ምርጫችሁ ፍቺ በሚሆንበት ጊዜ
“የትዳር ጓደኛችሁ ቢሞት ጥሩ የትዳር ጓደኛ ባትሆኑም እንኳ ሰዎች ችግራችሁን ይረዱላችኋል። ባለቤታችሁ ጥሏችሁ ከሄደ ግን አንዳንዶች ጥሩ የትዳር ጓደኛ እንዳልነበራችሁ አድርገው ያስባሉ። እባካችሁ እርዱኝ!”—በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት የንቁ! አንባቢ።
በትዳር ላይ የሚፈጸም ውስልትናና ፍቺ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ሊፈጥር ይችላል። ምንም እንኳ ብዙዎች አጥጋቢ ምክንያት ኖሯቸው ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ዕርቅ ለመፍጠርና ትዳራቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ቢወስኑም ሌሎች አምላክ የሰጣቸውን አማራጭ በመጠቀም አመንዝራውን የትዳር ጓደኛ ለመፍታት የሚወስኑበት በቂ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። (ማቴዎስ 5:32፤ 19:9) ለምሳሌ ያህል የአንዲት ታማኝ ሚስትና የልጆቿ አጠቃላይ ደህንነትና መንፈሳዊነት አደጋ ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በጾታ ግንኙነት በሚተላለፍ በሽታ እለከፋለሁ የሚል ስጋት ሊያድርባት ይችላል። ወይም ደግሞ ምንዝር የፈጸመውን ባሏን ይቅርታ ብታደርግለትም እንኳ እውነተኛ የመተማመን መንፈስ ሰፍኖ በትዳር ጓደኝነት ከእሱ ጋር ኑሮዋን መቀጠል እንደምትችል አድርጋ እንድታስብ የሚያደርጋት ምንም መሠረት አይኖር ይሆናል።
“በሕይወቴ እንዲህ ያለ ለውሳኔ የሚቸግር ጉዳይ ገጥሞኝ አያውቅም” ስትል አንዲት በጣም የተረበሸች ሚስት ተናግራለች። በእርግጥም አስቸጋሪ ውሳኔ ነው። ውሳኔውን አስቸጋሪ የሚያደርገው የተፈጸመው የክህደት ድርጊት በጣም የሚጎዳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍቺ ሕይወቷን በሙሉ በብዙ መልኩ ሊለውጡ የሚችሉ መዘዞች የሚያስከትል በመሆኑም ጭምር ነው። ስለዚህ አንዲት ሚስት ከሃዲውን የትዳር ጓደኛዋን መፍታት አለመፍታት የራሷ የግል ውሳኔ ነው። ተበዳይዋ የትዳር ጓደኛ ይህን ውሳኔ የማድረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ መብት ያላት በመሆኑ ሌሎች ይህን መብቷን ሊያከብሩላት ይገባል።
የሚያሳዝነው ግን ብዙዎች ኪሳራውን በሚገባ ሳያሰሉ ለመፋታት የሚጣደፉ መሆኑ ነው። (ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።) ፍቺ የሚያስከትላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ልጆች ካሏችሁ
“በራሳቸው ችግሮች በእጅጉ የተዋጡ ወላጆች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይዘነጋሉ ወይም ችላ ይላሉ” ሲል ካፕልስ ኢን ክራይስስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ስለዚህ ለመፋታት በምታስቡበት ጊዜ የልጆቻችሁን መንፈሳዊነትና ደህንነት ግምት ውስጥ አስገቡ። ፍቺው ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፈጸሙ በልጆቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንደሚቀንሰው ብዙ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ቢሆን የዋህነት አንድ ሰው ‘ለሰው ሁሉ ገር፣ በትዕግሥት የሚጸናና የማይጣላ’ እንዲሆን ይረዳዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25a
አንድ ሰው ለመፋታት በሚመርጥበት ጊዜ የሚፋቱት ባልና ሚስቱ እንጂ ልጆቹ እንዳልሆኑ ሊጤን ይገባዋል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ልጆቹ እናታቸውም ሆነ አባታቸው ያስፈልጓቸዋል። እርግጥ የልጆቹን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ የተለየ ውሳኔ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም የሃይማኖትና የግል አመለካከት ልዩነቶች ልጆቹ ከሁለቱም ወላጆቻቸው ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ እንቅፋት መሆን የለባቸውም።
