ምዕራፍ 29
ሙሴ የሸሸበት ምክንያት
ሙሴ ከግብፅ ሲሸሽ ተመልከት። እያሳደዱት ያሉትን ሰዎች አየሃቸው? ሙሴን ለመግደል የፈለጉበትን ምክንያት ታውቃለህ? እስቲ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንመርምር።
ሙሴ በግብፅ ገዥ በፈርዖን ቤት ውስጥ አደገ። በጣም ጥበበኛና ታላቅ ሰው ሆነ። ሙሴ ግብፃዊ አለመሆኑን ከዚህ ይልቅ የወለዱት ወላጆቹ እስራኤላውያን ባሪያዎች መሆናቸውን ያውቅ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው ወገኖቹ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ሄዶ ለመመልከት ወሰነ። በጣም አስከፊ የሆነ ድርጊት ይፈጸምባቸው ነበር። አንድ ግብፃዊ አንድን እስራኤላዊ ባሪያ ሲመታው ተመለከተ። ሙሴ ዙሪያውን ተመለከተና ማንም የሚያየው እንደሌለ ሲያውቅ ግብፃዊውን መታውና ገደለው። ከዚያም ሙሴ ሰውዬውን አሸዋ ውስጥ ደበቀው።
በሚቀጥለው ቀን ሙሴ እንደገና ወገኖቹን ለመመልከት ሄደ። ከባርነት ነፃ እንዲወጡ ልረዳቸው እችላለሁ ብሎ አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ተመለከተና ጥፋተኛውን ሰውዬ ‘ወንድምህን ለምን ትመታዋለህ?’ አለው።
ሰውዬው ‘አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ ያደረገህ ማን ነው? ያንን ግብፃዊ እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ነው?’ አለው።
በዚህ ጊዜ ሙሴ በጣም ፈራ። በግብፃዊው ላይ የፈጸመውን ነገር ሰዎች እንዳወቁት ተገነዘበ። ፈርዖንም ሙሴ የፈጸመውን ነገር ሰማና እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። ሙሴ ከግብፅ የሸሸው በዚህ ምክንያት ነው።
ሙሴ ከግብፅ ከወጣ በኋላ ከዚያ ርቆ ወደሚገኘው ወደ ምድያም ምድር ተጓዘ። በዚያ ስፍራም ከዮቶር ቤተሰብ ጋር ተገናኘና ሲፓራ የተባለችውን የዮቶር ልጅ አገባ። ሙሴ እረኛ ሆነና የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ጀመር። በምድያም ምድር 40 ዓመት ኖረ። አሁን 80 ዓመት ሆኖታል። ከዕለታት አንድ ቀን ሙሴ የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ መላውን የሙሴ ሕይወት የለወጠ አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጸመ። ገጹን ግለጥና ይህ አስገራሚ ነገር ምን እንደሆነ እንመልከት።