ክፍል 4
አምላክ ማን ነው?
ሰዎች ብዙ አማልክት ያመልካሉ። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነ ያስተምራሉ። እውነተኛው አምላክ አቻ የሌለው፣ የሁሉ የበላይና ዘላለማዊ ነው። በሰማይና በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን በሙሉ የፈጠረውም ሆነ ለእኛ ሕይወት የሰጠን እሱ ነው። በመሆኑም ልናመልከው የሚገባው እሱን ብቻ ነው።
አምላክ ስም አለው፤ ስሙም ይሖዋ ይባላል። አምላክ ለሙሴ (ለሙሳ) እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ወደ እናንተ ልኮኛል።’ ይህ ለዘላለም ስሜ ነው፤ ከትውልድ እስከ ትውልድ የምታወሰውም በዚህ ነው።” (ዘፀአት 3:15) ይሖዋ የሚለው ስም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 7,000 ያህል ጊዜ ይገኛል። መዝሙር 83:18 ስለ አምላክ ሲናገር “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል [ነህ]” ይላል።
ማንም ሰው አምላክን አይቶት አያውቅም። አምላክ ለሙሴ “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” ብሏቸዋል። (ዘፀአት 33:20) አምላክ የሚኖረው በሰማይ ስለሆነ ሰው ሊያየው አይችልም። በመሆኑም በጣዖት፣ በሥዕል ወይም አምላክን እንደሚወክል በሚታሰብ ምስል ፊት መጸለይ ስህተት ነው። ይሖዋ አምላክ በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷል፦ “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ።” (ዘፀአት 20:2-5) በኋላም አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ብሏል።—ኢሳይያስ 42:8
አንዳንድ ሰዎች በአምላክ ቢያምኑም እሱን ማወቅም ሆነ ከእሱ ጋር መቀራረብ እንዲሁም እሱን መፍራት እንጂ መውደድ ከባድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተስ ምን ይመስልሃል? አምላክ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንደሚሰጥ ይሰማሃል? እሱን ማወቅ አልፎ ተርፎም ከእሱ ጋር መቀራረብ የምትችል ይመስልሃል? እስቲ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ አምላክ ባሕርያት ምን እንደሚሉ እንመልከት።