ምዕራፍ 3
የሃይማኖት ምርጫህ ልዩነት ያመጣል
1. አንዳንድ ሰዎች ስለ ሃይማኖት ምን ብለው ያምናሉ?
“ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው” በማለት ብዙ ሰዎች ይናገራሉ። ‘ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው’ ይላሉ። ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ሁሉንም ሃይማኖቶች አምላክ ይቀበላቸዋል ማለት ስለሚሆን የትኛውንም ሃይማኖት መከተሉ ለውጥ አይኖረውም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ሁሉንም ይቀበላልን?
2. (ሀ) ፈሪሳውያን ኢየሱስን ምን አደረጉበት? (ለ) ፈሪሳውያን አባታችን ማን ነው ይሉ ነበር?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ ፈሪሳውያን ተብለው የሚጠሩ የአንድን ሃይማኖታዊ ቡድን ተከታዮች ነበሩ። ፈሪሳውያን አንድ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓት አቋቋሙ። በአምላክም የተወደደ እንደሆነ አድርገው ያምኑ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን ኢየሱስን ለመግደል ይሞክሩ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ” አላቸው። እነርሱ ግን ለዚህ መልስ ሲሰጡ “አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው” አሉት።—ዮሐንስ 8:41
3. ኢየሱስ ስለ ፈሪሳውያን አባት ምን አለ?
3 ነገር ግን አባታቸው በእርግጥ አምላክ ነበርን? ያንን ዓይነት ሃይማኖታቸው አምላክ ተቀብሎት ነበርን? በፍጹም አልተቀበለውም። ምንም እንኳን ፈሪሳውያን ቅዱሳን ጽሑፎችን ቢይዙና እየተከተሉአቸው እንዳሉ አድርገው ቢያስቡም ዲያብሎስ በተሳሳተ አቅጣጫ መርቷቸው ነበር። ኢየሱስም ይህንኑ ሲነግራቸው እንደዚህ አላቸው፦ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። . . . ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”—ዮሐንስ 8:44
4. ኢየሱስ የፈሪሳውያንን ሃይማኖት እንዴት ተመለከተው?
4 የፈሪሳውያን ሃይማኖት ውሸት እንደነበረ ግልጽ ነው። የዲያብሎስን እንጂ የአምላክን ፍላጎት ለማስፋፋት የሚያገለግል አልነበረም። ስለዚህ ኢየሱስ ሃይማኖታቸውን እንደ ጥሩ አድርጎ በመመልከት ፋንታ አወገዘው። ለእነዚያ ሃይማኖተኛ ፈሪሳውያን እንዲህ አላቸው፦ “መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፣ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።” (ማቴዎስ 23:13) በሐሰተኛ አምልኮታቸው የተነሳ ኢየሱስ እነዚያን ፈሪሳውያን ግብዞችና መርዘኛ እባቦች ብሎ ጠርቷቸዋል። በመጥፎ አካሄዳቸው ምክንያት ወደ ጥፋት በሚመራው መንገድ እየሄዱ እንዳሉ ነገራቸው።—ማቴዎስ 23:25-33
5. በዓለም ላይ ያሉት ብዙ ሃይማኖቶች ወደ አንድ ስፍራ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ያለመሆናቸውን ኢየሱስ እንዴት አሳየ?
5 እንግዲያው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንዱ የመዳን ሥፍራ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው ብሎ አላስተማረም። በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን በትክክለኛው መንገድ ስለማያመልኩት ወደ ጥፋት በሚወስደው መንገድ በመጓዝ ላይ ናቸው። ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ እየተከተሉ ያሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
6. የእስራኤልን ሕዝብ አምልኮ በመመርመር ምን ልንማር እንችላለን?
6 አምላክ ከጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገውን ግንኙነት መመልከቱ አምላክ በሚቀበለው መንገድ እርሱን ማምለኩ የቱን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል። እስራኤላውያን በዙሪያቸው የነበሩት አሕዛብ ከሚከተሉት የሐሰት ሃይማኖት እንዲርቁ አምላክ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳግም 7:25) እነዚያ ሕዝቦች ልጆቻቸውን ለአማልክቶቻቸው ይሰዉ ነበር። እንዲሁም ርኩሰት ያለበት የጾታ ግንኙነት፣ ግብረ ሰዶም ጭምር ይፈጽሙ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:20-30) አምላክ እስራኤላውያንን ከእነዚህ ድርጊቶች እንዲርቁ አዘዛቸው። እርሱን ባለመታዘዝ ሌሎች አማልክትን ሲያመልኩ ቀጥቷቸዋል። (ኢያሱ 24:20፤ ኢሳይያስ 63:10) እንግዲያው ለመከተል የመረጡት ሃይማኖት በእርግጥ ልዩነት አምጥቶ ነበር።
ዛሬም የሐሰት ሃይማኖት አለን?