በተጨማሪም የሕፃናት ስሜት በቀላሉ የሚጎዳ መሆኑና በቂ ማጽናኛና ፍቅር የሚያስፈልጋቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም። “ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸውን መቀጠላቸው” ይላል አንድ መጽሐፍ፣ “ልጆቹ አዲሱን ክስተት መቋቋም የሚችሉበትን ሁኔታም ሆነ መሠረት ይፈጥርላቸዋል።” ከዚህም ሌላ በየዕለቱ ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት መስጠቱም እንዲረጋጉ ሊረዳቸው ይችላል።—ዘዳግም 6:6, 7፤ ማቴዎስ 4:4
ገንዘብ ነክ ጉዳዮችና የፍርድ ቤት ሙግቶች
ፍቺ ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች የተወሰነ ገቢን፣ ንብረትን፣ ምቾትንና ምናልባትም ደግሞ በጣም የሚወዱትን ቤትም ጭምር እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። አንድ ግለሰብ ያደገውን ወጪውንና የቀነሰውን ገቢውን አጣጥሞ ለመኖር ሊገደድ ስለሚችል ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ትክክለኛ በጀት ማውጣቱ ጥበብ ነው። ብዙ ገንዘብ በማውጣት ወይም ዕዳ ውስጥ በመግባት ያጡትን ነገርና በስሜት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ መነሳሳት ተገቢ አይደለም።
ለመፋታት ከወሰናችሁ የጋራ የባንክ ሂሳባችሁን እንዴት እንደምትይዙም ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር መነጋገር ይኖርባችኋል። ለምሳሌ ያህል ገንዘቡን አላግባብ የመጠቀም ችግር እንዳይፈጠር የየራሳችሁን የባንክ ሂሳብ እስክትከፍቱ ድረስ ሁለታችሁም ካልፈረማችሁ በስተቀር ገንዘብ እንዳይወጣ ከባንኩ ሥራ አስኪያጅ ጋር መዋዋል ትችላላችሁ።
በተጨማሪም ተቆራጭ የሚሆነውን ገንዘብ መጠን በሚመለከት ለምታደርጉት ድርድር ይረዳችሁ ዘንድ ገቢውንና ወጪውን በትክክል በጽሑፍ አስፍሮ መያዙ ጥበብ ነው። ከዚህም ሌላ በብዙ አገሮች ሰዎች አዲስ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ግብር ለሚሰበስቡ ባለ ሥልጣናት የማሳወቅ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው።
ከዚህም በላይ አብዛኞቹ ሰዎች ከፍቺ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጥሩ ተሞክሮ ያለው የሕግ ባለሙያ ያማክራሉ። አንዳንድ አገሮች ሸምጋዮችን ወይም አደራዳሪዎችን በመጠቀም ባልና ሚስት ሁለቱም የሚስማሙበት አንድ የጋራ ጭብጥ ላይ እንዲደርሱ ካደረጉ በኋላ ስምምነቱ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ ያደርጋሉ። ብዙ ወላጆች በተለይ ልጆች ያሏቸው ከሆኑ የጠላትነት መንፈስ የማይፈጥር የሕግ ባለሙያ እርዳታ መጠቀም ይመርጣሉ። እነዚህ ወላጆች የሚፈለገውን መሥዋዕትነት ሁሉ ከፍለው ለመርታት ከመጣር ይልቅ በተቻለ መጠን ሊፈጠር የሚችለውን ግጭትና ጉዳት ለመቀነስ ይጥራሉ። አንዳንዶቹ ቁሳዊ ነገሮች ያን ያህል ከፍተኛ የስሜትና የገንዘብ መሥዋዕትነት ሊከፈልላቸው የሚገቡ አይደሉም።
ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ረገድ የሚታይ ለውጥ
“ብዙ ሰዎች ለተፋቱ ጓደኞቻቸው የሚኖራቸውን ጥርጣሬና ጥሩ ያልሆነ ስሜት አቅልለን መመልከት የለብንም” ሲሉ አንዲት ተመራማሪ አስታውቀዋል። ታማኟ የትዳር ጓደኛ ሕጋዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ መብቶቿ ከሚፈቅዱላት ውጪ ምንም ነገር ባታደርግም እንኳ ለትዳሩ መፍረስ መንስኤዋ እሷ እንደሆነች አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ቀዝቀዝ ያለ ሰላምታ በመስጠት እንዲያም ሲል ግለሰቧን ከናካቴው በማግለል ይህን ስሜታቸውን ይገልጹ ይሆናል። አልፎ ተርፎም የቀድሞ የቅርብ ጓደኞቿ ጥላቻቸውን በግልጽ እስከማሳየት ሊደርሱ ይችላሉ።
ብዙዎች ከትዳር ጓደኛው ጋር የተፋታ ሰው ምን ያህል እርዳታ እንደሚያስፈልገው አይገነዘቡም። አጠር ያለ ደብዳቤ ወይም ፖስት ካርድ መላኩ ብቻ በቂ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ “የሌሎችን ችግርና ስሜት በሚገባ የሚረዱና አብሯችሁ ወደ አንድ ቦታ የሚሄድ ሰው ወይም የሚያጫውታችሁ ሰው ትፈልጉ እንደሆነ አለዚያም ደግሞ አንድ ነገር እንዲደረግላችሁ ትፈልጉ እንደሆነ ደውለው የሚጠይቁ” ጓደኞች አሉ ሲል ዲቮርስ ኤንድ ሴፓሬሽን የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ” ያስፈልገዋል።—ምሳሌ 18:24
