ለቤተሰብ | ትዳር
ይቅርታ መጠየቅ የሚቻልበት መንገድ
ተፈታታኙ ነገር
አንተና የትዳር ጓደኛህ በሆነ ጉዳይ ተጋጭታችኋል። ‘ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልገኝም፤ ጭቅጭቁን የጀመርኩት እኔ አይደለሁም!’ ትል ይሆናል።
ያጨቃጨቃችሁን ጉዳይ ብትተዉትም በመካከላችሁ ግን ውጥረት እንደሰፈነ ነው። አሁንም ይቅርታ ስለመጠየቅ ታስባለህ፤ ሆኖም “ይቅርታ” የምትለዋን ቃል ማውጣት ይተናነቅሃል።
ምክንያቱ ምንድን ነው?
ኩራት። “በውስጤ ኩራት ቢጤ ስላለብኝ አንዳንድ ጊዜ ‘ይቅርታ’ የሚለውን ቃል ማውጣት ከባድ ይሆንብኛል” በማለት ቻርልዝa የተባለ ባለትዳር በሐቀኝነት ተናግሯል። አንተም ኩራት ካለብህ ለተፈጠረው ችግር የተወሰነ አስተዋጽኦ እንዳደረግክ አምነህ መቀበል ሊያሳፍርህ ይችላል።
አመለካከት። ይቅርታ መጠየቅ የሚያስፈልግህ ጥፋተኛው አንተ ከሆንክ ብቻ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ጂል የተባለች ባለትዳር እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የእኔ እንደሆነ ካመንኩ ‘ይቅርታ’ ማለት ቀላል ይሆንልኛል። ሆኖም ሁለታችንም ትክክል ያልሆነ ነገር ከተናገርን ይህን ማድረግ ይከብደኛል። ያጠፋነው ሁለታችንም እስከሆንን ድረስ እኔ ይቅርታ የምጠይቅበት ምን ምክንያት አለ?”
ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የትዳር ጓደኛህ ከሆነ ደግሞ ይቅርታ ላለመጠየቅ በቂ ምክንያት እንዳለህ ይሰማህ ይሆናል። ጆሴፍ የተባለ አንድ ባለትዳር “ምንም ጥፋት እንደሌለብህ እርግጠኛ ከሆንክ ንጹሕ መሆንህን ለማሳየት የምትሞክረው ይቅርታ ባለመጠየቅ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
አስተዳደግ። ምናልባት ያደግከው ይቅርታ መጠየቅ እምብዛም ባልተለመደበት ቤተሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ደግሞ ጥፋትን አምኖ መቀበልን አልተማርክ ይሆናል። በዚህ ረገድ በልጅነትህ ጥሩ ሥልጠና ካላገኘህ አዋቂ ከሆንክ በኋላ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ሊከብድህ ይችላል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስለ ትዳር ጓደኛህ አስብ። ከዚህ በፊት አንድ ሰው ይቅርታ ሲጠይቅህ ምን እንደተሰማህ ለማስታወስ ሞክር። ታዲያ የትዳር ጓደኛህም ለምን እንዲህ እንዲሰማት አታደርግም? ጥፋተኛ እንደሆንክ ባይሰማህም እንኳ የትዳር ጓደኛህ እንደዚያ ስለተሰማት ወይም ድርጊትህ ያላሰብከውን ውጤት ስላስከተለ ብቻ ይቅርታ መጠየቅ ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ የትዳር ጓደኛህ ቅሬታ ቶሎ እንዲወገድ ሊረዳ ይችላል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሉቃስ 6:31
ስለ ትዳርህ አስብ። ይቅርታ መጠየቅን እንደ ሽንፈት ሳይሆን እንደ ድል ቁጠረው። ምክንያቱም ምሳሌ 18:19 ቅሬታን ይዞ የሚቆይ ሰው “ከተመሸገች ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው” ይላል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሥር መልሶ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ደግሞ ከባድ ምናልባትም ጨርሶ የማይቻል ነገር ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግን ይቅርታ የምትጠይቅ ከሆነ በመካከላችሁ የተፈጠረው አለመግባባት ወደከፋ ችግር እንዳያመራ ማድረግ ትችላለህ። በሌላ አባባል ከራስህ ስሜት በላይ ትዳርህን ታስቀድማለህ ማለት ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 2:3
ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣን ሁን። እርግጥ ነው፣ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ ላልሆንክበት ጉዳይ ይቅርታ መጠየቅ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። ሆኖም የትዳር ጓደኛህ ጥፋተኛ መሆኗ አንተ ተገቢ ያልሆነ ምግባር እንድታሳይ ሰበብ ሊሆንህ አይገባም። ስለዚህ ጉዳዩ ውሎ አድሮ መረሳቱ አይቀርም ብለህ በማሰብ ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ቅድሚያውን ወስደህ ይቅርታ መጠየቅህ የትዳር ጓደኛህም ይቅርታ መጠየቅ ቀላል እንዲሆንላት ያደርጋል። ደግሞም ይቅርታ በጠየቅክ ቁጥር ለሌላ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ማቴዎስ 5:25
ከልብህ እንደሆነ አሳይ። ላደረግከው ነገር ሰበብ አስባብ መደርደር ይቅርታ እንደመጠየቅ አይቆጠርም። በተጨማሪም “ጉዳዩ እንኳ ይህን ያህል የሚያስቆጣ አይመስለኝም! ለማንኛውም ይቅርታ” በማለት የለበጣ ይቅርታ መጠየቅም ቢሆን ተገቢ አይደለም። ጥፋትህን አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛህ ቅር መሰኘቷ ተገቢ እንደሆነ አመንክም አላመንክ ዞሮ ዞሮ ያስከፋት ነገር እንዳለ ተረዳላት።
እውነታውን አምነህ ተቀበል። እንደማንኛውም ሰው አንተም ስህተት እንደምትሠራ በትሕትና አምነህ ተቀበል! በተፈጠረው ችግር ውስጥ የአንተ እጅ እንደሌለበት ቢሰማህም እንኳ ሁኔታውን ከራስህ አንጻር ብቻ አትመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ክሱን አስቀድሞ ያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይህም ሌላው ወገን መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 18:17) ስለ ራስህና ስለ ድክመትህ ትክክለኛ አመለካከት መያዝህ ይቅርታ መጠየቅ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል።
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።