ምዕራፍ 20
ሕይወትንና ደምን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገህ ትይዛቸዋለህን?
1. (ሀ) አምላክ ሕይወትን እንዴት አድርጎ ይመለከተዋል? (ለ) የአምላክን የሕይወት ስጦታ እንደምናደንቅ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
አምላክ ለሕይወት ያለው አመለካከት ከዓለም አመለካከት በጣም የተለየ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። በአምላክ ፊት ሰብዓዊ ሕይወት ቅዱስ ነገር ነው። አንተስ ሕይወትን እንደዚህ አድርገህ ትመለከታለህን? በሕይወት መኖራችን ሙሉ በሙሉ የተመካው “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ” በሚሰጠው አምላክ ላይ ነው። (ሥራ 17:25–28፤ መዝሙር 36:9) የአምላክ አመለካከት ካለን የራሳችንን ሕይወት ከጉዳት እንጠብቃለን። ሆኖም የአሁኑን ሕይወታችን ለማዳን ብለን መለኮታዊ ሕግ አናፈርስም። አምላክ በልጁ ላይ ከልብ ለሚያምኑት የሰጠውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደ ውድ ኃብት አድርገን እንይዛለን። — ማቴዎስ 16:25, 26፤ ዮሐንስ 6:40፤ ይሁዳ 21
2. ዓለም ለሕይወት የማንን አመለካከት ታንጸባርቃለች? ይህስ አንዳንድ ጊዜ እንዴት ያለ ክርክር ያመጣል?
2 ከዚህ አንጻር ግን የዚህ ዓለም ገዥ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ “ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ” እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44፤ 12:31) የአመጸኝነትን መንገድ መከተል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሰው ልጆች ላይ ሞትን አምጥቷል። ብዙ ውጊያ የተካሄደበት የዓለም ታሪክ የእርሱን መንፈስ ያንጸባርቃል። ይሁን እንጂ ሰይጣን መልኩን ለውጦ ሊቀርብ ይችላል። ስለዚህ የእርሱ አስተሳሰብ ያደረባቸው ሰዎች ‘ሃይማኖተኛ መሆን ጥሩ ቢሆንም አንድ ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ ከወደቀ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚጠቅስ ይልቅ የእነርሱን “የባለ ሞያዎች” ምክር ቢሰማ ይጠቀማል’ ብለው ይከራከራሉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 11:14, 15 ጋር አወዳድር) ከመሞትና ከመኖር አንዱን እንድትመርጥ የሚያስገድድህ ሁኔታ ቢመጣብህ ልብህ ወዴት ያዘነብላል? ፍላጎታችን ይሖዋን ለማስደሰት መሆን አለበት።
3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረውን ለማወቅ መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ዘፍጥረት 9:3–6ንና ሥራ 15:28, 29ን አንብበህ ከጥቅሶቹ ጋር ያሉትን ጥያቄዎች መልስ።
3 የአምላክ ቃል “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነው” በማለት በሕይወትና በደም መካከል በጣም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳለ ይገልጻል። ሕይወት ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ ደምም አምላክ ቅዱስ አድርጎታል። ደም የእርሱ ንብረት ነው፤ ጥቅም ላይ መዋል የሚችለውም እርሱ በፈለገው መንገድ ብቻ ነው። (ዘሌዋውያን 17:3, 4, 11፤ ዘዳግም 12:23) እንግዲያው አምላክ ደምን በሚመለከት ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በጥንቃቄ ብንመረምር ጥሩ ነው።
ዘፍጥረት 9:3–6ን አንብብ
የእንስሳትን ደም ከመብላት ራስህን ለመጠበቅ በአካባቢህ ካሉት ከየትኞቹ ልማዶች መጠንቀቅ ያስፈልግሃል?
ከላይ ያለው ጥቅስ በቁጥር 4 ላይ ስለ እንስሳት ደም በሚናገረው መሠረት የሰውን ደም ስለ መጠጣት እንዴት ይሰማሃል? (በድሮ ዘመን ሮማውያን በግላዲያተር ትርኢት ጊዜ ሰዎች መሬት ላይ የሚፈሰውን ደም ይጠጡ ነበር)
በቁጥር 5ና 6 ላይ እንደተገለጸው የሰውን ደም ያፈሰሰ ሰው በአንደኛ ደረጃ መልስ መስጠት ያለበት ለማን ነው?
ሥራ 15:28, 29ን አንብብ
ይህ ጥቅስ ትእዛዙ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሚያገለግል ያሳያልን? ትእዛዙ በእኛም ላይ ይሠራልን?
የጥቅሱ አነጋገር የሰውን ደም የማይጨምር ነውን?
ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር ትእዛዙን ለመጣስ እንደምንችል ጥቅሱ ያመለክታልን?
4. እዚህ ላይ በተገለጸው መሠረት አንድ ሰው የደም ዕዳ ተካፋይ እንዳይሆን ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያሳያሉ?
4 የሰውን ደም በሚመለከት ሰውን እስካልገደልኩ ድረስ የደም ዕዳ አይኖርብኝም ለማለት አንችልም። በአምላክ ፊት የደም ዕዳ ያለበት የማንኛውም ድርጅት ክፍል ከነበርን የኃጢአቱ ተባባሪ ላለመሆን ከድርጅቱ ጋር የነበረንን ግንኙነት ማቋረጥ እንዳለብን ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። (ራእይ 18:4, 24፤ ሚክያስ 4:3) እንደዚህ ያለው እርምጃ በፍጥነት መወሰድ ያለበት ነው።
5. በመስክ አገልግሎት ተግቶ መሥራት ከደም ዕዳ ነፃ ከመሆን ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?
5 በታላቁ መከራ ስለሚመጣው ጥፋት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ የታዘዙት የአምላክ አገልጋዮች ከደም ዕዳ ነፃ ለመሆን መልዕክቱን በታማኝነት ማወጅ ያስፈልጋቸዋል። (ከሕዝቅኤል 3:17–21 ጋር አወዳድር) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲያከናውነው በተሰጠው አገልግሎት ምክንያት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ባለ ዕዳ እንደሆነ አድርጎ ያስብ ነበር። ከደማቸው ኃላፊነት ነፃ እንደሆነ የተሰማው ስለ አምላክ የመዳን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ከመሰከረላቸው በኋላ ብቻ ነው። (ሮሜ 1:14, 15፤ ሥራ 18:5, 6፤ 20:26, 27) በመስክ አገልግሎት የምታሳየው ትጋት በሁሉም የይሖዋ ምስክሮች ላይ የተጣለውን ኃላፊነት እንደምትገነዘብ ያንጸባርቃልን?
6. አደጋ እንዳይደርስ በምናደርገው ጥንቃቄና ለሕይወት ቅድስና በምናሳየው አክብሮት መካከል ምን ግንኙነት አለ?
6 የሞት አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችንም አክብደን ልናስብባቸው ይገባል። በሙሴ ሕግ ሳያውቅ ሌላውን የገደለ ሰው ከደም ዕዳ ንጹሕ እንደሆነ ተደርጎ አይታይም ነበር። ልዩ ልዩ ቅጣቶች ይሰጡ ነበር። (ዘፀአት 21:29, 30፤ ዘዳግም 22:8፤ ዘኁልቁ 35:22–25) የነገሩ መሠረታዊ ሥርዓት ወደ ልባችን ገብቶ ከሆነ በመኪና አነዳዳችን ወይም ለሕይወት አደገኛ የሆነ የቂልነት ሙከራ በማድረግ ወይም በቤታችንና በመሥሪያ ቤታችን ለሰው ሕይወት አደገኛ የሆነ ነገር እንዲኖር በመፍቀድ ሌሎች በድንገት እንዲሞቱ ምክንያት እንዳንሆን እንጠነቀቃለን። ለእነዚህ ነገሮች ያለህ አቋም የሕይወትን ቅድስና ሙሉ በሙሉ እንደምታምንበት ያንጸባርቃልን?
ደምን ለሕክምና ብንጠቀምበትስ?
7. (ሀ) የአንድን ሰው ደም ለሌላው መስጠት ለደም ቅድስና የሚስማማ አድራጎት ነውን? (ለ) ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ የሚያገልግለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ልማዶች ብቻ ነው ብሎ መከራከር ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው?
7 ነገሩ አዲስ ባይሆንም በተለይ በ20ኛው መቶ ዘመን የሌላውን ሕይወት ለማትረፍ ሲባል ሐኪሞች ለሕመምተኞች ደም ይሰጣሉ። ይህ በሰፊው ይሠራበታል። በዚህ መንገድ ለሕመምተኞች አንዳንድ ጊዜ ሙሉው ደም በሌላ ጊዜ ደግሞ የደሙ ዋና ዋና ክፍሎች ብቻ ይሰጣሉ። እርግጥ ይህ የሕክምና ዘዴ ሕመምተኛው እንደማይሞት ዋስትና አይሰጥም። እንዲያውም አንዳንድ ሕመምተኞች ደም ስለተሰጣቸው ብቻ ይሞታሉ። ከዚህ ይበልጥ የሚያሳስበን ጉዳይ ግን አለ። ‘ከደም ራቁ’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ይህንንም የሕክምና አሠራር ይመለከታልን? አዎን። ከማንኛውም ፍጡር (ከሰው ወይም ከእንስሳ) የተወሰደ ደም ወደ ሰውነታችን እንዲገባ ማድረግ መለኮታዊን ሕግ ያፈርሳል። ለደም ቅድስና ግድ እንደሌለን ያሳያል። (ሥራ 15:19, 20) ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ተእዛዝ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ልማዶች የሚያገለግል ነው በማለት ዘመናዊ የሕክምና ዘዴዎችን ከዕገዳው ውጭ ለማድረግ ምንም መሠረት አይኖረንም። ነገሩን በሚከተሉት መንገዶች ምክንያቱን በማጤን አስብበት:- ጥይት የተፈለሰፈው ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ ዘመናት ቆይቶ ስለሆነ አትግደል የሚለው ትአዛዝ በአሁኑ ጊዜ ሌላውን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በጠመንጃ መግደልን አይመለከትም ብሎ የሚከራከር ማን ነው? ሥካርን የሚከለክለው ትእዛዝ የሚሠራው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት መጠጦች እንጂ አሁን ላሉት ኃይለኛ መጠጦች አይደለም ብሎ መከራከር ምክንያታዊ ይሆናልን? አምላክን ከልብ ማስደሰት ለሚፈልጉት ሁሉ ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ የሚያስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነው።
8. (ሀ) አንድ ዓይነት የሕክምና ዘዴ ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ ነው ወይም አይደለም ብለህ ለመወሰን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ዶክተር ከሰውነትህ ደም ቀድቶ ለማስቀመጥና ቀዶ ጥገና ሲያደርግልህ ሊጠቀምበት ቢፈልግ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠታዊ ሥርዓቶች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ሊረዱህ ይችላሉ? (ሐ) አንድ ሰው ደሙ በአንድ መሣሪያ በኩል አልፎ ወደ ሰውነቱ እንዲገባ የሚያስፈልገው ሕክምና ቢያጋጥመው እንዴት ብሎ ሊያስብ ይችል ይሆናል?
8 ይሁን እንጂ አንዳንድ የሕክምና ዘዴ አደናጋሪ በመሆኑ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል። ችግሩ ሊፈታ የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ሐኪሙ ስለ ሕክምና አሰጣጡ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥህ ጠይቀው። ከዚያ በኋላ ነገሩን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እያስተያየህ በጸሎት መርምረው። ዶክተሩ በቀዶ ጥገናው ጊዜ አስፈላጊ ከሆነ እንድንጠቀምበት ከሰውነትህ ጥቂት ደም ቀድተን ብናስቀምጥስ ብሎ ሐሳብ ሊያቀርብልህ ይችላል። በዚህ ትስማማለህን? በሙሴ በኩል በተሰጠው የአምላክ ሕግ መሠረት ከአንድ ፍጡር የሚወጣ ደም ወደ መሬት መፍሰስ እንዳለበት አስታውስ። (ዘዳግም 12:24) እርግጥ እኛ በሕጉ ሥር አይደለንም፣ ሆኖም ሕጉ የሚያስተላልፈው መሠረታዊ መልእክት ደም ቅዱስ እንደሆነና ከፍጡሩ ሲወጣ የአምላክ የእግሩ መቀመጫ በሆነችው ምድር ላይ መፍሰስ አለበት የሚል ነው። (ከማቴዎስ 5:34, 35 ጋር አወዳድር) ታዲያ ደምን ለትንሽ ጊዜም ቢሆን በአንድ ዕቃ አቆይቶ በኋላ ወደ ሰውነት ተመልሶ እንዲገባ ማድረግ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? ነገር ግን ዶክተሩ በቀዶ ጥገና ጊዜ ወይም ሌላ ዓይነት ሕክምና ሲሰጥህ ደምህ በአንድ መሣሪያ በኩል አልፎ ወደ ሰውነትህ ተመልሶ እንዲገባ ይደረጋል ቢልህስ? በዚህስ ትስማማለህን? አንዳንዶች በመሣሪያው ወስጥ ያለው ፈሳሽ ደም እስካልተቀላቀለበት ድረስ ሕክምናውን በንጹሕ ሕሊና ሊቀበሉት እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። መሣሪያውን ደም የሚዘዋወርባቸው የሰውነት ክፍሎች ቅጥያ አድርገው ይመለከቱታል። እርግጥ ሁኔታዎች ይለያያሉ፤ ስለዚህ ውሳኔውን የምታደርገው አንተው ነህ። ሆኖም ውሳኔህ በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖርህ የሚያደርግ መሆን አለበት። — 1 ጴጥሮስ 3:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19
9. (ሀ) ከደም ለመራቅ ያለህ ውሳኔ እንዲከበርልህ አስቀድመህ እንዴት ያሉ ጥንቃቄዎች መውሰድ አለብህ? (ለ) ድንገተኛ ሁኔታ በሚያጋጥምበትም ጊዜ ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ደስ ከማይል ጭቅጭቅ ለመዳን የሚቻለው እንዴት ነው? (ሐ) አንድ ዶክተር ወይም ፍርድ ቤት በግድ ደም መውሰድ አለብህ ብሎ ቢወስን ምን ታደርጋለህ?
9 ሐኪምህ ‘ከደም ለመራቅ’ ያለህን ውሳኔ እንዲያከብርልህ ሕክምና የሚያስፈልገው ድንገተኛ ነገር ከመፈጠሩ በፊት አነጋግረው። ለሕክምና ሆስፒታል መሄድ የሚያስፈልግህ ከሆነ ደም እንደማትፈልግ አስቀድመህ በጽሑፍ ግለጽ። በተጨማሪም ሕክምናውን ለሚያደርግልህ ዶክተር ስለ አቋምህ አነጋግረው። ነገር ግን ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥምህስ? ብዙውን ጊዜ ከዶክተሩ ጋር አክብሮት የተሞላበትና ምክንያታዊ ውይይት በማድረግ ደስ ከማይል ጭቅጭቅ መዳን ይቻላል። ክርስቲያናዊ ሕሊናህን በሚያከብር መንገድ ችሎታውን አንተን ለመርዳት እንዲጠቀምበት አጥብቀህ ጠይቀው። (ምሳሌ 15:1፤ 16:21, 23) ነገር ግን ሐኪሞች ለእኛ አስበው ደም አለምውሰዳችን ለሕይወታችን አደገኛ እንደሆነ ቢገልጹና ደም ለመውሰድ እንድንስማማ ሊያስገድዱን ቢሞክሩስ? የይሖዋ መንገዶች ትክክል እንደሆኑ ያለን እምነት በአቋማችን ጥብቅ እንድንሆን ይረዳናል። ከሰው ይልቅ አምላክን መታዘዝ ስለምንፈልግ ለይሖዋ ያለን ታማኝነት ደምን ላለመውሰድ ቁርጥ ያለ አቋም እንዲኖረን ሊያደርግ ይገባል። — ሥራ 5:29፤ ከኢዮብ 2:4ና ከምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር።
ነገሩ ምን ያህል ከባድ ጉዳይ ነው?
10. ደም የሚሰጠው ሕይወት ለማዳን ነው የሚለው አነጋገር ስለ ጉዳዩ ያለንን አመለካካት የማይለውጠው ለምንድን ነው?
10 ደም መውሰድን የሚደግፉ ክርክሮች ይሖዋን ገና ላላወቁት ሰዎች ለሕይወት ከፍተኛ አክብሮት የሚያሳዩ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ መንገድ የሚከራከሩ ብዙ ሰዎች ጽንስን በማስወረድ ሕይወት ቢጠፋ ግድ እንደሌላቸው አንዘነጋውም። ይሖዋ ስለ ሕይወትና ስለ ደም ከማንኛውም የሕክምና “ባለሞያ” የበለጠ ያውቃል። የእርሱ ትእዛዛት ሁሉ ጠቃሚያችን ሆነው ተገኝተዋል። የአሁኑን ሕይወታችንና የወደፊቱን ተስፋችን ይጠብቁልናል። (ኢሳይያስ 48:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ ከዚህ የተለየ ነውን?
11. (ሀ) ይሖዋ እሥራኤላውያን ደምን በምን መንገድ ብቻ እንዲጠቀሙበት ፈቅዶላቸው ነበር? (ለ) ይህስ ለእኛ ለክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ ደም በምን መንገድ ብቻ ሊሠራበት እንደሚችል የተናገረው ቃል የደምን ቅድስና ማክበር የቱን ያህል ከባድ ጉዳይ እንደሆነ ያሳያል። “የሥጋ ሕይወቱ በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና በመሰዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች ከእናንተ ማንም ደም አይበላም . . . አልሁ።” (ዘሌዋውያን 17:11, 12) ከዚህ ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ በይሖዋ መሰዊያ ላይ ይፈስ የነበረው የእንስሳት ደም ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ደም የሚያመለክት ነበር። (ዕብራውያን 9:11, 12፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19) እንግዲያው የአምላክ ሕግ ሰው ደምን ለሌላ ዓላማ እንዳይጠቀምበት መከልከሉ የኢየሱስን ደም ቅድስና አጉልቶ ያሳያል። ደምን አላግባብ ብንጠቀምበት ይሖዋ በልጁ በኩል ያደረገልንን የመዳን ዝግጅት ማቃለላችን እንደሆነ ከዚህ ለመረዳት እንችላለን።
12. አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሞት ቢመጣበት በሕይወት ለመቆየት ብሎ ደምን ያላግባብ የማይጠቀምበት ለምንድን ነው?
12 ወደ ሞት አፋፍ የሚያደርስ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጀርባችንን ለአምላክ ብናዞር እንዴት ያለ አጭር አመለካከት ይሆናል! ከልብ የሚሠሩ ጠንቃቃ ሐኪሞች የሚሰጡትን አግልግሎት ብናደንቅም የአሁኑ ሕይወት እንጂ ሌላ ነገር የሌለን ይመስል የራሳችንን ወይም የቤተሰቦቻችንን ሕይወት ለጥቂት ቀናት ወይም ዓመታት ለማቆየት ብለን የአምላክን ሕግ በመጣስ የጭንቀት ሙከራ አናደርግም። በፈሰሰው የኢየሱስ ደምና ይህ ደም በከፈተው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ እምነት አለን። የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች፣ የሞቱትም ጭምር፣ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚሰጣቸው በሙሉ ልባችን እናምናለን። — ዮሐንስ 11:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:10
የክለሣ ውይይት
● ሕይወትንና ደምን ቅዱስ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ዓለም ከዚህ የተለየ አቋም በመደገፍ ለምን ይከራከራል?
● እንስሳትን በሚመለከት ለደማቸው ቅድስና አክብሮት የምናሳየው እንዴት ነው?
● ሁላችንም ሰብዓዊ ሕይወትን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገን እንደምንመለከት በምን ልዩ ልዩ መንገዶች ማሳየት ይገባናል? እንደዚህ ማድረግስ የቱን ያህል አስፈላጊ ነው?