የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆችና ዘርፈ ብዙ ችግሮቻቸው
“ብዙ ዓይነት ስሜት ይፈራረቅብኛል። መታጠቢያ ቤት ዘግቼ ሳለቅስ የማድርበት ጊዜ አለ። በጣም ከባድ ነው።”—ጃነት፣ ሦስት ልጆችን ያለ አባት የምታሳድግ እናት
አንድ ወላጅ ልጆቹን ብቻውን ለማሳደግ እንዲገደድ የሚያደርጉት ምክንያቶች ብዙ ናቸው። አንዳንድ ቤተሰቦች አንደኛውን ወላጅ የሚያጡት በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በበሽታ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የአንዳንድ ልጆች ወላጆች ተጋብተው ለመኖር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ለምሳሌ፣ በስዊድን ግማሽ የሚያክሉ ልጆች የሚወለዱት ከጋብቻ ውጭ ነው። በፍቺ ምክንያት የሚፈጠሩ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችም ይኖራሉ። ከአሜሪካ ሕፃናት መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተወሰነውን የልጅነት ዕድሜያቸውን በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ እንደሚያሳልፉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የችግሩን ባሕርይ መረዳት
ባሎቻቸውን በቅርቡ በሞት ያጡ እናቶች በጣም ከባድ የሆነ ሸክም ይወድቅባቸዋል። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ማጣታቸው ያስከተለባቸውን ሐዘን ገና ሳይወጡ የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን ለመሸከም ይገደዳሉ። የሚደርስባቸውን የኢኮኖሚ ችግር መወጣትና ልጆቻቸውን ማጽናናት ብርቱ ጥረት ማድረግን ስለሚጠይቅባቸው ከአዲሱ ኃላፊነታቸው ጋር መላመድ በርካታ ወራት ብሎም ዓመታት ሊወስድባቸው ይችላል። ባሏን በሞት ያጣችው እናት እነዚህን ተጨማሪ ኃላፊነቶች ለመወጣት በጣም ሊከብዳት ይችላል። በዚህ ምክንያት አንድ ልጅ ማበረታቻና ማጽናኛ በሚያስፈልገው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የወላጁን እንክብካቤና ጥበቃ በበቂ መጠን ሳያገኝ ይቀራል።
ሕጋዊ ባላቸው ካልሆነ ሰው የወለዱ የትዳር ጓደኛ የሌላቸው እናቶች አብዛኛውን ጊዜ በጣም ወጣቶችና በቂ ተሞክሮ የሌላቸው ናቸው። መደበኛ ትምህርታቸውን የመጨረስ አጋጣሚም አላገኙ ይሆናል። በቂ የሆነ የሥራ ችሎታ ስለማይኖራቸው በአነስተኛ ደመወዝ የመቀጠርና በድህነት ኑሮ የመማቀቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ወላጆቻቸው ወይም ሌሎች ዘመዶቻቸው ካልረዷቸው ደግሞ ልጃቸውን የሚጠብቅ ወይም ሞግዚት የሚሆን ሰው ለመፈለግ ይገደዳሉ። በተጨማሪም ሳታገባ ወልዳ ልጅዋን ብቻዋን የምታሳድግ እናት እንደ ሃፍረትና ብቸኝነት ከመሰሉት የሚረብሹ ስሜቶች ጋር መታገል ይኖርባታል። አንዳንዶች የልጅ እናት መሆናቸው ተስማሚ ባል የማግኘት ዕድላቸውን ሊያጨልምባቸው እንደሚችል ይሰማቸዋል። እንደዚህ ባለው ቤት ውስጥ ያደጉ ልጆች ትልቅ በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ስለተወለዱበት ሁኔታና ስለተነጠላቸው ወላጅ ብዙ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ይረብሿቸዋል።
የሚፋቱ ወላጆችም በተመሳሳይ ከፍተኛ ውጥረት ያጋጥማቸዋል። አንዳንድ ወላጆች በፍቺው ምክንያት ከፍተኛ ብስጭት ሊያድርባቸው ይችላል። አንዳንድ ወላጆች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ስለሚቀንስባቸውና የተጣሉ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ለልጆቻቸው ስሜታዊ እንክብካቤ መስጠት ያቅታቸዋል። በዕድሜያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ ዓለም የገቡ እናቶች የቤት ውስጥ ኃላፊነቶቻቸውን መወጣት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ከፍቺው በኋላ ሁኔታዎች ባላሰቡት መንገድ ተለዋውጠውባቸው ለተደናገጡት ልጆቻቸው ትኩረት ለመስጠት ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል።
የተፋቱ ወላጆች የሚያጋጥሟቸው በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ችግሮች
የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች የልጆቻቸው ፍላጎቶች የተለያዩ እንደሆኑና ሁልጊዜ እንደሚለዋወጡ ይገነዘባሉ። የተፋቱ ወላጆች ልጆቻቸው መንፈሳዊ መመሪያ ሊያገኙ የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ልዩ የሆነ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል።
