ጥናት 11
በየቀኑ ጥሩ ዓይነት አነጋገር መጠቀም
1. አነጋገራችን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?
1 “አቤቱ፣ . . . የአፌ ቃል . . . በፊትህ ያማረ ይሁን።” (መዝ. 19:14) የእኛም ቃል በይሖዋ ፊት ያማረ እንዲሆን ከፈለግን ተገቢ ስለሆኑ ነገሮችና ለአምላክ አገልጋይ በሚገባ አነጋገር መጠቀም ይኖርብናል። ንግግራችን በመንግሥት አዳራሽ በምንገኝበት ወይም በመስክ አገልግሎት በምንሰማራበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቀናት የታመንን የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን የሚያረጋግጥ እንዲሆን እንፈልጋለን። እንዲህ ካደረግን በየቤታችን፣ በሥራ ቦታችንና በትምህርት ቤታችን የምን ጠቀምበት አነጋገር በአገልግሎታችን ላይ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል። — 2 ቆሮ. 6:3
2, 3. አነጋገራችንና የቃላት አመራረጣችን ትልቅ ቦታ የሚኖራቸው ለምንድን ነው?
2 አነጋገራችን በጣም አስፈላጊ የሆነ ቦታ አለው። ይህም የድምፃችንን ቃናና በፊታችን ላይ የሚነበበውን ስሜት ይጨምራል። የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ያለን ደስታ በፊታችን ላይ መታየት ይኖርበታል። የወዳጅነት አቀራረብና ሞቅ ያለ ፈገግታ ሰዎችን ይማርካል። የምንናገራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ክብደት ያላቸው ቢሆኑም ልብንም ደስ ያሰኛሉ። ስለዚህ የጋለ መንፈስ ይኑርህ። “በድን” ወይም ቀዝቃዛ የሆነ አነጋገር ከምናቀርበው የተስፋ መልእክት ጋር አይስማማም።
3 ጥሩ አነጋገር እየለመድክ በምትሄድበት ጊዜ ቃላትና ሐረጎች ልክ እንደ ሰው የራሳቸው የሆነ “ባሕርይ” እንዳላቸው ትገነዘባለህ። መራራ ወይም ጣፋጭ፣ ለስላሳ ወይም ሻካራ፣ የሚያንጹ ወይም ቅስም የሚሰብሩ፣ ወዳጅነትን ወይም ጠላትነትን የሚገልጹ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ትክክለኛውን ቃል ወይም ሐረግ መምረጥ የግድ አስፈላጊ ነው። በተለይ የምንናገረው የእውነትን ቃል ወይም የመንግሥቱን ምሥራች በሚሆንበት ጊዜ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
4. የቃላት እውቀታችንን ልናሰፋ የምንችለው እንዴት ነው?
4 የቃላት እውቀትህን ማስፋት። ማንኛውንም መዝገበ ቃላት በመመልከት ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋን ለማወደስ በምንጠቀምባቸው ቃላት ረገድ እጥረት የለም። ይሁን እንጂ ጥያቄው ባሉት ቃላት በሚገባ የምትጠቀመው ምን ያህል ነው? የሚለው ነው። በምታነብበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ የማትረዳው ቃል ሲያጋጥምህ የቃሉን ትርጉም ወዲያው ወይም ርዕሰ ትምህርቱን አንብበህ ከጨረስክ በኋላ ከመዝገበ ቃላት አውጥተህ ትመለከታለህን? ይህን በማድረግ ያለህን የቃላት እውቀት እንድታሳድግ ይረዳሃል። በተጨማሪም ስትሰማቸው ወይም ስታያቸው የምታውቃቸው ነገር ግን በዕለታዊ ንግግርህ የማትጠቀምባቸው ብዙ ቃላት እንዳሉ ትገነዘባለህ። እነዚህን ቃላት ተስማሚ የሆነ አጋጣሚ በምታገኝበት ጊዜያት ሁሉ ለመጠቀም ልዩ ጥረት አድርግ። ጥሩ የንግግር ችሎታ ዘወትር መኮትኮት በክርስቲያን አገልጋይነትህና አስተማሪነትህ በጣም ይጠቅምሃል።
5, 6. ቃላትን በትክክል ለመጠቀም የሚረዳን ምንድን ነው?
