ማርያም (የኢየሱስ እናት)
ፍቺ:- በመለኮታዊ ምርጫ ኢየሱስን የወለደች ከፍተኛ ሞገስ ያገኘች ሴት ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማርያም የተባሉ አምስት ሌሎች ሴቶች ተጠቅሰዋል። ይህችኛዋ ማርያም ከይሁዳ ነገድ የሆነች፣ የንጉሥ ዳዊት ተወላጅ፣ የኤሊ ልጅ ናት። ቅዱስ ጽሑፉ እሷን የሚያስተዋውቀን ለዮሴፍ ታጭታ እንደነበረ በመግለጽ ነው። እርሱም ከይሁዳ ነገድ የሆነና የዳዊት ተወላጅ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም ከሚናገረው ምን ልንማር እንችላለን?
(1) አምላክ በመልእክተኞቹ በኩል የሚነግረን ነገር መጀመሪያ ላይ የሚከብድ ወይም የማይቻል መስሎ ቢታይም ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ ስለመሆኑ ትምህርት እናገኛለን።—ሉቃስ 1:26–37
(2) አንድ ነገር የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ከተነገረን በድፍረትና ሙሉ በሙሉ በአምላክ በመተማመን ያንን ነገር ስለመፈጸም። (ሉቃስ 1:38ን ተመልከት። በዘዳግም 22:23, 24 ላይ እንደተገለጸው አንዲት ያላገባች አይሁዳዊት ልጃገረድ አርግዛ ብትገኝ ከባድ ቅጣት ይደርስባት ነበር።)
(3) አንድ ሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ቦታ ትንሽም ይሁን ትልቅ አምላክ ሊጠቀምበት የሚችል ስለመሆኑ።—ሉቃስ 2:22–24ን ከዘሌዋውያን 12:1–8 ጋር አወዳድር።
(4) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የላቀ ቦታ ስለመስጠት። (ሉቃስ 2:41፤ ሥራ 1:14። አይሁዳውያን ሚስቶች ባሎቻቸው ለማለፍ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ረጅም ጉዞ ሲያደርጉ አብረዋቸው የመሄድ ግዴታ አልነበረባቸውም። ማርያም ግን አብራ ሄዳለች።)
(5) የሥነ ምግባር ንጽሕናን ስለመውደድ።—ሉቃስ 1:34
(6) የአምላክን ቃል በትጋት ለልጆች ስለማስተማር። (ይህም ኢየሱስ በ12 ዓመቱ ባደረገው ነገር ታይቷል። ሉቃስ 2:42, 46–49ን ተመልከት።)
ማርያም ኢየሱስን ስትወልድ በእውነት ድንግል ነበረችን?
ሉቃስ 1:26–31:- መልአኩ ገብርኤል:- “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” በማለት ያበሰረው ማርያም ለተባለች “አንዲት ድንግል” ነበር። ቁጥር 34 “ማርያምም መልአኩን:- ወንድ ስለማላውቅ [“እኔ ድንግል ነኝ” የ1980 ትርጉም፤ “ከወንድ ጋር ሩካቤ ሥጋ ሳልፈጽም” አዓት ] ይህ እንዴት ይሆናል?” ብላ እንደጠየቀችው ይገልጻል። ማቴዎስ 1:22–25 እንዲህ ሲል ጨምሮ ይገልጻል:- “በነቢይ ከጌታ ዘንድ:- እነሆ፣ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፣ ትርጓሜውም:- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።”
ታዲያ ይህ ምክንያታዊ ነውን? የሰውን ልጅ የመራቢያ አካል የሠራ ፈጣሪ ከሰው ችሎታ በላይ በሆነ መንገድ በማርያም ማኅፀን ውስጥ አንድ የእንቁላል ሴል እንዲያድግ ማድረግ ፈጽሞ አያስቸግረውም። ይሖዋ በሰማይ የሚኖረውን የበኩር ልጁን የሕይወት ኃይልና ባሕርያት በተአምር ወደ ማርያም ማኅፀን አዛወረው። በማርያም ማኅፀን ውስጥ የነበረው ፅንስ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነው መንፈስ ቅዱስ እድገቱን ይከታተል ነበር።—ሉቃስ 1:35፤ ዮሐ. 17:5
ማርያም ዕድሜዋን በሙሉ ድንግል ሆና ኖራለችን?