ለምሳሌ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ የተፋቱ ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተዳደር መብት አላገኙ ይሆናል። በመሆኑም ከልጆቻቸው ጋር መገናኘት የሚችሉበት ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከሚገኙበት ጊዜ ጋር እንዲጋጠም በማድረግ ስብሰባ ይዘዋቸው ለመሄድ ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው ዝግጅት ልጁ ከክርስቲያን ጉባኤ እንዳይራራቅ ይረዳዋል። ይህ ደግሞ ወላጆቻቸው ለተፋቱባቸው ልጆች በጣም ጠቃሚ ነው።
ከልጆቻቸው ጋር ብዙ የመገናኘት አጋጣሚ የሌላቸው የተፋቱ ወላጆች ፍቅራቸውንና አሳቢነታቸውን ለልጆቻቸው ለመግለጽ የሚያስችሏቸውን መንገዶች መፈለግ ይኖርባቸዋል። አንድ ወላጅ በዚህ ረገድ እንዲሳካለት በየጊዜው የሚለዋወጠውን የልጁን ስሜታዊ ፍላጎት በንቃት መከታተል ይኖርበታል። በተለይ ልጁ ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርስና በማኅበራዊ ጉዳዮች የመካፈልና ጓደኛ የማፍራት ፍላጎቱ እያየለ ሲመጣ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
በተጨማሪም አንድ ጥሩ ወላጅ የልጁን አቅም፣ ጠባይና አስተሳሰብ ይረዳል። (ዘፍጥረት 33:13) ወላጆችና ልጆች ተቀራርቦ መነጋገርና አብሮ መጫወት በጣም ሊያስደስታቸው ይገባል። ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መስመር ሁልጊዜ ክፍት መሆን ይኖርበታል። የወላጁ ሕይወት ከልጁ የተነጠለ አይደለም፣ የልጁም ሕይወት ከወላጁ የተነጠለ አይደለም።
ምክንያታዊ የመሆን አስፈላጊነት
ከፍቺው በኋላ ልጆች ከሁለቱም ወላጆች ጋር አዘውትረው ቢገናኙ ይጠቀማሉ። ወላጆቹ የተለያየ ሃይማኖታዊ እምነት ቢኖራቸውና አንደኛው የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ሌላኛው ባይሆንስ? ዘወትር ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ አላስፈላጊ የሆኑ ግጭቶችን ያስወግዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ምክንያታዊ ነው የሚል ስም ይኑራችሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:5 ፊሊፕስ) ልጆች ሁለቱም ወላጆቻቸው የየግል ሃይማኖታቸው የሚጠይቅባቸውን የማድረግ መብት እንዳላቸውና ይህንንም መብታቸውን ሊያከብሩላቸው እንደሚገባ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል።
ምሥክር ያልሆነው ወላጅ ልጁ በራሱ ቤተ ክርስቲያን በሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ እንዲገኝ ሊያስገድድ ይችላል። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ወላጅ ምን ልታደርግ ትችላለች? እርሷም እምነቷን ለልጅዋ ልታካፍል ትችላለች። ከጊዜ በኋላ ልጁ ከእናቱና ከሴት አያቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ደንቦችን እንደተማረው እንደ ወጣቱ ጢሞቴዎስ በሃይማኖት ረገድ የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ልጁ በሌላ ሃይማኖት በሚካሄድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ መገኘት ከከበደው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ንዕማን እውነተኛ አምላኪ ከሆነም በኋላ ወደ ሬሞን ቤት እየገባ ያመልክ የነበረውን ንጉሥ ያጅብ እንደነበረ ሊያስታውስ ይችላል። ይህ ታሪክ ልጁ ባልለመደው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ቢገኝም የይሖዋ ፍቅርና አሳቢነት እንደማይለየው ሊያረጋግጥለት ይችላል።—2 ነገሥት 5:17-19
አንድ ጥሩ ወላጅ የልጁን ወይም የልጆቹን አስተሳሰብ ለመቅረጽና ስሜታቸውን ለመረዳት ይችላል። (ዘዳግም 6:7) እርግጥ ነው፣ ሕጋዊ ትዳር መሥርተው የማያውቁ ወላጆች በቀድሞ አኗኗራቸው እፍረት ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ወላጆች፣ ልጆች ሁለት የሥጋ ወላጆች እንዳሏቸው ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል። ልጆች ስለ ሁለቱም ወላጆቻቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። በተጨማሪም እንዲሁ በመጥፎ አጋጣሚ የተገኙ ሳይሆኑ የሚፈለጉ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ። ወላጅዬው ስለሌላው ወላጅ በአክብሮት በመናገርና ልጁ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች በዕድሜው ሊረዳ የሚችላቸውንና ማወቅ ያለበትን መልሶች በመስጠት ተረጋግቶና ተማምኖ እንዲኖር መርዳት ይችላል።
ወላጆች አንድ ልጅ ስለ ፍቅርና ስለ ሥልጣን ያለው አመለካከት የሚቀረጸው ከወላጁ ጋር ባለው ግንኙነት እንደሆነ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። አንድ ክርስቲያን ወላጅ ሥልጣኑን በፍቅርና በአግባብ መጠቀሙ ልጁ ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲፈጥርና ለጉባኤው ዝግጅቶች አክብሮት እንዲያድርበት ሊያደርገው ይችላል።—ዘፍጥረት 18:19
የልጆች ትብብር አስፈላጊ ነው
በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆችም በበኩላቸው የእነርሱ ትብብር ለመላው ቤተሰብ ስኬት አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 6:1-3) ለወላጅ ሥልጣን ታዛዥ መሆናቸው ወላጃቸውን እንደሚወዱና ወላጃቸው ያሉበትን ተደራራቢ ኃላፊነቶች በመወጣት ደስታና ምቾት ያለበት ቤተሰብ ለመምራት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ ያሳያል። የሐሳብ ልውውጥ በጋራ የሚካሄድ ነገር በመሆኑ በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ወላጃቸው በቤተሰቡ ውስጥ ጥሩ የመግባባትና ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ መንፈስ እንዲሰፍን የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ እንዳለባቸው መረዳት ይገባቸዋል።—ምሳሌ 1:8፤ 4:1-4
እንደነዚህ ያሉት ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በሁለት ወላጆች በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች ፈጥነው ኃላፊነት እንዲሸከሙ ይጠበቅባቸዋል። ልጆች በትዕግሥትና በፍቅር መመሪያ እየተሰጣቸው የኑሮ ኃላፊነቶችን የመሸከም ችሎታ እያዳበሩ ሲሄዱ ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ በራሳቸው የሚተማመኑና ለራሳቸው አክብሮት ያላቸው ይሆናሉ። በተጨማሪም ቤቱ ያልተዝረከረከና ሥርዓታማ እንዲሆን አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎች ለልጆች ሊሰጡ ይችላሉ።
ይህ ሲባል ግን የትዳር ጓደኛ የሌላት አንዲት ወላጅ ልጆቿን የወላጅ መመሪያ የማያስፈልጋቸውና ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ የሕፃን አዋቂዎች ታደርጋቸዋለች ማለት አይደለም። እንዲያውም አንድን ትንሽ ልጅ ብቻውን አለጠባቂ መተው ተገቢ አይደለም።
የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ባልንጀራ ማድረግ እንዳለባቸው ያስባሉ። ሆኖም መቀራረብ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ልጅ ወላጅ እንደሚያስፈልገውና የወላጁ ምሥጢረኛ ወይም ባልንጀራ ለመሆን የሚያስችለው ብስለት እንደሌለው መዘንጋት የለባቸውም። ልጆቻችሁ እንደ ወላጅ እንድትሆኑላቸው ይፈልጋሉ።
የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆችና ልጆቻቸው በፍቅር እየተሳሰቡ ሲረዳዱ የተሳካለት ቤተሰብ መገንባት ይችላሉ። በአንድ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ቁጥር እየበዛ በሄደ መጠን ሁሉም ሰው የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆችና ልጆቻቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መረዳትና ፍቅራዊ ማበረታቻና ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን ይገባዋል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
በጥቅሉ ሲታይ ልጆቻቸውን ያለ አባት ወይም ያለ እናት የሚያሳድጉ ወላጆች በጋብቻ ተሳስረው የሚኖሩ ወላጆችን ያህል ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ አይችሉ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ሕጋዊ የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች ካላገቡት ሰው ጋር አብረው ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚኖረው ዝምድና በሕጋዊ መንገድ የተመሠረተ ትዳርን ያህል የጸና አይሆንም። በመሆኑም በእንዲህ ዓይነት ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ የእንጀራ አባቶች ወይም የእንጀራ እናቶች ለማየት ሊገደዱ ይችላሉ።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ “በአማካይ ሲታይ እናትም አባትም ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች ይልቅ በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ሥነ ምግባራዊ ሕይወታቸው ሊበላሽ የሚችልበት ዕድል በልጦ ተገኝቷል።” ይሁን እንጂ በእንዲህ ዓይነት ጥናቶች ላይ የተካሄደው ጠለቅ ያለ ምርመራ “በተለያዩ ዓይነት ቤተሰቦች ውስጥ በሚኖሩ ልጆች ላይ ለሚታየው ልዩነት ዋነኛው ምክንያት” የገቢ መጠን ማነስ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል። እንዲህ ሲባል ግን በአንድ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ሕይወት የጨለመ ነው ማለት አይደለም። ተገቢው መመሪያና ሥልጠና ከተሰጣቸው አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸውን ሁኔታዎች መቋቋም ይችላሉ።