ጥናት 3
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዋነኛው መማሪያ መጽሐፋችን
1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ የጀመረውና ያለቀው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በምን ያህል መጠን ተሰራጭቷል?
1 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምንጠቀምበት ዋነኛ መማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የምሥራቹ አገልጋዮች እንደመሆናችንም ከዚህ መጽሐፍ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደተዘጋጀ፣ በውስጡ ምን ነገሮችን እንደያዘና እንዴት እንደምንጠቀምበት ማወቅ ይገባናል።
2 መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ የጀመረው በ1513 ከዘአበ ሙሴ እንዲጽፍ በታዘዘ ጊዜ ነበር። ተጽፎ ያለቀው ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ ጽሑፉን በጨረሰበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ ላይ ከአሥራ ስድስት መቶ ዘመናት በኋላ ነበር። በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊልም ሆነ በሙሉ 2,000 በሚያህሉ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ይገኛል። በሚልዮን በሚቆጠር ብዛት የሚታተሙ መጻሕፍት በጣም ጥቂቶች ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሺህ ሚልዮን በሚቆጠር ብዛት ታትሞ ተሰራጭቷል። ይህን በሚያክል ብዛት የተሠራጨ መጽሐፍ ፈጽሞ የለም። እርግጥ ነው፤ አንድ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ መጻፉ ወይም በመቶ ለሚቆጠሩ ዘመናት ተጠብቆ መቆየቱ ወይም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከበሬታ ማግኘቱ ብቻውን መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው አያረጋግጥም። በመለኮት የተደረሰና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖረው ይገባል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ቢመረምሩ በቂና አሳማኝ ማስረጃዎች እንዳሉት ለማረጋገጥ ይችላሉ።
3, 4. መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በምን ዓይነት መልክ ነበር? በምዕራፎችና በቁጥሮች የተከፋፈለውስ መቼ ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ሲሆን አሁን በምናውቀው መልኩ ስድሳ ስድስት መጻሕፍት አሉት። የመጽሐፎቹ ትክክለኛ ቁጥር (አንዳንዶቹ ቢጣመሩ ወይም ለየብቻቸው ቢሆኑ) ወይም የእያንዳንዱ መጽሐፍ ቅደም ተከተል ቢለያይ ይህን ያህል አስፈላጊ ጉዳይ አይደለም። በመንፈስ የተጻፉት መጻሕፍት ዝርዝር ከተጠናቀቀ በኋላ እንኳን መጻሕፍቱ ለብዙ ዘመናት አንድ ላይ ሳይጠቃለሉ ለየብቻቸው ተነጣጥለው ይገኙ ነበር። የመጻሕፍቱ የጥንት ዝርዝሮችም የቅደም ተከተል ልዩነት ነበራቸው። በጣም አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ በዝርዝሩ ውስጥ የተጠቃለሉት መጻሕፍት የትኞቹ መሆናቸው ነው። በመንፈስ ለመጻፋቸው በቂ ማስረጃ ሊቀርብላቸው የሚችሉት መጻሕፍት በአሁኑ ጊዜ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ሆነው የተመደቡት ብቻ ናቸው። ሌሎች ጽሑፎችን ለመጨመር የተደረገው ጥረት በሙሉ ከረዥም ዘመናት በፊት ጀምሮ ብርቱ ተቃውሞ ሲያጋጥመው ቆይቷል።
4 መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በመስመር ላይ መደዳውን በሰፈሩ ፊደላት ነበር። በዐረፍተ ነገሮችና በሥርዓተ ነጥቦች ለመከፋፈል ሙከራ የተደረገው ከዘጠነኛው መቶ ዘመን እዘአ ጀምሮ ነው። የኅትመት ሥራ በመፈልሰፉ ምክንያት በዘመናችን የሚገኘው ሥርዓተ ነጥብ ዋነኛ ገጽታዎች የተደራጁት በአሥራ አምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፎችና በቁጥሮች የተከፋፈለው (የኪንግ ጄምስ ትርጉም 1,189 ምዕራፎችና 31,102 ቁጥሮች አሉት) በመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች አልነበረም። መከፋፈል የጀመሩት ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ነበር። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በቁጥሮች የከፋፈሉት ማሶሬትስ የሚባሉት የአይሁድ ምሁራን ናቸው። ከዚያም በኋላ በአሥራ ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ በምዕራፎች ተከፋፈለ።
5, 6. መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሣሽነት ተጻፈ ሲባል ምን ማለት ነው? በመጻሕፍቱ መካከል የአጻጻፍ ልዩነት የኖረው በምን ምክንያት ነው?
