ጥሩ የገንዘብ አጠቃቀም ችሎታ አዳብር
ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” የሚል አባባል ያለ ይመስላቸዋል። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ግን “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” የሚል ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:10 አ.መ.ት) በእርግጥም አንዳንድ ሰዎች ለገንዘብ ፍቅር ያደረባቸው ከመሆኑም በላይ ብዙ ሀብት ለማከማቸት በጣም ይደክማሉ። አንዳንዶች የገንዘብ ባሪያዎች የሆኑ ሲሆን በዚህም ምክንያት ለአስከፊ ችግሮች ተዳርገዋል። ይሁን እንጂ ገንዘብን ጥሩ አድርገን ከተጠቀምንበት ጠቃሚ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል” በማለት ይናገራል።—መክብብ 10:19 ሆሊ ባይብል—ኢዚ ቱ ሪድ ቨርዥን
ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ አያያዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ጥሩ የገንዘብ አጠቃቀም ችሎታ እንዲኖርህ የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ይዟል። የገንዘብ አያያዝን በሚመለከት ምክር የሚሰጡ ሰዎች ቀጥሎ የቀረቡትን አምስት ነጥቦች በሥራ ማዋል ጠቃሚ መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን እነዚህ ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዓመታት በፊት በውስጡ ከያዛቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይስማማሉ።
ገንዘብ አጠራቅም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የጥንት እስራኤላውያን ከሀብታቸው ውስጥ የተወሰነውን እንዲያስቀምጡ ትምህርት ተሰጥቷቸው እንደነበር ያሳያል። በየዓመቱ በብሔራዊ በዓላት ላይ መገኘት ስለነበረባቸው ከበዓላቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ የሚጠቀሙበት አሥራት (ወይም አንድ አሥረኛ) እንዲያስቀምጡ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 14:22-27) ሐዋርያው ጳውሎስም የጥንት ክርስቲያኖች የተቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት የሚያስችል መዋጮ መስጠት እንዲችሉ በየሳምንቱ የተወሰነ ገንዘብ እንዲያስቀምጡ አበረታቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:1, 2) ገንዘብ አጠቃቀምን በሚመለከተ ምክር የሚሰጡ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ሰዎች ገንዘብ እንዲያጠራቅሙ ያበረታታሉ። አንተም ደሞዝ እንደተቀበልክ ምንም ነገር ከማድረግህ በፊት ለማጠራቀም ያሰብከውን ገንዘብ በባንክ ወይም አስተማማኝ በሆነ ሌላ ቦታ አስቀምጥ። እንዲህ ማድረግህ ገንዘቡን ለማጥፋት እንዳትፈተን ይረዳሃል።
በጀት አውጣ። ገንዘብህን በዕቅድ ለማውጣት፣ ወጪህን ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ የሚያስችልህ ብቸኛው ጠቃሚ መንገድ ይህ ነው። ጥሩ በጀት ማውጣትህ ገንዘብህ ምን ላይ እንደዋለ እንድታውቅ የሚያስችልህ ከመሆኑም በላይ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያወጣሃቸው ግቦች ላይ እንድትደርስ ይረዳሃል። ገቢህ ምን ያህል እንደሆነ እወቅ፤ ወጪህ ደግሞ ከገቢህ ያነሰ ይሁን። የግድ በሚያስፈልጉህና በምትፈልጋቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ጣር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ አድማጮቹን አንድ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ‘ወጪያቸውን እንዲያሰሉ’ አሳስቧቸው ነበር። (ሉቃስ 14:28) መጽሐፍ ቅዱስ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ከመግባት እንድንቆጠብ ምክር ይሰጠናል።—ምሳሌ 22:7
ዕቅድ አውጣ። ወደፊት ምን ነገሮች እንደሚያስፈልጉህ በጥንቃቄ አስብ። ለምሳሌ ያህል ቤት ለመግዛት ብለህ ብድር ለመውሰድ ካሰብክ አነስተኛ ወለድ ከሚያስከፍል ድርጅት መበደርህ ጥሩ ውሳኔ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም ቤተሰብ ያለው አንድ ሰው የቤተሰቡ አባላት ችግር ላይ እንዳይወድቁ በማሰብ የሕይወት፣ የጤና፣ የአካል ጉዳት ወይም ሌላ ዓይነት የመድኅን ዋስትና መግባቱ ጥሩ እንደሆነ ይሰማው ይሆናል። ወደፊት ስለሚያስፈልጉህ ነገሮች ማሰብ ጡረታ ለምትወጣበት ጊዜ ዕቅድ ማውጣትንም ሊጨምር ይችላል። ምሳሌ 21:5 “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በማለት ያሳስበናል።
ተማር። የተለያዩ ሙያዎች በማዳበር እንዲሁም አካላዊና ስሜታዊ ጤንነትህን በመንከባከብ የተሻለ አቋምና ችሎታ እንዲኖርህ ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ የኋላ ኋላ ይክስሃል። መማርን የዕድሜ ልክ ልማድ አድርገው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብንና ጥንቃቄን” ከፍ አድርገን እንድንመለከትና እነዚህን ባሕርያት እያዳበርን እንድንሄድ ያሳስበናል።—ምሳሌ 3:21, 22 የ1954 ትርጉም፤ መክብብ 10:10
ሚዛናዊ ሁን። ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከገንዘብ ይልቅ ለሰዎች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች የላቀ ደስታ አላቸው። አንዳንዶች ከስግብግብነት የተነሳ ሚዛናቸውን ስተዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እነዚህ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው በሚገባ ከተሟሉላቸው በኋላ ሀብት ማሳደድ ይጀምራሉ። አንድ ሰው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከተሟላለት በኋላ የግድ ያስፈልገዋል የሚባል ምን ነገር አለ? በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል” በማለት መጻፉ ምንም አያስደንቅም። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ባለን ረክተን የመኖር ስሜት ማዳበራችን የገንዘብ ፍቅር እንዳይጠናወተን ለመከላከል እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳናል።
በእርግጥም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው። የምትፈቅድለት ከሆነ ገንዘብ ጌታህ ሊሆን ይችላል። በጥሩ ሁኔታ ከተጠቀምክበት ግን ከቤተሰብህ፣ ከጓደኞችህና ከአምላክህ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደመመሥረት ያሉ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማከናወን የምትችልበት ነፃነት ሊያስገኝልህ ይችላል። ይሁንና በዚህ ዓለም ውስጥ ስለ ገንዘብ ከመጨነቅ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን የሚቻል አይመስልም። ታዲያ ገንዘብ ምንጊዜም የጭንቀት መንስኤ ሆኖ ይቀጥላል? ድህነት ሊወገድበት የሚችል ምን ተስፋ አለ? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የቀረበው የመጨረሻው ክፍል ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
ገቢህ ምን ያህል እንደሆነ እወቅ፤ ወጪህ ደግሞ ከገቢህ ያነሰ ይሁን
የግድ በሚያስፈልጉህና በምትፈልጋቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ጣር
አንድ ሰው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከተሟላለት በኋላ የግድ ያስፈልገዋል የሚባል ምን ነገር አለ?