5 በትክክለኛው ቃል መጠቀምን ተማር። ሁለት ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም ቢኖራቸውም አነስተኛ የትርጉም ልዩነት ይኖራቸውና ቃሎቹን የምትጠቀምበት ለተለያዩ ሁኔታዎች ሊሆን ይችላል። ይህንን ካስተዋልህ አድማጮችህን ቅር ከማሰኘት ትድናለህ። ንግግርህም በይበልጥ ግልጽነት ያለው ይሆናል። ቃሉን በጥሩ መዝገበ ቃላት ማየት ይጠቅማል። አንዳንድ መዝገበ ቃላት የእያንዳንዱን ቃል ተመሳሳይና ተቃራኒ ቃል ይዘረዝራሉ። እንደነዚህ ካሉት መዝገበ ቃላት አንድን ሐሳብ ሊገልጹ የሚችሉ የተለያዩ ቃላትን ብቻ ሳይሆን አንድ ቃል ያሉትን የተለያዩ ተዛማጅ ትርጉሞች ለማወቅ ትችላለህ። ይህም ለአንድ ሁኔታ የሚያገለግለውን ትክክለኛ ቃል በምትመርጥበት ጊዜ በጣም ይጠቅምሃል። በተጨማሪም በትክክለኛው ቃል መጠቀም ብዙ ቃላት ከመደርደር ያድንሃል፤ ወደ ነጥቡም እንድትደርስ ይረዳሃል። ቃላት ሲበዙ ዋና ሐሳቦች ይድበሰበሳሉ። ስለዚህ ሐሳብህን በጥቂት ቃላት መግለጽን ተለማመድ። በጥቂት ቃላት ሐሳብህን በሚገባ መግለጽ ስትችል ድምቀትና ትርጉም በሚጨምሩ ገላጭ ቃላት በመጠቀም አነጋገርህን ለወጥ ማድረግ ጀምር።
6 የቃላት እውቀትህን በምታሰፋበት ጊዜ የቃላቱን አዲስነት ብቻ ሳይሆን የቃላቱን የተለየ ባሕርይ አስብ። ብርታትን የሚገልጹ ግሦች፣ ድምቀትን የሚገልጹ ቅጽሎች ወይም ገላጭ ቃሎች፣ ንግግር አሰልቺ እንዳይሆን የሚረዱ የመሸጋገሪያ ሐረጎች፣ ሞቅ ያለ የፍቅር መንፈስን የሚገልጹ የደግነት ቃላት አሉ። የማኅበሩን ጽሑፎች በምታነብበት ጊዜ ልትመርጣቸው የምትችል ብዙ የተለያዩ ቃላትና ሐረጎች ታገኛለህ።
7, 8. የቃላት እውቀታችን ሠፊ በሚሆንበት ጊዜ እንዴት ስላለው አደጋ መጠንቀቅ ይኖርብናል?
7 እርግጥ የቃላት እውቀትህን የምታሰፋው አዋቂነትህ እንዲታይልህ ለማድረግ አይደለም። ዓላማችን ዕውቀት ለማስተላለፍ እንጂ የአድማጮቻችንን አድናቆት ለማትረፍ አይደለም። አመለካከታችን ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸውን የመሰለ መሆን ይኖርበታል። “ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን [በባዕድ ቋንቋ] ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።” (1 ቆሮ. 14:9, 19) የአንድ ሰው ንግግር ለመረዳት የሚያስቸግር ከሆነ ልክ በባዕድ ቋንቋ እንደተናገረ ያህል ይሆናል። በተጨማሪም ዝርዝር ነገሮችን ማወቅ የማያስፈልጋቸው አድማጮች ሲሆኑ ሳያስፈልግ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ብዙ አለማተኮር ጥበብ ይሆናል። በተራ ጭውውት እንኳ ውስብስብ በሆነ አነጋገርና ረዣዥም በሆኑ ቃላት የአድማጮችን አድናቆት ለማግኘት መሞከር ተገቢ አይደለም። አስፈላጊው ነገር አድማጮቻችን የምንናገረውን ለመረዳት መቻላቸው ነው። ምሳሌ 15:2 እንደሚለው “የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል።” ጥሩና በቀላሉ የሚገቡ ቃላትን መምረጥ ንግግራችን የማይጥምና አሰልቺ ሳይሆን የሚቀሰቅስና የሚያስደስት እንዲሆን ያስችላል። — ቆላ. 4:6
8 በተጨማሪም ቃላትን በትክክል ማንበብን ወይም መናገርን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ቃላትን በትክክል አንብብ። የቃላትን ትክክለኛ አነባበብ ወይም አባባል ለማወቅ መዝገበ ቃላትን መመልከት ወይም ሌሎች እንዴት እንደሚናገሩ መከታተል ይቻላል። ይህም በአነጋገር ጥራት ረገድ ግድየለሽ እንዳትሆን ይረዳሃል። በዕለታዊ ንግግራችን ማስወገድ የሚገባን ሌላው ነገር አንዳንድ ቃላትን ወይም በቃላት መጨረሻ ላይ የሚገኙ ፊደላትን መዝለል ወይም መዋጥ ነው። ጥርስህን ገጥመህ አትናገር። ቃላትን በጥራት ተናገር። ግልጽ በሆነ መንገድ ለመናገር እንድትችል አፍህን ከፈት አድርገህ ተናገር።
9–12. ከምን ዓይነት አነጋገር መራቅ ይኖርብናል? ለምንስ?
