ልጃችሁ ኢንተርኔት ይጠቀማል?
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በቤታቸው፣ በትምህርት ቤት ወይም በጓደኛቸው ቤት ሆነው ኢንተርኔት ይጠቀማሉ፤ በቀላሉ ሊይዙት የሚችሉ ከኢንተርኔት ጋር የሚያገናኝ መሣሪያ አሊያም ሞባይል ስልክ ካላቸው ደግሞ በየትኛውም ቦታ ሆነው ኢንተርኔት መጠቀም ይችላሉ። ወላጅ ከሆናችሁ በቁም ነገር ልታስቡበት የሚገባ አንድ እውነታ አለ፦ ልጆቻችሁ በኢንተርኔት አጠቃቀም ረገድ ከእናንተ ይበልጥ እውቀት ሊኖራቸው የሚችል ከመሆኑም ሌላ በኢንተርኔት ስለሚያከናውኗቸው ነገሮች እንዳታውቁ ማድረግም ይችሉ ይሆናል።
ታዲያ ይህ ጉዳይ ሊያሳስባችሁ ይገባል? አዎ። በዚህ ረገድ ምንም ልታደርጉ አትችሉም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። እርግጥ ነው፣ ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ልጃችሁ ብዙ እውቀት ሊኖረው እናንተ ደግሞ ሁሉ ነገር እንግዳ ሊሆንባችሁ ይችላል። ያም ቢሆን ስለ ኢንተርኔት መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች መማር ትችላላችሁ። ልጃችሁን ከአደጋ ለመጠበቅ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ረገድ የግድ ሁሉንም ነገር ማወቅ አያስፈልጋችሁም።
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ታገኛላችሁ። መጀመሪያ ግን ልጃችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀም ሊያጋጥሙት ከሚችሉት አደገኛ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ካናዳ ውስጥ ሞባይል ስልክ ካላቸው ወጣቶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት በስልካቸው አማካኝነት ኢንተርኔት መጠቀም ይችላሉ