የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የሚያስተሳስር ፍቅር
በ1978 በሰሜን አትላንቲክ የተነሳው ከባድ ዓውሎ ነፋስ ክዊን ኤልዛቤት 2 የተሰኘችውን ግዙፍ ዘመናዊ መርከብ ክፉኛ መታት። ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃ የሚያክል ከፍታ ያለው ማዕበል መርከቧን መትቶ እንደ ቡሽ ብቅ ጥልቅ አደረጋት። በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ቁሳቁሶችና መንገደኞች በኃይል ተመትቶ እንደ ተሰባበረ ሸክላ ተፈነጣጥረው በየቦታው ወደቁ። የሚያስደንቀው ግን 1, 200 በሚሆኑት መንገደኞች ላይ የደረሰው ጉዳት በጣም ቀላል ነበር። በጥሩ ምህንድስና፣ በጠንካራ ዕቃዎችና ግሩም በሆነ መንገድ መሠራቷ መርከቧ ከመሰባበር እንድትተርፍ አድርጓታል።
ከብዙ መቶ ዓመታት በፊትም አንዲት ሌላ መርከብ ከባድ ዓውሎ ነፋስ በድንገት አግኝቷት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎች 275 ሰዎች በመርከቧ ውስጥ ነበሩ። መርከበኞቹ ኃይለኛው ዓውሎ ነፋስ መርከቧን ይሰባብራታል የሚል ፍራቻ ስላደረባቸው መርከቧን “ለማጠናከር” ዙሪያዋን በሰንሰለት ወይም በገመድ አሠሩ። በመርከቧ ላይ የነበሩት ሁሉም መንገደኞች ከሞት የተረፉ ሲሆን መርከቧ ግን ሙሉ በሙሉ ተሰባብራለች።— ሥራ ምዕራፍ 27
በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ መከራዎች አንዳንድ ጊዜ በሚናወጥ ባሕር ላይ በሚጓዝ መርከብ ውስጥ እንዳለን ሆኖ እንዲሰማን ሊያደርጉን ይችላሉ። የስጋት፣ የብስጭትና የጭንቀት ማዕበሎች ፍቅራችን በጣም እስኪፈተን ድረስ ሊውጡን ይችላሉ። እንዲህ ያሉትን ዓውሎ ነፋሶች ለመቋቋምና ከመሰባበር ለመዳን እኛም አንዳንድ እርዳታዎች ያስፈልጉናል።
ዓውሎ ነፋሶች በሚነሱበት ጊዜ
ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳየው እምነትና ጽናት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተመዝግቦ ይገኛል። ለቀድሞ የክርስትና ጉባኤዎች ሲል እንደ ባሪያ አገልግሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:24-28) በጌታ ሥራ ያከናወናቸው ነገሮች ለሰዎች ከፍተኛ ፍቅርና ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንደነበረው ግልጽ ምሥክር ይሆናሉ። ሆኖም ጳውሎስ ያሳለፈው ሕይወት ሁልጊዜ ሰላማዊ ጉዞ ነበር ማለት አይደለም። ሐዋርያው ቃል በቃልም ይሁን በምሳሌያዊ ሁኔታ ብዙ ማዕበሎችን ተቋቁሞ አሸንፏል።
በጳውሎስ ዘመን አንድ መርከብ ከባድ ማዕበል ከገጠማት በመርከቧ ውስጥ ያሉት መንገደኞች ሕይወት መዳንና የመርከቧ ደህንነት የተመካው በመርከቧ ሠራተኞች ጥሩ ችሎታና በመርከቧ ጥንካሬ ላይ ነበር። ሐዋርያው ምሳሌያዊ ማዕበሎች ባጋጠሙት ጊዜ ከዚህ ያላነሰ ነገር አስፈልጎት ነበር። ጳውሎስ የደረሰበትን ራብና ጥም፣ እስርና ድብደባ ተቋቁሞ ያለፈ ቢሆንም እንኳ መንፈሳዊነቱንና ስሜታዊ ጽናቱን እንዲሁም አፍቃሪ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለውን ሁኔታ የሚፈታተን ከሁሉ የከፋ ከባድ ማዕበል የመጣበት ከክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ነበር።
ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ ጉባኤ ለማቋቋም አንድ ዓመት ተኩል ጠንክሮ ሠርቷል። ከቆሮንቶስ ወንድሞች ጋር ያሳለፈው ጊዜ ለመንጋው የአሳቢነት ስሜት አሳድሮበታል። እንዲያውም ጳውሎስ የእነርሱ አባት እንደሆነ አድርጎ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 4:15) ሆኖም ለጉባኤው ጥቅም ሲል ከፍተኛ ፍቅር ያሳየና ብዙ የለፋ ቢሆንም እንኳ በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በጳውሎስ ላይ የዘለፋ ቃላት ተናግረው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 10:10) የራሱን ምቾት መሥዋዕት በማድረግ ብዙ ነገሮችን አከናውኖ ሳለ እነዚህ አስተያየቶች እንዴት ያሉ ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ!