9 ሊወገድ የሚገባው አነጋገር። በዕለታዊ ሕይወታችን ልናስወግዳቸው ስለሚገቡ አነጋገሮች የአምላክ ቃል መመሪያ ይሰጠናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያሳፍርና ረብ የሌለው ወይም ጸያፍ ነገር መናገር አይገባችሁም” ሲል ይመክረናል። (ኤፌ. 5:3, 4 የ1980 ትርጉም። ) አሳፋሪና የብልግና ንግግሮችን ማስወገድ ይኖርብናል። በተጨማሪም ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎአል:- “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።” (ኤፌ. 4:29) ስለዚህ ክርስቲያኖች የእርግማንና ሻካራ የሆኑ ቃላትን ማስወገድ ይገባቸዋል። አንዳንድ ሰዎች እንደነዚህ ባሉት ቃላት መጠቀማቸው ለንግግራቸው ኃይል የሚጨምር ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ኃይል ያላቸው ብዙ ሌሎች ቃላት አሉ። እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የእነርሱን ሻካራ አነጋገር የምንቀዳበት ምንም ምክንያት የለንም። ቀላል የሆኑ ቃላት ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ንጹሕና ትክክለኛ መሆን ይገባቸዋል።
10 በተጨማሪም ከትክክለኛ የሰዋስው ሕግጋት ጋር የሚቃረኑ የአነጋገር ፈሊጦችን ማስወገድ ያስፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ እንደነዚህ ባሉት አነጋገሮች የሚጠቀሙት በመዝናኛው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ዓለማዊ ሰዎች ናቸው። ወይም በዘመናዊ ዘፈኖች አማካኝነት የተስፋፉ ቃላት ናቸው። ሰዎች እነዚህን በመዝናኛው ዓለም የሚነገሩትን አባባሎች የመቅዳት ዝንባሌ አላቸው። ክርስቲያኖች ግን እንደነዚህ ያሉትን የአነጋገር ፈሊጦች መቅዳት የለባቸውም። ይህን ብናደርግ ከዓለምና ከዓለም መንገዶች ጋር አንድ እንደሆንን ተደርገን እንቆጠራለን። የዕጽ አስተላላፊዎችና ወንጀለኞች ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗር ያላቸው ሰዎች የራሳቸው የሆኑ ቃላት አሏቸው። ተራው አድማጭ ሊረዳቸው በሚያዳግቱ ቃላት ይጠቀማሉ። የእኛ አነጋገር ግን እንደነዚህ ባሉት ዓለማዊ ተጽእኖዎች መነካት አይኖርበትም። — ሮሜ 12:2
11 ክርስቲያኖች አክብሮት የጎደላቸውን ቃላት ለማስወገድ ጠንቃቆች መሆን ይገባቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ንግግራቸውን ጠበቅ የማድረግ ወይም የእርግማን ቃላት ምትክ እንዲሆኑ ብቻ ሲሉ “እግዚአብሔርን” “በስመ አብ” “ጂሰስ” በሚሉት ቃላት ይጠቀማሉ። በእንግሊዝኛው “ጎድ” እና “ጂሰስ” ከሚሉት ቃላት የተወሰዱ እንደ “ጎሽ”፣ “ጎሊይ” እና “ጊይ” የመሳሰሉ ሌሎች የፈሊጥ ቃላትም አሉ። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን እነዚህን የማዳነቂያ ቃላት እንደ ቃለ አጋኖ አድርጎ ሊጠቀምባቸው አይገባም። — ዘጸ. 20:7፤ ማቴ. 5:34–37
12 ሰዎች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ነገር አንዳንድ ጊዜ ቅር ሊያሰኘን ይችላል። ቢሆንም አንድ ክርስቲያን በቁጣ ወይም በስድብ ቃላት መመለስ አይገባውም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እናንተ ደግሞ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ” ብሎአል። (ቆላ. 3:8) ስለዚህ የሌሎች ሰዎች አነጋገር ቢያናድድህም መንፈስህን መቆጣጠር ጥበብ ይሆናል። — ምሳሌ 14:29፤ ያዕ. 3:11
13–16. የሰዋስው ችሎታችንንና የአነጋገር ልማዳችንን ለማሻሻል የሚረዳን ምንድን ነው?