ለማገገም መጣር
አንዲት የልጆች እናት ከተፋታች ከአሥራ ስድስት ዓመታት በኋላ “አሁንም ቢሆን ከሰዎች ጋር በምሆንበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ከባድ የብቸኝነት ስሜት የሚሰማኝ ጊዜ አለ” ስትል በግልጽ ተናግራለች። ይህን ሁኔታ መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? “በሥራ ቦታ ራሴን በሥራ በማስጠመድ፣ ልጄን በመንከባከብና ቤቴን ጥሩ አድርጌ በመያዝ ይህን ስሜት መከላከል የምችልበት ዘዴ ቀይሻለሁ። በተጨማሪም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ እምነቴን ለጎረቤቶቼ ማካፈልና ለሌሎች ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ጀመርኩ። ይህ በእጅጉ ረድቶኛል” ስትል ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ ተናግራለች።
ባልየው በትዳሩ ላይ የፈጸመው ውስልትና ይፋ የወጣበትን ቀን፣ ቤቱን ጥሎ የሄደበትን ቀንና የፍርድ ቤት ብይን የተላለፈበትን ቀን የመሰሉ አንዳንድ የተወሰኑ ወቅቶች መጥፎ ትዝታዎችና ስሜቶች ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። የዕረፍት ጊዜያትንና የጋብቻ ክብረ በዓላትን የመሳሰሉ ባልና ሚስቱ አብረው ያሳልፏቸው የነበሩ አስደሳች ወቅቶች ትውስ እያሉ ስሜትን ክፉኛ ሊረብሹ ይችላሉ። “እነዚህን ቀናት ከቤተሰቤ ጋር ወይም ደግሞ ያለሁበትን ሁኔታ ከሚያውቁ የቅርብ ጓደኞቼ ጋር ለማሳለፍ ዕቅድ አወጣለሁ” ትላለች ፓት። “የቀድሞዎቹን ትውስታዎች ሽረው በአእምሮ ውስጥ አዲስ ትዝታ የሚቀርጹ ነገሮችን እናደርጋለን። ከሁሉ ይበልጥ የሚረዳኝ ግን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድናና ስሜቴን የሚረዳልኝ መሆኑን ማወቄ ነው።”
ተስፋ አትቁረጡ
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የሚያደርጉና አምላክ በሰጣቸው መብት ተጠቅመው አመንዝራውን ባለቤታቸውን ለመፍታት የሚመርጡ ታማኝ ባለ ትዳሮች የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸውም ሆነ ይሖዋ ይተወኛል ብለው ሊሰጉ አይገባም። አምላክ የሚጠላው ‘ልቅሶና ሐዘን ያስከተለውን’ አመንዝራው የትዳር ጓደኛ የፈጸመውን የማታለል ድርጊት ነው። (ሚልክያስ 2:13-16) የ“ርኅራኄ” አምላክ የሆነው ይሖዋ የሚወዱት ሰው ሲከዳ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ያውቃል። (ሉቃስ 1:78፤ ኤርምያስ 3:1፤ 31:31, 32) እንግዲያው ‘ይሖዋ ፍትሕ እንደሚወድና ታማኝ አገልጋዮቹን እንደማይተዋቸው’ እርግጠኛ ሁን።—መዝሙር 37:28 NW
እርግጥ ነው፣ በትዳር ላይ የሚፈጸመውን ውስልትናም ሆነ አስከፊ መዘዞቹን መጀመሪያውኑ ማስወገድ ቢቻል የተሻለ ይሆን ነበር። ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?b የተባለው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የቤተሰብ መመሪያ መጽሐፍ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አስደሳች ትዳር እንዲገነቡና በትዳራቸው ላይ ከመወስለት እንዲታቀቡ ረድቷቸዋል። አስደሳች ትዳር መገንባት፣ ልጆችን ማሠልጠንና የትዳር ችግሮችን መፍታት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ምዕራፎች ይዟል። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ይህን ርዕሰ ጉዳይ የሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በታኅሣሥ 8, 1997 እና በሚያዝያ 22, 1991 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትሞች ላይ “ልጅን የማሳደግ መብት—ሚዛናዊው አመለካከት ምንድን ነው?” በሚል ጭብጥ በወጡት ተከታታይ ጽሑፎች ላይና “ወላጆቻቸው የተፋቱባቸውን ልጆች መርዳት” በሚል ጭብጥ በወጣው ጽሑፍ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቺ ለልጆች አይበጅም
