ምዕራፍ 48
ተአምራት ቢፈጽምም በናዝሬት እንኳ ተቀባይነት አላገኘም
ማቴዎስ 9:27-34፤ 13:54-58 ማርቆስ 6:1-6
ዓይነ ስውሮችንና ዱዳ የሆነን ሰው ፈወሰ
የናዝሬት ሰዎች አልተቀበሉትም
ኢየሱስ ቀኑን ያሳለፈው በሥራ ተጠምዶ ነው። ከዲካፖሊስ ክልል ከተመለሰ በኋላ፣ ደም ይፈስሳት የነበረችውን ሴት ፈወሰ፣ ከዚያም የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከሞት አስነሳ። ይሁን እንጂ ውሎው በዚህ አልተቋጨም። ኢየሱስ ከኢያኢሮስ ቤት ወጥቶ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልን” ብለው እየጮኹ ተከተሉት።—ማቴዎስ 9:27
እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን “የዳዊት ልጅ” ብለው መጥራታቸው ኢየሱስ የዳዊት ዙፋን ወራሽና መሲሕ መሆኑን እንደሚያምኑ ያሳያል። ኢየሱስ ለሰዎቹ ጩኸት መልስ አልሰጠም፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ጽናታቸውን ለመፈተን ይሆናል። ሰዎቹም ተስፋ አልቆረጡም። ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ሲገባ እነሱም ተከትለውት ገቡ። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “አዎ ጌታ ሆይ” ብለው በእርግጠኝነት መለሱለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ዓይናቸውን ዳስሶ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው።—ማቴዎስ 9:28, 29
ወዲያውኑ ማየት ቻሉ! ኢየሱስ እንደ ሌላ ጊዜው ሁሉ በዚህ ጊዜም፣ እሱ ያደረገላቸውን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ሰዎቹ ግን በደስታ ስለፈነጠዙ ስለ እሱ በይፋ አወሩ።
እነዚህ ሁለት ሰዎች እየወጡ እያለ ሌሎች ደግሞ ጋኔን ስላደረበት ዱዳ የሆነ ሰው ወደ እሱ አመጡ። ኢየሱስ ጋኔኑን ካስወጣለት በኋላ ዱዳው ወዲያው መናገር ጀመረ። ሕዝቡም በዚህ እጅግ ተደንቀው “በእስራኤል ምድር እንዲህ ያለ ነገር ታይቶ አያውቅም” አሉ። በቦታው ፈሪሳውያንም ተገኝተዋል። ተአምራቱን መካድ አይችሉም፤ በመሆኑም ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም “አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” በማለት ተአምራቱን የፈጸመበትን ኃይል በተመለከተ ትችት ሰነዘሩ።—ማቴዎስ 9:33, 34
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ተመለሰ፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አብረውት ናቸው። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በዚያ ባለው ምኩራብ አስተምሮ ነበር። መጀመሪያ ላይ ሰዎቹ በተናገረው ነገር ቢደነቁም በኋላ ላይ ግን በትምህርቱ ቅር በመሰኘት ሊገድሉት ሞክረው ነበር። አሁን ደግሞ ኢየሱስ የቀድሞ ጎረቤቶቹን ለመርዳት ሌላ ሙከራ አደረገ።
ኢየሱስ በሰንበት ቀን ለማስተማር ወደ ምኩራብ ሄደ። ብዙ ሰዎች የተደነቁ ሲሆን እንዲያውም “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ተአምራት የማድረግ ችሎታ ከየት አገኘ?” ብለው ጠየቁ። ከዚያም እንዲህ አሉ፦ “ይህ የአናጺው ልጅ አይደለም? እናቱስ ማርያም አይደለችም? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉም? እህቶቹስ ሁሉ የሚኖሩት ከእኛ ጋር አይደለም? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?”—ማቴዎስ 13:54-56
ሰዎቹ፣ ኢየሱስ ከእነሱ የተለየ እንደሆነ አልተሰማቸውም። ‘ከልጅነቱ ጀምሮ እናውቀዋለን፤ ታዲያ እንዴት መሲሕ ሊሆን ይችላል?’ ብለው አስበው ይሆናል። ኢየሱስ ታላቅ ጥበብ ያለውና ተአምራት የፈጸመ ቢሆንም ይህን ሁሉ እያዩ ሊቀበሉት አልፈለጉም። የራሱ ዘመዶች እንኳ ሳይቀር በቅርብ የሚያውቁት ሰው በመሆኑ ተሰናክለውበታል፤ በዚህም የተነሳ ኢየሱስ “ነቢይ በገዛ አገሩና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አለ።—ማቴዎስ 13:57
በእርግጥም አለማመናቸው ኢየሱስን እጅግ አስደንቆታል። ስለሆነም “ጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን በመጫን ከመፈወስ በቀር” በዚያ ሌላ ተአምር አልፈጸመም።—ማርቆስ 6:5, 6