ምዕራፍ 8
የምትፈልገው ምን ዓይነት ጓደኞችን ነው?
1–5. (ሀ) ከሌሎች ጋር መወዳጀት የሕይወትህን ደስታ የሚጨምረው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ጓደኛን የምትገልጸው እንዴት ነው? (ምሳሌ 18:24)
እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት ለሕይወት ብዙ ደስታ ይጨምራል። “ብቸኞችና” ከሌሎች የሚገለሉ ሆነው ደስተኞች የሆኑ ሰዎች እምብዛም የሉም። ጓደኝነት ይህን ያህል ለደስታህ ተጨማሪ ምክንያት የሚሆነው ምን ቢኖረው ነው?
2 ከጓደኛ ጋር ሆኖ አንድን ሥራ መሥራት ከዚህ ልዩ ተሞክሮ የሚገኘውን ደስታ የሚጨምረው ይመስላል። አንድ ጊዜ ኢየሱስ የጠፋውን በጉን ስላገኘው እረኛና የጠፋውን ድሪሟን ስላገኘች ሴት ተናግሮ ነበር። እያንዳንዳቸው ወዳጆቻቸውን ጠርተው “ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ” ብለዋል። (ሉቃስ 15:6, 9) አዎን፤ በተፈጥሮህ ጥሩ ነገሮችን ከጓደኞችህ ጋር ለመካፈል ትፈልጋለህ፤ በዚህም የተነሳ ደስታህ እጥፍ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ አያውቅምን?
3 በሌላ በኩል ደግሞ ነገሮች አልሳካ ብለውህ በምታዝንበት ጊዜ ጥሩ ጓደኛ ከኀዘንህ እንድትገላገል በማድረግ ብዙ ሊረዳህ ይችላል። የሚያሰጋ ሁኔታ ሲያጋጥም ጓደኞች እውነተኛ ረዳቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ከአደጋ ሊያስጠነቅቁህና እንድታመልጥም ሊረዱህ ይችላሉ። ወደፊት መራመዱ አዳጋች ሲሆንብህ አይዞህ እያሉ ሊያደፋፍሩህ ይችላሉ። “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” በማለት ከሚናገረው ከምሳሌ 17:17 ጋር ትስማማ ይሆናል።
4 ይህ ጥቅስ እውነተኛ ወዳጆች ተለይተው የሚታወቁበትን ትልቅ ምልክት ያጎላል:- እሱም ታማኝነት ነው። ጓደኛ ወይም ወዳጅ መሆን ማለት የወዳጅነት መልክ ከማሳየት የበለጠ ነገር ነው። እውነተኛ ጓደኛ ለአንተና ለጥቅምህ በታማኝነት ይቆማል። ጓደኞችህ እንዲህ ዓይነት ናቸውን?
5 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጎረቤታቸውን ከመርዳት ይልቅ ከእርሱ በልጠው ለመገኘት የሚፈልጉ ይመስላል። “ጓደኞች” በሚባባሉ ሰዎች ዘንድም እንኳን ብዙውን ጊዜ የሚታየው የታማኝነት ሳይሆን የውድድር መንፈስ ነው። ብዙ ወዳጅነቶች የሚቆዩት አንደኛው ወገን አንድ ዓይነት ለውጥ እንዲያደርግ ወይም ሌላውን ወገን ለመጥቀም ሲል የራስ ወዳድነት ጥቅሙን እንዲተው የሚያስገድድ ሁኔታ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ነው። በዚህ የውድድር ዓለም ውስጥ እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት ቀላል አይደለም።
6–8. ዮናታንና ኩሲ የዳዊት ወዳጆች መሆናቸውን ያረጋገጡት በምን መንገዶች ነው?
6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእርግጥ ጥሩ የሆነ ጓደኛ በማግኘት በኩል ምሳሌ የሚሆነን ዳዊት ነው። ዳዊት በጣም ግዙፉን ጦረኛ ጠላት ጎልያድን ድል ካደረገ በኋላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ወዳጅነት እንዳገኘ ሳትሰማ አትቀርም። ዮናታን ቀናተኛ ቢሆን ኖሮ ዳዊት በእሥራኤል ላይ የንግሥናን ሥልጣን ሊቀናቀነው እንደሚችል በማሰብ ሊጠላው ይችል ነበር። በዚህ ፈንታ ዮናታን የአምላክ ሞገስ በዳዊት ላይ መሆኑን በመገንዘብ “የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፣ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው።” (1 ሳሙኤል 18:1) ዮናታን ዳዊትን የወደደው በጀግንነቱና በይሖዋ ላይ በነበረው እምነቱ ምክንያት ነበር። ዮናታን ራሱም እንደ ዳዊት ያለ ለአምላክ ያደረ ሰው ኖሮ መሆን ይኖርበታል። ለጋራ ወዳጅነት ከዚህ የተሻለ መሠረት ሊኖር አይችልም።
7 በተጨማሪም ከዚህ በኋላ በዳዊት የንግሥና ዘመን ከቅርብ አማካሪዎቹ አንዱ ስለነበረው የዳዊት ወዳጅ ስለ ኩሲ ለማንበብ ትችላለህ። ኩሲ በሕይወቱ ቆርጦ የአቤሴሎምን የክዳት ሴራ ለማክሸፍ እንደሞከረ የሚገልጸውን ታሪክ ማንበብ ስሜትን ይቀሰቅሳል።—2 ሳሙኤል 15:10–37፤ 16:16 እስከ 17:16 ተመልከት።
8 ምናልባት እንዲህ ዓይነት ወዳጆች ይኖሩህ ይሆናል። ከሌሉህ ግን እንዲህ ዓይነት ጓደኞችን ልታተርፍ የምትችለው እንዴት ነው? ከልብ ጥረት ማድረግን ቢጠይቅም ከውጤቱ አንፃር ጥረቱ በእርግጥ መደረግ የሚገባው ነው።
ጥሩ ጓደኞችን መፈለግ
9–13. (ሀ) አንድ ሰው ጥሩ ጓደኞችን ለማፍራት የሚችለው እንዴት ነው? ቁሳዊ ንብረቶችን በመስጠት ወይም በማካፈል ወዳጆች ለማግኘት መጣር ጥበብ የጎደለው የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በመዝሙር 101:5–7 ላይ እንደተገለጸው የምን ዓይነት ሰዎችን የቅርብ ወዳጅነት ማራቅ የተሻለ ነው?
9 ‘ጓደኛ ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ጓደኛ መሆን ነው’ የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር በጣም እውነትነት አለው። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች እነርሱ የሚያደንቋቸው ሌሎች ወጣቶች ሲያገልሏቸው በጥልቅ ይሰማቸዋል። ወይም ደግሞ ጓደኞች ያበጁና በኋላ ጓደኝነቱ ይቋረጣል። በዚህ ይበሳጫሉ። ምናልባት ጓደኝነት በሁለት በኩል የሚያስኬድ መንገድ መሆኑንአይገነዘቡት ይሆናል።
10 ስለዚህ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን ብንጠይቅ መልካም ነው:- ለሌሎች ጓደኛ ለመሆን ምን እያደረግሁ ነው? ለሌሎች ምን ያህል ልባዊና ከራስ ወዳድነት የራቀ ስሜት አለኝ? ለደስታቸውና ለእነርሱ ጥቅም አስተዋጽኦ ለማድረግ ምን እያደረግሁ ነው? ሌሎች እኔን ለጓደኝነት እንዲፈልጉኝ የሚያደርጉ ምን ጠባዮችን እያፈራሁ ነው?
11 የምታገኛቸው ወዳጆች ዓይነት በአብዛኛው የሚመካው እነሱን ለማግኘት በምትጥርበት መንገድ ላይ ነው። አንዳንዶች ጓደኞች ለማፍራት የሚሞክሩት ለእነርሱ ብዙ ገንዘብ በማጥፋት ወይም እንደ ስቴሪዮ ማጫወቻና የዘፈን ክሮች ወይም የስፖርት መሣሪያዎች በመሳሰሉት ቁሳዊ ንብረቶቻቸው የሚያገኙትን ደስታ እንዲካፈሉ በመጋበዝ ነው። እውነት ነው፣ ይህ አድራጎት አንዳንዶችን ይስብልህ ይሆናል። የምሳሌ መጽሐፍ “የባለጠጋ ወዳጆች ግን ብዙዎች” እንደሆኑና “ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ” መሆኑን ይናገራል። አዎን፣ አንድ ሰው ገንዘቡን እንደልብ በሚያወጣበት ጊዜ የጓደኝነት መልክ ያሳያሉ። ገንዘቡ ሲያልቅ ግን “ጓደኞቹም” በንነው ይጠፋሉ።—ምሳሌ 14:20፤ 19:6
12 ጥሩ ጓደኞች በቁሳዊ ንብረትም ሆነ በማቆላመጥ ወይም ያሉትን ሁሉ እሺ በማለት “ሊገዙ” የሚችሉ አይደሉም። ሊገዛ የሚችል ጓደኛ ሁሉ የቱንም ያህል ብዙ ዋጋ ቢወጣበት ጥሩ ጓደኛ አይደለም። እውነተኛ ጓደኞች የሚማረኩት በአንተነትህ፣ በባሕሪዮችህ ነው እንጂ ከአንተ ሊያገኙት በሚችሉት ነገር አይደለም።
13 ስለዚህ ለሰዎች የወዳጅነት መንፈስ ማሳየት ጥሩ ቢሆንም እውነተኛ ወዳጆች የምትፈልግ ከሆነ የቅርብና ምስጢር የምታካፍላቸው ጓደኞች አድርገህ በምትይዛቸው ሰዎች ረገድ መራጭ መሆን ያስፈልግሃል። ዳዊት መራጭ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “ትዕቢተኛንና ትምክህተኛን ሰው አልታገሥም። ለእግዚአብሔር ታማኞች የሆኑትን እወዳለሁ፤ በቤቴም እንዲኖሩ እፈቅድላቸዋለሁ። አንድም ሐሰተኛ [አታላይ አዓት] በቤቴ አይኖርም።” (መዝሙር 101:5–7 የ1980 ትርጉም) ወጣቶች በዛሬው ጊዜ የቅርብ ወዳጆች ስለሚያደርጓቸው ሰዎች መራጭ መሆን በጣም የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
ጥሩ ምርጫ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት
14–16. (ሀ) የአንድ ሰው ጓደኞች እርሱን የሚነኩት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ጓደኛህ ለሆነ ሰው እርሱ የሚያደርገውን እንደማትስማማበት ብትነግረው ጓደኝነታችሁ እንዴት ይነካል?
14 በዙሪያህ ካሉ ሰዎች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ አብረህ ከሆንክ እነርሱን ወደ መምሰል እንደምታዘነብል የተረጋገጠ የማህበራዊ ግንኙነት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። የጓደኛ ምርጫህ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ወይም ወደፊት ምን ዓይነት ሰው እንደሚወጣህ የሚናገረው ብዙ ነገር አለ። የቅርብ ጓደኞችህ አንተን “ይቀርጹሃል።”
15 ታማኝ፣ ጨዋ፣ ለሰው አሳቢ የሆኑና ለአምላክና ለቃሉ አክብሮት ያላቸው እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ድፍረት ያላቸውን ጓደኞች ትመርጣለህን? ወይስ ሌላውን “ሠራሁለት” ለማለት በመቻላቸው የሚኩራሩና እውነተኛ ድፍረት በማሳየት ፈንታ ለመታየት ሲሉ ወደ አደገኛ ሁኔታ ዓይናቸውን ጨፍነው የሚገቡ ሰዎች ይማርኩሃል? በውርርድ ለመርታት ወይም በሌሎች ላለመሰደብ ሲሉ በብልግና ለመካፈል ወይም ለመስረቅ፣ አደንዛዥ እፅ ለመውሰድና ምንም ሳይሆኑ እንዳመለጡ ጉራ ለመንዛት የተዘጋጁ ናቸውን? ወደሚጎዳህ ነገር አብራሃቸው እንድትገባ “ሊያጠምዱህ” የሚሞክሩ ከሆነ “ጓደኞች” ተብለው ሊጠሩ ይገባቸዋልን?
16 የእንዲህ ዓይነት ሰዎች የቅርብ ጓደኛ ከሆንክ አንድም ወደሚሉህ ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብረህ ለመሄድ ወይም እነርሱ የሚሉትን አልስማማበትም ለማለት እንደምትገደድ አስታውስ። አልስማማም ማለትህ ምናልባት የጓደኝነታችሁ ማቆሚያ ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ከእነርሱ ጋር አለመስማማትህን እንደ ነቀፌታ ወይም እንደ ዘለፋ ሊመለከቱት ስለሚችሉ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሌሎች በሠሩት ላይ ማላገጥ ይወዳሉ። እነርሱ ራሳቸው ግን እንዲገሰጹ አይፈልጉም። ምሳሌ 9:8 እንደዚህ ስላለ ሰው ይናገርና በአንፃሩ “ጠቢብን ገስጽ ይወድድህማል” ይላል። እውነተኛ ጓደኞች እርስ በርሳቸው በግልጽ በመነጋገር ለመሻሻል ወይም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለመተራረም እርስ በርስ የሚረዳዱ ናቸው። በአስተሳሰባቸውም ሆነ በንግግራቸው ቀጥተኛ የሆኑ ጓደኞች ካሉህ በዋጋ ሊተመን የማይቻል ሀብት አለህ ማለት ነው። እውነተኛ ጓደኞች ውድና ብርቅ እንደሆነው አልማዝ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን በአንፃሩ ሐሰተኛ ጓደኞች እንደ ተራ ድንጋይ የትም የሚገኙ መሆናቸው ነው።
17–19. (ሀ) በአምላክ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ከማያምን ሰው ጋር የቅርብ ጓደኛ ብትሆን እንዴት ልትነካ ትችላለህ? (ምሳሌ 11:9፤ ዘፍጥረት 34:1, 2) (ለ) እንዲህ ዓይነቱን ሰው በእርግጥ ለመርዳት የምትፈልግ ከሆነ ይህን ልታደርግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች አምላክ መኖሩን ስለማይቀበሉና በቃሉ ስለማያምኑ “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚል ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። በጥንት ዘመን በትግል ሜዳ ውስጥ ከአራዊት ጋር እንዲታገሉ የተፈረደባቸው ሰዎች የሚሰማቸው እንደዚህ ነበር። በይሖዋ አምላክና እርሱ ለታማኝ ሰዎች ሕይወትን መልሶ ለመስጠት ባለው ኃይሉ እምነት አልነበራቸውም። አንተም ወጣት እንደመሆንህ መጠን ሕይወትን ገና መጀመርህ ነው። ታዲያ እነዚያ ከአራዊት ጋር ሲታገሉ እንዲሞቱ የተፈረደባቸው እስረኞች የነበራቸውን ዓይነት ዝንባሌ ለመያዝ ትፈልጋለህን? ሐዋርያው ጳውሎስ ያን ጊዜ የነበረውን ‘ለዛሬ ብቻ የመኖር’ አመለካከት ከጠቀሰ በኋላ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:32, 33) የዚህን ማስጠንቀቂያ እውነተኝነት አስታውስ። ስለ አሁኑ ጊዜ ብቻ የሚያስቡ ሰዎችን የቅርብ ጓደኛ ለማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ተስፋህንም ሆነ ዘላቂና አስደሳች ሕይወት ለመጨበጥ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያበላሹብህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።
18 አንዳንድ ጊዜ አንድ ወጣት ወይም አንዲት ወጣት አጠራጣሪ አኗኗርና ስም ካለው ወይም ካላት ሌላ ወጣት ጋር የሚቀራረቡት እርሱን ወይም እርሷን ለመርዳት ነው ይሉ ይሆናል። ሌሎችን ለመርዳት መፈለግ ጥሩ ነገር ነው። ይሁንና በራስ ወዳድነት ደስታቸው የምትተባበር ከሆነ ምን ያህል እርዳታ እየሰጠሃቸው ነው? ለምሳሌ ያህል አንድ ሕፃን ልጅ ጭቃ ውስጥ ገብቶ ብታይ ሳሙና ይዘህ ወደ ጭቃው በመግባት እዚያው ልታጥበው ትሞክራለህን? አንተም ራስህ ከመቆሸሽ በቀር ምንም አትጠቅመውም። ልጁን ቀርበህ ለማጽዳት ከመሞከርህ በፊት ከጭቃው እንዲወጣ ልታበረታታው መጣር ይገባሃል።
19 እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን መጥፎ ጠባይ ያለው ሰው ለቅርብ ጓደኝነት መምረጥ በሰውየው ላይ (እንዲሁም በአንተ ላይ) መጥፎ ውጤት አለው። ለምን? ምክንያቱም ምን ጊዜም የአንተ ድጋፍ እንደማይለየው በመተማመን በዚያው በመጥፎ መንገዱ እንዲቀጥልበት ሊያደፋፍረው ስለሚችል ነው። ከእርሱ ጋር የምታደርገው መቀራረብ ጥሩ ምክሮችን ልታስገነዝበው በምትችልበት ጊዜ ብቻና ያ ምክር ወደሚብራራበት ቦታ አብሮህ እንዲሄድ በመጋበዝ ቢወሰን ይበልጥ የሚበጅ እርዳታ አይሆንምን?
ከሁሉ የበለጡት ወዳጆች
20. በጓደኛ ምርጫችን ራሳችንን የአምላክ ጠላቶች ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
20 አጠራጣሪ ልማድ ካላቸው ሰዎች ጋር የምታደርገው መቀራረብ ከሁሉም በላይ ከአምላክና ከልጁ ጋር ያለህን ዝምድና እንዴት ሊነካው እንደሚችል አጥብቀህ ልታስብበት ይገባሃል። በያዕቆብ 4:4 ላይ ‘የዓለም ወዳጅ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት አድርጓል’ የሚል እውነት ተገልጿል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ከጠቅላላው ዓለም ጋር ባለን ዝምድና ረገድ የሚሠራውን ያህል በዓለም ካለ ከማንኛውም ሰው ጋር በሚኖረን ዝምድናም ላይ ይሠራል። የአንድን ሰው ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ከተቀበልን ወይም የእርሱን ጓደኝነት የምንመርጥ ከሆነ ‘የዓለም ወዳጆች’ መሆናችንን ማሳየታችን አይደለምን?
21–23. (ሀ) አምላክና ክርስቶስ በእርግጥ ወዳጆቹ ለሆኑለት ሰው የሚመጡለት ጥቅሞች ምንድን ናቸው? (ሮሜ 8:35, 38, 39) (ለ) በእርግጥ ወዳጆቻችን እንዲሆኑ እንደምንፈልግ የምናሳየውስ እንዴት ነው?
21 አሁንና ለወደፊቱም ደስታ ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ የአምላክንና የልጁን ወዳጅነት አብልጠህ መውደድን ተማር። አምላክ እስከ አሁን ድረስ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ጽድቅን የሚወዱ ሰዎች በእርግጥ አስደሳች በሆኑ ሁኔታዎች ሥር የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያለውን ታላቅ ዓላማ በየጊዜው በስፋት እየገለጸላቸው ወዳጅነቱን ሲያሳያቸው ቆይቷል። የአምላክ ልጅም በምድር ሳለ ቀና ልብ ላላቸው ሰዎች ያለውን ታማኝ ፍቅር አረጋግጧል። ለደቀ መዛሙርቱ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 15:13, 14
22 ይሖዋ አምላክና ልጁ ወዳጅ መስለው እንደሚጠጉህ እንደ ብዙዎች ሰዎች አይደሉም። ሰለቸን ብለው አይተዉህም ወይም ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ ጥለውህ አይሸሹም። ትምክህትህን በእነርሱ ላይ ከጣልክ በመከራ ጊዜ እርዳታቸውና ድጋፋቸው በእርግጥ እንዳልተለየህ ትገነዘባለህ።
23 እነዚህን ታላላቅ ወዳጆች በእርግጥ ታደንቃለህን? ወዳጅነታቸውንስ ትመኛለህን? ወዳጅነታቸውን የምታደንቅና የምትመኝ ከሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” በማለት የጻፈውን ግዴታ የሚቀበሉና ከግዴታውም ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎችን ወዳጅ አድርገህ በመያዝ ግለጸው። (1 ዮሐንስ 5:3) እንዲህ ዓይነቶቹ ጓደኞች በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ከጐንህ የሚቆሙ ጥሩ ወዳጆች መሆናቸውን ያሳያሉ።
[ገጽ 61 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጓደኛ እንዲኖርህ ከፈለግህ አንተ ራስህ ጓደኛ መሆን ያስፈልግሃል
[በገጽ 63 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ጓደኞች እንደ አልማዝ ናቸው