚህ ሥራ ለመሳተፍ ይጓጉ ነበር። አንተስ ልጅ ሳለህ እንደዚህ ይሰማህ ነበር?
2 ልጆቻችሁን አሳትፉአቸው:- ከቤት ወደ ቤት ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ለማስጀመር ያልደረሱ በጣም ትንንሽ ልጆች እንኳን መጽሔት ማበርከት ይችላሉ። ለዚህ የሚያስፈልገው ጥቂት አጫጭር አረፍተ ነገሮች ተጠቅሞ ቀላል አቀራረብ መለማመድ ብቻ ነው። ምናልባትም በመጽሔቱ ሽፋን ላይ የሚገኘውን ሥዕል ተጠቅሞ አጠር ያለ ሐሳብ መስጠት በቂ ሊሆን ይችላል። ብዙ የቤት ባለቤቶች ብዙውን ጊዜ ስለ ልጆቹ ቅንነትና ስለሚያሳዩት የታረመ ጠባይ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ከልጆች መጽሔቶች ለመውሰድ ፈቃደኛ ይሆናሉ። ልጆች ትንሽ እገዛ ከተደረገላቸው ይህንን ሥራ በጥሩ ሁኔታ ሊሠሩት ይችላሉ። በዚህ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እርግጥ፣ ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ የመመሥከር ችሎታቸውን በማሳደጉ በኩል መሻሻል ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ወላጆች ሊረዷቸው ይፈልጋሉ።
3 ማንዌል ከቤት ወደ ቤት መስበክ የጀመረው ገና በሦስት ዓመቱ ነበር። ወላጆቹ አጭር አቀራረብ በቃል አስጠንተውት ነበር። ከእነርሱ ጎን ተሰልፎ በቅንዓት ከመስበኩም በላይ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮችና ትራክቶች አበርክቷል። መደበኛ ባልሆነ መንገድም ይመሰክራል። በአንድ ወቅት ወላጆቹ ማንዌልን ለማዝናናት ወደ አንድ መናፈሻ ቦታ ሲወስዱት በራሱ ተነሳስቶ እዚያ ለሚገኙት ሰዎች ጥቂት ትራክት አበረከተላቸው። ማንዌል አሁንም ገና ትንሽ ልጅ ቢሆንም ለአገልግሎት ያለው ቅንዓት ለወላጆቹና ለመላው ጉባኤ ትልቅ የማበረታቻ ምንጭ ሆኖላቸዋል።—ምሳሌ 22:6
4 በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ እያንዳንዱ ቅዳሜ “የመጽሔት ቀን” ተብሎ ተሰይሟል። እናንተ ወላጆች በዚህ ሥራ ለመካፈል በአዲስ መንፈስ እንድትነሳሱና ልጆቻችሁም በዚህ ልዩ የአገልግሎት መብት በተቻለ መጠን አዘውትረው ይካፈሉ ዘንድ እንድትረዷቸው እናበረታታችኋለን።