“ነፃነት አፍቃሪዎች” ወደተባለው የወረዳ ስብሰባ እንድትመጡ ተጋብዛችኋል
ከኅዳር ወር 1989 ጀምሮ የነፃነት ጉዳይ ከምን ጊዜም ይበልጥ ጎላ ተደርጓል። በተለይም የምሥራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ለ40 እና ከዚያ ለበለጡ ዓመታት አጥተውት የነበረውን የፖለቲካ ነፃነት አግኝተዋል።
ይሁን እንጂ ከማንኛውም የፖለቲካ ነፃነት የበለጠ አስፈላጊነት ያለው ሌላ ዓይነት ነፃነት አለ። ስለዚህኛው ነፃነት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማንበብ እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ፦ “እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) አዎ፤ በሮሜ 6:18, 22 ላይ እንደምናነበው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች ሰውን ከመፍራትና ከኃጢአትና ከሞት ምርኮኛነት ነፃ ወጥተዋል። እንዲሁም “የይሖዋ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” የሚል ቃል እናነባለን። (2 ቆሮንቶስ 3:17) እንዲያውም የአምላክ ቃል “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብራማ ነፃነት” እንደሚደርስ ብሩህ ተስፋ ይዞልናል።—ሮሜ 8:21
ባሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ክርስቲያናዊ ነፃነት ለማግኘት ከፈለገ እውነተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። ይህ ግን ቀላሉን መንገድ መከተል ማለት አይደለም። ይህን ነፃነት ሊነጥቁን ካሰፈሰፉት ኃይሎች፤ ይኸውም ከሰይጣን ዲያብሎስ፣ እርሱ ከሚመራው ክፉ ዓለምና ከወረስነው የኃጢአት ዝንባሌ አንጻር ሲታይ ይህን ነፃነት ለማግኘት ተጨማሪ ጥረት ያስፈልጋል። ይሖዋ አምላክ በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት እርዳታ አዘጋጅቶልናል።—ሉቃስ 11:13
ሁሉም ነፃነት አፍቃሪዎች ነፃነታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ለማጠናከርና ለመርዳት የዚህ ዓመቱ የወረዳ ስብሰባ “ነፃነት አፍቃሪዎች” የሚለውን አጠቃላይ መልእክት ያጎላል። እነዚህ ስብሰባዎች ዐርብ እለት ጧት በ4:20 ጀመረው እስከ እሑድ 10:15 ድረስ የሚቀጥል የሦስት ቀን እርዝማኔ ይኖራቸዋል። ወደ ስብሰባዎቹ የሚመጡ ሁሉ በሚያነቃቁ ንግግሮች፣ አስደሳች ቃለ ምልልሶች፣ ውጤታማ ትዕይንቶችና ስሜት የሚስቡ ዘመናዊ ድራማዎች በመንፈሳዊ ይነቃቃሉ፣ ይታነጻሉም። በሌላም በኩል ከቆዩና ከአዲስ ጓደኞች ጋር መገናኘቱ የሚያመጣውን ልብን የሚያሞቅ ደስታ፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች በሺህ ከሚቆጠሩ ሌሎች ጋር ሆኖ የመዘመሩንና ከልብ የመነጩ ሕዝባዊ ጸሎቶች ላይ የመካፈሉን ደስታም አነስተኛ ግምት አንሰጠውም።
ሁሉም የይሖዋ ውስን አገልጋዮች ዐርብ ዕለት ጧት እነዚህ ስብሰባዎች ሲጀምሩ ከመገኘት ምንም ነገር እንዲያደናቅፋቸው ፈጽሞ አይፍቀዱ። እንዲሁም ስትመጡ መጽሐፍ ቅዱስና የመዝሙር መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ማስታወሻ ለመያዝ እንድትችሉ ደብተርና እርሳስ ይዛችሁ መምጣትን አትርሱ። እንዲሁም የነፃ ሕዝቦች ክፍል በመሆን ለሚያስፈልጓችሁ መንፈሣዊ ነገሮች ንቁ ሆናችሁ እንድትመጡ እንጋብዛችኋለን።—ማቴዎስ 5:3