ደም ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነው
ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ ሊያሳስብህ እንደሚገባ አያጠራጥርም። ምክንያቱም ደም ከሕይወትህ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነገር ነው። ደም ኦክስጅንን በመላው ሰውነትህ ያመላልሳል፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ደግሞ ያስወግዳል፣ ራስህን ከሙቀት ለውጦች ጋር እንድታስማማ ይረዳሃል፣ በተጨማሪም ከበሽታ ጋር በምታደርገው ውጊያ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል።
ሕይወት ከደም ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ያለው መሆኑ የተገለጸው ዊልያም ሃርቬ በ1628 የደምን ዝውውር ሥርዓት በንድፍ ከማስቀመጡ ከበርካታ ዓመታት በፊት ነው። የዋና ዋናዎቹ ሃይማኖቶች መሠረታዊ ግብረ ገብ በአንድ ሕይወት ሰጪ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ሕይወት ሰጪ ደግሞ ስለ ሕይወትና ደም ያለውን አመለካከት ገልጿል። አንድ ክርስቲያን የሆነ አይሁዳዊ የሕግ ሰው ስለዚህ አምላክ እንዲህ ብሏል:- “እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣል። በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን፣ እንኖርማለን።”a
እንዲህ ባለው ሕይወት ሰጪ የሚያምኑ ሁሉ እርሱ የሚሰጣቸው መመሪያዎች በሙሉ ለዘላቂ ደህንነታችን የሚበጁ እንደሆኑ ያምናሉ። አንድ ዕብራዊ ነቢይ ይህ ሕይወት ሰጪ ‘የሚረባንን ነገር የሚያስተምረንና በምንሄድበት መንገድ የሚመራን’ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ በኢሳይያስ 48:17 ላይ የሚገኘው መተማመኛ ሁላችንንም ሊጠቅሙ በሚችሉት የግብረ ገብ ሕግጋቱ በታወቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ታዲያ ይህ መጽሐፍ ስለ ደም አጠቃቀም ምን ይላል? ሕይወትን እንዴት በደም ማዳን እንደሚቻል ይናገራልን? መጽሐፍ ቅዱስ ደም በጣም ውስብስብ የሆነ ባዮሎጂያዊ ፈሳሽ ብቻ እንዳልሆነ ያመለክታል። ደምን ከ400 ለሚበልጡ ጊዜያት ሲጠቅስ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሕይወትን ስለማዳን የሚገልጹ ናቸው።
ቀደም ባሉት ዘመናት በተጻፈ አንድ ጥቅስ ላይ ፈጣሪ እንዲህ ብሏል:- “ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ። . . . ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ።” ቀጥሎም “ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ” ካለ በኋላ ነፍስ መግደልን አውግዟል። (ዘፍጥረት 9:3-6) ይህን የተናገረው አይሁዶች፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ከፍተኛ ከበሬታ ለሚሰጡት የጋራ አባታችን ለሆነው ለኖህ ነው። በዚህ መንገድ መላው የሰው ዘር በፈጣሪ አመለካከት ደም ሕይወትን የሚወክል እንደሆነ ተነግሮታል። ይህ የአመጋገብ ሥርዓትን ብቻ የሚመለከት ተራ ሕግ አልነበረም። ሥነ ምግባራዊ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓትን የሚመለከት እንደሆነ ግልጽ ነው። የሰው ደም ትልቅ ቦታ የተሰጠው ሲሆን ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ ሊሠራበት አይገባም። ቆየት ብሎ አምላክ ከደም ጋር ዝምድና ያላቸው ጥያቄዎች ሥነ ምግባርን የሚመለከቱ መሆናቸውን እንድንገነዘብ የሚያስችሉ ዝርዝር ሁኔታዎችን ገልጿል።
ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ሕግ በሰጠበትም ጊዜ ደምን በድጋሚ ጠቅሷል። በዚህ ሕግ ውስጥ የተንጸባረቀውን ጥበብና ግብረ ገብ በአክብሮት የሚመለከቱ ሰዎች በርካታ ቢሆኑም ስለ ደም የተሰጡትን ጠንካራ ሕጎች የተገነዘቡት ግን ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሚከተለው ሕግ ተሰጥቶ ነበር:- “ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፣ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ። የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና።” (ዘሌዋውያን 17:10, 11) ከዚያም ቀጥሎ አምላክ አንድ አዳኝ የገደለውን እንስሳ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ገለጸ። “ደሙን ያፈስሳል፣ በአፈርም ይከድነዋል። . . . የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ። የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ።”—ዘሌዋውያን 17:13, 14
የአይሁዳውያን ሕግ ለጤንነት ይጠቅም እንደነበረ የሳይንስ ሊቃውንት ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል እዳሪ ሲወጡ ከሰፈር ውጭ እንዲወጡና በአፈር እንዲከድኑት ያዝዝ ነበር። በተጨማሪም በሽታ አስተላላፊ የሆኑ የሥጋ ዓይነቶችን እንዳይበሉ ታዝዘው ነበር። (ዘሌዋውያን 11:4-8, 13፤ 17:15፤ ዘዳግም 23:12, 13) ስለ ደምም የተሰጠው ሕግ ጤንነትን የሚመለከት ገጽታ ቢኖረውም በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ደም ምሳሌያዊ ትርጉም ነበረው። ፈጣሪ የሰጠውን ሕይወት ይወክላል። ሕዝቡ ለደም ልዩ ዓይነት አያያዝ በማድረግ ሕይወታቸው የተመካው በፈጣሪ ላይ መሆኑን ያሳዩ ነበር። አዎን፣ ደም የማይወስዱበት ዋነኛ ምክንያት ጤንነታቸውን የሚጎዳ በመሆኑ ሳይሆን ለአምላክ ልዩ ትርጉም ያለው ነገር በመሆኑ ነበር።
ሕጉ ሕይወትን ለማቆየት ብሎ ደም መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ደንግጓል። “ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ። በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፣ አትብላው።”—ዘዳግም 12:23-25፤ 15:23፤ ዘሌዋውያን 7:26, 27፤ ሕዝቅኤል 33:25b
በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች በአደጋ ወቅት ይህን ሕግ መጣስ ይቻላል ብለው ቢያስቡም የአምላክ ሕግ ግን ይህን አይፈቅድም ነበር። እስራኤላውያን ወታደሮች በጦርነት ምክንያት በተፈጠረ አስቸጋሪ ሁኔታ ያረዷቸውን ከብቶች “ከደሙ ጋር በሉ።” እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ሥጋውን ከነደሙ በልተው ሕይወታቸውን እንዲያቆዩ ተፈቅዶላቸው ነበርን? በፍጹም አልተፈቀደላቸውም። ድርጊታቸው ከባድ ኃጢአት እንደሆነ የጦር አዛዣቸው ገልጾላቸዋል። (1 ሳሙኤል 14:31-35) ስለዚህ ሕይወት ውድ ነገር ቢሆንም የሕይወታችን ፈጣሪ እሱ የሰጣቸው ደንቦች በአደገኛ ሁኔታዎች ሊጣሱ እንደሚችሉ አልተናገረም።
ደምና እውነተኛ ክርስቲያኖች
ሰብዓዊ ሕይወትን በደም በማዳን ረገድ የእውነተኛ ክርስትና አቋም ምንድን ነው?
ኢየሱስ ጽኑ አቋም የነበረው ሰው ነው። ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠውም በዚህ ምክንያት ነው። ፈጣሪ ደም መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን እንደተናገረና ይህም ሕግ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ተፈጻሚነት እንዳለው ያውቅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ አስገዳጅ ሁኔታ ቢያጋጥመው እንኳን ስለ ደም የተሰጠውን ሕግ እንደሚያከብር የምናምንበት በቂ ምክንያት አለን። ኢየሱስ “ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም።” (1 ጴጥሮስ 2:22) ስለዚህ ለተከታዮቹ ሁሉ ምሳሌ ሆኗል። ምሳሌ የሆነው ለሕይወትና ለደም አክብሮት በማሳየት ጭምር ነው። (የኢየሱስ የገዛ ራሱ ደም በዚህ ያንተን ሕይወት በሚመለከት ታላቅ ጉዳይ ውስጥ እንዴት እንደገባ ወደፊት እንመለከታለን።)
ኢየሱስ ከሞተ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ክርስቲያን የሚሆን ሰው ለእስራኤላውያን የተሰጡትን ሕጎች በሙሉ መጠበቅ ይኖርበታል ወይስ አይኖርበትም የሚል ጥያቄ በተነሳ ጊዜ የሆነውን ነገር ልብ በል። በዚህ ጥያቄ ላይ ውይይት የተደረገው ሐዋርያት በአባልነት ይገኙበት በነበረው የክርስቲያኖች የአስተዳደር አካል ምክር ቤት ነበር። የኢየሱስ የእናቱ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ለኖኅና ለእስራኤል ብሔር ስለ ደም የተሰጠው ሕግ ከሚገኝባቸው ጽሑፎች ጠቅሷል። ይህ ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋልን?—ሥራ 15:1-21
ይህ ምክር ቤት የደረሰበትን ውሳኔ ለጉባኤዎች በሙሉ አስተላለፈ። ክርስቲያኖች ለሙሴ የተሰጠውን ሕግ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም [ደሙ ያልፈሰሰ ሥጋ] ከዝሙትም” ‘መራቅ እንደሚያስፈልጋቸው’ ገልጸዋል። (ሥራ 15:22-29) ሐዋርያት የአመጋገብን ሥርዓት የሚመለከት ተራ ደንብ ማስተላለፋቸው አልነበረም። ውሳኔያቸው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጥብቅ የተከተሉትን መሠረታዊ የሆነ የግብረ ገብ ደንብ የሚደነግግ ነበር። ይህ ከሆነ አሥር ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላም “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ነፍሳቸውን” መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።—ሥራ 21:25
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሄዱ ታውቃለህ። ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ የክርስትና ግብረ ገብ ጣዖት አለማምለክንና ዝሙት አለመፈጸምን እንደሚጨምር ይስማሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐዋርያት ደም መውሰድን ከእነዚህ ክፉ ድርጊቶች ጋር በእኩል ደረጃ እንዳስቀመጡ ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። ውሳኔያቸውን ሲያጠቃልሉ እንዲህ ብለዋል:- “ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።”—ሥራ 15:29
ሐዋርያዊው ድንጋጌ በክርስቲያኖች ሁሉ ላይ ተፈጻሚነት እንዳለው ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይታመን ነበር። ዩሴቢየስ በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ገደማ ላይ ትኖር የነበረች አንዲት ሴት ብዙ ሥቃይ ደርሶባት ልትሞት በተቃረበችበት ጊዜ ክርስቲያኖች “የማሰብ ችሎታ የሌላቸውን እንስሳት ደም እንኳን መብላት አልተፈቀደላቸውም” እንዳለች ጽፏል። ይህች ሴት የመሞት መብት ያላት መሆኑን ለማረጋገጥ ስትል የተናገረችው አልነበረም። በሕይወት የመኖር ፍላጎት የነበራት ቢሆንም ለመኖር ስትል የምታምንበትን መሠረታዊ ሥርዓት ለመጣስ አልፈለገችም። የሚያምኑበትን መሠረታዊ ሥርዓት ከግል ጥቅማቸው የሚያስቀድሙ ሰዎችን በአክብሮት አትመለከትምን?
ጆሴፍ ፕርስትሊ የተባሉት የሳይንስ ሊቅ እንዲህ ብለዋል:- “ለኖህ የተሰጠው ደም መብላትን የሚከለክለው ሕግ በዘሮቹ ሁሉ ላይ የተጣለ ግዴታ ይመስላል። . . . የሐዋርያትን ድንጋጌ፣ የድንጋጌውን ባሕርይና ስፋት በትክክል አልተረዱም ሊባሉ የማይችሉት የጥንት ክርስቲያኖች በነበራቸው ምግባር መሠረት እንደምንረዳው ከሆነ ፍጹማዊና ዘላለማዊ ሕግ እንዲሆን የታቀደ ነበር ከሚለው መደምደሚያ ልናመልጥ አንችልም። ምክንያቱም ክርስቲያኖች ለበርካታ መቶ ዘመናት ደም አይበሉም ነበር።”
ደምን በመድኃኒትነት ስለመጠቀምስ ምን ሊባል ይችላል?
በደም ላይ የተጣለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እገዳ በኖህ፣ በሙሴም ሆነ በሐዋርያት ዘመን የማይታወቅ የነበረውን ደምን በደም ሥር መውሰድ የመሰለውን የሕክምና አጠቃቀም ያጠቃልላልን?
በደም አማካኝነት የሚሰጠው ዘመናዊ ሕክምና በነዚህ የጥንት ዘመናት የማይታወቅ ቢሆንም ደምን ለሕክምና መጠቀም ዘመን አመጣሽ ነገር አይደለም። ከ2,000 ዓመታት በፊት ጀምሮ በግብጽና በሌሎች አገሮች የሰው “ደም ለሥጋ ደዌ ፍቱን መድኃኒት ነው” ተብሎ ይታመን ነበር። አንድ ሐኪም የአሦር ብሔር በቴክኖሎጂ ረገድ በመሪነት ደረጃ ላይ ይገኝ በነበረበት ዘመን ለንጉሥ አስራዶን ወንድ ልጅ የተሰጠውን ሕክምና ገልጿል:- “[መስፍኑ] በጣም ስለተሻለው ጌታዬ ንጉሥ በጣም ሊደሰት ይችላል። ከ22ኛው ቀን ጀምሬ የሚጠጣው ደም ሰጠሁት። ለ3 ቀናት ይጠጣዋል። ከዚያ በኋላ ለውስጥ ደዌ ደግሞ ለተጨማሪ 3 ቀናት (ደም) እሰጠዋለሁ።” አስራዶን ከእስራኤላውያን ጋር ግንኙነት የነበረው ንጉሥ ነው። እስራኤላውያን ግን የአምላክ ሕግ ያግዳቸው ስለነበረ ፈጽሞ ደምን መድኃኒት ይሆነናል ብለው አልጠጡም።
በሮማውያን ዘመንስ ደም በመድኃኒትነት አገልግሎ ነበረን? የሥነ ፍጥረት ተመራማሪ የነበረው ፕሊኒ (በሐዋርያት ዘመን ይኖር የነበረ ነው) እና አረታየስ የተባለው የሁለተኛው መቶ ዘመን ሐኪም የሰው ደም ለሚጥል በሽታ ይሰጥ እንደነበረ ዘግበዋል። ቆየት ብሎ ደግሞ ተርቱልያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጨዋታ ሥፍራዎች ከክፉ ወንጀለኞች የሚፈሰውን ትኩስ ደም ተስገብግበው የሚልፉትንና . . . ከሚጥል በሽታቸው ለመፈወስ ቀድተው የሚወስዱትን ሰዎች ተመልከቱ።” ከዚያም እነዚህን ሰዎች ከክርስቲያኖች ጋር በማነጻጸር ክርስቲያኖች “የእንስሳትን ደም እንኳን በምግባቸው ውስጥ አይጨምሩም። . . . ክርስቲያኖችን ለመፈተን በደም የተሞላ ቋሊማ ስጧቸው። በሕጋቸው ፈጽሞ ያልተፈቀደ መሆኑን ታረጋግጣላችሁ።” ስለዚህ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ደም ከሚወስዱ ሞታቸውን ይመርጡ ነበር።
ሥጋና ደም (Flesh and Blood) የተባለው መጽሐፍ “ደም . . . በሕክምናና በአስማት ውስጥ የነበረውን ቦታ ሳያጣ ኖሯል” ብሏል። “ለምሳሌ ያህል በ1483 የፈረንሳዩ ሉዊ 11ኛ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። በሽታው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰበት ሄዶ ነበር። የተሰጡት መድኃኒቶች በሙሉ እንግዳ የሆነ ባሕርይ ቢኖራቸውም ምንም ሳይረዱት ቀሩ። ከአንድ ሕፃን ተወስዶ የተሰጠውን ደም በመውሰድ እድናለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር።”
ደምን በደም ሥር መስጠትስ? በዚህ ሕክምና ላይ ሙከራ መደረግ የጀመረው በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር። በኮፐንሃገን ዩኒቨርሲቲ የአናቶሚ ፕሮፌሰር የነበረው ቶማስ ባርቶሊን (1616-80) የሚከለተውን የተቃውሞ ሐሳብ ሰንዝሯል:- ‘ደምን ለውስጥ ደዌዎች መፈወሻ ለመጠቀም የሚሞክሩ ሰዎች ደምን ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ ከመጠቀማቸውም በላይ ከባድ ኃጢአት ይሠራሉ። የሰው ሥጋ መብላት የተወገዘ ነው። ታዲያ የገዛ ከርሳቸውን በሰው ደም የሚያረክሱትን ሰዎች የማንጸየፈው ለምንድን ነው? ከተቆረጠ ደም ሥር የተወሰደ ባዕድ ደም በአፍም ሆነ በደም መውሰጃ መሣሪያዎች መውሰድም ከዚህ የተለየ አይደለም። የዚህ ተግባር አመንጪዎች ደም መብላትን የሚከለክለው መለኮታዊ ሕግ ሊያስደነግጣቸው ይገባል።’
ስለዚህ ባለፉት መቶ ዘመናት ይኖሩ የነበሩ አስተዋይ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊው ሕግ ደምን በደም ሥር በመውሰድም ሆነ በአፍ በመውሰድ ላይ እኩል ተፈጻሚነት እንዳለው ተገንዝበው ነበር። ባርቶሊን እንደሚከተለው በማለት ደምድሟል:- “[ደም] በየትኛውም መንገድ ቢወሰድ ዓላማው አንድና ተመሳሳይ ነው። ደም የሚሰጠው በሽተኛውን ለማበርታት ወይም ለማሻል ነው።”
እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው አጠቃላይ ነጥቦች የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ለድርድር የማይቀርብ ሃይማኖታዊ አቋም እንድትረዳ ሳያስችሉህ አይቀሩም። የይሖዋ ምሥክሮች ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣሉ። ጥሩ የሕክምና እርዳታ እንዲደረግላቸውም ይፈልጋሉ። ቢሆንም የአምላክን ደንብ ላለመጣስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይህ ደግሞ እርስ በርሱ የሚጋጭ አቋም አይደለም። ሕይወት የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን የሚገነዘቡና በዚህም ምክንያት ሕይወትን የሚያከብሩ ሁሉ ሕይወታቸውን ደም በመውሰድ ለማቆየት አይሞክሩም።
ይሁን እንጂ ደም ሕይወት እንደሚያድን ለበርካታ ዓመታት ሲነገር ቆይቷል። ዶክተሮች፣ ብዙ ደም ፈሷቸው ደም በደም ሥር ሲሰጣቸው በአፋጣኝ የዳኑ ሰዎች እንዳሉ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ‘ደም መውሰድ ከሕክምና አንጻር ጥሩ ነው ወይስ ጥሩ አይደለም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በደም አማካኝነት የሚሰጥ ሕክምና ጠቃሚ ስለመሆኑ የሕክምና ማስረጃ ይቀርባል። ስለዚህ ደምን በተመለከተ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችልህን መረጃ ማግኘት ያስፈልግሃል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጳውሎስ በሥራ 17:25, 28 ላይ የተናገረው ነው።
b ከጊዜ በኋላ በቁርዓን ውስጥ ተመሳሳይ ድንጋጌዎች ተጽፈዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ቁርጥ ባለና በማያሻማ ቃል [በሥራ 15 ላይ] የተነገረው ደንብ ሊሻር የማይችል እንደሆነ ስለተገለጸ ሐአዋርያት ለጊዜው ብቻ የሚቆይ፣ ዘላቂ ያልሆነ ሕግ እንደሆነ አድርገው እንዳልተመለከቱት ጠንካራ ማስረጃ ይአሆናል።”—የስታስበርግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ሩስ
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማርቲን ሉተር ሐዋርያዊው ድንጋጌ ያለውን አንድምታ እንደሚከተለው በማለት አመልክቷል:- “ከዚህ ጉባኤ ድንጋጌ ጋር የምትስማማ ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን ከፈለግን . . . ከእንግዲህ ወዲህ ማንም መስፍን፣ ጌታ፣ ጨዋ፣ ወይም አርሶ አደር በደም የተቀቀለ የዝይ፣ የድኩላ፣ የአጋዘን ወይም የዓሳማ ሥጋ መብላት እንደሌለበት አጥብቀን ማስተማር ይኖርብናል። . . . ጨዋዎችና አርሶ አደሮች በተለይ ከቀይና ደም ከገባበት ቋሊማ መራቅ ይኖርባቸዋል።”
[ምንጭ]
Woodcut by Lucas Cranach
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የአምላክና የሰዎች አመለካከት በጣም ይለያያል። በእኛ ዓይን በጣም አስፈላጊ ሆኖ የሚታየው ነገር ዳርቻ የሌለው ጥበብ ባለው ፈጣሪ ግምት እዚህ ግባ የማይባል ሲሆን በእኛ አመለካከት ከቁም ነገር የማይገባ መስሎ የሚታየው ነገር በአምላክ ዘንድ በጣም ትልቅ ቦታ ያለው ይሆናል። ይህ ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ የነበረ ሁኔታ ነው።”—“ደም መብላት ሕጋዊ ስለመሆኑ የተደረገ ምርምር፣” አለክሳንደር ፒሪ፣ 1787
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Medicine and the Artist by Carl Zigrosser/Dover Publications
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቲያኖች የአስተዳደር አካል ታሪካዊ የሆነ ጉባኤ አድርጎ አምላክ ስለ ደም የሰጠው ሕግ ዛሬም ተፈጻሚነት ያለው መሆኑን አረጋግጧል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ውጤት ቢያስከትልባቸው አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ለመተላለፍ ፈቃደኞች አልሆኑም
[ምንጭ]
የዠሮም ቀለም ቅብ፣ 1883, courtesy of Walters Art Gallery, Baltimore