ምዕራፍ 100
ኢየሱስ በአንድ የአትክልት ቦታ
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ክፍል ወጥተው ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሄዱ። ከዚህ በፊት እዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ መጥተዋል። ኢየሱስ ንቁ እንዲሆኑና እንዲጸልዩ ነገራቸው። ከዚያም ትንሽ ራቅ አለና መሬት ላይ ተደፍቶ ጸለየ።
በኋላ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ቦታ ተመለሰ። ምን እያደረጉ የነበረ ይመስልሃል? ተኝተው ነበር! ኢየሱስ ነቅተው እንዲጠብቁ ሦስት ጊዜ የነገራቸው ቢሆንም ወደ እነርሱ በተመለሰ ቁጥር ተኝተው ያገኛቸው ነበር። ኢየሱስ መጨረሻ ወደ እነርሱ ተመልሶ ሲመጣ ‘በእንዲህ ያለ አስጨናቂ ጊዜ ላይ እንዴት ትተኛላችሁ? ለጠላቶቼ የምሰጥበት ሰዓት ደርሷል’ አላቸው።
ወዲያውኑ የብዙ ሰዎች ድምፅ ተሰማ። ተመልከት! ሰዎቹ ሰይፍና ዱላ ይዘው እየመጡ ነው! በደንብ እንዲታያቸውም ችቦ ይዘዋል። እየቀረቡ ሲመጡ ከመካከላቸው አንዱ ፈንጠር ብሎ ወጣና በቀጥታ ወደ ኢየሱስ መጣ። ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ኢየሱስን ሳመው። ሰውየው አስቆሮቱ ይሁዳ ነው! ኢየሱስን የሳመው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ‘ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠኛለህን?’ ሲል ጠየቀው። አዎ፣ ይሁዳ ኢየሱስን መሳሙ አንድ ምልክት ነበር። ከይሁዳ ጋር ያሉት ሰዎች የሚፈልጉት ሰው ማለትም ኢየሱስ የትኛው እንደሆነ መለየት ያስችላቸዋል። ስለዚህ የኢየሱስ ጠላቶች እርሱን ለመያዝ ተጠጉ። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ኢየሱስን ሲወስዱት ዝም ብሎ መመልከት አልፈለገም። ይዞት የመጣውን ሰይፍ መዘዘና አጠገቡ ያለውን ሰው መታው። ሰይፉ የሰውየውን ጭንቅላት ለትንሽ ስቶ የቀኝ ጆሮውን ቆረጠው። ሆኖም ኢየሱስ የሰውየውን ጆሮ ዳሰሰውና ፈወሰው።
ኢየሱስ ጴጥሮስን ‘ሰይፍህን ወደ ቦታው መልስ። አባቴ እኔን ለማዳን በሺህ የሚቆጠሩ መላእክትን እንዲልክልኝ ልጠይቀው እንደምችል አታውቅምን?’ አለው። አዎ፣ ኢየሱስ መጠየቅ ይችል ነበር! ሆኖም ኢየሱስ ጠላቶቹ እሱን የሚወስዱበት ጊዜ እንደደረሰ ያውቅ ስለነበረ አምላክን መላእክት እንዲልክለት አልጠየቀውም። ስለዚህ ይዘውት እንዲሄዱ ፈቀደላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ምን እንደደረሰበት እስቲ እንመልከት።