ምዕራፍ ሁለት
“መንገድ፣ እውነትና ሕይወት”
1, 2. ያለማንም እርዳታ በራሳችን ወደ አምላክ መቅረብ የማንችለው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን አድርጎልናል?
መንገድ ጠፍቶህ ያውቃል? አንድ ወዳጅህን ወይም ዘመድህን ለመጠየቅ ስትሄድ መንገዱ ጠፍቶህ የነበረበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። በማታውቀው መንገድ ላይ እየተጓዝክ በነበረበት በዚያ ወቅት በመንገድህ ላይ ያገኘኸውን ሰው አቅጣጫውን እንዲጠቁምህ ጠይቀኸው ሊሆን ይችላል። ሰውየው አቅጣጫውን ከመጠቆም ይልቅ በደግነት ተነሳስቶ “ና ተከተለኝ። እዚያው ድረስ አደርስሃለሁ” ቢልህ ምን ይሰማሃል? ትልቅ እፎይታ እንደሚሰማህ ግልጽ ነው!
2 ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ አድርጎልናል ማለት ይቻላል። ያለማንም እርዳታ በራሳችን ወደ አምላክ መቅረብ አንችልም። የሰው ልጆች በወረሱት ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት “ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል”፤ ወደ አምላክ መድረስ የሚቻልበት መንገድ ጠፍቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:17, 18) በመሆኑም መንገዱን ለማግኘት እርዳታ ያስፈልገናል። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ በደግነት ተነሳስቶ ምክርና መመሪያ ከመስጠት የበለጠ ነገር አድርጎልናል። ምዕራፍ 1 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ “ተከታዬ ሁን” የሚል ግብዣ አቅርቦልናል። (ማርቆስ 10:21) ከዚህም በተጨማሪ ይህን ግብዣ ለመቀበል እንድንነሳሳ የሚያደርገንን ምክንያት ነግሮናል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 14:6) ወደ አብ መቅረብ የሚቻለው በወልድ በኩል ብቻ የሆነው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት። ከዚያም እነዚያን ነጥቦች በአእምሯችን በመያዝ ኢየሱስ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ቁልፍ ሚና
3. ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው በኢየሱስ በኩል የሆነው ለምንድን ነው?
3 ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻለው በኢየሱስ በኩል የሆነበት ዋነኛው ምክንያት፣ አምላክ ይህን ቁልፍ ሚና እንዲጫወት የመረጠው ልጁን ስለሆነ ነው።a አብ ዓላማዎቹን በማስፈጸም ረገድ ወሳኝ የሆነ ቦታ ሰጥቶታል። (2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ቆላስይስ 1:18-20) ወልድ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና ለመረዳት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከሰይጣን ጋር በማበር በይሖዋ ላይ ባመፁ ጊዜ በኤደን የአትክልት ስፍራ ምን እንደተፈጸመ መመልከት ይኖርብናል።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1-6
4. በኤደን የተነሳው ዓመፅ ምን ጥያቄ አስነስቷል? ይሖዋስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ምን ለማድረግ ወሰነ?
4 በኤደን የተነሳው ዓመፅ የአምላክን ፍጥረታት ሁሉ የሚመለከት ጥያቄ አስነስቷል፦ ይሖዋ የተባለው አምላክ በእርግጥ ቅዱስ፣ ጥሩ፣ ጻድቅና አፍቃሪ ነው? ለዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሖዋ ፍጹም ከሆኑት መንፈሳዊ ልጆቹ መካከል አንዱን ወደ ምድር ለመላክ ወሰነ። ይህ የአምላክ ልጅ የሚሰጠው ተልእኮ ቀላል አልነበረም፤ የአባቱን ስም ማስቀደስ እንዲሁም ቤዛ በመሆን የሰው ልጆችን ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ መስጠት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም የሚመረጠው ልጅ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን የሰይጣን ዓመፅ ላስከተለው ችግር ሁሉ እልባት ማስገኘት ነበረበት። (ዕብራውያን 2:14, 15፤ 1 ዮሐንስ 3:8) ይሁንና ይሖዋ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍጹም የሆኑ መንፈሳዊ ልጆች አሉት። (ዳንኤል 7:9, 10) ታዲያ ይህን እጅግ አስፈላጊ ኃላፊነት እንዲወጣ የሚመርጠው የትኛውን ልጁን ይሆን? ይሖዋ የመረጠው፣ በኋላ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የተጠራውን “አንድያ ልጁን” ነው።—ዮሐንስ 3:16
5, 6. ይሖዋ በልጁ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው? እንዲህ እንዲተማመንበት ያደረገውስ ምንድን ነው?