13 ትክክለኛ የሆነ የሰዋስው አገባብ። አንዳንድ ሰዎች የንግግራቸው ሰዋስው በጣም ጥሩ እንዳልሆነ ሊገነዘቡ ይችላሉ። ምናልባት ያደጉት በሌላ አገር ይሆናል፣ ወይም ወጣት በነበሩበት ጊዜ በቂ ትምህርት አላገኙ ይሆናል። በዚህ ችግራቸው ተስፋ መቁረጥ አይኖርባቸውም። ለምሥራቹ ሲሉ ራሳቸውን ለማሻሻል ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሊወስዱ የሚችሉአቸው ጠቃሚ እርምጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል የቤተሰብ ንባብ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን እርማት ለማድረግ ይረዳል። ስለ ሰዋስው ያለን አብዛኛው ዕውቀት ሌሎች ሲናገሩ ከመስማት ያገኘነው ነው። ስለዚህ የጎለመሱና ጥሩ ትምህርት ያላቸው ወንድሞች የሚናገሩትን በጥንቃቄ አዳምጥ። መጽሐፍ ቅዱስንና የማኅበሩን ጽሑፎች በምታነብበት ጊዜ የዐረፍተ ነገሩን አቀነባበርና በተለያዩ ሁኔታዎች የተሠራባቸውን የቃላት ዓይነቶች በትኩረት ተከታተል። የራስህን አነጋገር ከእነዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ጋር ለማመሳሰል ሞክር።
14 ወጣት የሆኑ ሁሉ በትምህርት ቤት እያሉ ጥሩ ሰዋስውና አነጋገር ለመማር በሚያስችላቸው አጋጣሚ ሁሉ በሚገባ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ስለ አንድ ዓይነት የሰዋስው ሕግ እርግጠኛ ካልሆንህ አስተማሪህ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጥህ ጠይቅ። ውጤታማና ጥሩ የምሥራቹ አገልጋይ ለመሆን ስለምትፈልግ ትጉህ የምትሆንበት በቂ ምክንያት አለህ።
15 በየቀኑ በጥሩ አነጋገር ለመጠቀም ጥረት አድርግ። ስለ ዕለታዊ ንግግሩ ግድ የለሽ የሆነና መጥፎ የአነጋገር ልማድ ያለው ሰው ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች በጥሩ ሁኔታ ለመናገር አይችልም። በጥሩ ሁኔታ ለመናገር ልምምድ ያስፈልጋል። ዕለታዊ በሆኑ የሕይወት ጉዳዮች በጥሩ አነጋገር የምትጠቀም ከሆንክ ግን መድረክ ላይ ሆነህ ስትናገር ወይም ለሌላ ሰው ስለ አምላክ እውነት ስትመሰክር በጥሩ አነጋገር ለመጠቀም ቀላል ይሆንልሃል።
16 በየዕለቱ ጥሩ አነጋገር መለማመድ ልባችንና አእምሮአችን ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ለሚያስፈጽማቸው ታላላቅ ዓላማዎች ያለንን አድናቆት ለመግለጽ በሚያስችሉን ግሩም ቃላት እንዲሞላ ይረዳናል። ይህን ስናደርግ በሉቃስ 6:45 ላይ የሚገኘው የኢየሱስ ቃል እውነት መሆኑን ለመመልከት እንችላለን። “መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል።”