የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ እምነት የማይጥሉብኝ ለምንድን ነው?
“ወላጆቼ ብቻዬን ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ቢፈቅዱልኝ ደስ ይለኛል። ከቤት ወጥቼ ዓለምን መዞር እፈልጋለሁ አላልኩም። ለምሳሌ፣ እናቴ ከቤት ልጠፋ እንዳሰብኩ በመጠርጠር ሳትጨነቅ አክስቴን ለመጠየቅ እንድሄድ እንዲፈቀድልኝ እፈልጋለሁ።”—የ18 ዓመቷ ሣራa
“ከጓደኞቼ ጋር አንድ ቦታ መሄድ እንደምፈልግ ለወላጆቼ ስነግራቸው እምነት የማይጥሉብኝ ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ እጠይቃቸዋለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ‘አንቺን እናምንሻለን፤ የማናምነው ጓደኞችሽን ነው’ የሚል መልስ ይሰጡኛል። እንዲህ ሲሉኝ ደግሞ ያበሳጨኛል!”—የ18 ዓመቷ ክሪስቲን
የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ፣ ገንዘብን ከማግኘት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። ለማግኘት ከባድ ቢሆንም በቀላሉ ልናጣው እንችላለን። ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖረን ፈጽሞ በቂ እንዳልሆነ ሊሰማን ይችላል። የ16 ዓመቷ ኢልያና እንዲህ ብላለች:- “ወደ አንድ ቦታ መሄድ እንደምፈልግ ለወላጆቼ ስነግራቸው የጥያቄ መዓት ያዥጎደጉዱብኛል። የት እንደምሄድ፣ ከእነማን ጋር እንደምሄድ፣ ሄጄ ምን እንደማደርግና መቼ እንደምመለስ ይጠይቁኛል። እርግጥ ወላጆቼ ናቸው፤ ሆኖም እንዲህ በጥያቄ ሲያጣድፉኝ እበሳጫለሁ!”
አንዳንድ ጊዜ፣ ወላጆችህ ይበልጥ እምነት ሊጥሉብህ እንደሚገባ ይሰማሃል? እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ በቅድሚያ አመኔታ የማግኘቱ ጉዳይ በበርካታ ወላጆችና ወጣቶች መካከል የሚነሳ አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት።
ማደግ የሚያስከትለው ጭንቀት
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ከአባቱና ከእናቱ እንደሚለይ’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:24) ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች፣ የጉርምስና አሊያም የኮረዳነት ወቅት ዋነኛ ዓላማው ሙሉ ሰው ወደ መሆን ደረጃ ላይ እንድትደርሱ እናንተን ማዘጋጀት ነው። እዚህ ደረጃ ላይ ስትደርሱ ከቤት ለመውጣት ዝግጁ ከመሆናችሁም በላይ የራሳችሁን ቤተሰብ ልትመሠርቱም ትችላላችሁ።
ይሁን እንጂ ሙሉ ሰው ወደ መሆን ደረጃ የመሸጋገሩ ሂደት የተወሰነ ዕድሜ ላይ ስትደርስ ዘው ብለህ እንደምትገባበት በር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሂደት ደረጃ ከመውጣት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የጉርምስናን ዕድሜ እስክታልፍ ድረስ ደረጃውን ቀስ በቀስ ትወጣዋለህ። እርግጥ ነው፣ ደረጃውን ምን ያህል ወጥተሃል በሚለው ጉዳይ ላይ በአንተና በወላጆችህ መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። በጓደኛ ምርጫ ረገድ ወላጆቿ እምነት እንደማይጥሉባት የሚሰማት ማሪያ እንዲህ ብላለች:- “ሃያ ዓመቴ ቢሆንም አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ አንስማማም። ወላጆቼ ከመጥፎ ሁኔታ ለመራቅ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌለኝ ይሰማቸዋል። እኔ ደግሞ ከአሁን በፊት ከመጥፎ ሁኔታዎች እንደራቅሁ ላስረዳቸው እሞክራለሁ፣ ሆኖም ይህ በቂ እንደሆነ አይሰማቸውም!”
ማሪያ የሰጠችው ሐሳብ እንደሚያሳየው አመኔታ የማትረፍ ጉዳይ በወጣቶችና በወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በቤተሰብህ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል? ከሆነ ወላጆችህ የበለጠ እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ጥበብ የጎደለው እርምጃ በመውሰድህ ምክንያት በወላጆችህ ዘንድ የነበረህን አመኔታ ካጣህ ይህንን መልሰህ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?
እምነት የሚጣልብህ መሆንህን በተግባር አሳይ
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች “ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) አንድ ሰው ራሱን መፈተንና ማንነቱን በተግባር ማሳየት ይችላል። ጳውሎስ ይህን ሐሳብ በዋነኝነት የጻፈው በጉርምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወጣቶችም ይሠራል። አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ዘንድ አመኔታ ማትረፍህ፣ እምነት የሚጣልብህ ሆነህ በመገኘትህ ላይ የተመካ ነው። ይህ ሲባል ፍጹም መሆን አለብህ ማለት አይደለም። ደግሞም የማይሳሳት ሰው የለም። (መክብብ 7:20) ይሁንና በጥቅሉ ሲታይ ባሕርይህ፣ ወላጆችህ በአንተ ላይ እምነት እንዳይጥሉ የሚያደርጋቸው ነው?
ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሆነን ለመኖር እንናፍቃለን’ በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18 NW) እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የት እንደምሄድ እንዲሁም ምን እንደማደርግ ስጠየቅ እውነቱን እናገራለሁ?’ በዚህ ረገድ ራሳቸውን በሐቀኝነት የመረመሩ አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን ሐሳብ ተመልከት።
ሎሪ:- “ከአንድ የምወደው ልጅ ጋር በምስጢር ኢሜይል እጻጻፍ ነበር። ወላጆቼ ነገሩን ደረሱበትና እንዳቆም ነገሩኝ። እኔም ከልጁ ጋር መጻጻፌን እንደማቆም ቃል ገባሁላቸው። ይሁን እንጂ ቃሌን መጠበቅ አልቻልኩም። በዚህ መልኩ ሁኔታው ለአንድ ዓመት ቀጠለ። ከልጁ ጋር መልእክት እላላካለሁ፤ ወላጆቼ ሁኔታውን ይደርሱበታል፤ ከዚያም ይቅርታ እጠይቅና ለማቆም ቃል እገባለሁ። ከዚያ ግን እንደገና ከልጁ ጋር እጻጻፋለሁ። ሁኔታው በዚህ መልኩ በመቀጠሉ በመጨረሻ ወላጆቼ በማንኛውም ነገር በእኔ ላይ እምነት መጣል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ!”
የሎሪ ወላጆች፣ በልጃቸው ላይ እምነት መጣል ያልቻሉት ለምን ይመስልሃል? ሎሪ፣ ወላጆቿ ችግሩን አስመልክተው ለመጀመሪያ ጊዜ ካነጋገሯት በኋላ በእነሱ ዘንድ ያላትን አመኔታ ላለማጣት ምን ማድረግ ነበረባት? መልስህን ከዚህ በታች ጻፍ።
․․․․․
ቤቨርሊ:- “ወላጆቼ ከወንዶች ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ እምነት ሊጥሉብኝ እንደሚችሉ አይሰማቸውም ነበር። እንዲህ የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ አሁን ገብቶኛል። በሁለት ዓመት ከሚበልጡኝ የተወሰኑ ወንዶች ጋር አላግባብ እቀራረብ ነበር። በተጨማሪም ከእነሱ ጋር ለረጅም ሰዓታት በስልክ አወራለሁ፤ እንዲሁም ሰብሰብ የምንልበት አጋጣሚ ሲፈጠር ከእነዚህ ልጆች ጋር ካልሆነ በስተቀር ከማንም ጋር አላወራም ነበር። ወላጆቼ ለአንድ ወር ያህል ስልኬን የወሰዱብኝ ከመሆኑም ባሻገር እነዚህ ልጆች ወደሚገኙበት ቦታ እንዳልሄድ ከለከሉኝ።”
የቤቨርሊ ወላጆች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በልጃቸው ላይ እምነት መጣል ያቃታቸው ለምን ይመስልሃል? ቤቨርሊስ የወላጆቿን አመኔታ መልሳ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለች?
․․․․․
አኔት:- “በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት እኔና ጓደኛዬ ከአንድ የግብዣ ቦታ አንድ አንድ ቢራ ወደ ቤታችን ወሰድን፤ ወላጆቻችን እንዲህ እንድናደርግ እንደማይፈቅዱልን ብናውቅም ዘና ለማለት ያህል ቆየት ብለን ልንጠጣ ወሰንን። የጓደኛዬ እናት የቢራውን ጣሳ አገኙት። ከዚያም እኔም ቢራ እንደጠጣሁ ታወቀ። ከምንም ነገር በላይ የከበደኝ እናቴ ምን ያህል እንዳዘነችብኝ ፊቷ ላይ መመልከቴ ነበር!”
አኔት ታናሽ እህትህ ብትሆን በእናታችሁ ዘንድ ያላትን አመኔታ መልሳ ማግኘት እንድትችል ምን ምክር ትሰጣት ነበር?
․․․․․
እንደገና የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ
ከላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች አንተም በፈጸምከው ድርጊት የተነሳ የወላጆችህን አመኔታ አጥተህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህም እንኳ ወላጆችህ እንደገና እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ኃላፊነት እንደሚሰማህ የሚያሳይ ተግባር ለማከናወን ጥረት ባደረግህ መጠን ወላጆችህም የበለጠ እምነት እየጣሉብህ ይሄዳሉ። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከባንክ ገንዘብ የተበደረን አንድ ሰው እንውሰድ። ይህ ሰው የተበደረውን ገንዘብ በየጊዜው የሚከፍል ከሆነ የባንኩን አመኔታ ያተርፋል፤ አልፎ ተርፎም ባንኩ ወደፊት ተጨማሪ ብድር እንዲወስድ ሊፈቅድለት ይችላል። ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በትንንሽ ነገሮችም እንኳ ሳይቀር እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ካስመሠከርክ ወደፊት ወላጆችህ ይበልጥ እምነት ይጥሉብሃል።
አኔት ይህ እውነት መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች:- “ወጣት እያላችሁ በሌሎች ዘንድ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አይገባችሁም። አሁን ከቀድሞው የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው ሆኛለሁ፤ እንዲሁም ነገሮችን ማከናወን ያለብኝ በወላጆቼ ዘንድ ያለኝን አመኔታ በማያሳጣኝ መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል።” ታዲያ አንተ ከዚህ ምን ትማራለህ? ወላጆቼ እምነት አይጥሉብኝም ብለህ ከማማረር ይልቅ እምነት የሚጣልብህ ሰው እንድትሆን የሚያስችሉህን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት አድርግ።
ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ በታች በተገለጹት ነገሮች ረገድ እምነት የሚጣልብህ ነህ? ማሻሻያ ማድረግ በሚያስፈልግህ ነጥቦች ላይ ምልክት አድርግ።
□ በተባልኩት ሰዓት ቤት በመግባት
□ ሰዓት በማክበር
□ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን
□ ክፍሌን በንጽሕና በመያዝ
□ በስልክ አጠቃቀም
□ ቃሌን በመጠበቅ
□ በገንዘብ አጠቃቀም
□ መጎትጎት ሳያስፈልገኝ በሰዓቱ ከእንቅልፌ በመነሳት
□ እውነቱን በመናገር
□ ስህተቴን በማመንና ይቅርታ በመጠየቅ
□ በሌሎች ነገሮች
ምልክት ባደረግክባቸው ነገሮች ረገድ ማሻሻያ በማድረግ እምነት የሚጣልብህ ሰው ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። “ቀድሞ ስለነበራችሁበት ሕይወትም፣ . . . አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርግ። (ኤፌሶን 4:22) ቃላችሁ “‘አዎ’ ቢሆን አዎ ይሁን።” (ያዕቆብ 5:12) “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌሶን 4:25) “ለወላጆቻችሁ በሁሉም ነገር ታዘዙ።” (ቈላስይስ 3:20) ከጊዜ በኋላ ያደረግኸው እድገት ወላጆችህን ጨምሮ በሰው ሁሉ ፊት መታየቱ አይቀርም።—1 ጢሞቴዎስ 4:15
የቻልከውን ያህል ጥረት ብታደርግም እንኳ ወላጆችህ የሚገባህን ያህል እምነት እንዳልጣሉብህ ቢሰማህስ? ሁኔታውን አንስተህ ለምን ከእነሱ ጋር አትነጋገርም? ወላጆችህ የበለጠ እምነት ሊጥሉብህ እንደሚገባ በመግለጽ ቅሬታህን ከመናገር ይልቅ የእነሱን አመኔታ ለማግኘት አንተ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብህ በአክብሮት ጠይቃቸው። በዚህ ረገድ ያለህን ግብ በግልጽ ንገራቸው።
ወላጆችህ በአንተ ላይ የጣሉትን ገደብ ወዲያውኑ እንዲያነሱልህ አትጠብቅ። ወላጆችህ ቃልህን እንደምትጠብቅ እርግጠኛ መሆን እንደሚፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን አጋጣሚ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ለማሳየት ተጠቀምበት። በጊዜ ሂደት ወላጆችህ ከበፊቱ የበለጠ እምነት ሊጥሉብህ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው የቤቨርሊ ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። እንዲህ ብላለች:- “የሌሎችን አመኔታ ማጣት ቀላል ቢሆንም ማግኘቱ ግን ከባድ ነው። በአሁኑ ወቅት ወላጆቼ እምነት እየጣሉብኝ ነው፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ስሜት ይፈጥራል!”
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
◼ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረግህ ቢሆንም ወላጆችህ በአንተ ላይ የበለጠ እምነት ለመጣል የሚቸገሩት ለምን ሊሆን ይችላል?
◼ ወላጆችህ ከበፊቱ ይበልጥ እምነት እንዲጥሉብህ የምትፈልግ ከሆነ ከእነሱ ጋር መወያየትህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
እምነት የሚጣልብህ ሰው እንድትሆን የሚያስችሉህን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት አድርግ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]
እምነት የሚጣልበት ሙሉ ሰው ወደ መሆን ደረጃ የመሸጋገሩ ሂደት ደረጃ ከመውጣት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የጉርምስናን ዕድሜ እስክታልፍ ድረስ ደረጃውን ቀስ በቀስ ትወጣዋለህ
[ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )
ሙሉ ሰው መሆን
የጉርምስና ወቅት
ልጅነት