ምዕራፍ 18
“የዓለም መጨረሻ” ደርሷል!
1. የክርስቶስ ምድራዊ ተከታዮች እርሱ በሰማይ መግዛት መጀመሩን እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንንና መላእክቱን ከሰማይ አውጥቶ ሲጥላቸውና መንግሥታዊ ግዛቱን ሲጀምር የሰይጣንና የክፉ ሥርዓቱ ፍጻሜ ቀረበ ማለት ነበር። (ራዕይ 12:7-12) ይሁን እንጂ በምድር ያሉት የክርስቶስ ተከታዮች ይህ እነርሱ በዓይናቸው ሊያዩት የማይችሉት ሁኔታ በሰማይ ላይ እንደተፈጸመ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ እንደተገኘና “የዓለም መጨረሻ” እንደቀረበ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ማወቅ የሚችሉት ኢየሱስ የሰጠው “ምልክት” መፈጸሙን በመከታተል ነው።
2. የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምን ብለው ጠየቁት?
2 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ እያለ አራት ሐዋርያቱ “ምልክት” እንዲሰጣቸው ሊጠይቁት መጡ። በእንግሊዝኛው የኪንግ ጀምስ ቨርሽን ትርጉም መሠረት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥያቄውን እንደሚከተለው አንብበውታል:- “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?” (ማቴዎስ 24:3) ይሁን እንጂ “የመምጣትህ” እና “የዓለም መጨረሻ” የሚለው አነጋገር ትርጉም ምንድን ነው?
3. (ሀ) “የመምጣትህ” እና “የዓለም መጨረሻ” የሚሉት ቃላት ትክክለኛ ትርጉማቸው ምንድን ነው? (ለ) እንግዲያው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡት ጥያቄ በትክክል የሚተረጐመው እንዴት ነው?
3 እዚህ ላይ “የመምጣትህ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ፓሩስያ ሲሆን “መገኘት” ማለት ነው። እንግዲያው ክርስቶስ በዓይን ባይታይም እንኳ “ምልክቱ” ሲፈጸም በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ እንደተገኘ እናውቃለን ማለት ነው። “የዓለም መጨረሻ” የሚለው አነጋገርም ቢሆን በጣም የሚያሳስት ነው። ይህ አባባል የመሬት ፍጻሜ ማለት ሳይሆን የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንግዲያው የሐዋርያቱ ጥያቄ እንደሚከተለው ተብሎ በትክክል ሊነበብ ይችላል:- “ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ምልክትስ ምን ይሆናል?” — ማቴዎስ 24:3 አዲሲቱ ዓለም ትርጉም
4. (ሀ) ኢየሱስ የሰጠው “ምልክት” ምን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? (ለ) “ምልክቱ” ከጣት አሻራ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው በምን መንገድ ነው?
4 ኢየሱስ እንደ “ምልክት” አድርጎ አንድን የሚፈጸም ሁኔታ ብቻ አልጠቀሰም። የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮችንና ሁኔታዎችን ዘርዝሯል። ከማቴዎስ በተጨማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ‘የመጨረሻ ቀኖችን’ ለይተው የሚያሳውቁ ተጨማሪ ሁኔታዎች ጠቅሰዋል። እነዚህ አስቀድመው የተነገሩ ነገሮች ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “የመጨረሻ ቀኖች” ብለው በሚጠሩት ጊዜ ውስጥ ይፈጸማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4) እነዚህ የሚፈጸሙ ነገሮች በአንድ ሰው የጣት አሻራ ውስጥ እንዳሉ ልዩ ልዩ መስመሮች ናቸው። ማንም ሌላ ሰው የዚያ ዓይነት የጣት አሻራ ሊኖረው አይችልም። ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ የራሳቸው የሆኑ መለያ ምልክቶች ወይም ሁናቴዎች ይዘዋል። እነዚህ ምልክቶች አንድ ላይ ተዳምረው እንደ ጣት አሻራ ይሆናሉ። የትኛውም ሌላ ዘመን የዚህ ዓይነት “አሻራ” አይኖረውም።
5, 6. በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ስለ ‘መጨረሻው ቀን’ የሚገልጹ 11 ማስረጃዎችን ስትመረምር ስለ ‘ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን’ ምን ለመረዳት ትችላለህ?