5 ይሖዋ አንድያ ልጁን መምረጡ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም! አብ በአንድያ ልጁ ሙሉ በሙሉ ይተማመንበታል። ወልድ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ ዘመናት በፊት ይሖዋ ይህ ልጁ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስበትም ታማኝነቱን እንደሚጠብቅ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 53:3-7, 10-12፤ የሐዋርያት ሥራ 8:32-35) ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። የማሰብ ችሎታ እንዳላቸው ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ወልድም የፈለገውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለው። ያም ሆኖ ይሖዋ በልጁ ስለሚተማመን ታማኝነቱን እንደሚጠብቅ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ እንዲተማመንበት ያደረገው ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ስለሚያውቀው ነው። ይሖዋ ልጁን በሚገባ ያውቀዋል፤ እንዲሁም ልጁ እሱን ለማስደሰት ምን ያህል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አሳምሮ ያውቃል። (ዮሐንስ 8:29፤ 14:31) ወልድ አብን ይወደዋል፤ ይሖዋም ወልድን ይወደዋል። (ዮሐንስ 3:35) አብና ወልድ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር በመካከላቸው የማይበጠስ አንድነትና የጠበቀ የመተማመን ስሜት እንዲኖር አድርጓል።—ቆላስይስ 3:14
6 ወልድ ከሚጫወተው ወሳኝ ሚና፣ አብ በእሱ ላይ ካለው የመተማመን ስሜት እንዲሁም አብንና ወልድን ካስተሳሰራቸው የጠበቀ ፍቅር አንጻር ሲታይ ‘ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው’ መባሉ ምን ያስገርማል? ይሁንና ወደ አብ መቅረብ የምንችለው በወልድ በኩል ብቻ የሆነበት ሌላም ምክንያት አለ።
አብን በሚገባ የሚያውቀው ወልድ ብቻ ነው
7, 8. ኢየሱስ አብን ‘ከወልድ በስተቀር’ ማንም በሚገባ እንደማያውቀው መናገሩ ትክክል ነው የምንለው ለምንድን ነው?
7 ወደ ይሖዋ መቅረብ ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች አሉ። (መዝሙር 15:1-5) አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማሟላትና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ከወልድ የተሻለ የሚያውቅ ማን ይኖራል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ሁሉንም ነገር ለእኔ ሰጥቶኛል፤ ከአብ በስተቀር ወልድን በሚገባ የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብን በሚገባ የሚያውቅ ማንም የለም።” (ማቴዎስ 11:27) ኢየሱስ አብን ‘ከወልድ በስተቀር’ ማንም በሚገባ እንደማያውቀው የተናገረው ሐሳብ ትክክልና ምንም ያልተጋነነ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
8 ወልድ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደመሆኑ መጠን ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ቅርበት አለው። (ቆላስይስ 1:15) እስቲ አስበው፦ ፍጥረት ሀ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ወደ ሕልውና እስከመጡበት ጊዜ ድረስ አባትና ልጅ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ሁለቱ ብቻ አብረው ኖረዋል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በመካከላቸው የጠበቀ ቅርርብ ተፈጥሯል። (ዮሐንስ 1:3፤ ቆላስይስ 1:16, 17) ወልድ ከአባቱ ጋር ሲኖር የአባቱን አመለካከት፣ ፈቃድ፣ መሥፈርቶችና መንገዶች የመማር ግሩም አጋጣሚ አግኝቶ እንደነበር ልብ በል። በእርግጥም ኢየሱስ አባቱን ከማንም በተሻለ ያውቀዋል መባሉ የተጋነነ አይደለም። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ያለው እንዲህ ያለ ቅርበት ከማንም በተሻለ ሁኔታ የአባቱን ማንነት ለሌሎች እንዲገልጥ አስችሎታል።
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ የአባቱን ማንነት የገለጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
9 ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት እንዲሁም አባቱ ከአምላኪዎቹ ምን እንደሚጠብቅ በሚገባ እንደሚያውቅ ያሳያሉ።b ኢየሱስ አባቱን በሌላ በሚያስደንቅ መንገድም ገልጦታል። ኢየሱስ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሏል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ በተናገረውና ባደረገው ነገር ሁሉ አባቱን ፍጹም በሆነ ሁኔታ መስሏል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ ስለተጠቀመባቸው አሳማኝና ማራኪ አገላለጾች፣ ሌሎችን እንዲፈውስ ስላነሳሳው ርኅራኄና እንባውን እስከማፍሰስ ስላደረሰው የሐዘኔታ ስሜት ስናነብ ይሖዋም በዚያ ቦታ ቢሆን ኖሮ ልክ እንዲሁ ይናገርና ያደርግ እንደነበር ማሰብ እንችላለን። (ማቴዎስ 7:28, 29፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 11:32-36) ወልድ የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች፣ አብ ነገሮችን በምን መንገድ እንደሚያከናውንና ፈቃዱ ምን እንደሆነ በግልጽ አሳይተዋል። (ዮሐንስ 5:19፤ 8:28፤ 12:49, 50) በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የኢየሱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግና ምሳሌውን መከተል ይኖርብናል።—ዮሐንስ 14:23
10 ኢየሱስ ይሖዋን በቅርበት ስለሚያውቀውና ፍጹም በሆነ መንገድ ስለሚመስለው፣ ይሖዋ ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉት በወልድ በኩል እንዲሆን መወሰኑ አያስገርምም። ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ የሆነበትን ምክንያት ከተረዳን፣ አሁን ደግሞ ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እንመልከት።—ዮሐንስ 14:6
“እኔ መንገድ . . . ነኝ”
11. ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?
11 በኢየሱስ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አምላክ መቅረብ እንደማይቻል ተመልክተናል። እስቲ ይህ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው በጥልቀት እንመርምር። ኢየሱስ “መንገድ” ተብሎ የተጠራው ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው በእሱ በኩል ብቻ ስለሆነ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ይህ ቤዛ ባይከፈልልን ኖሮ ወደ አምላክ መቅረብ አንችልም ነበር። ኃጢአት በሰዎችና በአምላክ መካከል እንደ ጋሬጣ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቅዱስ በመሆኑ ኃጢአት በእሱ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። (ኢሳይያስ 6:3፤ 59:2) ሆኖም የኢየሱስ መሥዋዕት ይህ ጋሬጣ እንዲወገድ አድርጓል፤ የኃጢአት መሸፈኛ ወይም ማስተሰረያ ሆኖ አገልግሏል። (ዕብራውያን 10:12፤ 1 ዮሐንስ 1:7) አምላክ በክርስቶስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት ከተቀበልንና በዝግጅቱ ላይ እምነት ከጣልን የይሖዋን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። ‘ከአምላክ ጋር የምንታረቅበት’ ሌላ ምንም መንገድ የለም።—ሮም 5:6-11
12. ኢየሱስ “መንገድ” የሆነው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ከጸሎት ጋር በተያያዘም “መንገድ” ነው ሊባል ይችላል። የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ልመና እንደሚሰማልን እርግጠኞች ሆነን ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ የምንችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው። (1 ዮሐንስ 5:13, 14) ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት ይሰጣችኋል። . . . ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ጠይቁ፤ ትቀበላላችሁ።” (ዮሐንስ 16:23, 24) ስለዚህ በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብና ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራት እንችላለን። (ማቴዎስ 6:9) ኢየሱስ በሌላም አቅጣጫ ይኸውም በምሳሌነቱ “መንገድ” ነው ሊባል ይችላል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ኢየሱስ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሎታል። በመሆኑም ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል። እንግዲያው ወደ ይሖዋ መቅረብ ከፈለግን የኢየሱስን ፈለግ መከተል ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 2:21
‘እኔ እውነት ነኝ’
13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ንግግሩ ሁሉ እውነት የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “እውነት” እንዲሆን ምን ማድረግ ነበረበት? ለምንስ?
13 ኢየሱስ፣ አባቱ በመንፈሱ ስላስጻፈው ቃል ሁልጊዜ እውነት ይናገር ነበር። (ዮሐንስ 8:40, 45, 46) ከአንደበቱ የማታለያ ቃል ወጥቶ አያውቅም። (1 ጴጥሮስ 2:22) ተቃዋሚዎቹ እንኳ “የአምላክን መንገድ በእውነት [እንደሚያስተምር]” አምነው ተቀብለዋል። (ማርቆስ 12:13, 14) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘እኔ እውነት ነኝ’ ብሎ ሲናገር በንግግሩ፣ በስብከቱና በትምህርቱ እውነትን ለሌሎች ማሳወቁን መግለጹ ብቻ አልነበረም። ይህ ከመናገር ያለፈ ብዙ ነገርን ይጨምር ነበር።
14 ይሖዋ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ መሲሑ ወይም ስለ ክርስቶስ በርካታ ትንቢቶችን እንዲጽፉ በመንፈሱ እንደመራቸው አስታውስ። እነዚህ ትንቢቶች ስለ ኢየሱስ ሕይወት፣ አገልግሎትና ሞት ዝርዝር መረጃዎችን የያዙ ናቸው። በተጨማሪም የሙሴ ሕግ መሲሑን የሚያመለክቱ ትንቢታዊ ጥላነት ያላቸውን ሐሳቦች ይዟል። (ዕብራውያን 10:1) ታዲያ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ስለ እሱ የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደርግ ይሆን? ይሖዋ እውነተኛ ትንቢት የሚናገር አምላክ መሆኑ የሚረጋገጠው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ከባድ ኃላፊነት የተጣለው በኢየሱስ ላይ ነው። ኢየሱስ በአኗኗሩ ማለትም በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ፣ በትንቢት የተነገሩት ነገሮች እውን እንዲሆኑ አድርጓል። (2 ቆሮንቶስ 1:20) በዚህ መንገድ ኢየሱስ “እውነት” ሆኗል። ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩት ነገሮች ሁሉ እውነት እንዲሆኑ አድርጓል።—ዮሐንስ 1:17፤ ቆላስይስ 2:16, 17
“እኔ . . . ሕይወት ነኝ”
15. በወልድ እንደምናምን በተግባር ማሳየት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ምን ያስገኝልናል?
15 ሕይወትን ማለትም “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት የምንችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ በመሆኑ ኢየሱስ “ሕይወት” ነው ሊባል ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐንስ 3:36) በአምላክ ልጅ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው? ያለእሱ ሕይወት ማግኘት እንደማንችል ጽኑ እምነት አለን ማለት ነው። ከዚህም በላይ እምነታችንን በሥራ እናሳያለን፣ ከኢየሱስ መማራችንን እንቀጥላለን፣ እሱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ተግባራዊ እናደርጋለን እንዲሁም ምሳሌውን እንከተላለን። (ያዕቆብ 2:26) በዚህ መንገድ በአምላክ ልጅ እንደምናምን ማሳየታችን ዘላለማዊ ሕይወት ያስገኝልናል፤ ይህም “ትንሽ መንጋ” ለሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሰማይ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት፣ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ለሆኑት “ሌሎች በጎች” ደግሞ ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ያስገኝላቸዋል።—ሉቃስ 12:32፤ 23:43፤ ራእይ 7:9-17፤ ዮሐንስ 10:16
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ለሞቱ ሰዎች እንኳ “ሕይወት” የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
16 ስለ ሞቱ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ ለእነሱም ቢሆን “ሕይወት” ነው። ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የአልዓዛርን እህት ማርታን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” ብሏት ነበር። (ዮሐንስ 11:25) ይሖዋም ለልጁ “የሞትና የመቃብር ቁልፎች” በአደራ ሰጥቶታል፤ ይህም የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ሥልጣን እንደሰጠው ያመለክታል። (ራእይ 1:17, 18) ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ እነዚህን ቁልፎች ተጠቅሞ የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር በመክፈት በውስጡ ያሉት በሙሉ እንዲወጡ ያደርጋል።—ዮሐንስ 5:28, 29
17 ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” ብሎ በአጭሩ በመናገር የምድራዊ ሕይወቱንና አገልግሎቱን ዓላማ ጠቅለል አድርጎ ገልጿል። እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛም ትልቅ ትርጉም አላቸው። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” እንዳለም አስታውስ። (ዮሐንስ 14:6) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ ዛሬም ትልቅ ትርጉም አላቸው። በመሆኑም ኢየሱስን እስከተከተልን ድረስ መንገዳችንን ስተን እንደማንጠፋ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “ወደ አብ” የሚወስደውን መንገድ ሊያሳየን የሚችለው እሱ ብቻ ነው።
ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
18. እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ መሆን ምን ማድረግ ይጠይቃል?
18 ኢየሱስ ከሚጫወተው ወሳኝ ሚና እንዲሁም ስለ አብ ካለው የጠለቀ እውቀት በመነሳት፣ ወልድን ለመከተል የምንመርጥበት በቂ ምክንያት አለን። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንዳየነው እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ መሆናችንን በዋነኝነት የሚያረጋግጠው የምንናገረው ነገር አሊያም ለእሱ ያለን ስሜት ሳይሆን ተግባራችን ነው። ክርስቶስን መከተል ሕይወታችንን እሱ ባስተማራቸው ትምህርቶች መምራትና የእሱን ምሳሌ መኮረጅ ይጠይቃል። (ዮሐንስ 13:15) ይህ አሁን እያነበብከው ያለኸው ለጥናት የሚረዳ መጽሐፍ በዚህ ረገድ ትልቅ እገዛ ሊያደርግልህ ይችላል።
19, 20. ይህ ለጥናት የሚረዳ መጽሐፍ ክርስቶስን ለመከተል በምታደርገው ጥረት እገዛ የሚያደርግልህ እንዴት ነው?
19 በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት በጥልቀት እናጠናለን። ምዕራፎቹ በሦስት ክፍሎች ተመድበዋል። በመጀመሪያ የኢየሱስን ባሕርያትና ነገሮችን ያከናወነበትን መንገድ ጠቅለል አድርገን እንቃኛለን። በሁለተኛ ደረጃ በቅንዓት በመስበክና በማስተማር ረገድ የተወውን ምሳሌ እንመረምራለን። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ፍቅርን እንዴት እንዳንጸባረቀ እንመለከታለን። ከምዕራፍ 3 ጀምሮ “ኢየሱስን መከተል የምትችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። በሣጥኑ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶችና ጥያቄዎች በአነጋገራችንም ሆነ በተግባራችን ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለን እንድናስብ ያደርጉናል።
20 ይሖዋ አምላክ፣ በወረስከው ኃጢአት ምክንያት መንገዱ ጠፍቶህ ከእሱ ርቀህ እንዳትቀር ዝግጅት ስላደረገ ሊመሰገን ይገባል። ይሖዋ፣ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት የምንችልበትን መንገድ እንዲያሳየን በፍቅር ተነሳስቶ ልጁን ሲልክልን ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆበታል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ኢየሱስ “ተከታዬ ሁን” በማለት ያቀረበውን ግብዣ በመቀበልና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ይሖዋ ላሳየን እንዲህ ላለው ታላቅ ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት እንደምትነሳሳ ተስፋ እናደርጋለን።—ዮሐንስ 1:43
a ወልድ ወሳኝ የሆነ ሚና ስለሚጫወት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ትንቢት አዘል መጠሪያዎችና የማዕረግ ስሞች ተሰጥተውታል።—“ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡ አንዳንድ የማዕረግ ስሞች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ለምሳሌ ኢየሱስ በማቴዎስ 10:29-31፤ 18:12-14, 21-35፤ 22:36-40 ላይ የተናገራቸውን ሐሳቦች ተመልከት።