ጳውሎስ ፍቅሩን ያለገደብ የገለጸላቸው እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል ጨካኝና አንኳሳሽ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? በኃይለኛ አውሎ ነፋስ ሥር እንደወደቀች መርከብ ጳውሎስም እንክትክቱ የወጣ ያህል የስሜት መደቆስ ደርሶበት መሆን አለበት። ቀደም ሲል ያከናወናቸው ጥረቶቹ ሁሉ ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ቆጥሮ ወይም የምሬት ስሜት ተሰምቶት በቀላሉ ተስፋ ለመቁረጥ ምን ያህል ቀላል ይሆንለት ነበር! ታዲያ ጳውሎስን የጠበቀው ነገር ምን ነበር? ያልጠበቀው ነገር ሲደርስበት እንደ መርከብ እንዳይሰባበር የረዳው ምንድን ነው?
እንዳንለያይ አጣብቆ የያዘን ፍቅር
ጳውሎስ ጥንካሬና ውስጣዊ ግፊት የሚያገኘው ከየት እንደሆነ ሳይገልጽ አንባቢዎቹን እንዲገምቱ አልተዋቸውም። “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 5:14) ጳውሎስ ከሁሉ የላቀው የጥንካሬና የውስጣዊ ግፊት ምንጭ ምን እንደሆነ በቀጥታ አመልክቷል። አስገዳጁ ኃይል “የክርስቶስ ፍቅር” ነው። ይህን ጥቅስ አስመልክቶ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝረዋል:- “ጳውሎስ አገልግሎታችንን የሙጥኝ ብለን እንድንይዝ የሚያደርገን እኛ ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ነው አላለም። . . . እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ በጉዞ ላይ የመጨረሻው ጣቢያ ላይ ሳይደርሱ ከመሃል ማቋረጥ ማለት ይሆን ነበር። እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር እኛ ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ያለማቋረጥ ያቀጣጥለዋል እንዲሁም ይመግበዋል።”—ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
በእርሱ የሚያምኑ የሰው ዘሮችን ለማዳን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት በመሠቃያ እንጨት ላይ የጣር ሞት ለመሞት ራሱን በማቅረብ ክርስቶስ ያሳየው ፍቅር ጳውሎስ ለክርስቶስና ለወንድማማች ማኅበር ጥቅም ሲል ማገልገሉን እንዲቀጥል አነሳስቶታል፣ ገፋፍቶታል እንዲሁም አስገድዶታል። ስለዚህ የክርስቶስ ፍቅር ጳውሎስን ተቆጣጥሮታል፣ ራስ ወዳድ እንዳይሆን ገትቶታል እንዲሁም ዓላማው አምላክንና ሰዎችን በማገልገል ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጎታል።
በእርግጥም አንድ ክርስቲያን በሕይወት ጎዳና ላይ በታማኝነት እንዲጓዝ ከበስተኋላው ሆኖ የሚገፋፋው የክርስቶስ ፍቅር ነው። በአካላችን፣ በስሜታችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ድካም ሊያመጡ ከሚችሉ መከራዎች ጋር ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ አስገዳጅ የሆነው የክርስቶስ ፍቅር አነስተኛ ውስጣዊ ግፊት ያለው ሰው ተስፋ ቆርጦ የሚያቆምበትን እክል አልፈን ወደፊት እንድንራመድ ያስችለናል። ለመጽናት የሚያስችለንን ጥንካሬ ይሰጠናል።
እንዲደግፈንና ከውስጥ እንዲገፋፋን ፍጹም ባልሆነው ስሜታችን ላይ መታመን አንችልም። በተለይ ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ሲሰማንና ያልጠበቅነው ነገር ደርሶብን ስናዝን ይህ አባባል የበለጠ ይሠራል። በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቶስ ፍቅር ምንም ዓይነት የግል ችግር ቢገጥመን አገልግሎታችንን የሙጥኝ ብለን እንድንይዝ፣ የመደገፍና የመገፋፋት ኃይል አለው። አንድ ክርስቲያን ሌሎች ሰዎች ከሚገምቱት በላይ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ራሱ ከሚገምተው በላይ የክርስቶስ ፍቅር እንዲጸና ሊያደርገው ይችላል።
ከዚህም በላይ የክርስቶስ ፍቅር ጸንቶ የሚኖር ስለሆነ የሚያስከትለውም በጎ ውጤት ማብቂያ አይኖረውም። የማይናወጥ ወይም የማይከስም አስገዳጅ ኃይል ነው። “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” (1 ቆሮንቶስ 13:8) ምንም ይምጣ ምን እርሱን በታማኝነት እንድንከተለው ያስችለናል።
በስሜት ላይ የሚደርሱ ፈተናዎች ወደ ውጭ የሚጎትት ተጽዕኖ ሊያስከትሉብን ይችላሉ። ስለዚህ ክርስቶስ ለእኛ ባሳየው ፍቅር ላይ ማሰላሰል እንዴት ያለ አስፈላጊ ነገር ነው። የክርስቶስ ፍቅር እንዳንነጣጠል አጣብቆ ይይዘናል። የእርሱ ፍቅር እምነታችን እንዳይጠፋ ለመከላከል ያስችለናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:14-19) ከዚህም በላይ የክርስቶስ ፍቅር እንዲገለጥ ያደረገውን ይሖዋ አምላክን ለማክበር የቻልነውን ያህል ሁሉ እንድናደርግ የክርስቶስ ፍቅር ያስገድደናል።—ሮሜ 5:6-8