5 በዚህኛው መጽሐፍ በምዕራፍ 16 ላይ ክርስቶስ በ1914 ስለመመለሱና በጠላቶቹ መካከል መግዛት ስለመጀመሩ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ተመልክተናል። አሁን ደግሞ የክርስቶስን መገኘትና የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” የሚያሳዩትን ተጨማሪ ‘የምልክቱ’ የተለያዩ ገጽታዎች በጥንቃቄ መርምራቸው። እነዚህን አስቀድሞ የተነገሩ ነገሮች በሚቀጥሉት አራት ገጾች ውስጥ በምትመረምርበት ጊዜ ከ1914 ጀምሮ እንዴት ሲፈጸሙ እንደቆዩ አስተውል።
“ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።”—ማቴዎስ 24:7
ይህ የምልክቱ ክፍል ከ1914 ጀምሮ ሲፈጸም መቆየቱን እንደተመለከትክ የተረጋገጠ ነው! በዚያ ዓመት አንደኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። በታሪክ ውስጥ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እንደዚህ ያለ አሰቃቂ ጦርነት ታይቶ አያውቅም ነበር። አጠቃላይ የሆነ ጦርነት ነበር። አንደኛው የዓለም ጦርነት ከ1914 በፊት በነበሩት 2, 400 ዓመታት ውስጥ ከተደረጉት ከፍተኛ ጦርነቶች ሁሉ እጅግ በጣም የሚበልጥ ነበር። ሆኖም ይህ ጦርነት ካበቃ ከ21 ዓመታት በኋላ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረ። እርሱም ያስከተለው ጥፋት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በአራት እጥፍ ይበልጣል።
አሰቃቂ ጦርነቶች መደረጋቸውን ቀጥለዋል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ካበቃ በኋላ በዓለም ዙሪያ በተደረጉ 150 ጦርነቶች ከ25 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። በእያንዳንዱ ቀን በዓለም ላይ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በአማካይ 12 ጦርነቶች ይደረጋሉ። እንዲሁም ሌላ የዓለም ጦርነት ይነሣል የሚል የማያቋርጥ ስጋት አለ። ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በምድር ላይ የሚገኙትን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በሙሉ ከ12 ጊዜ በላይ ሊያጠፉ የሚችሉ በቂ የኑክሌር መሣሪያዎች አሏት!
“ራብም (የምግብ እጥረትም) . . . ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:7
አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ረሀብ መጣ። በሰሜናዊ ቻይና ውስጥ ብቻ በምግብ ማጣት ምክንያት በየዕለቱ 15, 000 ሰዎች ይሞቱ ነበር። ይሁን እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምግብ እጥረቱ ከዚያ የከፋ ነበር። በዚያን ጊዜ የምድር አንድ አራተኛ ሕዝብ ተርቦ ነበር! ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምድር ላይ ለሚገኙት ብዙ ሰዎች ምግብ ማግኘቱ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።
“ባላደጉት አገሮች ውስጥ በየ8.6 ሴኮንዶች አንድ ሰው ተመጣጣኝ ምግብ ካለማግኘት በሚመጣ በሽታ ይሞታል” በማለት በ1967 የወጣው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ገልጿል። አሁንም በሚልዮን የሚቆጠሩ ይኸውም በየዓመቱ 50 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በከባድ ረሐብ ይሞታሉ! በ1980 የምድር ሩብ ሕዝብ (1, 000, 000, 000 ሰዎች) በቂ ምግብ ለማግኘት ባለመቻላቸው የተነሳ ተርበው ነበር። ምግብ ተትረፍርፎ በሚገኝባቸው ቦታዎችም ቢሆን ብዙዎቹ በጣም ድሀ ስለሆኑ ለመግዛት አቅም የላቸውም።
“በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር (ወረርሽኝ በሽታ) . . . ይሆናል።”—ሉቃስ 21:11
አንደኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ወዲያው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከታዩት በየትኛውም ወረርሽኝ በሽታዎች ከሞቱት የሚበልጡ ሰዎች በስፓንሽ ፍሉ (በሕዳር በሽታ) ረግፈዋል። በጠቅላላው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 21 ሚልዮን ያህል ነበር! ሆኖም ቸነፈርና በሽታ ሰውን ማጥቃታቸውን ቀጥለዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ በልብና በካንሰር በሽታ ይሞታሉ። የአባለዘር በሽታም በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። እንደ ወባ፣ ቢልሃርዝያ፣ የሚያሳውር በሽታ የመሳሰሉት በየአገሩ በተለይም በእስያ፣ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ እየተስፋፉ ነው።
“የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:7
ከ1914 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በታሪክ ተመዝግቦ በሚገኝ በየትኛውም ዘመን ከደረሰው በጣም ብዙ ጊዜ የሚበልጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደርሷል። ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ይኸውም ከ856 እዘአ ጀምሮ እስከ 1914 ድረስ የ1, 973, 000 ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ 24 ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰው ነበር። ከ1915 እስከ 1978 ድረስ ባሉት 63 ዓመታት ውስጥ ግን በ43 ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች በጠቅላላው 1, 600, 000 የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል።
“የዓመፅ ብዛት”—ማቴዎስ 24:12
ከመላው ዓለም ዓመፅና ወንጀል እየጨመሩ መሆናቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ይመጣሉ። እንደ መግደል፣ ሴትን አስገድዶ ማስነወርና ዝርፊያ የመሳሰሉት የዓመፅ ወንጀሎች በአሁኑ ጊዜ በጣም በዝተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየሴኮንዱ በአማካይ አንድ ከባድ ወንጀል ይፈጸማል። በብዙ ቦታዎች ማንም ሰው በቀንም እንኳ ቢሆን በመንገድ ላይ ተማምኖ አይጓዝም። ማታ ማታ ሰዎች ወደ ውጭ ለመውጣት በመፍራት በተቆለፉና በተቀረቀሩ ቤቶች ውስጥ ይቀመጣሉ።
“ሰዎች በፍርሃት ይዝላሉ።”—ሉቃስ 21:26 አዓት
በዛሬው ጊዜ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለው ትልቁ ስሜት ምናልባት ፍርሃት ሳይሆን አይቀርም። የመጀመሪያዎቹ የኑክሌር ቦምቦች ከፈነዱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአቶሚክ ሳይንቲስት የሆኑት ሐሮልድ ሲ ኡሬይ:- “ወደፊት ፍርሃትን እንበላለን፣ በፍርሃት እንተኛለን፣ በፍርሃት እንኖራለን፣ በፍርሃትም እንሞታለን” ብለው ነበር። የብዙ ሰዎች ሁኔታ ልክ እንደዚህ ነው። ይህም ፍርሃት ምን ጊዜም አሳሳቢ በሆነው የኑክሌር ጦርነት ሥጋት ብቻ የመጣ አይደለም። ሰዎች ወንጀልን፣ የአካባቢ መበከልን፣ በሽታን፣ የዋጋ መናርንና ደኅንነታቸውንና ሕይወታቸውን ስጋት ላይ የሚጥሉ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ይፈራሉ።
‘ለወላጆች አለመታዘዝ’—2 ጢሞቴዎስ 3:2
በዛሬው ጊዜ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያላቸው ሥልጣን በጣም ትንሽ ነው። ወጣቶች በሁሉም ዓይነት ሥልጣን ላይ ያምፃሉ። ስለዚህም በምድር የሚገኝ የትኛውም አገር በወጣቶች ወንጀል ተወሯል። በአንዳንድ አገሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ከባድ ወንጀሎች የሚፈጽሙት ከ10 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ናቸው። ግድያ፣ ሴቶችን አስገድዶ ማስነወር፣ ጥቃት ማድረስ፣ ቅሚያ፣ ዝርፊያ፣ የመኪና ስርቆት የመሳሰሉትን ነገሮች ሁሉ ልጆች ይፈጽማሉ። በታሪክ ውስጥ ለወላጆች አለመታዘዝ ይህንን ያህል የተስፋፋበት ጊዜ በፍጹም የለም።
“ገንዘብን የሚወዱ”—2 ጢሞቴዎስ 3:2
ዛሬ በየትም ቦታ ስግብግብነትን ልትመለከት ትችላለህ። ብዙዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ይሰርቃሉ ወይም ይገድላሉ። ስግብግብ የሆኑ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌሎችን በሽታ ላይ ሊጥሉ ወይም ሊገድሉ እንደሚችሉ የታወቁትን ነገሮች የሚያመርቱና የሚሸጡ መሆናቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ሰዎች ገንዘብ ‘አምላኬ ነው’ በማለት በግልጽ ወይም በአኗኗራቸው ሁኔታ ይናገራሉ።
“ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ”—2 ጢሞቴዎስ 3:4
በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን የሚያስደስተውን ሳይሆን ራሳቸውን ወይም ቤተሰቦቻቸውን የሚያስደስተውን ነገር ብቻ ስለማድረግ ያስባሉ። ብዙዎቹ በተለይ አምላክ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ይኸውም ዝሙትን፣ ምንዝርን፣ ስካርን፣ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድንና ደስታ ያመጣሉ የሚባሉ ሌሎች ነገሮችን ይወዳሉ። ንጹሕ ሆነው ደስታ የሚያመጡ ነገሮችም ቢሆኑ ስለ አምላክ ከመማርና እርሱን ከማገልገል ይልቅ እነርሱ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
“የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:5
የዓለም መሪዎችም ሆኑ ተራው ሕዝብ አምላክን የሚወዱ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ። ምናልባት በቤተክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይገኙ ይሆናል። ለሃይማኖታዊ ጉዳዮችም መዋጮዎችን ይሰጡ ይሆናል። የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሥልጣናቸውን ሲቀበሉ እጃቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አድርገው ቃለ መሐላ ይፈጽሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ አብዛኛውን ጊዜ “የአምልኮት መልክ” ብቻ ነው። ልክ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው እውነተኛው የአምላክ አምልኮት በዛሬው ጊዜ በብዙዎቹ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያንቀሳቅስ ኃይል አይደለም። ጥሩ ነገር ለማድረግ በሚገፋፋ ኃይል አይመሩም።
‘ምድርን ማበላሸት’—ራዕይ 11:18
የምንተነፍሰው አየር፣ የምንጠጣው ውሃና ምግባችን የሚበቅልበት ምድር ተበክሏል። ሁኔታው በጣም አሳሳቢ በመሆኑም ሳይንቲስቱ ባሪ ኮሞነር እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል:- “ያለ ዕረፍት ምድርን ማቆሸሹ ካልተገታ በስተቀር ፕላኔታችን የሰው መኖሪያ መሆን ወደማትችልበት ደረጃ ትደርሳለች ብዬ አምናለሁ።”
6 ከዚህ በላይ ያለውን ከተመለከትክ በኋላ ክርስቶስ የሰጠው “ምልክት” እና ደቀ መዛሙርቱ የተነበዩአቸው ማስረጃዎች አሁን እየተፈጸሙ እንዳሉ ግልጽ አልሆነልህምን? ሌሎች ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻ ቀኖች” ብሎ በተነበየለት ጊዜ ውስጥ በእርግጥ እንደምንኖር ለማሳየት እዚህ ላይ የተዘረዘሩት ነገሮች በቂ ናቸው።
7. (ሀ) ስለ ክርስቶስ መገኘትና ስለ “መጨረሻ ቀኖች” የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጣም ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ይመጣል ሲል አስቀድሞ ከተናገረው ተቃራኒ ከ1914 በፊት የዓለም መሪዎች ምን ይመጣል ይሉ ነበር?
7 ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ‘እንደ ጦርነት፣ ረሃብ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ ያሉት ነገሮች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሲፈጸሙ ኖረዋል፤ ስለዚህ እነዚህ እንደገና ይፈጸማሉ ብሎ ትንቢት መናገሩ አስቸጋሪ አይሆንም’ ይሉ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ነገር አስብ:- መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ነገሮች እንደሚደርሱ አስቀድሞ ከመናገሩም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚፈጸሙ ጭምር አመልክቷል። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በ1914 በሕይወት በነበረው ትውልድ ላይ እንደሚደርሱ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ከ1914 በፊት የነበሩ የታወቁ የዓለም መሪዎች ወደፊት ምን ይመጣል ብለው ሲናገሩ ነበር? ለዓለም ሰላም እንደ አሁኑ ጊዜ አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረው አያውቁም እያሉ ሲናገሩ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የተነበያቸው አሰቃቂ ችግሮች ጊዜያቸውን ጠብቀው ልክ በ1914 ጀመሩ! እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ የዓለም መሪዎች 1914 በታሪክ ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
8. (ሀ) ኢየሱስ የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እንደሚያይ የተናገረለት ትውልድ የትኛው ነው? (ለ) እንግዲያው ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን?
8 ከ1914 ወዲህ ያለውን ዘመን ልዩ በሚያደርጉት ነገሮች ላይ ካተኮረ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ይህ ሁሉ [የዚህ ሥርዓት ፍጻሜም ጭምር] እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።” (ማቴዎስ 24:34, 14) ኢየሱስ የትኛውን ትውልድ ማለቱ ነበር? በ1914 በሕይወት የነበሩትን ሰዎች ትውልድ ማለቱ ነበር። ከዚያ ትውልድ ውስጥ በሕይወት የቀሩት ሰዎች በጣም አርጅተዋል። ይሁን እንጂ ከእነርሱ ውስጥ አንዳንዶቹ የዚህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ለማየት በሕይወት ይቆያሉ። እንግዲያው ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን:- በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክፋት ሁሉና ክፉ ሰዎች ድንገተኛ ፍጻሜያቸው በአርማጌዶን ላይ ይመጣል።
[በገጽ 149 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የመንግሥት ሥልጣኑን ከዓይን በተሰወረ መንገድ መያዙን የሚያሳውቁ የሚታዩ ማስረጃዎች ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል
[በገጽ 154 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1914—አርማጌዶን
በ1914 ከነበረው ትውልድ ውስጥ አንዳንዶቹ ሰዎች የነገሮችን ሥርዓት ፍጻሜ ያያሉ፤ በሕይወትም ያልፉታል