ምዕራፍ 88
ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር
ኢየሱስ በአንድ በኩል ለቁሳዊ ሀብት በሌላ በኩል ደግሞ ለአምላክ ባሪያዎች መሆን እንደማንችል በመግለጽ ቁሳዊ ሀብትን ትክክለኛ በሆነ መንገድ መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ እየነገራቸው ነበር። ፈሪሳውያንም ይህን እያዳመጡ ነበር። ገንዘብ ወዳዶች ስለነበሩ ያሾፉበት ጀመር። ስለዚህ እንዲህ አላቸው:- “ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና።”
በዓለማዊ ሀብት የበለጸጉ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ሥልጣንና አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ የሚለወጥበት ጊዜ ደርሶ ነበር። እነዚህ ሰዎች ይዋረዳሉ። በመንፈሳዊ የጎደሏቸው ነገሮች እንዳሉ የሚገነዘቡ ሰዎች ግን ከፍ ከፍ ሊደረጉ ነው። ኢየሱስ በመቀጠል ፈሪሳውያንን እንዲህ ባላቸው ጊዜ ይህን ለውጥ አመልክቷል:-
“ሕግና ነቢያት እስከ [አጥማቂው] ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ በኃይል ይገቡባታል። ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል።”
ጻፎችና ፈሪሳውያን የሙሴን ሕግ በጥብቅ እንከተላለን ብለው በማሰብ ይኩራሩ ነበር። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አንድን ሰው ተአምራዊ በሆነ መንገድ ማየት እንዲችል ሲያደርገው “እኛ . . . የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን” በማለት ጉራቸውን ነዝተው ነበር። ሆኖም አሁን የሙሴ ሕግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን አምላክ ወደመረጠው ንጉሥ ማለትም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመምራት የታለመለትን ዓላማ ፈጽሟል። ስለዚህ ከዮሐንስ አገልግሎት ጀምሮ ሁሉም ዓይነት ሰዎች በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትና ድሆች የሆኑ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
የሙሴ ሕግ የተፈጸመ በመሆኑ ሕጉን የመጠበቁ ግዴታ የሚያበቃበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ሕጉ በተለያዩ ምክንያቶች ፍቺን ይፈቅድ ነበር፤ አሁን ግን ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ሚስቱንም የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፣ ከባልዋም የተፈታችውን የሚያገባ ያመነዝራል።” ፈሪሳውያን በተለይ በብዙ ምክንያቶች ፍቺን የሚፈቅዱ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቶቹ መግለጫዎች ምንኛ አበሳጭተዋቸው ይሆን!
ኢየሱስ ለፈሪሳውያን መናገሩን በመቀጠል ስለ ሁለት ሰዎች የሚገልጽ አንድ ምሳሌ ተናገረ። ሰዎቹ ቦታቸው ወይም ያሉበት ሁኔታ በመጨረሻ በሚያስገርም መንገድ እንደሚለወጥ በምሳሌው ላይ ተገልጿል። እነዚህ ሰዎች የሚያመለክቱት እነማንን እንደሆነና የነበሩበት ሁኔታ መለዋወጡ ምን ማለት እንደሆነ ልትገምት ትችላለህን?
ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፣ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቊስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፣ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቊስሎቹን ይልሱ ነበር።”
ኢየሱስ እዚህ ላይ ሀብታሙን ሰው፣ ፈሪሳውያንንና ጻፎችን ብቻ ሳይሆን ሰዱቃውያንንና የካህናት አለቆችንም ጨምሮ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። በመንፈሳዊ መብቶችና አጋጣሚዎች ረገድ ሀብታሞች ነበሩ፤ በተጨማሪም ሀብታሙ ሰው የነበረው ዓይነት ሁኔታ ነበራቸው። ንጉሣዊ ቀይ ልብስ መልበሳቸው ያላቸውን የላቀ ቦታ የሚያመለክት ሲሆን ነጩ የተልባ እግር ደግሞ ተመጻዳቂነታቸውን ያመለክታል።
ይህ ኩሩው የሀብታሙ ሰው ክፍል ድሆች የሆኑትን ተራ ሰዎች አምሃሬትስ ወይም የመሬት ሰዎች ብሎ በመጥራት በከፍተኛ ንቀት ይመለከታቸው ነበር። ስለዚህ ለማኙ አልዓዛር ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ተገቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብና መብቶች የነፈጓቸውን እነዚህን ሰዎች ያመለክታል። በመሆኑም ተራው ሕዝብ በቁስል እንደተወረሰው አልዓዛር በመንፈሳዊ እንደ ታመሙና ከውሾች ጋር ከመሆን የተሻለ ለሌላ ለምንም ነገር እንደማይበቁ ተደርገው በመታየት ይናቁ ነበር። ሆኖም እነዚህ የአልዓዛር ክፍል አባላት መንፈሣዊ ምግብ ስለተራቡና ስለተጠሙ ከሀብታሙ ሰው ማዕድ የሚወድቀውን ማንኛውንም የመንፈሳዊ ምግብ ፍርፋሪ ለማግኘት በር ላይ ሆነው ይጠብቃሉ።
አሁን ኢየሱስ በመቀጠል የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሁኔታ እንደተለዋወጠ ገለጸ። ይህ ለውጥ ምንድን ነው? ለውጡስ ምን ያመለክታል?
ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር የነበሩበት ሁኔታ ተለዋወጠ
ሀብታሙ ሰው መንፈሳዊ መብቶችና አጋጣሚዎች ያገኙትን ሃይማኖታዊ መሪዎች ሲያመለክት አልዓዛር ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ የተራቡትን ተራ ሰዎች ያመለክታል። ኢየሱስ ሰዎቹ የነበሩበት ሁኔታ በሚያስገርም አኳኋን እንደተለዋወጠ በመግለጽ ታሪኩን መናገሩን ቀጠለ።
ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ድሀውም ሞተ፣ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ።”
ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር የሰዎችን ቡድን የሚያመለክቱ እንጂ ቃል በቃል ራሳቸውን የቻሉ ሰዎች ስላልሆኑ ሞታቸውም ምሳሌያዊ እንደሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ሞታቸው የሚወክለው ወይም የሚያመለክተው ነገር ምንድን ነው?
ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ‘ሕግና ነቢያት እስከ አጥማቂው ዮሐንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን የአምላክ መንግሥት እየተሰበከ ነው’ ብሎ በመናገር በሁኔታዎች ላይ ለውጥ እንደተከሰተ አመልክቷል። ስለዚህ ሀብታሙ ሰውም ሆነ አልዓዛር ቀድሞ ለነበሩበት ሁኔታ የሞቱት በዮሐንስና በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት ነው።
በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት የአልዓዛር ክፍል አባላት ቀድሞ ለነበሩበት መንፈሳዊ ድህነት ሞተው መለኮታዊ ሞገስ ወደሚያገኙበት ደረጃ ደርሰዋል። ቀደም ሲል ከሃይማኖት መሪዎቹ መንፈሳዊ ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ለማግኘት ይጠባበቁ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከኢየሱስ ያገኟቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እያሟሉላቸው ነው። በዚህ መንገድ በታላቁ አብርሃም በይሖዋ አምላክ እቅፍ ውስጥ ገብተዋል ወይም ሞገሱን አግኝተዋል።
በሌላ በኩል የሀብታሙ ሰው ክፍል አባላት ግትር አቋም በመያዝ ኢየሱስ ያስተማረውን የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው መለኮታዊ ሞገስ አጥተዋል። በዚህ መንገድ ሞገስ ያላቸው መስለው ይኖሩ ለነበረበት የቀድሞ ሁኔታቸው ሞተዋል። እንዲያውም በምሳሌያዊ ሥቃይ ውስጥ እንዳሉ ተደርጎ ተገልጿል። አሁን ሀብታሙ ሰው ምን ብሎ እንደተናገረ ተመልከት:-
“አብርሃም አባት ሆይ፣ ማረኝ፣ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ።” የሀብታሙን ሰው ክፍል አባላት የሚያሠቃያቸው በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚታወጁት የአምላክ እሳታማ የፍርድ መልእክቶች ናቸው። ከሥቃያቸው ትንሽ አረፍ እንዲሉ ደቀ መዛሙርቱ እነዚህን መልእክቶች ማወጃቸውን ጋብ እንዲያደርጉላቸው ፈለጉ።
“አብርሃም ግን:- ልጄ ሆይ፣ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጸናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፣ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ።”
የአልዓዛር ክፍልና የሀብታሙ ሰው ክፍል የነበሩበት ሁኔታ አስገራሚ በሆነ መንገድ እንዲህ መለዋወጡ ምንኛ ፍትሃዊና ተገቢ ነው! ከጥቂት ወራት በኋላ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አሮጌው የሕግ ቃል ኪዳን በአዲሱ ቃል ኪዳን ሲተካ የሁኔታዎቹ ለውጥ ተጠናቋል። በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኙት ፈሪሳውያንና ሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ ደቀ መዛሙርቱ መሆናቸው በዚያን ጊዜ በማያሻማ መንገድ ግልጽ ሆኗል። ስለዚህ ምሳሌያዊውን ሀብታም ሰውና የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በመካከል የሚለያቸው “ታላቅ ገደል” የማይለወጠውን የአምላክ የጽድቅ ፍርድ ያመለክታል።
ሀብታሙ ሰው በመቀጠል ‘አብርሃም አባት ሆይ፣ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት ስደደው፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና’ ሲል ለመነው። በዚህ አባባሉ ሀብታሙ ሰው ከሌላ አባት ጋር ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዳለው አምኗል። ሀብታሙ ሰው ‘አምስቱ ወንድሞቹ’ ማለትም ሃይማኖታዊ አጋሮቹ ‘ወደዚህ የሥቃይ ሥፍራ’ እንዳይመጡ አልዓዛር የአምላክን የፍርድ መልእክቶች ኃይል ቀዝቀዝ እንዲያደርግላቸው ለምኗል።
“አብርሃም ግን:- ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው።” አዎን፣ ‘አምስቱ ወንድሞቹ’ ከሥቃዩ ማምለጥ እንዲችሉ ከተፈለገ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያመለክቱት የሙሴና የነቢያት መጻሕፍት የሚሉትን መከተልና ከዚያም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለባቸው። ሆኖም ሀብታሙ ሰው “አይደለም፣ አብርሃም አባት ሆይ፣ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ” በማለት ተቃወመ።
ይሁን እንጂ “ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፣ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም” የሚል መልስ ተሰጠው። አምላክ ሰዎችን ለማሳመን ሲል ልዩ ምልክቶች ወይም ተአምራት አይፈጽምም። ሞገሱን ማግኘት ከፈለጉ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብና በሥራ መተርጎም አለባቸው። ሉቃስ 16:14-31፤ ዮሐንስ 9:28, 29፤ ማቴዎስ 19:3-9፤ ገላትያ 3:24፤ ቆላስይስ 2:14፤ ዮሐንስ 8:44
▪ የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ሞት ምሳሌያዊ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? ሞታቸውስ ምን ያመለክታል?
▪ ኢየሱስ በዮሐንስ አገልግሎት መጀመሪያ ላይ ምን ለውጥ እንደተከሰተ አመልክቷል?
▪ ከኢየሱስ ሞት በኋላ የሚወገደው ነገር ምንድን ነው? ይህስ በፍቺ ጉዳይ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?
▪ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ በሀብታሙ ሰውና በአልዓዛር የተመሰሉት እነማን ናቸው?
▪ በሀብታሙ ሰው ላይ የደረሰው ሥቃይ ምንድን ነው? ከሥቃዩ እፎይታ ለማግኘት ምን እንዲደረግለት ጠይቋል?
▪ ‘ታላቁ ገደል’ ምን ያመለክታል?
▪ የሀብታሙ ሰው እውነተኛ አባት ማን ነው? አምስቱ ወንድሞቹስ እነማን ናቸው?