ምዕራፍ 15
ስለ መንግሥቱ በተነሳው ጥያቄ የሰዎች በሁለት መከፈል
1. ስለ መንግሥቱ በተነሳው ጥያቄ ላይ ሰዎች በሁለት ወገን እየተከፈሉ መሆናቸው ለእያንዳንዳችን አሳሳቢ ጉዳይ የሚሆነው ለምንድን ነው?
በያንዳንዳችን ፊት ውሳኔ የሚጠይቅ አንድ ትልቅ ጉዳይ ተደቅኗል። በክርስቶስ ለምትመራው የይሖዋ መሲሐዊት መንግሥት የሚኖረን አቋም ጥያቄ ላይ ወድቋል። ለዚህ ጥያቄ በሚሰጡት ምላሽ የሁሉም ብሔራት ሕዝቦች በሁለት ወገን እየተከፈሉ ነው። እያንዳንዱ ሰው በሚመርጠው ጐዳና መሠረት ከሁለቱ ጎራዎች በአንዱ ውስጥ ይመደባል። ከሁለቱ ቡድኖች አንደኛው ብቻ ከመጪው የዓለም ጥፋት በሕይወት ይተርፋል።— ማቴዎስ 24:40, 41
2. (ሀ) ይህች መሲሐዊት መንግሥት ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ከተነሳው ጥያቄ ጋር ተዛምዶ ያላት እንዴት ነው? (ለ) መንግሥቲቱ በቅርቡ ምን ትሆናለች? እንግዲያው ስለ ምን ነገር አጥብቀን ማሰብ ይኖርብናል?
2 ይሖዋ የተቀባውን ልጁን፣ መሲሑን፣ ቀደም ሲል በሰማይ በማንገሥ ዙፋን ላይ አስቀምጦታል። “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 ሲፈጸሙ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብን ርስቱ፣ ጠቅላላዋን ምድር ደግሞ ንብረቱ አድርጎ ሰጥቶታል። (መዝሙር 2:6, 8) አምላክ ለምድር ያለውን ጥበባዊና ፍቅራዊ ዓላማ ለማስፈጸም በይሖዋ የተቀባው ንጉሥ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠባትን መሲሐዊት መንግሥት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባታል። በዚህም ምክንያት ለመንግሥቲቱ ያለህ ዝንባሌ ስለ ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ምን እንደሚሰማህ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በቅርቡ ይህች መሲሐዊት መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የሰውን ዘር ጉዳዮች የሚቆጣጠረውን ጠቅላላ የፖለቲካ ሥርዓት ‘ትፈጫለች፤ ታጠፋውማለች’፤ በኋላም በጠቅላላው ምድር ላይ ብቻዋን የምትገዛ መንግሥት ትሆናለች። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 19:11–21) መንግሥቲቱ ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥ ስትጀምር አንተ የት ትገኝ ይሆን? በእርሷ እየተመሩ ፍጹም ሕይወት ከሚያገኙት ደስተኛ ነዋሪዎች መካከል ትገኝ ይሆን? ኢየሱስ አሁን ያሉ ሰዎች የዚህ አጋጣሚ ተካፋይ ሊሆኑ የሚችሉበትን መሠረት አስታውቋል።
ንጉሡና ‘ወንድሞቹ’
3. በማቴዎስ 25:31–33 ላይ ኢየሱስ የገለጸው ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ስለ ‘ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ለሐዋርያቱ በተናገረበት ጊዜ ብዙ ምሳሌዎችን ጠቅሷል። በመጨረሻው ምሳሌው ላይ እንዲህ አለ:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል። አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በእርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።” — ማቴዎስ 24:3፤ 25:31–33
4. (ሀ) ይህ ምሳሌ ከዳንኤል 7:13, 14 ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? (ለ) ራሳችንን ምን እያልን ብንጠይቅ እንጠቀማለን?
4 ኢየሱስ በዚሁ ትንቢት መጀመሪያ ላይ በተደጋጋሚ እንዳደረገው እዚህም ላይ ራሱን “የሰው ልጅ” ብሎ እንደጠራ ልብ በል። (ማቴዎስ 24:27, 30, 37, 39, 44) በዚህ ቃል መጠቀሙ ከስድስት መቶ ዘመናት በፊት ለዳንኤል የተሰጠውን ትንቢታዊ ራእይ ያስታውሰናል። ይህን በሚመለከት ነቢዩ ቀጥሎ ያለውን ጽፎ ነበር:- “በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፣ የሰው ልጅ የሚመስል [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም [ወደ ይሖዋ አምላክ] ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” (ዳንኤል 7:13, 14፤ ዕብራውያን 2:5–8) ይህ የመግዛት ሥልጣን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቀደም ሲል ተሰጥቷል። ከ1914 ጀምሮ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል። በግልህ ለአገዛዙ ምን ምላሽ ሰጥተሃል? አምላክ ራሱ የጠቅላላዋ ምድር ገዥ አድርጎ ለሾመው ተገቢ አክብሮት እንዳለህ አኗኗርህ ይመሰክራልን?
5. አንድ ሰው ኢየሱስን እንደ ንጉሥ አድርጎ በመቀበል በታማኝነት እንደሚያገለግለው ቢናገር ክርስቶስ የአባባሉን እውነተኛነት የሚለካው እንዴት ነው?
5 ቃል ብቻ አይበቃም። በአምላክ መንግሥት አምናለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስንም እወዳለሁ ብሎ መናገሩ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች በሰጠው ምሳሌ ላይ የአንድ ሰው አባባል እውነተኛነት የሚለካበት ቁልፍ የሆነው ነገር በምድር ላይ ላሉት የክርስቶስ ተወካዮች፣ ይኸውም ‘ለወንድሞቹ’ በሚያደርግላቸው ነገር ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሚኖረው በሰማይ ላይ ስለሆነ በዓይን ሊታይ አይችልም። — ማቴዎስ 25:40, 45
6. እነዚህ የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ እነማን ናቸው?
6 ‘ወንድሞቹ’ እነማን ናቸው? ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ ወራሽ እንዲሆኑ አምላክ ከሰው ልጆች መካከል የመረጣቸው ሰዎች ናቸው። ቁጥራቸው 144,000 ሲሆን በምድር ላይ የእነርሱ አባል የሆኑ ጥቂት ቀሪዎች ይገኛሉ። (ራእይ 14:1, 4) በአምላክ መንፈስ ‘እንደገና ስለ ተወለዱ’ የአምላክ ልጆች ናቸው፤ በዚህም ምክንያት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ “ወንድሞች” ተብለዋል። (ዮሐንስ 3:3፤ ዕብራውያን 2:10, 11) ኢየሱስ ለእነዚህ ‘ወንድሞቹ፣’ “ከሁሉ ለሚያንሰው” እንኳን የሚደረገውን ነገር ለእርሱ እንደተደረገ ያህል ይቆጥረዋል።
7. የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ የአብያተ ክርስቲያናት አባላት ያልሆኑት ለምንድን ነው?
7 በጊዜያችን እነዚህ የክርስቶስ “ወንድሞች” የሚገኙት የት ነው? በሕዝበ ክርስትና የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች መካከል ልታገኛቸው ትችላለህን? ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ተከታዮቹ ምን ብሎ ነበር? “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና አባሎቻቸው በእርግጥ እንደዚህ ያለ አቋም አላቸው ሊባል ይቻላልን? በአብዛኛው ዝንባሌያቸውና አድራጎታቸው እነርሱ በሚኖሩበት የዓለም ክፍል ውስጥ የተለመዱትን ነገሮች ያንጸባርቃል። አብያተ ክርስቲያናት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባታቸው በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው። በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በሚረቀቅበት ጊዜ የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክና የአይሁድ ሃይማኖት ተወካዮች በአማካሪነት ተገኝተው ነበር። በቅርብ ዓመታት የሮም ጳጳሳት የተባበሩት መንግሥታትን “የመጨረሻው የስምምነትና የሰላም ተስፋ” እንዲሁም “የመጨረሻው የሰላምና የፍትህ ሸንጎ” በማለት አወድሰውታል። 300 ያህል ሃይማኖቶችን ያቀፈው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤም ፖለቲካዊ ዓመፆችን ለመደገፍ በገንዘብም እንኳን ሳይቀር ረድቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሮማዊው አገረ ገዥ ለጲላጦስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎታል። — ዮሐንስ 18:36
8. (ሀ) የክርስቶስን ‘ወንድሞች’ ለይተህ ለማወቅ የረዳህ ምንድን ነው? (ለ) የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለእነርሱ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
8 በዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ባለማድረግ መንግሥቱን በዓለም ዙሪያ ለማወጅ በብርቱ የተጋደለውና ከመንግሥቱ ጎን ጸንቶ የቆመው አንድ ቡድን ብቻ መሆኑን ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ይህም ቡድን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ነው። የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ቀሪ አባላት በእነርሱ መካከል ይገኛሉ። የጌታቸውንና የሐዋርያቱን ምሳሌ በመከተል ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ይነግራሉ። (ሉቃስ 8:1፤ ሥራ 8:12፤ 19:8፤ 20:20, 25) በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ (በወቅቱ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይባሉ በነበሩት) የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ “በፊትም ሆነ አሁን ዋና ሥራችሁ ስለ መጪዋ የመሲሑ ክብራማ መንግሥት ማወጅ ነው” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። በ1922 በተደረገው ተመሳሳይ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይም ይኸው ነጥብ እንደገና ጐላ ተደርጎ ተጠቅሷል:- “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚል ብርቱ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ነበር። በማንኛውም ዘዴ እየተጠቀሙ በዓለም ዙሪያ እስከ ዛሬ ድረስ ልክ እንደዚሁ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። (ማቴዎስ 24:14) በእነርሱ የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት ስለ መንግሥቲቱ የተነሳው ጥያቄ ለአንተም ሊቀርብ ችሏል። ታዲያ ጥያቄውን በሚመለከት ምን እያደረግህ ነው?
‘ከወንድሞቼ ለአንዱ አደረጋችሁት’
9. (ሀ) በማቴዎስ 25:35–40 ላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ከመንግሥቱ አገልግሎት ጋር የተዛመዱት እንዴት ነው? (ለ) እንግዲያው በየትም ቦታ ያሉ ሰዎች ምን ፈተና ተደቅኖባቸዋል?
9 በመንፈስ የተቀቡት የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ከዓለም ተለይተው እየኖሩ የአምላክን መንግሥት በድፍረት በመስበካቸው ከባድ ፈተናዎች ደርሰውባቸዋል። (ዮሐንስ 15:19, 21) አንዳንዶቹ ረሀብ፣ ጥማትና እርዛት አጋጥሟቸዋል። ብዙዎቹ በማያውቁት አገር ለማገልገል ሲሉ የተወለዱበትን ስፍራ ትተው ሄደዋል። አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ የታመሙ፣ በአሳዳጆችም የታሠሩና የተገደሉ አሉ። በክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ላይ የደረሱት እነዚህ ሁኔታዎች በሁሉም አገር በሚገኙ ሰዎች ፊት አንድ ፈተና እንዲደቀን አድርገዋል። ለአምላክና ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር እነዚህን የሰማያዊ መንግሥት አምባሳደሮች በችግራቸው እንዲደርሱላቸው ያደርጋቸው ይሆን? (ማቴዎስ 25:35–40፤ ከ2 ቆሮንቶስ 5:20 አዓት ጋር አወዳድር።) ንጉሡ ለራሱ እንደተደረገ ያህል የሚቆጥረው እነርሱ የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ምክንያት እርዳታ ሲያደርጉላቸው ነው እንጂ በሰብዓዊ ርኅራኄ አነሳሽነት የሚያደርጉትን ደግነት አይደለም።— ማርቆስ 9:41፤ ማቴዎስ 10:42 አዓት
10. (ሀ) ‘ፍየሎቹ’ የሚያነሱት ክርክር ዋጋ ቢስ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከዚህ በተቃራኒ “በጎቹ” ምን አቋም ወስደዋል?
10 ኢየሱስ ይህን የመሰለ እርዳታ የሚያደርጉትን ከበጎች ጋር አመሳስሏቸዋል። ‘ወንድሞቹን’ ሳይረዱ የቀሩት ግን በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ ፍየሎች ተብለው ተጠቅሰዋል። ‘ፍየሎቹ’ ኢየሱስ ክርስቶስን መቼ አየነውና ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ አገልጋዮቹን ልኮባቸዋል፤ አገልጋዮቹም ማንነታቸውን በግልጽ አሳውቀዋል። ሁሉም “ፍየሎች” የክርስቶስን ‘ወንድሞች’ አያሳድዱ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰማያዊውን ንጉሥ ተወካዮች ለመርዳት የሚያንቀሳቅስ ፍቅር አላሳዩም። (ማቴዎስ 25:41–45) ሰይጣን ዲያብሎስ በስውር የሚገዛውን ዓለም ሙጥኝ ብለው ይዘዋል። ‘በጎቹም’ ቢሆኑ ክርስቶስን ቃል በቃል ሊያዩት አይችሉም። ይሁን እንጂ ‘ከፍየሎች’ ጋር ሲወዳደሩ እነዚህን የአምላክን መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በመደገፍ ከክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ጋር ለመቆጠር እንደማይፈሩ አረጋግጠዋል። “በጎቹ” የሚያደርጉትን ያውቃሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራዋን የአምላክ መንግሥት የሚደግፍ ቁርጥ ያለ ምርጫ አድርገዋል። በንጉሡ ፊት አድራጎታቸው ዋጋ ያገኘውም ለዚህ ነው።
11. (ሀ) ብዙ ሰዎች የክርስቶስን ‘ወንድሞች’ አግኝተዋቸው የማያውቁ ከሆነ እዚህ ላይ በተገለጸው መሠረት እንዴት ሊፈረድባቸው ይችላል? (ለ) ይህ ሥራ እንደሚሳካ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
11 ሆኖም በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች በዚህ መሠረት ሊፈረዱ የሚችሉት እንዴት ነው? አባቱ ሰማያዊ መንግሥት የሚሰጣቸው ‘ወንድሞቹ’ “ታናሽ መንጋ” ብቻ እንደሚሆኑ ኢየሱስ ተናግሮ አልነበረምን? (ሉቃስ 12:32) ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ውስጥ አንዱንም በግል አግኝተው አያውቁም። ይህ እውነት ቢሆንም የክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ለዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ማዕከል መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል። በዚህ የተደራጀ ሕዝብ አማካይነት አንገብጋቢው የመንግሥቱ ጥያቄ በየትም ቦታ ለሚኖሩት ሰዎች እየቀረበላቸው ነው። ይህን ሁሉ ሥራ ኢየሱስ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ከሰማይ የሚመራው ሲሆን በመላእክቱም ይታገዛል። የአምላክ መንግሥት እንዳይሰበክ መንግሥታዊ እገዳ በተደረገባቸው አገሮችም ሳይቀር ሰዎች በሁለት ወገን እንዲከፈሉ የሚያደርገው ይህ ሥራ ምንም ኃይል ሳይበግረው በምድር ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች በመካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጐን ለመቆም ችለዋል።
12. (ሀ) “በጎቹ” የወሰዱትን አቋም ግልጽ የሚያደርጉት እንዴት ነው? (ለ) ይህንንስ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
12 ይህን አቋም የሚያሳዩት እንዴት ነው? ከቅቡዓኑ ጐን ተሰልፈው መንግሥቲቱ እየገዛች መሆኗንና የዓለምን ሥርዓት በቅርቡ እንደምታወድም በቅንዓት በመስበክ ነው። በዚህ ምክንያት ለይሖዋ መሲሐዊት መንግሥት የቆሙ መሆናቸውን በይፋ አሳውቀዋል፤ ሌሎችም አርአያቸውን እንዲከተሉ በፍቅር አጠንክረው እያሳሰቡ ነው። እነዚህ ትክክለኛ ልብ ያላቸው ሰዎች ይህን ለማድረግ የሚያንቀሳቅሳቸው ከመጪው ጥፋት በሕይወት ለመትረፍ ያላቸው ምኞት ብቻ አይደለም። ይሖዋንና መንገዶቹን ከልብ ያፈቅራሉ። ክርስቶስ ንጉሥ የሆነበት መንግሥት መዘጋጀቱ ልባቸውን በአመስጋኝነት ይሞላዋል፤ ሌሎችም ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ሁሉ በመንግሥቱ ምሥክርነት ሥራ ይሳተፋሉ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው ‘በቅድሚያ የአምላክን መንግሥት ይፈልጋሉ’፤ የቁሳዊ ነገሮች ጭንቀት ይህን ወደ ሁለተኛ ደረጃነት እንዲያወርደው አይፈቅዱለትም። በዚህ መንገድ ለታላቅ በረከት ከተሰለፉት መካከል ይሆናሉ። — ማቴዎስ 6:31–33
‘መንግሥቱን ትወርሳለህን?’
13. (ሀ) ይሖዋ ለእነዚህ በግ መሰል ሰዎች ሽልማት ለመስጠት ያሰበው ከመቼ ጀምሮ ነው? (ለ) ‘መንግሥቱን ይወርሳሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
13 በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት “በጎች” በመጨረሻው የሚያገኙት ሽልማት በእርግጥ አስገራሚ ነው። ንጉሡ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ሆኖ እንዲህ ይላቸዋል:- “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት [“ከተመሠረተበት” አዓት] ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” (ማቴዎስ 25:34) “ዓለም ከተመሠረተበት” ይኸውም አዳምና ሔዋን በዘፍጥረት 3:15, 16 መሠረት፣ አምላክ የሰውን ዘር ለማዳን ባወጣው ዝግጅት መጠቀም የሚችሉ ልጆች ካፈሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ይሖዋ ለእነዚህ “በጎች” ሽልማት ለመስጠት አሳብ ነበረው። (ከሉቃስ 11:50, 51 ጋር አወዳድር።) ወደፊት በምትመለሰው ገነት ውስጥ አዳም ያጠፋውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ‘መንግሥት ይወርሳሉ’ ሲባል ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም “በጎቹ” የሰማያዊት መንግሥት ወራሽ ከሆኑት የንጉሡ ‘ወንድሞች’ ጋር አንድ እንዳልሆኑ ምሳሌው ያሳያል። ስለዚህም “በጎቹ” የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች መሆን አለባቸው። በሊዴልና ስኮት የተዘጋጀው ግሪክ–ኢንግሊሽ ሌክሲከን (የግሪክኛና የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት) እዚህ ላይ “መንግሥት” ተብሎ የተተረጎመው ባሲሊያ የሚባለው የግሪክኛ ቃል “በንጉሥ መገዛት” ማለት ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል። በዚህኛው አገባብ ይኼኛው ትርጉሙ እንደሚሠራ ግልጽ ነው።
14. ‘በፍየሎቹ’ ላይ የሚበየነው ፍርድ “በጎቹ” ከሚያገኙት ውርሻ ተቃራኒ የሚሆነው እንዴት ነው?
14 ‘ፍየሎቹ’ “ወደ ዘላለም ጥፋት” ሲሄዱ ማለትም በእሳት እንደተቃጠሉ ያህል ድምጥማጣቸው ሲጠፋ መሲሐዊው ንጉሥ ‘ለበጎቹ’ ጥላ ከለላ ይሆንላቸዋል። (ማቴዎስ 25:41, 46 አዓት፤ ከራእይ 21:8 ጋር አወዳድር።) መሞት ሳይኖርባቸው ታላቁን መከራ በሕይወት ካለፉ በኋላ ሰይጣንና ክፉው የነገሮች ሥርዓቱ ከሚያሳድሩት እኩይ ተጽዕኖ ነፃ ወደምትሆነው ክብራማ “አዲስ ምድር” ይገባሉ። ስለ መንግሥቲቱ በተነሳው ጥያቄ ላይ አሁን ትክክለኛ ውሳኔ ስላደረጉ ይህን በረከት ይቀዳጃሉ።
15. (ሀ) ይህ ምሳሌ በአሁኑ ጊዜ እንደሚፈጸም እንዴት እናውቃለን? (ለ) እንግዲያው የሞትና የሕይወት ጉዳይ የሆነው ሥራ ምንድን ነው?
15 ‘ፍየሎቹ’ ለዘላለም ይጠፋሉ ስለ ተባለ ምሳሌው የሚፈጸመው ገና ወደፊት፣ ምናልባትም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ነው ብሎ ማሰብ ከባድ ስህተት ነው። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ምልክት ክፍል አድርጎ መስጠቱ ይህን አስተሳሰብ ይቃረናል። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ የገለጻቸው ነገሮች የሚፈጸሙት እርሱ ከነገሠ በኋላ፣ ‘ወንድሞቹ’ ገና በሥጋ እያሉ፣ እርሱ የጠቀሳቸው መከራዎችም ሲደርሱባቸው ነው። እኛ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንገኛለን። ይህ ጊዜ በፍጥነት እያለቀ ነው። እንግዲያው በመንግሥቱ ላይ ሙሉ እምነት ማድረጋችን አስፈላጊ ሲሆን ሌሎች ሰዎችም ይህንን ዓይነት እርምጃ አሁንኑ የመውሰድን አስፈላጊነት እንዲያስተውሉ መርዳቱ ምን ያህል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!