ምዕራፍ 110
የጳውሎስ አዲስ ረዳት የሆነው ጢሞቴዎስ
ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ሆኖ የሚታየው ወጣት ጢሞቴዎስ ነው። ጢሞቴዎስ በልስጥራን ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖር ነበር። እናቱ ኤውንቄ ስትሆን አያቱ ደግሞ ሎይድ ይባላሉ።
ጳውሎስ ወደ ልስጥራን ሲመጣ ይህ ሦስተኛ ጊዜው ነበር። በመጀመሪያ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ጳውሎስና በርናባስ በስብከት ጉዟቸው ወቅት ወደዚህ ቦታ መጥተው ነበር። አሁን ደግሞ ጳውሎስ ከጓደኛው ከሲላስ ጋር ሆኖ እንደገና መጥቷል።
ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ምን እያለው እንዳለ ታውቃለህ? ‘ከሲላስና ከእኔ ጋር መሄድ ትፈልጋለህ? ራቅ ብለው በሚገኙ ቦታዎች ለሚኖሩ ሰዎች በምናከናውነው የስብከት ሥራ ልትረዳን ትችላለህ’ አለው።
‘አዎ፣ መሄድ እፈልጋለሁ’ ሲል ጢሞቴዎስ መለሰለት። ስለዚህ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጢሞቴዎስ ቤተሰቡን ተለይቶ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሄደ። ጉዟቸው ምን ይመስል እንደነበረ ከመመልከታችን በፊት ግን ጳውሎስ ምን ሁኔታዎችን እንዳሳለፈ እንመልከት። ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢየሱስ ከተገለጠለት 17 ዓመታት ገደማ አልፈዋል።
ጳውሎስ ወደ ደማስቆ የመጣው የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለማሳደድ እንደነበረ አስታውስ፤ አሁን ግን እሱ ራሱ ደቀ መዝሙር ሆኗል! ከጊዜ በኋላ አንዳንድ ጠላቶች ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ የሚሰጠውን ትምህርት ስላልወደዱት ሊገድሉት ፈለጉ። ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ጳውሎስ እንዲያመልጥ ረዱት። ቅርጫት ውስጥ ጨመሩትና በከተማይቱ ግንብ ላይ አሳልፈው ወደ ታች አወረዱት።
ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ለመስበክ ሄደ። የኢየሱስ ተከታዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያኖች የተባሉት በዚህ ቦታ ነው። ከዚያ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ ራቅ ብለው በሚገኙ አገሮች እንዲሰብኩ ተላኩ። ከእነዚህ ከተሞች አንዷ የጢሞቴዎስ መኖሪያ የሆነችው ልስጥራን ነበረች።
አንድ ዓመት ገደማ ካለፈ በኋላ ጳውሎስ በሁለተኛው ጉዞው ወደ ልስጥራን ተመለሰ። ጳውሎስና ሲላስ ከጢሞቴዎስ ጋር ሆነው ወዴት እንደሄዱ ታውቃለህ? እስቲ አንዳንዶቹን ቦታዎች ካርታው ላይ እንመልከት።
በመጀመሪያ በአቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ፤ ከዚያም አንጾኪያ ወደምትባል ከተማ ሄዱ። ቀጥሎም ወደ ጢሮአዳ ተጓዙ፤ ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄና ቤርያ ሄዱ። ካርታው ላይ አቴናን አየሃት? ጳውሎስ በዚህ ቦታ ሰብኳል። ከዚያ በኋላ አንድ ዓመት ተኩል በቆሮንቶስ ሲሰብኩ ቆዩ። በመጨረሻም በኤፌሶን ትንሽ ቆይታ አደረጉ። ከዚያም በጀልባ ወደ ቂሣርያ ተመልሰው መጡና ጳውሎስ ጥቂት ጊዜ ወደቆየባት ወደ አንጾኪያ ተጓዙ።
ስለዚህ ጢሞቴዎስ “ምሥራቹን” እንዲሰብክና ብዙ የክርስቲያን ጉባኤዎችን እንዲያቋቁም ጳውሎስን በመርዳት በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዟል። ስታድግ ልክ እንደ ጢሞቴዎስ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ትሆናለህ?