7, 8. (ሀ) በዓለም ጦርነቶች ጊዜ ሃይማኖቶች ምን አቋም ወሰዱ? (ለ) በጦርነት ጊዜ ሃይማኖቶች ስላደረጉት ነገር አምላክ እንዴት ይሰማዋል ብለው ታስባለህ?
7 ዛሬ ስላሉት በብዙ መቶ ስለሚቆጠሩት ሃይማኖቶች ምን ማለት ይቻላል? በሃይማኖት ስም የሚደረጉትን ብዙ ነገሮች አምላክ አይቀበላቸውም ቢባል ምናልባት ሳትስማማ አትቀርም። አሁን በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት በተረፉባቸው በቅርቡ በተደረጉት የዓለም ጦርነቶች ወቅት በሁለቱም ወገኖች የነበሩት ሃይማኖቶች ሕዝቦቻቸውን ግደሉ እያሉ አደፋፍረዋቸዋል። “ጀርመኖችን ግደሉ፣ አይዞአችሁ ግደሉአቸው” ሲሉ የለንደኑ አቡን ተናግረው ነበር። በሌላው በኩል ደግሞ የኮሎኝ ሊቀ ጳጳስ ጀርመናውያንን፦ “ለአገራችሁ ክብር እስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ ድረስ ተዋጉ ብለን በእግዚአብሔር ስም እናዛችኋለን” ብለው ነበር።
8 ስለዚህ ካቶሊኮች ካቶሊኮችን ሲገድሉ፣ ፕሮቴስታንቶችም እንደዚያው ሲያደርጉ ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው አድራጎቱን ተቀብለውታል። ሐሪ ኢመርሰን ፎስዲክ የተባሉ አንድ ቄስ ሳይሸሽጉ እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል፦ “ሌላው ቀርቶ በቤተክርስቲያኖቻችን ላይ የጦርነት ባንዲራ አውለብልበናል . . . በአንደኛው የአፋችን ክፍል የሰላሙን መስፍን እያሞገስን በሌላው በኩል ጦርነትን አወድሰናል።” ታዲያ የአምላክን ፈቃድ አደርጋለሁ ብሎ እየተናገረ ለጦርነት ክብር ስለሚሰጥ ሃይማኖት አምላክ እንዴት የሚሰማው ይመስልሃል?
9. (ሀ) የተለያዩ ሃይማኖቶች አባሎች ስለፈጸሙት ግፍ ብዙ ሰዎች እንዴት ይሰማቸዋል? (ለ) አንድ ሃይማኖት ራሱን የዓለም ክፍል ካደረገ ምን ብለን መደምደም አለብን?
9 በታሪክ ዘመናት ሁሉ የብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች አባላት በአምላክ ስም በፈጸሙት ብዙ ግፍ የተነሳ ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአምላክና ከክርስቶስ ዘወር ብለዋል። ለምሳሌ በእስላሞችና በሒንዱዎች፣ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች፣ እንዲሁም የመስቀል ጦርነቶች ተብለው ለተጠሩት በካቶሊኮችና በእስላሞች መካከል ለተደረጉት ጦርነቶች አምላክን ተጠያቂ ያደርጉታል። በክርስቶስ ስም በአይሁዶች ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቃዋሚዎችን ለማፈን የተጠቀመችባቸውን አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊቶች እንደምሳሌ አድርገው ይጠቅሳሉ። ይሁንና ምንም እንኳን ለእነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶች ተጠያቂ የሚሆኑት የሃይማኖት መሪዎች አምላክ አባታችን ነው ቢሉም ኢየሱስ እንዳወገዛቸው ፈሪሳውያን እነርሱም የዲያብሎስ ልጆች አልነበሩምን? ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክ ስለሆነ የዓለም ሕዝቦች የሚከተሉአቸውንም ሃይማኖቶች እንደሚቆጣጠራቸው መጠበቅ አይገባንምን?—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራዕይ 12:9
10. አንተ የማትቀበላቸው በሃይማኖት ስም የሚደረጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
10 ዛሬ በሃይማኖት ስም የሚደረጉ ነገር ግን አንተ ትክክል ናቸው ብለህ የማትስማማባቸው ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። በጣም የተጨማለቀ የብልግና ኑሩ እየኖሩ የአብያተ ክርስቲያናት የተከበሩ አባላት የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ብዙ ጊዜ ትሰማ ይሆናል። እንዲያውም በጣም መጥፎ በሆነ መንገድ እየኖሩ የቤተክርስቲያናቸው ጥሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተደርገው የሚታዩ ቄሶችን ታውቅ ይሆናል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ወንድ ከወንድ ጋር ግንኙነት ማድረግና ሳያገቡ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት አይደለም ብለው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ ብሎ እንደማይናገር ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም አምላክ ሕዝቡ እስራኤላውያን እንደነዚህ ያሉ ድርጊቶችን በመፈጸማቸው በሞት እንዲቀጡ አድርጓል። በዚሁ ምክንያት ሰዶምንና ገሞራን ደምስሶአቸዋል። (ይሁዳ 7) በቅርቡም በዚህ ዘመን ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ እንደዚያው ያጠፋቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ሃይማኖቶች “ከምድር ነገሥታት” ጋር ስለሚባልጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንዲት አመንዝራ ተመስለዋል።—ራዕይ 17:1, 2, 16
አምላክ የሚቀበለው አምልኮ
11. አምልኮታችን በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ምን ይፈለግበታል?
11 አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ስለማይቀበል ‘አምላክ ደስ በሚሰኝበት መንገድ እያመለክሁት ነውን?’ ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል። በዚያ መንገድ እያመለክን መሆናችንን እንዴት ለማወቅ እንችላለን? እውነተኛ አምልኮ ምን እንደሆነ የሚወስነው አምላክ እንጂ ሰው አይደለም። ስለዚህ አምልኮታችን በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በአምላክ የእውነት ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ ሆኖ መመሥረት ይኖርበታል። አቋማችን “እያንዳንዱ ሰው ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ አምላክ እውነተኛ ሆኖ እንዲገኝ እንፍቀድ” ሲል እንደጻፈው እንደ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አቋም መሆን አለበት።—ሮም 3:3, 4 አዓት
12. ኢየሱስ የፈሪሳውያን ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?
12 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፈሪሳውያን እንደዚያ አልተሰማቸውም። የራሳቸውን እምነቶችና ወጎች መሥርተው ከአምላክ ቃል ይልቅ እነርሱን ተከተሉ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። “ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።” (ማቴዎስ 15:1-9፤ ኢሳይያስ 29:13) እንግዲያው አምላክ እንዲቀበለን ከፈለግን የምናምነው ነገር ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር መስማማቱን ማረጋገጥ ያስፈልገናል።
13. አምላክ እንዲቀበለን ኢየሱስ ምን ማድረግ አለባችሁ አለ?
13 በክርስቶስ እናምናለን ብለን እየተናገርን እኛ ትክክል ነው ብለን የምናስበውን ማድረጋችን አይበቃም። በነገሩ ላይ የአምላክ ፈቃድ ምን መሆኑን ማወቃችን የግድ ያስፈልጋል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህንን አሳይቷል “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።”—ማቴዎስ 7:21
14.“በጐ ምግባር“ እየሠራን ብንሆንም ኢየሱስ ለምን እንደ “ዓመጸኞች“ ሊቆጥረን ይችላል?
14 እንግዲያው “በጐ ምግባሮች” ናቸው ብለን የምናምንባቸውን ነገሮች እያደረግን ይሆናል። ምናልባትም እነዚህን የምናደርገው በክርስቶስ ስም ይሆናል። ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ ሳናደርግ ከቀረን እነዚህ ሁሉ ዋጋ አይኖራቸውም። ክርስቶስ ቀጥሎ ከጠቀሳቸው ሰዎች ጋር እንመደባለን፦ “በዚያ ቀን ብዙዎች:- በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” (ማቴዎስ 7:22, 23) አዎን፣ እኛ ጥሩ ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እያደረግን ሊሆንና ሌሎች ሰዎችም በዚህ ምክንያት ሊያመሰግኑን እንዲያውም ሊያሞግሱን ይችላሉ። ይሁን እንጂ ትክክል ነው ብሎ አምላክ የተናገረውን እስካላደረግን ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ “ዓመፀኞች” አድርጎ ይቆጥረናል።
15. የጥንቶቹ የቤርያ ሰዎች የተከተሉት መንገድ እኛ ልንከተለው የሚገባን የጥበብ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው?
15 እንግዲህ ዛሬ ብዙ ሃይማኖቶች የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ስላልሆነ እኛ አባል የሆንንበት ሃይማኖታዊ ድርጅት የሚያስተምራቸው ነገሮች ከአምላክ ቃል ጋር ይስማማሉ በማለት በደፈናው ለመደምደም አንችልም። አንድ ሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሙ ብቻ ያ ሃይማኖት የሚያስተምራቸውና የሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገኘታቸውን አያረጋግጥም። ሁኔታው እንደዚያ መሆኑንና አለመሆኑን መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ቤርያ በተባለች ከተማ የነበሩት ሰዎች ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ከሰበከላቸው በኋላ እርሱ የሚነግራቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመራቸው ተመስግነዋል። (ሥራ 17:10, 11) በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማንኛውም መንገድ መስማማት ይኖርበታል። አንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተቀብሎ ሌላውን አልቀበልም ለማለት አይችልም።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ቅንነት ብቻውን በቂ አይደለም
16. አንድን ሰው አምላክ እንዲቀበለው ቅንነት ብቻ እንደማይበቃው ኢየሱስ እንዴት አሳየ?
16 ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፦ ‘አንድ ሰው በግሉ ለሚያምንባቸው ነገሮች ቅን ቢሆን የሚከተለው ሃይማኖት ስሕተት ከሆነ አምላክ አይቀበለውምን?’ እንግዲህ ‘ዓመጽ አድራጊዎች’ የሚሠሩት ነገር ትክክል ነው ብለው ቢያምኑበትም እንኳን ኢየሱስ እንደማይቀበላቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:22, 23) ስለዚህ ቅንነትም ቢሆን ብቻውን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። አንድ ጊዜ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” ብሎአቸዋል። (ዮሐንስ 16:2) እንደነዚህ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚገድሉ ሰዎች በዚህ አድራጎታቸው አምላክን እያገለገሉ እንዳሉ አድርገው በቅንነት ያምኑ ይሆናል፤ ነገር ግን እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ያደረጉትን አምላክ አይቀበለውም።
17. ጳውሎስ ቅን ቢሆንም እንኳን ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ምን አደረገ?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት እስጢፋኖስ ሲገደል ተባባሪ ሆኖ ነበር። ከዚያም ሌሎች ክርስቲያኖችን ለመግደል መንገድ ይፈልግ ነበር። (ሥራ 8:1፤ 9:1, 2) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፣ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።” (ገላትያ 1:13, 14) አዎን፣ ጳውሎስ ቅን ነበር፤ ቢሆንም ይህ ቅንነት ሃይማኖቱን ትክክለኛ አላደረገውም።
18. (ሀ) ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ ሃይማኖቱ ምን ነበር? (ለ) ጳውሎስና በዘመኑ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ሃይማኖታቸውን መለወጥ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
18 በዚያን ጊዜ ጳውሎስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አባል ነበር። ይህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ኢየሱስ ክርስቶስን አልቀበልም በማለቱ በአምላክ ዘንድ የተተወ ሆነ። (ሥራ 2:36, 40፤ ምሳሌ 14:12) ስለዚህ የአምላክን ተቀባይነት ለማግኘት ጳውሎስ ሃይማኖቱን መለወጥ አስፈለገው። በተጨማሪም ለአምላክ ቅንዓት ስለነበራቸው ስለ ሌሎች ሰዎች ጽፎአል። እነርሱ ቅን ነበሩ፤ ሆኖም ሃይማኖታቸው በአምላክ ዓላማዎች ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ስላልነበረ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም።—ሮም 10:2, 3
19. እውነት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አቅፎ ለመያዝ እንደማይችል የሚያሳየው ምንድን ነው?
19 እውነት ልዩ ልዩ የዓለም ሃይማኖቶች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች በሙሉ ለማቀፍ አይችልም። ለምሳሌ ሰዎች አካላቸው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለቻቸው አለዚያም የላቸውም። ምድር ለዘላለም ትኖራለች አለዚያም አትኖርም። አምላክ ክፋትን ያቆመዋል ወይም ደግሞ አያቆመውም። እነዚህና እነርሱን የመሳሰሉ ብዙ እምነቶች ወይ ትክክል አለዚያም ስህተት ናቸው። ሁለቱ የማይጣጣሙ ከሆኑ ሁለት ዓይነት እውነቶች ሊኖሩ አይችሉም። ከሁለት አንዳቸው እውነት ነው፤ ሁለቱ ግን እውነት ሊሆኑ አይችሉም። አንድ ነገር በእርግጥ ስህተት ከሆነ ያንን በቅንነት ማመኑና በሥራ ላይ ማዋሉ ትክክለኛ አያደርገውም።
20. በሃይማኖት ረገድ ትክክለኛውን “የመንገድ ካርታ“ ለመከተል የምንችለው እንዴት ነው?
20 አንተ የምታምነው ነገር ስህተት ለመሆኑ ማስረጃ ቢቀርብልህ እንዴት ሊሰማህ ይገባል? ለምሳሌ ያህል በመኪና ውስጥ ሆነህ ወደ አንድ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተጓዝክ ነው እንበል። የመንገዶች ካርታ አለህ፤ ነገር ግን ጊዜ ወስደህ በጥንቃቄ አልተመለከትከውም። አንድ ሰው በዚህ ሂድ ብሎህ ይሆናል። የነገረህ አቅጣጫ ትክክል ነው ብለህ በቅንነት በመቀበል እምነትህን በእርሱ ላይ ጥለሃል። ነገር ግን አቅጣጫው ትክክል አይደለም እንበል። አንድ ሰው መጥቶ ስህተትህን ቢያሳይህ ምን ታደርጋለህ? የራስህን ካርታ እያሳየ መንገድ እንደተሳሳትክ ቢነግርህስ? ኩራት ወይም እልህ መንገድ መሳሳትህን እንዳትቀበል ያደርግሃልን? እንግዲያውስ የራስህን መጽሐፍ ቅዱስ በመመርመር በተሳሳተ ሃይማኖታዊ መንገድ ላይ እየተጓዝክ መሆንህን ከተገነዘብክ ለመለወጥ ፈቃደኛ ሁን። ወደ ጥፋት ከሚወስደው መንገድ ተመለስ። ወደ ሕይወት በሚያመራው ጠባብ መንገድ ተጓዝ!
የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አስፈላጊ ነው
21. (ሀ) እውነትን ከማወቃችንም በተጨማሪ ምን ያስፈልገናል? (ለ) አንተ የምታደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች አምላክ እንደማይቀበላቸው ብታውቅ ምን ታደርጋለህ?
21 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ አምላክን በእውነት መንገድ ካላመለክኸው ይህ እውቀት ምንም ጥቅም የለውም። (ዮሐንስ 4:24) ዋጋ ያለው እውነትን በሥራ ላይ ማዋሉ፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉ ነው። “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ያዕቆብ 2:26) እንግዲያው ሃይማኖትህ አምላክን እንዲያስደስት ከተፈለገ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ በሥራ መተርጎም ይኖርበታል። ታዲያ አምላክ ስህተት ነው ብሎ የተናገረውን እያደረግህ መሆኑን ብታውቅ ለመለወጥ ፈቃደኛ ትሆናለህን?
22. እውነተኛውን ሃይማኖት ከተከተልን አሁንና ወደፊት ምን በረከቶችን አግኝተን ልንደሰት እንችላለን?
22 የአምላክን ፈቃድ ብታደርግ ከፊትህ ታላላቅ በረከቶች ይጠብቁሃል። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ትጠቀማለህ። እውነተኛውን ሃይማኖት ብትከተል የተሻልክ ሰው ትሆናለህ። የተሻልክ ወንድ፣ የተሻልክ ባል ወይም አባት፣ የተሻልሽ ሴት፣ የተሻልሽ ሚስት ወይም እናት፣ የተሻልክ ልጅ ትሆናለህ ወይም ትሆኚአለሽ። ይህ ሃይማኖትህ አምላካዊ ጠባዮችን እንድታፈራ ስለሚያደርግህ ትክክለኛውን ነገር በመሥራትህ ከሌሎች ጎልተህ ትታያለህ። ከዚህም ይበልጥ ግን ገነት በምትሆነው የአምላክ አዲስ ምድር ውስጥ ከሰላምና ከፍጹም ጤንነት ጋር የዘላለም ሕይወትን በረከቶች ለመቀበል ብቁ ትሆናለህ ማለት ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) ነገሩ ምንም አያጠያይቅም፤ የሃይማኖት ምርጫህ በእርግጥ ልዩነት ያመጣል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስን ለመግደል ይሞክሩ የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች አምላክን እያገለገሉ ነበርን?
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ጥፋት በሚወስደው መንገድ እየተጓዙ ናቸው ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። ወደ ሕይወት በሚያደርሰው ጠባብ መንገድ የሚጓዙት ግን ጥቂት ብቻ ናቸው
[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን . . . በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16
በቃል
በድርጊት
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃይማኖቱ ልዩ በመሆኑ የተነሳ ጳውሎስ ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር እሥጢፋኖስ ተወግሮ ሲገደል ተባባሪ ሆኗል
[በገጽ 33 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንገድ ብትሳሳት ኩራት ወይም እልህ ስህተትህን እንዳትቀበል ይከለክልህ ነበርን?