ከዓለም አካባቢ
የብሪታንያ የዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን፣ በ26 አገሮች ውስጥ በሚኖሩ 13,000 የሚያህሉ ሰዎች ላይ ያካሄደው ጥናት “በዓለም ዙሪያ ዋነኛው የመወያያ አጀንዳ ሙስና እንደሆነ” አመልክቷል። ይሁን እንጂ የዓለማችን ዋነኛ ችግር ድህነት ነው።—ቢቢሲ ኒውስ፣ ብሪታንያ
“በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ የኢየሱስን ልደት በሚያሳዩ ምስሎች ላይ ጂፒኤስ የተባለውን አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ መግጠም ጀምረዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢየሱስን ልደት የሚያሳዩትን ምስሎች መስረቅ በመላ አገሪቱ እጅግ ተስፋፍቷል።”—ዘ ዊክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የዩናይትድ ስቴትስ “ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን አማካሪ ኮሚቴ፣ ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም (ኃይለኛ ድካም የሚያስከትል በሽታ) ያለባቸው ሰዎች ደም ከመስጠት እንዲታገዱ ሐሳብ አቅርቧል፤ የዚህ አንዱ ምክንያት ይህን በሽታ የሚያመጣው ሬትሮቫይረስ [አንዳንድ ሬትሮቫይረሶች ኤድስ እና ካንሰር ሊያመጡ እንደሚችሉ ይታመናል] እንደሆነ ስለሚታሰብ ነው።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ብርሃን አልበገር ያሉ ባክቴሪያዎችን ይገድላል
በግላስኮ ስኮትላንድ የሚገኘው የስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ፣ በጣም ኃይለኛ የሆነ ብርሃን በመጠቀም አልበገር ያሉ ባክቴሪያዎችን ከሆስፒታሎች ለማስወገድ የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ አግኝቷል። ይህ ቴክኖሎጂ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን በማስወገድ ረገድ ጽዳት ከማካሄድና ፀረ ባክቴሪያ ኬሚካሎችን ከመጠቀም የበለጠ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። የማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን አንደርሰን እንደገለጹት ከሆነ በዚህ ቴክኖሎጂ “አማካኝነት በጣም ቀጭን የሆነ የብርሃን ጨረር በመላክ በባክቴሪያዎቹ ውስጥ ያሉትን ሞለኪውሎች ማንቀሳቀስ ይቻላል። ይህ ደግሞ ባክቴሪያዎቹ እንዲሞቱ የሚያደርግ ከፍተኛ ኬሚካል እንዲፈጠር ያደርጋል።”
የደን ምንጠራና ወባ
በሐሩር ክልል የሚገኙ ደኖች መመንጠራቸው በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 50 በመቶ ገደማ እንዲጨምር አድርጓል። ይህን ያሉት ብራዚል ውስጥ ከሚገኙ 54 የጤና ተቋማት ባሰባሰቡት መረጃና የደን ምንጠራዎችን በሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች ላይ ጥናት ያካሄዱ ተመራማሪዎች ናቸው። ጥናት በተደረገበት አካባቢ ዋነኛው የወባ በሽታ አምጪ ትንኝ አናፎሊስ ዳርሊንጊ የተባለው የወባ ትንኝ ዝርያ ነው። “የተመነጠረው አካባቢ የበለጠ ክፍት ቦታ እንዲፈጠርና ፀሐይ በከፊል ብቻ የሚያገኛቸው ኩሬዎች እንዲኖሩ ስለሚያደርግ ለትንኞች መራቢያ ምቹ ይሆናል” በማለት የዚህ ምርምር መሪ የሆኑት ሣራ ኦልሰን ተናግረዋል። በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነባቸው አካባቢዎች ከመጠን በላይ የሆነ የደን ምንጠራ የተካሄደባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ተደርሶበታል።
በራሪ ስኩዊድ
በቅርቡ የተገኘ የፎቶግራፍ መረጃ አንዳንድ የስኩዊድ ዝርያዎች በኃይል መስፈንጠር የሚያስችላቸውን ዘዴ በመጠቀም መብረር እንደሚችሉ አረጋግጧል። ሳይንቲፊክ አሜሪካን “ከ20 ሴንቲ ሜትር ያልበለጠ ቁመት ያላቸው ስኩዊዶች ከውኃ በላይ እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ከፍታ ሊዘልሉ እንደሚችሉ እንዲሁም መቅዘፊያዎቻቸውን እያራገቡና መቆንጠጫዎቻቸውን (ቴንታክል) እያወዛወዙ እስከ 10 ሜትር የሚደርስ ርቀት መወንጨፍ እንደሚችሉ” የባሕር ውስጥ የባዮሎጂ ባለሙያዎች ማስተዋላቸውን ገልጿል። ስኩዊዶች ውኃ ወደ ውስጥ በማስገባትና ይህን ውኃ በኃይል ገፍተው በማስወጣት ከባሕሩ ውስጥ ተፈትልከው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ኃይል ያገኛሉ። በሚበሩበት ጊዜ መቅዘፊያዎቻቸውን እንደ ክንፍ እንደሚጠቀሙበት የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ያሳያሉ።