5 በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉት መጻሕፍት ስብስብ። የታላቁን ደራሲ የይሖዋ አምላክን በመንፈስ የተነገረ ቃል ለመመዝገብ አርባ የሚያክሉ ግለሰቦች በጸሐፊነት አገልግለዋል። “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ነው።” ይህም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችንና ‘ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍትን’ ያጠቃልላል። (2 ጢሞ. 3:16 አዓት፤ 2 ጴጥ. 3:15, 16) “በመንፈስ አነሣሽነት ተጻፉ” ሲባል ጸሐፊዎቹ ስለ ዓለማዊ የሥነ ጥበብ ሰዎችና ገጣሚዎች እንደሚነገረው ስሜታቸውና የአእምሮአቸው ችሎታ ከፍተኛ ውጤት ሊያስገኝ ወደሚችልበት ደረጃ ተቀስቅሶ ነበር ማለት አይደለም። አምላክ ራሱ እንደጻፋቸው የሚቆጠሩ ስህተት የሌለባቸው ትክክለኛ ጽሑፎች እንዲገኙ አደረገ ማለታችን ነው። አምላክ የገዛ ራሱን መንፈስ እርሱ እየመራቸው ቃሉን በጻፉት ታማኝ ሰዎች ላይ እንዲሠራ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ለማለት ችሏል:- “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2 ጴጥ. 1:21) ይሁን እንጂ ቢያንስ በአንድ ወቅት አምላክ ራሱ የጻፈውን ቃል ለሰዎች አስተላልፏል። ይህም ቃል አሥርቱ ትዕዛዛት ሲሆን አምላክ “በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች” ለሙሴ ሰጥቷል። — ዘጸ. 31:18
6 በአንዳንድ ጊዜያት የሚጻፉትን ሐሳቦች ያስተላለፈው ቃል በቃል በመናገር ነበር። (ዘጸ. 34:27) በተጨማሪም ነቢያቱ የተወሰነ መልእክት እንዲያደርሱ ይታዘዙ ነበር። (1 ነገ. 22:14፤ ኤር 1:7) ይሁን እንጂ አምላክ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲጽፉ የተጠቀመባቸው ሰዎች በቃል የተነገራቸውን ቃል ብቻ እንዳልጻፉ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ዮሐንስ ራእዩን ከአምላክ መልአክ ከተቀበለ በኋላ ‘የሚያየውን በመጽሐፍ’ እንዲጽፍ ታዝዞ ነበር። (ራእይ 1:1, 2, 10, 11) ስለዚህ አምላክ የሚጻፉት ጽሑፎች ትክክልና ከዓላማው ጋር የሚስማሙ እንዲሆኑ የሚያስፈልገውን ቁጥጥር ቢያደርግም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያዩትን ራእይ ራሳቸው በመረጧቸው ቃላትና አነጋገሮች እንዲገልጹ ቢፈቀድላቸው ጥሩ እንደሚሆን ተመልክቶ ነበር። (መክ. 12:10) የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የአጻጻፍ ልዩነት የሚታይባቸው በዚህ ምክንያት እንደሆነ አያጠራጥርም።
7. አንዳንዶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች እነማን ነበሩ? ሁሉም የትኞቹን የእውነተኛ ነቢያት ብቃቶች አሟልተዋል?
