መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 3
“መሲሑን አገኘነው”
በእነዚህ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።
ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ዕብራውያን ነቢያት መሲሑ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግረዋል፤ መሲሕ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “የተቀባ” የሚል ትርጉም አለው። እነዚህ ነቢያት የመሲሑን የወደፊት ሕይወት በተመለከተ ማለትም የሚመጣበትን የትውልድ መስመር፣ የሚወለድበትን ቦታ እንዲሁም የሚገለጥበትን ጊዜና የሚደርስበትን ነገር የሚገልጹ ዝርዝር ጉዳዮችን ተናግረዋል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ ክርስቲያኖች፣ እነዚህ ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ተገንዝበዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ለወንድሙ ለስምዖን “መሲሑን አገኘነው” በማለት የተናገረውን የደቀ መዝሙሩን የእንድርያስን ስሜት ይጋራሉ። (ዮሐንስ 1:40, 41) ታዲያ መሲሑን በተመለከተ የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል ነበር? እስቲ መሲሑን አስመልክቶ ከተነገሩት በርካታ ትንቢቶች መካከል አራቱን ብቻ እንመልከት፤ እንዲሁም እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩትን ማስረጃዎች እንመርምር።
ትንቢት 1፦ “በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል።”—ኢሳይያስ 9:7
ፍጻሜ፦ የማቴዎስ ወንጌል የሚጀምረው “የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ መጽሐፍ” በማለት ነው። ከዚያም ማቴዎስ የኢየሱስ የዘር ሐረግ በዳዊት በኩል እንደመጣ የዘረዘረ ሲሆን የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስም እንዲሁ አድርጓል።—ማቴዎስ 1:1-16፤ ሉቃስ 3:23-38
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ጆሴፈስ ያዘጋጃቸው ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት የአይሁድ ቤተሰቦችን ስም ዝርዝር የያዙ የትውልድ ሐረግ መዛግብት በሕዝባዊ መዝገብ ቤቶች ይገኙ ነበር። እነዚያ መዛግብት ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. ስትደመሰስ ጠፍተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ኢየሱስ የዳዊት ዘር እንደሆነ በሰፊው ይታወቅ ነበር። (ማቴዎስ 9:27፤ 20:30፤ 21:9) ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ውሸት ቢሆን ኖሮ ማንኛውም ሰው ኢየሱስ የዳዊት ዘር መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ ሊያነሳ አልፎ ተርፎም ሐሰት መሆኑን ሊያጋልጥ ይችል ነበር። ሆኖም ማንም ሰው እንዲህ ለማድረግ እንደሞከረ የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም።
ትንቢት 2፦ “አንቺ ግን፣ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣ አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን የሆነ፣ የእስራኤል ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልኛል።”—ሚክያስ 5:2
ፍጻሜ፦ ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም ነበር። አውግስጦስ ቄሳር የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ ሲያወጣ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የነበረው ዮሴፍ “ከዳዊት ቤትና ወገን ስለነበር በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ በይሁዳ ወዳለችው ቤተልሔም ተብላ ወደምትጠራ የዳዊት ከተማ” ከማርያም ጋር መሄድ ነበረበት። እዚያ እያሉ ማርያም “የበኩር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ” ማለትም ኢየሱስን “ወለደች።”—ሉቃስ 2:1-7
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● ሮማውያን ግብር ለመሰብሰብና ለወታደራዊ ምልመላ ሲሉ በመካከለኛው ምሥራቅ የሕዝብ ቆጠራ ያካሂዱ እንደነበር የአርኪኦሎጂ ግኝቶች አረጋግጠዋል። እንዲህ ያሉ የሕዝብ ቆጠራዎች ይደረጉ እንደነበር ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ ግብፅን ያስተዳድር የነበረው ሮማዊ አገረ ገዥ በ104 ዓ.ም. ያወጣው አዋጅ ነው። አሁን በብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው የዚህ አዋጅ ቅጂ እንዲህ ይላል፦ “ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበት ጊዜ ስለደረሰ በተለያዩ ምክንያቶች በሌላ አውራጃ የሚገኙ ሁሉ የተለመደውን የሕዝብ ቆጠራ ትእዛዝ ለመፈጸም እንዲሁም መሬታቸውን በሚገባ ለማልማት ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኗል።”
● ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት በእስራኤል ውስጥ ቤተልሔም ተብለው የሚጠሩ ሁለት ከተሞች ነበሩ። አንደኛዋ በስተሰሜን ናዝሬት አቅራቢያ ትገኝ ነበር። ሌላዋ ደግሞ በይሁዳ ምድር ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ትገኝ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ ይህች ከተማ ቀደም ሲል ኤፍራታ ተብላ ትጠራ ነበር። (ዘፍጥረት 35:19) ሚክያስ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በትንቢት እንደተናገረው ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም ኤፍራታ ነው።
ትንቢት 3፦ “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል።”—ዳንኤል 9:25
ፍጻሜ፦ በዳንኤል ትንቢት ውስጥ በግልጽ የተቀመጠው ይህ ጊዜ እያንዳንዳቸው 7 ዓመታትን ያቀፉ 69 ‘ሱባዔዎችን’ ወይም ሳምንታትን የያዘ ሲሆን ይህም በድምሩ 483 ዓመታት ይሆናል። ኢየሩሳሌምን መጠገን የተጀመረው በ455 ዓ.ዓ. ነው። በትንቢቱ እንደተነገረው ከ483 ዓመታት (ከ69 የዓመታት ሳምንታት) በኋላ ማለትም በ29 ዓ.ም. ኢየሱስ ተጠምቆ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሲቀባ ቅቡዕ ወይም መሲሕ ሆነ።a—ሉቃስ 3:21, 22
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ ‘ሕዝቡ የክርስቶስን [መምጣት] ይጠባበቁ’ ነበር። (ሉቃስ 3:15) አይሁዳዊው ምሁር አባ ሂለል ሲልቨር፣ ኤ ሂስትሪ ኦፍ መሲያኒክ ስፔኪዩሌሽን ኢን ኢዝርኤል በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበረው ጊዜ ሁሉም ሰው መሲሑ በቅርቡ እንደሚገለጥ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። በተጨማሪም “መሲሑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁለተኛ ሩብ [ከ26 እስከ 50 ዓ.ም.] አካባቢ ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር” ብለዋል። አይሁዶች መሲሑን ይጠባበቁ የነበረው “በዚያ ዘመን በሰፊው ይታወቅ የነበረውን የዘመን ስሌት” መሠረት በማድረግ እንደነበረም ሲልቨር ጽፈዋል።
ትንቢት 4፦ “አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ።”—ኢሳይያስ 53:9
ፍጻሜ፦ ኢየሱስ የተገደለው ሞት ከተፈረደባቸው ሁለት ወንጀለኞች ጋር ነበረ፤ የተቀበረው ግን የአርማትያሱ ዮሴፍ የሚባል አንድ ባለጠጋ ተከታዩ ከዐለት ፈልፍሎ በሠራው መቃብር ውስጥ ነው።—ማቴዎስ 27:38, 57-60፤ ዮሐንስ 19:38
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● አይሁዳዊው ጆሴፈስንና ሮማዊውን ታሲተስን ጨምሮ ክርስቲያን ያልሆኑ ሌሎች በርካታ የታሪክ ምሁራን ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ እንደተገደለ መሥክረዋል።
● በፓለስቲና የተደረጉ የአርኪኦሎጂ ምርምሮች የተለያዩ ክፍሎች ያሏቸው ወይም ከዐለት ተፈልፍለው የተሠሩ መቃብሮች እንደነበሩ አረጋግጠዋል። እንደ አርማትያሱ ዮሴፍ ላለ ባለጠጋና ተሰሚነት ያለው ሰው አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት መቃብር ማዘጋጀት ያን ያህል የሚከብድ ነገር አልነበረም።
እስካሁን ያየነው መሲሑን አስመልክቶ ከተነገሩና በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ካገኙ በርካታ ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ እነዚህ በዝርዝር የተነገሩ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ሊያስተባብል የሚችል አንድም ሰው አይኖርም። እነዚህ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው ትንቢቶቹን ያስነገረው አምላክ እንደሆነ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል፤ እንዲሁም አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች በመሲሑ በኩል እንደሚያመጣቸው ቃል የገባቸው በረከቶች እንደሚፈጸሙ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።
በሚቀጥለው እትም ላይ ‘ኢየሱስ በእርግጥ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ከሆነ ተሠቃይቶ የሞተው ለምንድን ነው?’ የሚለውን ትኩረት የሚስብ ጥያቄ እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መሲሑ ከሚገለጥበት ጊዜ ጋር ተያያዥነት ስላለው ስለዚህ ትንቢት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ከገጽ 197-199 ተመልከት።
[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ስለ መሲሑ ከተነገሩ አራት ትንቢቶች ጋር የተያያዙ ዓመታት
1 መሲሑ ከንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚመጣ ትንቢት ተነገረ
1070 ዓ.ዓ.
ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነ
607 ዓ.ዓ.
ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ተደመሰሰች
455 ዓ.ዓ.
ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ትእዛዝ ወጣ
2 መሲሑ በይሁዳ ቤተልሔም እንደሚወለድ ትንቢት ተነገረ
2 ዓ.ዓ.
ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣው ኢየሱስ በይሁዳ ቤተልሔም ተወለደ
3 መሲሑ፣ ኢየሩሳሌምን ለመጠገን ትእዛዝ ከወጣ ከ483 ዓመታት በኋላ እንደሚመጣ ትንቢት ተነገረ
29 ዓ.ም.
ኢየሱስ ተጠምቆ መሲሕ ሆነ
4 መሲሑ ከኃጢአተኞች ጋር እንደሚሞትና ከባለጠጎች ጋር እንደሚቀበር ትንቢት ተነገረ
33 ዓ.ም.
ኢየሱስ ከወንጀለኞች ጋር ተገድሎ ከባለጠጎች ጋር ተቀበረ