ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎች
1. ይሖዋን ከልብ ማወደስ እንድንችል ምን አዲስ ዝግጅት ተደርጎልናል?
1 ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ አዲስ ዝግጅት ተግባራዊ ሆኗል፤ በዚህ ዝግጅት መሠረት አስፋፊዎች በመጋቢትና በሚያዝያ እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ መደበኛ ጉብኝት በሚያደርግበት ወር 30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ የመሆን አጋጣሚ ይኖራቸዋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት በሁለት ወራት ላይ የሚያርፍ ከሆነ 30 ሰዓት ለማገልገል የሚያመለክቱ አስፋፊዎች ከሁለቱ ወራት አንደኛውን በመምረጥ ረዳት አቅኚ መሆን ይችላሉ። ሁሉም ረዳት አቅኚዎች የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከዘወትርና ከልዩ አቅኚዎች ጋር በሚያደርገው ስብሰባ ላይ እስከ መጨረሻው ድረስ መገኘት ይችላሉ። በዚህ ዝግጅት መሠረት፣ 50 ሰዓት ለማገልገል ሁኔታችን የማይፈቅድልን ከሆነ 30 ሰዓት በማገልገል በዓመት ውስጥ እስከ አራት ጊዜ ድረስ ረዳት አቅኚ በመሆን ይሖዋን ‘እጅግ ማመስገን’ ወይም ማወደስ እንችላለን።—መዝ. 109:30፤ 119:171
2. የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ወቅት ረዳት አቅኚ የሚሆኑ አስፋፊዎች ምን አጋጣሚ ያገኛሉ?
2 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ወቅት፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ወቅት ብዙ ወንድሞች ረዳት አቅኚ የመሆን አጋጣሚ ስለሚኖራቸው ከእሱ ጋር በአገልግሎት በመካፈል እርስ በርስ መበረታታት ይችላሉ። (ሮም 1:11, 12) ብዙ ረዳት አቅኚዎች ከእሱ ጋር ለማገልገል ሲሉ በሳምንቱ መሀል ቢያንስ አንድ ቀን እረፍት ሊወስዱ ይችላሉ። ከሰኞ እስከ ዓርብ ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት የሚያሳልፉ ደግሞ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ቅዳሜ ወይም እሁድ አብሯቸው ማገልገል ይችል እንደሆነ ሊጠይቁት ይችላሉ። በተጨማሪም ረዳት አቅኚዎች ከዘወትር እና ከልዩ አቅኚዎች ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘታቸው በጣም እንደሚያበረታታቸው የታወቀ ነው!
3. የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ጥሩ አጋጣሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
3 በመጋቢት እና በሚያዝያ ወር፦ ቀደም ሲል የነበረውን ዝግጅት ተጠቅመው በመታሰቢያው በዓል ሰሞን 30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ የሚሆኑ ሁሉ አሁን እጥፍ “የምስጋና መሥዋዕት” ማቅረብ ይችላሉ። (ዕብ. 13:15) የመጋቢትና የሚያዝያ ወራት ረዳት አቅኚ በመሆን አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጡናል። በየዓመቱ በእነዚህ ወራት ላይ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው አስደሳች ዘመቻ ላይ የመካፈል አጋጣሚ እናገኛለን። በተጨማሪም በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ብዙዎች አገልግሎታቸውን ስለሚያሰፉ ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር ማገልገል እንችላለን። የመታሰቢያው በዓል ከተከበረ በኋላ ደግሞ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተከታትለን መርዳት ብሎም በልዩ ንግግሩ ላይ የመገኘት ፍላጎታቸው እንዲጨምር ማድረግ ይኖርብናል። ታዲያ ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስችሉትን እነዚህን ተጨማሪ አጋጣሚዎች ለመጠቀም ልባችሁ አልተነሳሳም?—ሉቃስ 6:45