ምዕራፍ 12
በጉባኤም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ
ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች በተናገረው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እየሰበኩ ነው። (ሥራ 1:8፤ ማቴ. 24:14) ይህን ለማከናወን ሲሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በነፃ በመስጠት መንፈሳዊ ነገሮችን ለሰዎች አካፍለዋል። ይሖዋ አብረውት ለሚሠሩት ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው በመተማመን በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት ማስቀደማቸውን ቀጥለዋል። (ማቴ. 6:25-34፤ 1 ቆሮ. 3:5-9) በስብከቱ ሥራ የተገኘው ውጤት እነዚህ ክርስቲያኖች የይሖዋ ሞገስና በረከት እንዳልተለያቸው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ
2 አንዳንድ ሰዎች የስብከት ሥራችንን ሲመለከቱ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለሕዝብ የምናሰራጨው ያለምንም ክፍያ እንደሆነ ሲያውቁ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብለው ይጠይቃሉ። እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማተምና ማዘጋጀት ብዙ ወጪ ይጠይቃል። በተጨማሪም ከሕትመት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለሚሠሩና ለስብከቱ ሥራ አመራር ለሚሰጡ እንዲሁም ምሥራቹ እንዲስፋፋ በሌሎች መንገዶች ድጋፍ ለሚያደርጉ ሰዎች የሚያስፈልጉትን የቤቴል ቤቶች መገንባትና መንከባከብ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነገር ነው። ከዚህም ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ በመስክ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን፣ ልዩ አቅኚዎችና በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ሌሎች ክርስቲያኖች በሥራው መቀጠል እንዲችሉ የተወሰነ ቁሳዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በአገራችን ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው?
3 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የሚያደንቁ ብዙ ሰዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በዋነኛነት ለሥራው ድጋፍ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መዋጮአቸውን በአገራቸው ላለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በቀጥታ ይልካሉ። በዚህ መንገድ፣ የይሖዋን የአምልኮ ቤት ለመገንባት በልግስና ድጋፍ የሰጡት የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች የነበራቸው ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ያሳያሉ። (ዘፀ. 35:20-29፤ 1 ዜና 29:9) አንዳንዶች ርስታቸውን ለድርጅቱ በመናዘዝ ስጦታ ይሰጣሉ። ግለሰቦች፣ ጉባኤዎችና ወረዳዎችም መጠነኛ መዋጮ ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉት መዋጮዎች አንድ ላይ ተዳምረው የስብከቱን ሥራ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይውላሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘባቸውንም ሆነ ሌሎች ጥሪቶቻቸውን የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት ማዋል መቻላቸው ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማቸዋል
4 የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘባቸውንም ሆነ ሌሎች ጥሪቶቻቸውን የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት ማዋል መቻላቸው ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈን የሚውል ገንዘብ የሚያስቀምጡበት ሣጥን ነበራቸው። (ዮሐ. 13:29) መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሴቶች፣ ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በንብረታቸው ያገለግሉ እንደነበር ይገልጻል። (ማር. 15:40, 41፤ ሉቃስ 8:3) ሐዋርያው ጳውሎስም አንዳንድ ክርስቲያኖች ምሥራቹ እንዲስፋፋ ለማድረግና እሱ የሚያከናውነውን አገልግሎት ለመደገፍ ባላቸው ፍላጎት ተነሳስተው በፍቅር ያደረጉለትን ቁሳዊ ድጋፍ በአመስጋኝነት ተቀብሏል። (ፊልጵ. 4:14-16፤ 1 ተሰ. 2:9) የይሖዋ ምሥክሮች በቀድሞ ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በአገልግሎት ቀናተኛ በመሆን እንዲሁም የልግስና መንፈስ በማሳየት ረገድ የተዉትን ምሳሌ ይከተላሉ። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “የሕይወትን ውኃ በነፃ” ማዳረስ ተችሏል።—ራእይ 22:17
የጉባኤ ወጪዎችን መሸፈን
5 የጉባኤው ወጪም ቢሆን የሚሸፈነው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። በስብሰባ ወቅት ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ይህን ያህል መስጠት አለበት ተብሎ አይወሰንም ወይም ገንዘብ እንዲሰጥ ጫና አይደረግበትም። ከዚህ ይልቅ ማንም ሰው “በልቡ ያሰበውን” እንዲሰጥ ሲባል በምንሰበሰብባቸው ቦታዎች የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ።—2 ቆሮ. 9:7
6 ለጉባኤው ወጪዎች የሚዋጣው ገንዘብ በዋነኝነት ከስብሰባ አዳራሹ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመሸፈንና አዳራሹን ለመንከባከብ ይውላል። የሽማግሌዎች አካል፣ ከተዋጣው ገንዘብ ላይ የተወሰነው በአገሪቱ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲላክና የዓለም አቀፉን ሥራ ለማስፋፋት እንዲውል ሊወስን ይችላል። ከዚያም ሐሳቡ ለጉባኤው ቀርቦ በድምፀ ውሳኔ እንዲጸድቅ ይደረጋል። በዚህ መንገድ ብዙ ጉባኤዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ በቋሚነት መዋጮ ያደርጋሉ። የጉባኤው አስፋፊዎች በሙሉ፣ አልፎ አልፎ ለሚኖሩት የጉባኤ ወጪዎች ንቁ ከሆኑ ገንዘብ ስለማዋጣት የሚገልጹ ማስታወቂያዎችን በተደጋጋሚ መናገሩ አስፈላጊ አይሆንም።
የመዋጮ ገንዝብ አያያዝ
7 ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ ሁለት ወንድሞች በመዋጮ ሣጥኑ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ያወጡና መጠኑን በጽሑፍ ያሰፍራሉ። (2 ነገ. 12:9, 10፤ 2 ቆሮ. 8:20) የተዋጣው ገንዘብ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እስኪላክ ወይም አስፈላጊ ለሆኑ የጉባኤ ወጪዎች እስኪውል ድረስ በጥንቃቄ እንዲያዝ የሽማግሌዎች አካል አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋል። የጉባኤውን ሒሳብ የሚይዘው ወንድም በየወሩ ለጉባኤው የሒሳብ ሪፖርት አዘጋጅቶ ያቀርባል፤ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ደግሞ በየሦስት ወሩ የጉባኤው ሒሳብ እንዲመረመር ዝግጅት ያደርጋል።
የወረዳ ወጪዎች
8 የወረዳ ስብሰባም ሆነ ሌሎች የወረዳው ወጪዎች የሚሸፈኑት በወረዳው ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት መዋጮ ነው። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች የወረዳውን ወጪዎች ለመሸፈን መዋጮ ማድረግ እንዲችሉ በስብሰባ ቦታዎች የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ። በተጨማሪም ቋሚ ወጪዎችን ለመሸፈን ጉባኤዎች በሌሎች ጊዜያት መዋጮ ሊያደርጉ ይችላሉ።
9 በአብዛኛው ወረዳዎች የራሳቸውን መሠረታዊ ወጪዎች መሸፈን ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ የወረዳው ወጪ ከተሸፈነ በኋላ የሚተርፈው ገንዘብ ደግሞ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ይደረጋል። በወረዳው የባንክ ሒሳብ ውስጥ ያለው ገንዘብ የወረዳ ስብሰባውን ወጪዎች ለመሸፈን ወይም ለቀጣዩ ስብሰባ አዳራሽ ኪራይ ገንዘብ እንደማስያዝ ላሉ በቅድሚያ መከፈል ያለባቸው ወጪዎች የማይበቃ ከሆነ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤዎች መዋጮ እንዲያደርጉ እንዲነገራቸው ሊያደርግ ይችላል። እያንዳንዱ የሽማግሌዎች አካል በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ጉባኤው ለወረዳው ምን ያህል ገንዘብ ማዋጣት እንደሚችል ይወስናል። ከዚያም የጉባኤው አስፋፊዎች በድምፀ ውሳኔ እንዲያጸድቁት ያደርጋል።
10 የወረዳውን ሽማግሌዎች ትኩረት የሚሹ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የወረዳው ሽማግሌዎች የወረዳ ስብሰባ በሚደረግበት ዕለት ይሰበሰባሉ። ወረዳው ከሚያወጣቸው የተወሰኑ ወጪዎች በስተቀር ሁሉንም ወጪዎች በተመለከተ ውሳኔ የሚደረገው ሽማግሌዎቹ በሚያሳልፉት ድምፀ ውሳኔ መሆን ይኖርበታል። በድምፀ ውሳኔ የጸደቀው የገንዘብ መጠን በትክክል ተጠቅሶ በጽሑፍ መስፈር ያለበት ከመሆኑም ሌላ ከወረዳው ገንዘብ ላይ ወጪ በሚደረግበት ጊዜ ሁሉ ፈቃድ ሊሰጥበት ይገባል።
11 የወረዳው ሒሳብ በየተወሰነ ጊዜው እንዲመረመር ዝግጅት መደረግ አለበት።
ድሆችን መርዳት
12 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የገንዘብ ሣጥን የሚይዙበት አንዱ ዓላማ ድሆችን ለመርዳት ነበር። (ማር. 14:3-5፤ ዮሐ. 13:29) ኢየሱስ “ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው” በማለት ስለተናገረ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ድሆችን የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። (ማር. 14:7) ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ኃላፊነት የሚወጡት እንዴት ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች በዕድሜ መግፋት፣ በአቅም ማነስ ወይም ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ሌላ ችግር ሳቢያ ቁሳዊ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እነዚህ ወንድሞች ያሉበትን ሁኔታ የሚያውቁ የቤተሰባቸው አባላት፣ ዘመዶቻቸው ወይም ሌሎች ሰዎች እርዳታ ለማበርከት ይነሳሱ ይሆናል። ይህም ሐዋርያው ዮሐንስ ከጻፈው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው፦ “የዚህ ዓለም ቁሳዊ ንብረት ያለው ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር ‘የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ አለ’ እንዴት ሊባል ይችላል? ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።” (1 ዮሐ. 3:17, 18፤ 2 ተሰ. 3:6-12) እውነተኛው አምልኮ ቁሳዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ትኩረት መስጠትንም ይጨምራል።—ያዕ. 1:27፤ 2:14-17
14 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። ጳውሎስ የሰጠው ምክር በ1 ጢሞቴዎስ 5:3-21 ላይ ይገኛል። እያንዳንዱ ክርስቲያን የገዛ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር የማሟላት ኃላፊነት አለበት። በዕድሜ ለገፉ ወይም የአቅም ገደብ ላለባቸው ክርስቲያኖች ልጆቻቸው፣ የልጅ ልጆቻቸው ወይም ሌሎች የቅርብ ዘመዶቻቸው እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይገባል። መንግሥት ወይም ማኅበራዊ ተቋማት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁሳዊ ድጋፍ የሚሰጡበት ዝግጅት ይኖር ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልገው ግለሰብ ዘመዶች ወይም ሌሎች ሰዎች ግለሰቡ ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆን ሊረዱት ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ጉባኤው ለረጅም ጊዜ በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩና ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞችንና እህቶችን በሆነ መንገድ መርዳት ሊያስፈልገው ይችላል። እነዚህን ወንድሞች ሊረዷቸው የሚችሉ የቤተሰብ አባሎች ወይም ዘመዶች ከሌሉ አሊያም ከመንግሥታዊ ተቋማት በቂ ድጋፍ የሚያገኙበት ዝግጅት ከሌለ የሽማግሌዎች አካል ለእነዚህ ወንድሞች የተወሰነ እርዳታ እንዲደረግ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል። ክርስቲያኖች፣ ያላቸውን ቁሳዊ ነገር ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞቻቸው ማካፈል መቻላቸው ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማቸዋል።
15 ብዙ ወንድሞችና እህቶች በስደት፣ በጦርነት፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ፣ በድርቅ ወይም በዚህ አስጨናቂ ዘመን በሚከሰቱ ሌሎች አደጋዎች ሳቢያ ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። (ማቴ. 24:7-9) ችግር በተከሰተበት አገር ያሉት ጉባኤዎች በዚያ ያሉትን ወንድሞቻቸውን መርዳት የሚችሉበት አቅም ከሌላቸው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በሌላ አገር ያሉ ወንድሞች የሚያስፈልገውን እርዳታ እንዲልኩ ያስተባብራል። ይህ አሠራር በይሁዳ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት በትንሿ እስያ የነበሩ ክርስቲያኖች በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞቻቸው ምግብ በመላክ ከሰጡት እርዳታ ጋር ይመሳሰላል። (1 ቆሮ. 16:1-4፤ 2 ቆሮ. 9:1-5) የእነሱን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር በተግባር የምናሳይ ከመሆኑም ሌላ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናስመሠክራለን።—ዮሐ. 13:35
የጽሑፍ ስርጭት
16 መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ረገድ ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ። በአብዛኛው የሽማግሌዎች አካል የጉባኤውን የጽሑፍ አቅርቦት የሚከታተል አንድ የጉባኤ አገልጋይ ይመድባል። የእነዚህን ጽሑፎች አቅርቦት እንዲከታተሉ የተመደቡት ወንድሞች ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱታል። ለጉባኤው የሚያስፈልጉ በቂ ጽሑፎች እንዲኖሩ ለማድረግ የተሟላ መዝገብ ይይዛሉ።
17 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ጊዜያችን፣ የማሰብ ችሎታችን፣ ጉልበታችን፣ ተሰጥኦዋችንና ቁሳዊ ንብረታችን አልፎ ተርፎም ሕይወታችን ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች እንደሆኑና እሱን ለማገልገል ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ እናውቃለን። (ሉቃስ 17:10፤ 1 ቆሮ. 4:7) ጥሪቶቻችንን ሁሉ በተገቢው መንገድ በመጠቀም ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ይሖዋ በሙሉ ነፍሳችን ለእሱ ያደርን መሆናችንን ለማሳየት ብለን በምናቀርበው ስጦታ ሁሉ እንደሚደሰት ስለምናውቅ ባሉን ውድ ነገሮች ሁሉ እሱን ማክበር እንፈልጋለን። (ምሳሌ 3:9፤ ማር. 14:3-9፤ ሉቃስ 21:1-4፤ ቆላ. 3:23, 24) ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏል። (ማቴ. 10:8) ራሳችንንም ሆነ ጥሪቶቻችንን ለይሖዋ አገልግሎት ስናውል በአጸፋው የላቀ ደስታ እናገኛለን።—ሥራ 20:35