ምዕራፍ አሥራ ሰባት
በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
ወደ አምላክ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?
1, 2. ጸሎትን እንደ ትልቅ መብት አድርገን ልንመለከተው የሚገባን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት የሚሰጠውን ትምህርት ማወቅ የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?
ምድር ግዙፍ ከሆነው ጽንፈ ዓለም ጋር ስትወዳደር በጣም ትንሽ ናት። እንዲያውም የሰው ልጆች ‘ሰማይንና ምድርን በፈጠረው’ በይሖዋ ፊት በገንቦ ውስጥ እንዳለች ትንሽ ጠብታ ናቸው። (መዝሙር 115:15፤ ኢሳይያስ 40:15) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል” ይላል። (መዝሙር 145:18, 19) ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ‘በእውነት ከጠራነው’ ለእኛ ቅርብ ከመሆኑም በላይ ይሰማናል። ወደ አምላክ መጸለይ መቻላችን እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!
2 ይሁን እንጂ ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከፈለግን እሱ በሚቀበለው መንገድ መጸለይ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት ምን እንደሚያስተምር ካላወቅን ይህን እንዴት ልናደርግ እንችላለን? ጸሎት ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት እንድናጠናክር የሚረዳን በመሆኑ ቅዱሳን ጽሑፎች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚሰጡትን ሐሳብ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።
ወደ ይሖዋ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
3. ወደ ይሖዋ መጸለያችን አስፈላጊ ነው የምንልበት አንዱ ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
3 ወደ ይሖዋ መጸለያችን አስፈላጊ ነው የምንልበት አንዱ ዋነኛ ምክንያት ይሖዋ ራሱ ወደ እሱ እንድንጸልይ የጋበዘን መሆኑ ነው። ቃሉ እንዲህ ሲል ያበረታታናል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ በደግነት ተገፋፍቶ ያደረገልንን እንዲህ ያለ ዝግጅት ማቃለል እንደማንፈልግ የታወቀ ነው!
4. ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለያችን ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያጠነክርልን እንዴት ነው?
4 ሌላው ምክንያት ደግሞ ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለያችን ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያጠናክርልን መሆኑ ነው። እውነተኛ ጓደኛሞች የሚነጋገሩት አንድ ነገር ሲፈልጉ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ጓደኛሞች እርስ በርስ የሚዋደዱ ከመሆናቸውም በላይ ሐሳባቸውን፣ የሚያስጨንቃቸውን ነገርና ስሜታቸውን አንዳቸው ለሌላው በነፃነት ሲገልጹ በመካከላቸው ያለው ወዳጅነት ይበልጥ ይጠነክራል። ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለን ወዳጅነትም በአንዳንድ ሁኔታዎች ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ስለ ዓላማዎቹ ምን እንደሚያስተምር በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት በሚገባ አጥንተሃል። በመሆኑም ይሖዋ እውን ሆኖልሃል። ጸሎት ሐሳብህንና የልብህን ስሜት በሰማይ ላለው አባትህ መግለጽ የምትችልበት አጋጣሚ ይሰጥሃል። እንዲህ ስታደርግ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ትቀርባለህ።—ያዕቆብ 4:8
ልናሟላቸው የሚገቡት ብቃቶች ምንድን ናቸው?
5. ይሖዋ የማይሰማው ጸሎት እንዳለ እንዴት እናውቃለን?
5 ይሖዋ ሁሉንም ጸሎቶች ይሰማል? በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን የነበሩትን ዓመጸኛ እስራኤላውያን ምን እንዳላቸው ተመልከት:- “አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል።” (ኢሳይያስ 1:15) ስለዚህ አንዳንድ ድርጊቶች አምላክ ጸሎታችንን እንዳይሰማ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ጸሎቶቻችን በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት ማግኘት እንዲችሉ ልናሟላቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሆኑ ብቃቶች አሉ።
6. አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ልናሟላው የሚገባን አንዱ ብቃት ምንድን ነው? ይህን ብቃት ልናሟላ የምንችለውስ እንዴት ነው?
6 በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ብቃቶች አንዱ እምነት ማሳየት ነው። (ማርቆስ 11:24) ሐዋርያው ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 11:6) እውነተኛ እምነት አምላክ እንዳለ እንዲሁም ጸሎቶችን እንደሚሰማና መልስ እንደሚሰጥ ከማወቅ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። እምነት የሚረጋገጠው በሥራችን ነው። የዕለት ተዕለት አኗኗራችን እምነት እንዳለን በግልጽ የሚያሳይ መሆን አለበት።—ያዕቆብ 2:26
7. (ሀ) ይሖዋን በጸሎት ስናነጋግር አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ወደ አምላክ በምንጸልይበት ጊዜ ትሕትናና ከልብ የመነጨ ስሜት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
7 በተጨማሪም ይሖዋ ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎች ጸሎታቸውን በትሕትናና ከልብ በመነጨ ስሜት እንዲያቀርቡ ይፈልጋል። ይሖዋን ስናነጋግር ትሕትና ማሳየታችን ተገቢ አይደለም? ሰዎች ብዙውን ጊዜ አንድን ንጉሥ ወይም ፕሬዚዳንት ማነጋገር የሚችሉበት አጋጣሚ ሲያገኙ መሪው ያለውን ሥልጣን አምነው በመቀበል ከፍተኛ አክብሮት ያሳያሉ። እንግዲያው በጸሎት ወደ ይሖዋ ስንቀርብ ከዚህ የበለጠ አክብሮት ልናሳይ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም! (መዝሙር 138:6) ይሖዋ “ሁሉን ቻይ” አምላክ ነው። (ራእይ 15:3) ወደ አምላክ በምንጸልይበት ጊዜ ወደ እሱ የምንቀርብበት ሁኔታ በእሱ ፊት ያለንን ቦታ በትሕትና አምነን እንደምንቀበል የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም እንዲህ ያለው ትሕትና የተለመደ አንድ ዓይነት ጸሎት ከመጸለይ ይልቅ ከልብ በመነጨ ስሜት እንድንጸልይ ይገፋፋናል።—ማቴዎስ 6:7, 8
8. ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት ነው?
8 አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ልናሟላው የሚገባን ሌላው ብቃት ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ነው። ይሖዋ የጸለይንበት ጉዳይ እንዲሳካልን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ይፈልጋል። ለምሳሌ ያህል “የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” ብለን ከጸለይን ምንም ሥራ ሳንንቅ በትጋት መሥራት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 6:11፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10) አንድን ዓይነት ሥጋዊ ድክመት ማሸነፍ እንድንችል እንዲረዳን ከጸለይን ወደ ፈተና ሊመሩን ከሚችሉ ሁኔታዎች መራቅ አለብን። (ቈላስይስ 3:5) ከእነዚህ መሠረታዊ የሆኑ ብቃቶች በተጨማሪ ጸሎትን አስመልክቶ የሚነሱ መልስ ልናገኝላቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ።
ጸሎትን በተመለከተ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን መመለስ
9. መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው? በማን በኩልስ?
9 መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘በሰማያት ወደሚኖረው አባታችን’ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) ስለዚህ መጸለይ ያለብን ወደ ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ቦታ አምነን እንድንቀበል ይፈልጋል። ምዕራፍ 5 ላይ እንደተማርነው ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው ቤዛ ለመሆንና እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለመቤዠት ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:12) ሊቀ ካህናትና ፈራጅ ሆኖ ተሹሟል። (ዮሐንስ 5:22፤ ዕብራውያን 6:20) በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሎቶቻችንን በኢየሱስ በኩል እንድናቀርብ መመሪያ ይሰጡናል። ኢየሱስ ራሱ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:6) ጸሎቶቻችን ተሰሚነት እንዲያገኙ ከፈለግን በልጁ በኩል ወደ ይሖዋ ብቻ መጸለይ አለብን።
10. በምንጸልይበት ጊዜ ለየት ያለ አኳኋን ሊኖረን የማያስፈልገው ለምንድን ነው?
10 በምንጸልይበት ጊዜ ለየት ያለ አኳኋን ሊኖረን ይገባል? በፍጹም። ይሖዋ እጃችንም ሆነ መላው ሰውነታችን አንድ ዓይነት ለየት ያለ አኳኋን እንዲኖረው አይፈልግም። መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ አኳኋን መጸለይ እንደምንችል ያስተምረናል። ተቀምጦ፣ ግምባርን ደፍቶ፣ ተንበርክኮም ሆነ ቆሞ መጸለይ ይቻላል። (1 ዜና መዋዕል 17:16፤ ነህምያ 8:6፤ ዳንኤል 6:10፤ ማርቆስ 11:25) ዋናው ነገር ሌሎች ሊያዩት በሚችሉት ለየት ያለ አኳኋን መጸለይ ሳይሆን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ መያዝ ነው። እንዲያውም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ወይም አንድ ድንገተኛና አጣዳፊ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥመን የትም ሆንን የት በልባችን ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። እንዲህ ያለውን ጸሎት ሌሎች ሰዎች ላያስተውሉት ቢችሉም እንኳ ይሖዋ ይሰማዋል።—ነህምያ 2:1-6
11. በጸሎታችን ልናካትታቸው የምንችላቸው አንዳንድ የግል ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
11 ስለምን ነገር ልንጸልይ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ “ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ [ይሖዋ] ይሰማናል” ሲል ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 5:14) ስለዚህ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ስለሚስማማ ነገር ሁሉ መጸለይ እንችላለን። ስለሚያስጨንቁን የግል ጉዳዮች ብንጸልይ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ይስማማል? እንዴታ! ወደ ይሖዋ መጸለይ ከአንድ የቅርብ ወዳጅ ጋር እንደመነጋገር ሊቆጠር ይችላል። ‘ልባችንን በአምላክ ፊት በማፍሰስ’ በግልጽ ልናናግረው እንችላለን። (መዝሙር 62:8) መንፈስ ቅዱስ ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግ የሚረዳን በመሆኑ ይህን መንፈስ እንዲሰጠን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዳ አመራርና ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። (ያዕቆብ 1:5) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ መጠየቅ አለብን። (ኤፌሶን 1:3, 7) እርግጥ ነው፣ የምንጸልየው ስለ ግል ጉዳዮቻችን ብቻ መሆን የለበትም። የቤተሰብ አባሎቻችንንና የእምነት ባልንጀሮቻችንን ጨምሮ ለሌሎች ሰዎችም መጸለይ ይኖርብናል።—የሐዋርያት ሥራ 12:5፤ ቈላስይስ 4:12
12. ከሰማያዊ አባታችን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በጸሎታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የምንችለው እንዴት ነው?
12 ከይሖዋ አምላክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጸሎታችን ውስጥ ቅድሚያውን ሊይዙ ይገባል። ለደግነቱ ከልብ የመነጨ ውዳሴና ምስጋና ልናቀርብለት ይገባል። (1 ዜና መዋዕል 29:10-13) ኢየሱስ በማቴዎስ 6:9-13 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የናሙና ጸሎቱ ላይ የአምላክ ስም እንዲቀደስ መጸለይ እንዳለብን አስተምሮናል። ከዚያ ቀጥሎ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነች በምድርም እንድትሆን መጸለይ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። ኢየሱስ ስለ ግል ጉዳዮች የተናገረው እነዚህን ዋና ዋና ነጥቦች ከጠቀሰ በኋላ ነው። እኛም በጸሎታችን ውስጥ ለአምላክ ቀዳሚውን ቦታ የምንሰጥ ከሆነ ከራሳችን ደኅንነት ይበልጥ የሚያሳስበን ነገር እንዳለ በተግባር እናሳያለን።
13. ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያላቸውን ጸሎቶች ርዝማኔ በተመለከተ ምን ያመለክታሉ?
13 ጸሎቶቻችን ምን ያህል ርዝማኔ ሊኖራቸው ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ በግልም ሆነ በሰዎች ፊት የሚቀርቡ ጸሎቶች ሊኖራቸው የሚገባውን ርዝማኔ በተመለከተ ያስቀመጠው ገደብ የለም። በማዕድ ፊት ከሚቀርብ አጠር ያለ ጸሎት አንስቶ ልባችንን ለይሖዋ እስከምናፈስበት ረጅም የሆነ የግል ጸሎት ድረስ የተለያየ ርዝማኔ ሊኖራቸው ይችላል። (1 ሳሙኤል 1:12, 15) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ብለው ረጅም ጸሎት የሚጸልዩ ተመጻዳቂ ሰዎችን አውግዟል። (ሉቃስ 20:46, 47) እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ይሖዋን ደስ አያሰኙትም። ትልቅ ግምት የሚሰጠው ከልብ በመነጨ ስሜት የምንጸልይ መሆናችን ነው። ስለዚህ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያላቸው ጸሎቶች ርዝማኔ እንደየሁኔታውና እንደየአስፈላጊነቱ ሊለያይ ይችላል።
14. መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሳንታክት ሁልጊዜ እንድንጸልይ’ ሲያበረታታን ምን ማለቱ ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያጽናናን ነገርስ ምንድን ነው?
14 ምን ያህል ጊዜ መጸለይ አለብን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሳንታክት ሁልጊዜ እንድንጸልይ፣’ ‘በጸሎት እንድንጸና’ እና ‘ሳናቋርጥ እንድንጸልይ’ ያበረታታናል። (ሉቃስ 18:1፤ ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) እርግጥ እንዲህ ሲባል ቀኑን ሙሉ ስንጸልይ መዋል አለብን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ላደረገልን መልካም ነገር ሁልጊዜ በማመስገንና አመራሩን፣ ማጽናኛውንና ማበረታቻውን እንዲሰጠን በመለመን አዘውትረን እንድንጸልይ ያሳስበናል። ይሖዋ በጸሎታችን ርዝማኔም ሆነ በጸሎታችን ብዛት ላይ ገደብ እንዳልጣለ ማወቁ የሚያጽናና አይደለም? የጸሎትን መብት ከልባችን የምናደንቅ ከሆነ በሰማይ ወዳለው አባታችን መጸለይ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እናገኛለን።
15. በግልም ሆነ በሰዎች ፊት በሚቀርቡ ጸሎቶች መደምደሚያ ላይ “አሜን” ማለት ያለብን ለምንድን ነው?
15 በጸሎታችን መደምደሚያ ላይ “አሜን” ማለት ያለብን ለምንድን ነው? “አሜን” የሚለው ቃል “እንዴታ” ወይም “ይሁን” ማለት ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሰፈሩት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በግልም ሆነ በሰዎች ፊት የምናቀርባቸውን ጸሎቶች ስንደመድም “አሜን” ማለታችን ተገቢ ነው። (1 ዜና መዋዕል 16:36፤ መዝሙር 41:13) ራሳችን በምናቀርበው ጸሎት መደምደሚያ ላይ “አሜን” ማለታችን ጸሎታችን ከልብ የመነጨ መሆኑን ያረጋግጣል። ሌላ ሰው ባቀረበው ጸሎት መደምደሚያ ላይ ድምፃችንን አውጥተንም ሆነ ሳናወጣ “አሜን” ማለታችን ደግሞ በጸሎቱ ላይ በተገለጹት ሐሳቦች እንደምንስማማ ያመለክታል።—1 ቆሮንቶስ 14:16
አምላክ ለጸሎቶቻችን መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?
16. ጸሎትን በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
16 በእርግጥ ይሖዋ ለጸሎት መልስ ይሰጣል? እንዴታ! ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሚያቀርቧቸው ከልብ የመነጩ ጸሎቶች መልስ እንደሚሰጥ እንድንተማመን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ለጸሎቶቻችን በተለያዩ መንገዶች መልስ ሊሰጥ ይችላል።
17. አምላክ ለጸሎቶቻችን መልስ ለመስጠት መላእክቱንና ምድራዊ አገልጋዮቹን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ ለጸሎት መልስ ለመስጠት መላእክቱንና ምድራዊ አገልጋዮቹን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። (ዕብራውያን 1:13, 14) መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ ይረዳቸው ዘንድ ወደ አምላክ ከጸለዩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ አገልጋዮች ጋር የተገናኙ ሰዎችን ታሪክ የሚገልጹ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች መላእክት የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እየመሩት እንዳሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። (ራእይ 14:6) ከዚህም ሌላ ይሖዋ አንድ ክርስቲያን እኛን ለመርዳት እንዲነሳሳ በማድረግ ከባድ ችግር ላይ በወደቅንበት ጊዜ ላቀረብናቸው ጸሎቶች መልስ ሊሰጠን ይችላል።—ምሳሌ 12:25፤ ያዕቆብ 2:16
18. ይሖዋ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቧቸው ጸሎቶች መልስ ለመስጠት ቅዱስ መንፈሱንና ቃሉን መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
18 በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ቅዱስ መንፈሱንና ቃሉን ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም አገልጋዮቹ ለሚያቀርቧቸው ጸሎቶች መልስ ይሰጣል። በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት አመራርና ብርታት በመስጠት ፈተናዎችን መቋቋም እንድንችል እንዲረዳን ለምናቀርባቸው ጸሎቶች መልስ ሊሰጠን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ብዙውን ጊዜ መመሪያ ለማግኘት ለምናቀርባቸው ጸሎቶች መልስ የምናገኘው ይሖዋ ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንድንችል እኛን ለመርዳት መሣሪያ አድርጎ ከሚጠቀምበት ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በግል ስናጠናም ሆነ ይህን መጽሐፍ የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ስናነብ ጠቃሚ የሆኑ ጥቅሶችን ልናገኝ እንችላለን። በክርስቲያን ጉባኤ ላይ በሚሰጡ ሐሳቦች ወይም አንድ አሳቢ የሆነ የጉባኤ ሽማግሌ በሚሰጠን ሐሳብ አማካኝነት ልናስብባቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦችን ልናስተውል እንችላለን።—ገላትያ 6:1
19. አንዳንድ ጊዜ ጸሎቶቻችን መልስ እንዳላገኙ ሆኖ ከተሰማን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
19 ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ሳይሰጠን እንደዘገ ሆኖ ከተሰማን ይህ የሆነው ይሖዋ መልስ መስጠት ስለተሳነው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለጸሎት መልስ የሚሰጠው ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታና እሱ በወሰነው ጊዜ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። የሚያስፈልጉንን ነገሮችም ሆነ እነዚህን ነገሮች እንዴት ሊያሟላልን እንደሚችል ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። ብዙውን ጊዜ ‘መለመናችንን፣ መፈለጋችንንና ማንኳኳታችንን’ እንድንቀጥል ያደርጋል። (ሉቃስ 11:5-10) በጸሎት መጽናታችን አምላክ ፍላጎታችን ከፍተኛ እንደሆነና እውነተኛ እምነት እንዳለን እንዲመለከት ያስችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ጸሎቶቻችንን እኛ ባላስተዋልነው መንገድ ሊመልስልን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድን ፈተና አስመልክተን የጸለይነውን ጸሎት ችግሩን በማስወገድ ሳይሆን ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት በመስጠት ሊመልስልን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:13
20. ውድ የሆነውን የጸሎት መብታችንን በሚገባ ልንጠቀምበት የሚገባን ለምንድን ነው?
20 የዚህ ግዙፍ ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ በተገቢው መንገድ በጸሎት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! (መዝሙር 145:18) እንግዲያው ይህን ውድ የሆነውን የጸሎት መብታችንን በሚገባ እንጠቀምበት። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጸሎት ሰሚ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን።