ግልፍተኝነት የበዛበት ዘመን የሆነው ለምንድን ነው?
ቼክ ሪፑብሊክ፣ ፕራግ ውስጥ አንድ ሰው ቡና ቤት በተቀመጠበት በጥይት ተገደለ። ለምን? ገዳይ ይህን እርምጃ የወሰደው ሟች በራሱ ቴፕ ያዳምጥ የነበረው ሙዚቃ ከመጠን በላይ ጮኸብኝ በሚል ስሜት በመበሳጨቱ ነው። በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን አንድ የመኪና አሽከርካሪ መስቀለኛ መንገድ ላይ በገና መጫወቻ ዱላ ተደብድቦ ተገደለ። ጥቃቱን የፈጸመው ሰው ሟች የመኪናውን መብራት ፊቱ ላይ ስላበራበት በመናደዱ ምክንያት እንደሆነ ማወቅ ተችሏል። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት እንግሊዛዊት ነርስ በሯን በቁጣ በርግዶ የገባው የቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ ናፍጣ አርከፍክፎ በእሳት ካያያዛት በኋላ ጥሏት ሄደ።
መንገድ ላይ፣ ቤት ውስጥ፣ በአውሮፕላን ውስጥ ስለሚከሰቱ የግልፍተኝነት ድርጊቶች የሚወጡ ዘገባዎች ከልክ በላይ የተጋነኑ ናቸው? ወይስ በአንድ ሕንፃ ግድግዳ ላይ እንደሚታዩ ስንጥቆች ሥር የሰደደ ችግር መኖሩን በገሃድ የሚያሳዩ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው? ማስረጃዎቹ ሥር የሰደደ ችግር መኖሩን ያሳያሉ።
የአሜሪካ የአውቶሞቢል ማኅበር (ኤ ኤ ኤ) የትራፊክ ደህንነት ተቋም በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት በጎዳናዎች ላይ “በአሽከርካሪዎች መካከል የሚፈጠረውን የከረረ ጠብ በተመለከተ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከ1990 አንስቶ በየዓመቱ 7 በመቶ ገደማ ጨምረዋል” ሲል ገልጿል።
የቤት ውስጥ ግልፍተኝነት በጣም ተስፋፍቷል። ለምሳሌ ያህል የአውስትራሊያ ግዛት በሆነችው በኒው ሳውዝ ዌልስ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በ1998 50 በመቶ ጨምረው መገኘታቸውን ፖሊስ አረጋግጧል። አውስትራሊያ ውስጥ ተጋብተው አሊያም እንዲሁ አብረው ከሚኖሩ አራት ሴቶች መካከል አንዷ አብሯት በሚኖረው ሰው እጅ አካላዊ ጥቃት ይፈጸምባታል።
በአውሮፕላን ውስጥም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መንገደኞች ድንገት በንዴት ቱግ ይሉና በአውሮፕላኑ ሠራተኞች፣ አብረዋቸው በሚጓዙት መንገደኞችና አልፎ ተርፎም በአውሮፕላኑ አብራሪዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ስጋት በማሳደሩ አንዳንድ የዓለማችን ታላላቅ አየር መንገዶች ጠበኛ ተሳፋሪዎችን ከወንበራቸው ጋር ጠፍረው ለማሰር የሚያገለግሉ ልዩ ቀበቶዎች ለአውሮፕላን ሠራተኞች አዘጋጅተውላቸዋል።
ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚሳናቸው ለምንድን ነው? እነዚህን የግልፍተኝነት ድርጊቶች የሚቆሰቁሰው ምንድን ነው? እነዚህን ስሜቶች በእርግጥ መቆጣጠር ይቻላል?
ግልፍተኝነት የበዛበት ምክንያት
ግልፍተኝነት በቁጣ ወይም በንዴት መገንፈል ማለት ነው። የግልፍተኝነት ድርጊት የሚፈጸመው ንዴት ለረዥም ጊዜ ታምቆ ከተያዘ በኋላ በድንገት ሲፈነዳ ነው። “አሽከርካሪዎች ለጠብ የሚጋበዙት አንድ ጊዜ በሚከሰት አጋጣሚ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአሽከርካሪው ባሕርይና በሕይወቱ ውስጥ በሚያጋጥመው እየጨመረ በሚሄድ ውጥረት ሳቢያ የሚፈጠር ነው” ሲሉ የኤ ኤ ኤ የትራፊክ ደህንነት ተቋም ፕሬዚዳንት ዴቪድ ኬ ዊሊስ ተናግረዋል።
በየቀኑ የሚደርሰን ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ ውጥረትን ያባብሳል። በዴቪድ ሌዊስ የተዘጋጀው ኢንፎርሜሽን ኦቨርሎድ በተባለው መጽሐፍ የኋላ ሽፋን ላይ የሚከተለው ሐሳብ ሰፍሯል:- “በዛሬው ጊዜ ብዙ ሠራተኞች ከፍተኛ መጠን ባለው መረጃ ተውጠዋል። . . . የሚቀርብላቸውን ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ . . . ለመረዳት የሚያደርጉት ጥረት ከባድ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ፣ ግድ የለሾች እንዲሆኑና ነገሮችን በትክክል እንዳያከናውኑ ያደርጋቸዋል።” አንድ ጋዜጣ ይህን የመረጃዎች ውርጅብኝ አስመልክቶ ምሳሌ ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- “በሥራ ቀናት የሚወጣ አንድ ጋዜጣ የሚይዘው መረጃ በ17ኛው መቶ ዘመን የኖረ አንድ ሰው ዕድሜ ልኩን ሊያገኝ ከሚችለው መረጃ ጋር የሚመጣጠን ነው።”
ወደ አፋችን የምናስገባውም ነገር ቁጣን የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል። መጠነ ሰፊ የሆኑ ሁለት ጥናቶች እየጨመረ የመጣ ጥላቻ ሲጋራ ከማጨስ፣ የአልኮል መጠጥ ከመጠጣትና ደካማ ከሆነ የአመጋገብ ልማድ ጋር ግንኙነት እንዳለው አሳይተዋል። እነዚህ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፉ የአኗኗር ዘይቤዎች ውጥረትንና ብስጭትን ያባብሳሉ። እንዲህ ያለው ብስጭት ደግሞ በስድብ፣ ትዕግሥት በማጣትና ተቻችሎ ባለመኖር ይገለጣል።
ምግባረ ብልሹነትና ፊልሞች
የአውስትራሊያ የወንጀል ምርምር ተቋም (ኤ አይ ሲ) ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር አዳም ግሬካር በምግባረ ብልሹነትና በወንጀል መካከል ስላለው ዝምድና ሐሳብ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “ለአክብሮትና ለመልካም ምግባር በአዲስ መልክ ትኩረት መስጠት አነስተኛ ወንጀሎችን ለመቀነስ የሚያስችል ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ ሊሆን ይችላል።” ተቋሙ ትዕግሥተኛ መሆንን፣ መቻቻልን እና ከተሳዳቢነት መቆጠብን ያበረታታል። ይህን ተግባራዊ አለማድረግ ከሥርዓት አልበኛነት ወደ ወንጀለኛነት ሊያመራ እንደሚችል ገልጿል። የሚያስገርመው ደግሞ ብዙዎች ያለባቸውን ብስጭትና ውጥረት ለመቀነስ የሚመርጡት የመዝናኛ ዓይነት አለመቻቻልንና ግልፍተኝነትን የሚያበረታታ ሆኖ ተገኝቷል። እንዴት?
“ልጆችና ጎልማሶች ግድያና እልቂት የሚያሳዩ ፊልሞችን ለማየት ወደ ሲኒማ ቤቶች ይጎርፋሉ። ጭካኔ የሞላባቸው የቪዲዮ ፊልሞች ትርፍ የሚገኝባቸው ንግድ ሆነዋል። ‘የጦር መሣሪያ አሻንጉሊቶች’ በወላጆቻቸው ዘንድ ሁልጊዜ ተቀባይነት ባያገኙም እንኳ በብዙ ልጆች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ናቸው። በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የጭካኔ ድርጊቶች በበርካታ አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያላቸው ሲሆን ቴሌቪዥን የሥነ ምግባር እሴቶችን በማስተላለፍ ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል” ሲል የኤ አይ ሲ ሪፖርት ዘግቧል። ይህ በጎዳና ላይም ሆነ ቤት ውስጥ ከሚታዩ የግልፍተኝነት ባሕርያት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ሪፖርቱ “አንድ ኅብረተሰብ ጠበኝነትን ባወገዘ መጠን በኅብረተሰቡ ውስጥ የግለሰቦች ሥነ ምግባር በዚያው መጠን እየተሻሻለ ይሄዳል” ሲል አስረድቷል።
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ቁጣ፣ ውጥረት ሲሰማን የምናሳየው ተፈጥሯዊ ምላሽ እንደሆነና ከፍተኛ ጫና ለሚያሳድረው ደንታ ቢስ ለሆነው ኅብረተሰብ የምንሰጠው ሊቀር የማይችል አጸፋ እንደሆነ ይናገራሉ። ታዲያ “ከተናደድክ፣ ይውጣልህ” የሚለው ሰፊ ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ በእርግጥ ጥሩ ምክር ነው?
ግልፍተኝነትን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው?
የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥፋት እንደሚያስከትል ሁሉ በኃይል የሚቆጣ ሰውም አብረውት በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ራሱንም ቢሆን ይጎዳል። በምን መንገድ? “በቁጣ መገንፈል ወደ ከፋ ጠብ ሊመራ ይችላል” ሲል ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (ጃማ) ገልጿል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ቁጣ የሚቀናቸው ወንዶች “ቁጡ ካልሆኑት ይልቅ በ50 ዓመት ዕድሜያቸው የመሞት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።”
በተመሳሳይም የአሜሪካ የልብ ሕመምተኞች ማኅበር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በቁጣ የመገንፈል ባሕርይ የተጠናወታቸው ወንዶች ቁጣቸውን ከሚቆጣጠሩ ወንዶች ይልቅ በጭንቅላታቸው ውስጥ ለሚፈጠር ደም የመፍሰስ አደጋ በሁለት እጥፍ የተጋለጡ ናቸው።” እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ይመለከታሉ።
ውጤታማ የሆነው ምክር የትኛው ነው? ዓለማዊ ምንጮች በሰጡት ምክርና ማኅበራዊ ኑሮን በተመለከተ ከፍተኛ ስርጭት ባለው ምንጭ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ተመልከት።
ቁጣን ተቆጣጠር፤ ግልፍተኝነትን አስወግድ
ዶክተር ሬድፎርድ ቢ ዊልያምስ ጃማ ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “‘ከተናደድክ፣ ይውጣልህ’ የሚለው ቀላል ምክር . . . ውጤታማ አይመስልም። እጅግ ጠቃሚ የሆነው ነገር ለምን እንደተቆጣህ ለማወቅ መሞከርና ከዚያም ለመቆጣጠር እርምጃ መውሰድ ነው።” ዶክተሩ ራስህን እንዲህ እያልክ እንድትጠይቅ ሐሳብ አቅርበዋል:- “(1) ይህ ጉዳይ ለእኔ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? (2) ለእውነታው ያለኝ አመለካከትና የሚሰማኝ ስሜት አግባብነት አለው? (3) የተሰማኝን ቁጣ ማስወገድ እንድችል ሁኔታው ሊስተካከል የሚችል ነው?”
ምሳሌ 14:29፤ 29:11 “ለትዕግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።”
ኤፌሶን 4:26, 27 “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።”
ፍራንክ ዶኖቫን ዲሊንግ ዊዝ አንገር—ሰልፍ ሄልፕ ሶሉሽንስ ፎር ሜን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥተዋል:- “ከቁጣ መራቅ ወይም በሌላ አባባል እንድትቆጣ ካደረገህ ቦታና ካስቆጡህ ሰዎች መራቅ ከፍተኛ ዋጋና ጠቀሜታ ያለው ስልት ነው።”
ምሳሌ 17:14 “የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው፤ ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው።”
በርትራም ሮትቻይልድ ዘ ሂውማኒስት በተባለው መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል:- “ቁጣ . . . በአንደኛ ደረጃ ግለሰቡ ራሱ ተጠያቂ የሚሆንበት ባሕርይ ነው። እንድንቆጣ የሚያደርጉን ምክንያቶች የሚቀመጡት አእምሯችን ውስጥ ነው። . . . መቆጣትህ ያስገኘልህ ጥቂት ጥቅም በመቆጣትህ ምክንያት ከሚፈጠሩ በርካታ ስህተቶች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ አይባልም። ራስ ላይ ደርሶ ከማየት ይልቅ ከቁጣ መራቁ የተሻለ ነው።”
መዝሙር 37:8 አ.መ.ት “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቁጣንም ተወው፤ ወደ እኩይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።”
ምሳሌ 15:1 “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች።”
ምሳሌ 29:22 አ.መ.ት “ቁጡ ሰው ጠብን ይጭራል፤ ግልፍተኛም ብዙ ኀጢአት ይሠራል።”
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ ያለውን ምክር ይደግፋሉ። አቅራቢያህ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝና ግልፍተኝነት በበዛበት ዘመን ብንኖርም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ በእርግጥ ውጤታማ እንደሆነ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቁጥጥር ያልተደረገለት ግልፍተኝነት እንደ እሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ጉዳት ያስከትላል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ይበልጥ ውጤታማ ነው