7 የሙሴ መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ ስለመሆናቸው ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖር አይችልም። ከጽሑፎቹ ከራሳቸው በቂ መረጃ ለማግኘት ይቻላል። ሙሴ በራሱ አሳብ ተነሳስቶ የእስራኤላውያን መሪ አልሆነም። በመጀመሪያ ላይ ሙሴ ከሚሰጠው ኃላፊነት ለመሸሽ ፈልጎ ነበር። (ዘጸ. 3:10, 11፤ 4:10–14) ሙሴን ያስነሳው አምላክ ሲሆን ተአምራት የማድረግ ኃይልም ሰጥቶታል። አስማተኛ ካህናት እንኳን ሙሴ የሚያደርጋቸው ነገሮች በአምላክ ኃይል የሚደረጉ መሆናቸውን ለመቀበል ተገድደው ነበር። (ዘጸ. 4:1–9፤ 8:16–19) ሙሴ የአምላክን ትዕዛዝ በመቀበልና ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘው መለኮታዊ ሥልጣን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን ቃላት በመጀመሪያ ለመናገር በኋላም ለመጻፍ ተነሳስቷል። (ዘጸ. 17:14) ሙሴ ከሞተ በኋላ የኢያሱ፣ የሳሙኤል፣ የጋድና የናታን ጽሑፎች (ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ አንደኛና ሁለተኛ ሳሙኤል) ተጨምረዋል። ንጉሥ ዳዊትና ንጉሥ ሰሎሞንም እያደገ ለመጣው የቅዱሳን ጽሑፎች ክምችት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከዚያም ከዮናስ እስከ ሚልክያስ ተነስተው የነበሩት ነቢያት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል። እነዚህ ነቢያት በሙሉ ይሖዋ ለእውነተኛ ነቢያት ያወጣቸውን ብቃቶች አሟልተዋል። በይሖዋ ስም ተናግረዋል፣ ትንቢታቸው በትክክል ተፈጽሟል፤ ሰዎችንም ወደ አምላክ መልሰዋል። — ዘዳ. 13:1–3፤ 18:20–22
8. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርገው እንደሚመደቡ የሚያረጋግጠው ዋነኛ ማስረጃ ምንድን ነው?
8 የቅዱሳን ጽሑፎችን አጻጻፍ በመንፈሱ የመራው አምላክ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ጽሑፎች በራሱ አመራር አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ አድርጓል ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። በዚህ ረገድ በአይሁዳውያን አፈታሪክ መሠረት እስራኤላውያን ከግዞት ተመልሰው በምድራቸው ላይ መኖር በጀመሩበት ጊዜ ከፍተኛ ሥራ ያከናወነው ዕዝራ ነው። ዕዝራ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመንፈስ ተነሳስተው ከጻፉት ሰዎች አንዱ ስለነበረ፣ በተጨማሪም ካህንና ‘ጥሩ ችሎታ ያለው የሙሴ ሕግ ጸሐፊ’ ስለነበረ ለዚህ ሥራ ጥሩ ብቃት ነበረው። (ዕዝራ 7:1–11) በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚመደቡት መጻሕፍት ተጠናቀው ነበር። ይህም አመዳደብ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙትን ሠላሳ ዘጠኝ ጽሑፎች ብቻ የያዘ ነበር። እነዚህን ጽሑፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አድርጎ የመደባቸው አንድ ዓይነት የሰዎች ጉባኤ አልነበረም። ከመጀመሪያ ጀምሮ መለኮታዊ ድጋፍ ነበራቸው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ሆነው ስለሚመደቡት መጻሕፍት ከሁሉ የበለጠውን ምሥክርነት የሚሰጠን ሊታበል የማይችለው የኢየሱስ ክርስቶስና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ቃል ነው። በመንፈስ በተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ ጊዜ ተጠቅመዋል፤ ከአዋልድ መጻሕፍት ግን አንድ ጊዜም አልጠቀሱም። — ሉቃስ 24:44, 45
9, 10. የክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ክፍል ተደርገው የሚመደቡ ለመሆናቸው ማረጋገጫ የሚሆነው ምንድን ነው?
9 ሃያ ሰባቱ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አጻጻፍና አሰባሰብም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተለየ አይደለም። ክርስቶስ ወንዶችን ስጦታ አድርጎ ሰጥቷል። አዎን፣ “አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ።” (ኤፌ. 4:8, 11–13) እነዚህ ሰዎች የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አድሮባቸው ስለነበረ ለክርስቲያን ጉባኤ የሚያገለግል ጠንካራ መሠረተ ትምህርት መሥርተዋል። የአምላክ መንፈስ ሐዋርያትን እያስተማረ፣ እየመራቸውና ከእርሱ የሰሟቸውን ነገሮች እያስታወሳቸውና ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን እየገለጸላቸው እንደሚረዳቸው ኢየሱስ ቃል ገብቶ ነበር። (ዮሐ. 14:26፤ 16:13) ይህም እነዚህ ሰዎች የጻፏቸው የወንጌል ታሪኮች ትክክለኛና እውነት እንዲሆኑ አስችሏል።
10 አንድ ጽሑፍ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርጎ የሚቆጠር መሆኑ የሚረጋገጠው በየትኛው ሐዋርያ ያልሆነ ጸሐፊ ወይም ስንት ጊዜ ተጠቀሰ በማለት አይደለም። የጽሑፉ ይዘት ራሱ ከመንፈስ ቅዱስ የተገኘ ለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት አለበት። ስለሆነም አጉል እምነቶችን፣ አጋንንታዊ ሥራዎችን ወይም የፍጡራንን አምልኮ የሚያደፋፍር ሊሆን አይችልም። ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማት ይኖርበታል። እያንዳንዱ መጽሐፍ ከመለኮታዊው ‘የጤናማ ቃል ምሳሌ’ እና ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር የሚስማማ መሆን ይገባዋል። (2 ጢሞ. 1:13) ሐዋርያት በመለኮታዊ ሥልጣን ይናገሩ እንደነበረ ግልጽ ነው። በመንፈስ የሚነገሩ ቃላት ሁሉ ከአምላክ የመጡ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ለመለየት የሚያስችል ‘ማስተዋል ከመንፈስ ቅዱስ’ ተቀብለው ነበር። (1 ቆሮ. 12:4, 10) የመጨረሻው ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ግን ይህ በመለኮታዊ አነሣሽነት የሚጽፉ ሰዎች ሰንሰለት ተቋረጠ። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው የሚመደቡት መጻሕፍት ስብስብ በራእይ፣ በዮሐንስ ወንጌልና በመልእክቶቹ ተደመደመ። እነዚህ ስልሳ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወጥ መጽሐፍና በመንፈስ የተጻፈ የይሖዋ የእውነት ቃል መሆኑን ያረጋግጣል።
11. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሌላ ከየትም ሊገኙ የማይችሉ እንዴት ያሉ መረጃዎች ይገኛሉ?
11 ይዘት። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ከሌላ ከየትም ሊያገኛቸው የማይችላቸውን መረጃዎች ይዟል። ለምሳሌ ያህል የዘፍጥረት ዘገባ ስለ ምድር አፈጣጠር ይገልጻል። የሰው ልጅ በምድር መድረክ ላይ መታየት ከመጀመሩ በፊት ስለተፈጸሙ ነገሮች ያሳውቀናል። (ዘፍ. 1:1–31) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ራሱ ካልገለጸ በስተቀር የማንም ሰብዓዊ ፍጡር ጆሮ ሊሰማቸው የማይችሉትን በሰማይ የተደረጉ ውይይቶች ይገልጽልናል። — ኢዮብ 1:6–12፤ 1 ነገ. 22:19–23
12, 13. ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንማራለን?
12 ከሁሉም በላይ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ጋር ያስተዋውቀናል። ሞገሱን የሰጣቸው አገልጋዮቹ የተመለከቷቸውን ተአምራዊ ራእዮች ይተርክልናል። (ዳን. 7:9, 10) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የማሶሬቲክ ግልባጭ ውስጥ ከ6,800 ጊዜ በላይ ከተጠቀሰው “ይሖዋ” ከተባለው የአምላክ ስም ጋር ያስተዋውቀናል። እንደ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕ፣ ምህረት፣ ትዕግሥት፣ ልግስና፣ የእውቀት ፍጽምና፣ የአቋም አለመለዋወጥና ስለመሳሰሉት የይሖዋ ዋነኛ ባሕርያት የምንማረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ዘጸ. 34:6, 7) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ልጅና እርሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስላለው ትልቅ ቦታ ይነግረናል። (ቆላ. 1:17, 18፤ 2:3፤ 2 ቆሮ. 1:20) የአምላክ ልጅ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር ያለንን ትውውቅ ከማንም የበለጠ አስፍቶልናል። ምክንያቱም “እኔን ያየ አብን አየ” ለማለት ችሎ ነበር። — ዮሐ. 14:9
13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አምላክ ዓላማ ሂደት የሚገልጹ ዝርዝር መረጃዎች ተሰጥተዋል። ለታዛዥ ሰዎች እንደሚፈጸሙ የተነገረላቸው በረከቶች በሙሉ ይሖዋ በሚያስነሳው አዳኝ ላይ የተመኩ ናቸው። ይህ አዳኝ የአምላክ ሴት “ዘር” እንደሚሆን አምላክ በኤደን የአትክልት ሥፍራ በተናገረው ቃል ገልጿል። (ዘፍ. 3:15) ከጊዜ በኋላ ይህ ዘር በአብርሃም በኩል እንደሚመጣ አምላክ ቃል ገባ። (ዘፍ. 22:18) ተስፋ የተደረገው አዳኝ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት” የዘላለም ንጉሥና ካህን እንደሚሆን አመለከተ። (መዝ. 110:4፤ ዕብ. 7:1–28) በክህነትና በመሥዋዕቶች ሥርዓት ላይ የተመሠረተውን የሕግ ቃል ኪዳን ለእስራኤላውያን ሰጠ። እነዚህ ሁሉ ‘ለሚመጡት በጎ ነገሮች ጥላ ነበሩ።’ (ዕብ. 10:1፤ ቆላ. 2:17) ለዳዊትም ንግሥና ለዘላለም ከቤቱ እንደማይወጣ ቃል ተገባለት። (2 ሳሙ. 7:11–16) የዚህ ተስፋ ወራሽና ሌሎቹ ትንቢቶች በሙሉ የመሠከሩለት አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ተገልጿል። አዎን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ ልዩ ትኩረት የተደረገው በመንፈስ የተጻፉት ጽሑፎች ዋነኛ መልእክት በሆነው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ይሖዋ ዓላማውን የሚያስፈጽመው በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የበላይነት በሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ነው።
14–17. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥነ ምግባር የሚሰጣቸው ምክሮች ለሁላችንም በጣም የሚጠቅሙን ለምንድን ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጽሐፍ በመሆኑም ረገድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። በታሪክ ውስጥ ለተፈጸሙ ነገሮች ልዩ ትርጉም ከመስጠቱም በላይ የተፈጸሙበትንም ምክንያት ያሳያል። (ሉቃስ 19:41–44) የአሁኖቹ ዓለማዊ መንግሥታት የወደፊት ዕጣ ምን እንደሚሆን ይገልጻል። (ዳን. 2:44) በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖርና አምላክ በቅርቡ ክፉዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋ በማመልከት በዘመናችን ስለሚፈጸሙት ሁኔታዎች መግለጫ ይሰጣል። — 2 ጢሞ. 3:1–5፤ መዝ. 37:9, 10
15 መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ አንችልም ነበር። (መክ. 12:13) የሰው ልጅ ጭፍን የሆነ ዕድል ወይም የአጋጣሚ ውጤት ሳይሆን ለሰው ልጆች ፍቅራዊ ዓላማ ያለው አምላክ ፍጡር መሆኑን በግልጽ ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ አምላክ ለእኛ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነና ከሕይወታችን እውነተኛ እርካታ እንዴት ማግኘት እንደምንችል ይገልጻል። — ራእይ 4:11፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4፤ መዝ. 16:11
16 የሰው ልጅ ከአምላክ ርቆ አካሄዱን በራሱ ሊያስተካክል እንደማይችል በታሪክ ተረጋግጧል። ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው መመሪያ የሚገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚያወግዛቸውንና የሚወዳቸውን ባሕርያት በመግለጽ የሥነ ምግባር መመሪያ ይሰጣል። (ገላ. 5:19–23) የሥነ ምግባር ገደቦችን ባፈራረሰው በዛሬው ዓለም ውስጥ በጣም ሊሠራ የሚችል መመሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። የአምላክን አመለካከት እንድናውቅና እርሱንም ለማስደሰት እንድንችል ይረዳናል። በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትንም መንገድ ያሳየናል። — ዮሐ. 17:3
17 ታዲያ ይህ የመጽሐፎች ሁሉ የበላይ የሆነው መጽሐፍ ዋነኛው መማሪያ መጽሐፋችን የሆነበት ምክንያት ግልጽ አይደለምን? ክርስቲያኖች የአምላክ ልጅ “ቃልህ እውነት ነው” ባለለት አምላክ የተደረሰውን ይህን መጽሐፍ ለመመርመር ከማንኛውም ነገር የበለጠ ትኩረት ይሰጣሉ። (ዮሐ. 17:17) ስለዚህ በቲኦክራሲያዊው የአገልግሎት ትምህርት ቤት የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።