ማቴ. 13:53–56:- “ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ:- ይህን ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ [በግሪክኛ አደልፎይ ] ያዕቆብና ዮሳ፣ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ [በግሪክኛ አደልፋይ ] ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” (በዚህ ጥቅስ መሠረት የማርያም ልጅ ኢየሱስ ብቻ ነበር ብለህ ትደመድማለህ ወይስ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆች ነበሯት?)
በማቴዎስ 13:55, 56 ላይ የተሠራባቸውን አደልፎይ እና አደልፋይ የተባሉትን የግሪክኛ ቃሎች አስመልክቶ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967፣ ጥራዝ 9፣ ገጽ 337) እንዲህ ይላል:- “በወንጌላውያን ዘመን ግሪክኛ ተናጋሪ በነበረው ዓለም እነዚህ ቃሎች ሙሉ የሥጋ ወንድምነትንና እህትነትን የሚያመለክት ትርጉም ነበራቸው፤ ግሪክኛ አንባቢዎችም የተረዷቸው በዚህ ትርጉም ነበር። በ4ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ (እዘአ በ380 ገደማ) ሄልቪዲየስ የተባለ ሰው በአንድ አሁን በማይገኝ ጽሑፍ ውስጥ ማርያም ብዙ ቤተሰብ ላላቸው እናቶች ምሳሌ እንደምትሆን ሲገልጽ ከኢየሱስ ሌላ ሌሎች ልጆች እንደነበሯት ጽፏል። ቅዱስ ጀሮም ማርያም ለዘላለም ድንግል ሆና ኖራለች በሚለው የቤተ ክርስቲያን ልማዳዊ እምነት በመገፋፋት ሄልቪዲየስን የሚቃወም (እዘአ በ383) ጽሑፍ ጽፎ ነበር። . . . ይህም ማብራሪያ እስከ ዛሬ ድረስ በካቶሊክ ምሁራን ዘንድ በጣም የታወቀ ነው።”
ማር. 3:31–35:- “እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና:- እነሆ፣ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። መልሶም:- እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። በዙሪያው ተቀምጠው ወደነበሩትም ተመለከተና:- እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ ነው፣ እኅቴም እናቴም አለ።” (እዚህ ላይ በኢየሱስ የሥጋ ወንድሞችና መንፈሳዊ ወንድሞች ማለትም በደቀ መዛሙርቱ መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እናያለን። የኢየሱስ እናት ተብላ የተጠቀሰችው እናቱ ሳትሆን ሌላ ሴት ነች የሚል ሰው ሊኖር አይችልም። ታዲያ የሥጋ ወንድሞቹን የአክስቱ ወይም የአጎት ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ሰበብ ማቅረብ ከዚህ ጋር ይስማማልን? ስለ ወንድሞች ሳይሆን ስለ ዘመዶች ሲናገር የተጠቀመበት ሌላ ቃል [ሲጌኖን ] በሉቃስ 21:16 ላይ ይገኛል።)
ማርያም የእግዚአብሔር እናት ነበረችን?
ማርያም በተአምር እንደምትወልድ የነገራት መልአክ የሚወለደው ልጅሽ እግዚአብሔር ይሆናል አላላትም። መልአኩ ያላት እንዲህ ነበር:- “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ . . . ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።”—ሉቃስ 1:31–35፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ዕብ. 2:14, 17:- “ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ [ኢየሱስ] . . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። . . . በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።” (ኢየሱስ አምላክም ሰውም ቢሆን ኖሮ “በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል” ይችል ነበርን?)