በ1988 ሟቿ የዌልሷ ልዕልት ዳያና በብሪታንያ ብቻ በየቀኑ 420 የሚሆኑ ልጆች ወላጆቻቸው ይፋታሉ ሲሉ ተናግረው ነበር። ከእነዚህ ልጆች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ሕፃናት ናቸው። የሚያሳዝነው ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ከፍቺ በኋላ ከአንደኛው ወላጃቸው ጋር የሚቆራረጡ መሆናቸው ነው።
ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በተለየ መልኩ “ወላጆቻቸው ከተፋቱባቸው ልጆች መካከል ፍቺውን በጸጋ የሚቀበሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው” ሲሉ አንዲት የታወቁ የጤና እና የሕክምና ደራሲ ገልጸዋል። “በቤተሰቡ ውስጥ ያለው መንፈስ ጥሩ ባይሆንም እንኳ አብዛኞቹ ልጆች ወላጆቻቸው አብረው ቢኖሩ ይመርጣሉ።” ባልና ሚስቱ ውስልትና በተፈጸመበት ወቅት ብዙ ቢጨቃጨቁም እንኳ ለልጆቻቸው የሚበጀው ትዳሩ እንዲፈርስ ማድረግ እንደሆነ አድርገው ለመደምደም መጣደፍ የለባቸውም። በአመለካከታቸውና በጠባያቸው ረገድ ለውጥ ማድረጋቸው ለመላው ቤተሰብ ጥቅም ሲሉ አብረው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።
“በትዳራቸው ላይ የሚማገጡ ባሎች” አሉ ደራሲዋ ፓሜላ ዊንፊልድ፣ “ማስተዋል የጎደለውን ድርጊታቸውን ተከትሎ የሚመጣው ፍቺ በልጆቻቸው ላይ የሚፈጥረውን ከባድ ኀዘን ማሰብ አለባቸው።”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አምላክ ሁሉንም ዓይነት ፍቺ ይጠላልን?
“በጣም ይረብሸኝ የነበረው ነገር” ትላለች ፓት፣ “‘ይሖዋ ፍቺን ይጠላል’ የሚለው ሐሳብ ነው። ‘እያደረግኩት ያለሁት ነገር ይሖዋን ደስ ያሰኘዋልን?’ የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ አእምሮዬ ውስጥ ይመላለስ ነበር።”
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሚልክያስ 2:16 ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት። በሚልክያስ ዘመን ብዙ እስራኤላውያን ወንዶች ወጣት የሆኑ አረማውያን ሴቶችን ለማግባት ሳይሆን አይቀርም፣ ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር። አምላክ ይህን የማታለልና የክህደት ድርጊት አውግዟል። (ሚልክያስ 2:13-16) በመሆኑም አምላክ የጠላው እንደ ቀላል ነገር በመመልከት ሚስቶቻቸውን እየፈቱ ሌሎችን ለማግባት መነሳሳታቸውን ነበር። ሆን ብሎ ምንዝር የሚፈጽምና ሚስቱን የሚፈታ ወይም ደግሞ ሚስቱ እንድትፈታው የሚገፋፋ ሰው ድርጊቱ ክህደት የተሞላበት ከባድ ኃጢአት ነው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሶች ሁሉንም ዓይነት ፍቺ የሚያወግዙ አይደሉም። የሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ይህን ያረጋግጡልናል:- “ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” (ማቴዎስ 19:9፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ ኢየሱስ ለቅዱስ ጽሑፋዊ ፍቺ ተቀባይነት ያለው መሠረት የሚሆነው ዝሙት እንደሆነ ገልጿል። እንዲያውም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ከፈታ በኋላ ተቀባይነት ባለው መንገድ ሌላ ማግባት የሚችለው በዚህ ምክንያት ብቻ ነው። ተበዳዩ ወገን ጥፋተኛውን የትዳር ጓደኛ ይቅር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ኢየሱስ የተናገረውን መሠረት አድርጎ በመጠቀም ያመነዘረውን የትዳር ጓደኛ ለመፍታት ቢመርጥ አምላክ የሚጠላውን ድርጊት መፈጸሙ ነው ሊባል አይችልም። አምላክ የሚጠላው በትዳሩ ላይ የማገጠው የትዳር ጓደኛ የፈጸመውን የክህደት ድርጊት ነው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ንጹሐን የትዳር ጓደኞችና ልጆቻቸው ፍቅራዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል