ጨው—ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ሸቀጥ
ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:13) ጨው የተነሰነሰበትን ነገር እንዳይበላሽ የማድረግ ኃይል ስላለው “ጨው” የሚለው ቃል በጥንቶቹም ሆነ በዘመናዊዎቹ ቋንቋዎች ከፍተኛ ዋጋና ክብር ያለውን ነገር ለማመልከት ተሠርቶበታል።
በተጨማሪም ጨው የሚለው ቃል አስተማማኝና ዘላቂ የሆነን ነገር ያመለክት ነበር። ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይለወጥና የማይሻር ቃል ኪዳን “የጨው ቃል ኪዳን” ተብሎ ተጠርቷል። ቃል ኪዳን ተጋቢዎቹ ጨው ያለበት ምግብ አብረው በመብላት ቃል መጋባታቸውን ያረጋግጡ ነበር። (ዘኁልቁ 18:19) በሙሴ ሕግ በመሠዊያ ላይ በሚቀርቡ መሥዋዕቶች ላይ ጨው መጨመር አስፈላጊ ነበር። ይህም ከመበላሸትና ከመበስበስ የጸዳ መሆኑን ያመለክት እንደነበረ አያጠራጥርም።
የታሪክ መረጃዎች
በታሪክ ዘመናት በሙሉ ጨው (ሶዲየም ክሎራይድ) ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ሸቀጥ ሆኖ በመቆየቱ በጨው የተነሣ ጦርነት እስከማንሳት የተደረሰበት ጊዜ ነበር። ለፈረንሣይ አብዮት መፈንዳት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ሉዊ 16ኛ በጨው ላይ የጣለው ከፍተኛ ቀረጥ ነበር። ጨው የመሸጫና መለወጫ መሣሪያም ሆኖ አገልግሏል። የአረብ ነጋዴዎች ጨው በወርቅ መሳ ለመሳ ይለውጡ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ አሞሌ ጨው በገንዘብነት አገልግሏል። ግሪኮች ለባሮቻቸው ይከፍሉ የነበረው ደመወዝ ጨው ስለነበረ “ለጨው የማይበቃ” የሚል አነጋገር ሊፈጠር ችሏል።
በመካከለኛው ዘመን ከጨው ጋር በተያያዘ አንዳንድ አጉል እምነቶች ተፈጥረው ነበር። ጨው መድፋት የጥፋት ምልክት ተደርጎ ይታይ ነበር። ለምሳሌ፣ “የመጨረሻው እራት” በተባለው የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ የቀለም ቅብ ሥዕል ላይ በአስቆሮቱ ይሁዳ ፊት ላይ የተገለበጠ የጨው ዕቃ ተስሏል። በሌላ በኩል ደግሞ እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ድረስ በግብዣ ገበታ ላይ የጨው ዕቃ ከተቀመጠበት ቦታ በላይ ወይም በታች መቀመጥ የአንድን ሰው ክብር ያመለክት ነበር። ከፍተኛ ክብር ያለው ሰው ከጨው ዕቃው በላይ ከገበታው ጫፍ አጠገብ ይቀመጥ ነበር።
የሰው ልጅ ከውቅያኖስ ውኃና ከአለት ጨው ማውጣት እንደሚቻል ካወቀ ረዥም ዘመን አልፏል። አንድ የቻይናውያን የመድኃኒት ቅመማ ጥንታዊ ጽሑፍ 40 የሚያክሉ የጨው ዓይነቶችን ከመዘርዘሩም በላይ ዛሬ ከሚሠራባቸው ዘዴዎች ጋር በጣም ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ዓይነት የጨው ማውጫ ዘዴዎችን ይገልጻል። ለምሳሌ በትልቅነቱ ከዓለም አንደኛ በሆነውና በሜክሲኮ፣ ባሃ ካሊፎርኒያ ሱር ግዛት በባይያ ሴባስትያን ቢስካይኖ የባሕር ጠረፍ ላይ በሚገኘው የጨው ማምረቻ ጨው የሚመረተው የውቅያኖሱን ውኃ በፀሐይ ሙቀት በማትነን ነው።
ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሆነ በዓለም ውቅያኖሶች ውስጥ የሚገኘው ውሃ ሙሉ በሙሉ እንዲደርቅ ቢደረግ የሚቀረው ጨው “19 ሚልዮን ኪሎ ሜትር ኩብ የሚሆን ትልቅ የጨው ቋጥኝ እንደሚፈጥር ወይም ከውኃ ወለል በላይ ካለው የአውሮፓ ምድር 14.5 እጥፍ የሚሆን ግዙፍ ቋጥኝ እንደሚያስገኝ” ተገምቷል። በሙት ባሕር ውስጥ የሚገኘው ጨው ደግሞ በውቅያኖስ ውስጥ ከሚገኘው ጨው በዘጠኝ እጥፍ ይበልጣል።
ጨው በዘመናችን የሚሰጠው ጥቅም
ዛሬም ቢሆን ጨው ምግብ ለማጣፈጥ፣ ሥጋ እንዳይበላሽ ለማድረግ፣ ሣሙናና መስተዋት ለመሥራትና ለሌሎች በርካታ አገልግሎቶች ስለሚውል ተፈላጊነቱ አልቀነሰም። በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ረገድ የሚሰጠው ጥቅምም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ በብዙ አገሮች እንቅርትና የአእምሮ ዘገምተኝነት የሚያስከትለውን የአዮዲን እጥረት ለማስወገድ ለገበያ በሚቀርበው ጨው ላይ አዮዲን ይጨመራል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ የጥርስ መቦርቦርን ለመከላከል በጨው ላይ ፍሎራይድ ይጨመራል።
ጨው የደምን መጠንና ግፊት በማስተካከል ለጥሩ ጤና ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የታወቀ ቢሆንም በጨውና በደም ግፊት መጨመር መካከል ስላለው ዝምድናስ ምን ለማለት ይቻላል? ሐኪሞች ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸው በሽተኞች ጨውና ሶዲየም በጣም እንዲቀንሱ ይመክራሉ። ከፍተኛ የደም ግፊት ካላቸው በሽተኞች መካከል ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት ጨው መውሰድ በሽታቸውን ያባብስባቸዋል። እንደነዚህ ያሉት በሽተኞች ጨው በሚቀንሱበት ጊዜ የደም ግፊታቸው እንደሚቀንስ ተረጋግጧል።
ጨው ምግብ እንደሚያጣፍጥ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢዮብም “የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን?” ብሎ በመጠየቅ ይህንኑ የጨው የማጣፈጥ ኃይል አመልክቷል። (ኢዮብ 6:6) በእርግጥም እንደ ጨው ያለውን ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ሸቀጥ ጨምሮ ‘ደስ እንዲለን ሁሉን አትርፎ የሚሰጠንን’ ፈጣሪያችንን ማመስገን ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:17
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ ከሆኑት የጨው ዓይነቶች አንዳንዶቹ (ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ )፦ (1) የባሕር ጨው፣ ሐዋይ፣ (2) ፍለር ደ ሴል፣ ፈረንሣይ፣ (3) ኦርጋኒክ ጥሬ የባሕር ጨው፣ (4) ሴል ግሪ (ግራጫ ጨው) ፈረንሣይ፣ (5) ያልደቀቀ የባሕር ጨው፣ (6) የተፈጨ ጥቁር ጨው፣ ሕንድ