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “ሁለት ነገሮች ከተሟሉ ማርያም በትክክል የእግዚአብሔር እናት ትሆናለች። ይኸውም ማርያም በእውነት የኢየሱስ እናት ከሆነችና ኢየሱስም በእርግጥ እግዚአብሔር ከሆነ ነው።” (1967፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 21) መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም የኢየሱስ እናት እንደሆነች ይናገራል። ነገር ግን ኢየሱስ እግዚአብሔር ነበርን? ቤተ ክርስቲያን የሥላሴን ትምህርት የፈጠረችው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ በኋላ ብዙ ቆይቶ በአራተኛው መቶ ዘመን ነበር። (ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1967፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 295፤ በገጽ 404 ላይ “ሥላሴ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።) በኒቂያ ጉባኤ፣ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን “ፍጹም አምላክ” ብላ ጠራችው። ከዚያ በኋላ በ431 እዘአ በተደረገው የኤፌሶን ጉባኤ ማርያም ቲዎቶኮስ ማለትም “ወላዲተ አምላክ” ወይም “የአምላክ እናት” ተብላ እንድትጠራ ቤተ ክርስቲያን አወጀች። ይሁን እንጂ ይህ አጠራርም ሆነ ሐሳቡ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ አይገኝም። (በገጽ 213–217 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ” በሚለው ሥር ተመልከት።)
ማርያም በተፀነሰችበት ጊዜ ንጽሕትና የአዳም ኃጢአት ያልነበረባት ነበረችን?
የዚህን እምነት አጀማመር አስመልክቶ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967፣ ጥራዝ 7፣ ገጽ 378–381) እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ . . . ቅዱስ ጽሑፉ ማርያም በተፀነሰችበት ጊዜ ከማንኛውም ኃጢአት ንጹሕ እንደነበረች አያስተምርም። . . . የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ማርያምን ቅዱስ አድርገው ይመለከቷትት ነበር እንጂ ከኃጢአት ፈጽማ የነጻች እንደሆነች አድርገው አይመለከቱም ነበር። . . . ይህ እምነት የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ክፍል የሆነው መቼ እንደሆነ በትክክል ማወቅ ባይቻልም በ8ኛው ወይም በ9ኛ መቶ ዘመን አጠቃላይ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ይመስላል። . . . [በ1854 ሊቀ ጳጳስ ፓየስ 9ኛ] ‘ቅድስት ድንግል ማርያም ከተፀነሰችበት ቅጽበት ጀምሮ ከመጀመሪያው አዳማዊ ኃጢአት ተጠብቃ ነበር’ የሚለውን ቀኖናዊ ትምህርት አቀረቡ።” ይህ እምነት በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ (1962–1965) በድጋሚ ጸድቋል።—ዘ ዶኩሜንትስ ኦቭ ቫቲካን 2 (ኒው ዮርክ፣ 1966)፣ በደብልዩ ኤም አቦት የተዘጋጀ፣ ገጽ 88
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:12፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ታዲያ ይህ ማርያምን ይጨምራልን? ማርያም የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት ኢየሱስን ከወለደች በኋላ ከርኩሰት ለመንጻት በኢየሩሳሌም የኃጢአት መሥዋዕት አቅርባለች። እርሷም ከአዳም ኃጢአትና አለፍጽምና ወርሳ ነበር።—ሉቃስ 2:22–24፤ ዘሌ. 12:1–8
ማርያም ከነሥጋዊ አካሏ ወደ ሰማይ አርጋለችን?
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 972) ሊቀ ጳጳስ ፓየስ 12ኛ ይህንን ቀኖናዊ ትምህርት የካቶሊክ እምነት ክፍል እንዲሆን በመደንገግ ስላወጡት አዋጅ አስተያየት ሲሰጥ:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ማርያም እርገት የሚናገር ግልጽ ማስረጃ የለም። ቢሆንም ሊቀ ጳጳሱ ስለዚህ ቀኖና ባወጡት አዋጅ ላይ ይህ እውነት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አጥብቀው ገልጸዋል” ይላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንዲህ ይላል:- “ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።” (1 ቆሮ. 15:50) ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ብሏል። እርሱም ከሙታን በተነሣ ጊዜ መንፈስ፣ እንዲያውም “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ” ሆኗል። መላእክት መናፍስት ናቸው። (ዮሐ. 4:24፤ 1 ቆሮ. 15:45፤ ዕብ. 1:13, 14) በምድር አካባቢ ብቻ በሚገኙ ነገሮች ተጠብቆ ሊኖር የሚችል ሥጋዊ አካል ይዞ ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል የሚያመለክት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሚሆነን ምንድን ነው? (በገጽ 333–336 ላይ “ትንሣኤ” በሚለው ሥር ተመልከት።)
አማላጃችን ማርያም ሆይ፤ ብሎ መጸለይ ተገቢ ነውን?
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ . . .” በተጨማሪም እንዲህ ብሏል:- “እኔ መንገድና፣ እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። . . . ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።”—ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 14:6, 14፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአብ የሚቀርቡ ጸሎቶች የሴትነትን ችግሮች በቀመሰችው በማርያም በኩል ቢቀርቡ የሚያገኙትን ያህል የሐዘኔታና የርኅራኄ መልስ ያገኛሉን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ እንዲህ ይላል:- “አባት ለልጆቹ የሚራራላቸውን ያህል፣ እግዚአብሔር የሚፈሩትን ይራራላቸዋል፤ እግዚአብሔር ከምን እንደተፈጠርን ያውቃል፤ አፈር መሆናችንንም ያስታውሳል።” “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው [“ይቅር ባይ” የ1980 ትርጉም ] ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” ነው። (መዝ. 103:13, 14 የ1980 ትርጉም ፤ ዘጸ. 34:6) ስለ ክርስቶስም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል:- “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”—ዕብ. 4:15, 16
የማርያምን ምስል ቅዱስ አድርጎ ማክበር ከመጽሐፍ ቅዱሱ ክርስትና ጋር ይስማማልን?
ይህንን አድራጎት 2ኛው የቫቲካን ጉባኤ (1962–1965) በሚገባ ደግፎታል። “ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ . . . በተለይ የቅድስት ማርያም ሥርዓተ አምልኮ በሚገባ እንዲስፋፋ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች በሙሉ ያሳስባል። ሲኖዶሱ የቤተ ክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ባለፉት መቶ ዘመናት እንዳሳሰቡት ለማርያም የሚሰጠው አምልኮ ከፍ ተደርጎ እንዲያዝና እንዲሁም ቀደም ባሉት ዘመናት የክርስቶስን፣ የቅድስት ማርያምንና የቅዱሳንን ምስሎች ቅዱስ አድርጎ ስለመመልከት የወጡት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ያዝዛል።”— ዘ ዶኩሜንትስ ኦቭ ቫቲካን 2፣ ገጽ 94, 95
ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ በገጽ 183–187 “ምስሎች” በሚለው ሥር ተመልከት።
በአንደኛው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ለማርያም ልዩ አክብሮት ሰጥቷት ነበርን?
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ተነሣሥቶ በጻፋቸው ጽሑፎች ውስጥ ስለማርያም የተናገረው ነገር የለም። ሐዋርያው ጳውሎስም በመንፈስ ተነሳስቶ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ስሟን ሳይጠቅስ “ሴት” በማለት ብቻ ተናግሯል።—ገላ. 4:4
ኢየሱስ ለእናቱ በተጠቀመበት አጠራር ምን ምሳሌ ትቶልናል?
ዮሐ. 2:3, 4:- “[በቃና በተደረገው የሠርግ ድግስ ላይ] የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት:- የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም:- አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።” (ኢየሱስ ልጅ ሳለ ለእናቱና ለአሳዳጊ አባቱ ይታዘዝ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ሙሉ ሰው ስለ ነበር በማርያም ፈቃድ የማይመራ መሆኑን በደግነትና ጥብቅ በሆነ አነጋገር ገልጾላታል። እርሷም እርማቱን በትሕትና ተቀብላለች።)
ሉቃስ 11:27, 28:- “[ኢየሱስ] ይህንም ሲናገር፣ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ:- የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። እርሱ ግን:- አዎን፣ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ።” (ለማርያም የተለየ አክብሮት መስጠት የሚገባ ቢሆን ኖሮ ይህ ለኢየሱስ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነበር። እሱ ግን እንዲህ አላደረገም።)
ለማርያም አክብሮት መስጠት የተጀመረበት ታሪካዊ አመጣጥ ምንድን ነው?
አንድሩ ግሪሌይ የተባሉት የካቶሊክ ቄስ እንዲህ ይላሉ:- “በምዕራቡ ዓለም ታሪክ ውስጥ በጣም ጠንካራ ከሆኑት ሃይማኖታዊ ምልክቶች አንዷ ማርያም ናት። . . . የማርያም አምልኮ ክርስትናን በቀጥታ ከጥንቶቹ የእናት እንስት አማልክት ሃይማኖቶች ጋር ይያያዛል።”—ዘ ሜኪንግ ኦቭ ዘ ፖፕስ 1978 (ዩ ኤስ ኤ፣ 1979)፣ ገጽ 227
ማርያም የአምላክ እናት ናት የሚለው ትምህርት የጸደቀበት ቦታ ራሱ የሚያስገርም ነው። “የኤፌሶን ጉባኤ በ431 በቲዎቶኮስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰብስቦ ነበር። በዚህች በአርጤሚስ ወይም እንደ ሮማውያን አጠራር ዳያና በተባለች ሴት አምላክ አምልኮ ከፍተኛ ዝና ባተረፈችው የኤፌሶን ከተማና የአርጤምስ ምስል ከሰማይ ወረደ በሚባልበትና በአፈ ታሪክ የማርያም ጊዜያዊ መኖሪያ ነበር በሚባለው በዚህ ቦታ ‘ወላዲተ አምላክ’ የሚለው የማዕረግ ስም ተቀባይነት ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነበር።”—ዘ ከልት ኦቭ ዘ ማዘር ጎደስ (የእናት እንስት አምላክ አምልኮ) (ኒው ዮርክ፣ 1959)፣ ኢ ኦ ጄምስ፣ ገጽ 207
አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-
‘በድንግል ማርያም ታምናላችሁ?’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል እንደነበረች በግልጽ ይናገራል፤ እኛም ይህን እናምናለን። የኢየሱስ አባት አምላክ ነበር። መልአኩ ለማርያም በትክክል እንደነገራት የተወለደው ሕፃን የአምላክ ልጅ ነበር። (ሉቃስ 1:35)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከማርያም እንዲወለድ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ አስበው ያውቃሉ? . . . ከኃጢአትና ከሞት ነጻ ሊያወጣ የሚችል ትክክለኛ ቤዛ ሊገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ስለነበረ ነው።—1 ጢሞ. 2:5, 6፤ ምናልባትም ዮሐንስ 3:16ን መጨመር ይቻላል።’
ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘አዎ፣ እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም የሚናገረውን ነገር ሁሉ እናምናለን። ኢየሱስን በድንግልና እንደወለደች መጽሐፍ ቅዱስ በማያወላውል መንገድ ይገልጻል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያምና ከሷ ልንማራቸው ስለሚገቡ ነገሮች የሰጠው መግለጫ ደስ የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ። (በገጽ 254 ላይ በሰፈረው ሐሳብ ተጠቀም።)’
‘እናንተ በድንግል ማርያም አታምኑም’
እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የአምላክን ልጅ የወለደችው ድንግል እንደነበረች የማያምኑ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። እኛ ግን እናምናለን። (ስለዚህ ጉዳይ ከሚናገሩት መጽሐፎቻችን መካከል አንዱን አውጣና ለቤቱ ባለቤት አሳይ።)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ ለመዳን ከፈለግን ከኛ የሚፈለግ ተጨማሪ ነገር የሚኖር አይመስልዎትም? . . . ኢየሱስ ለአባቱ በጸለየበት ጊዜ የተናገረውን ልብ ይበሉ። (ዮሐ. 17:3)’