ለሁሉም ሕዝቦች የሚሆን ንጹሕ ልሳን
“በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”—ሶፎንያስ 3:9
1, 2. (ሀ) ይሖዋ የሶፎንያስ 3:9ን ትንቢት በመፈጸም በዘመናችን ምን በማድረግ ላይ ነው? (ለ) የሶፎንያስ ትንቢት እንዴት እንደሚነካን ለመረዳት የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?
ይሖዋ አምላክ በዘመናችን በጣም አስደናቂ የሆነ ሥራ በማከናወን ላይ ነው። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን አንድ እያደረገ ነው። ከብዙ ጊዜ በፊት በቅዱስ ቃሉ አስቀድሞ እንደተናገረው ይህን የሚያደርገው እነዚህን ሰዎች አዲስ ልሳን ወይም ቋንቋ በማስተማር ነው።—ሶፎንያስ 3:9
2 ይህ ልሳን ወይም ቋንቋ ምንድን ነው? አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? ይህን ቋንቋ ለመማር በበኩላችን ምን ይፈለግብናል?
የንግግር ስጦታ
3. (ሀ) አዳም ምን አስደናቂ ስጦታ ተሰጥቶት ነበር? (ለ) አዳም ይናገረው የነበረው ቋንቋ ምንድን ነው?
3 በንግግር አማካይነት ከሌሎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ መቻሉ የሰውን ዘር ከሁሉም ዓይነት የእንስሳ ፍጥረታት የሚለየው መለኮታዊ ስጦታ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም በእውቀት ለማሰብ የሚችል አንጎል ተሰጥቶት ነበር። የድምፅ አውታሮች፣ ምላስ፣ ለንግግር የሚረዱ ከንፈሮች እንዲሁም መነጋገሪያ ቃላትና አዳዲስ ቃሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ችሎታ ተሰጥቶት ነበር። አዳም ይሖዋ ሲያነጋግረው ለመስማት ይችል ነበር፤ እንዲሁም አዳም አሳቦቹን በቃላት መግለጽ ይችል ነበር። (ዘፍጥረት 1:28-30፤ 2:16, 17, 19-23) ለአዳም የተሰጠው ቋንቋ በኋላ ዕብራይስጥ በመባል የሚታወቀው ቋንቋ እንደሆነ ከሁኔታዎች በግልጽ መረዳት ይቻላል። ቢያንስ ቢያንስ ሰው በኖረባቸው በመጀመሪያዎቹ 1,757 ዓመታት ሁሉም ሰዎች ይህንን አንድ ቋንቋ ይናገሩ እንደነበረ ከሁኔታዎች በግልጽ ለመረዳት ይቻላል።—ዘፍጥረት 11:1
4. በናምሩድ ዘመን የተፈጸሙ ሁኔታዎች በሰው ቋንቋ ላይ ለውጥ ያመጡት እንዴት ነው?
4 በኋላም በናምሩድ ዘመን ክፉ ሰዎች የጀመሩትን ጥረት ለማክሸፍ ይሖዋ የባቤልን ግንብ ለመሥራት በፈቃደኝነት የተሰባሰቡትን የሁሉንም ሰዎች ቋንቋ እንዲዘበራረቅ አደረገ። (ዘፍጥረት 11:3-9) ይሖዋ በመጀመሪያ ይናገሩት የነበረውን የጋራ መግባቢያ ቋንቋቸው እንዳይታወሳቸው ከአእምሮአቸው ከፋቀ በኋላ አዲስ ቋንቋ በአእምሮአቸው ውስጥ የተከለ ይመስላል። ይህ ለውጥ አዳዲስ መነጋገሪያ ቃሎችን ብቻ ሳይሆን አዲስ ሰዋሰውንና አዲስ ዓይነት አስተሳሰብን የሚጨምር ነበር። ይሖዋ በባቤል ከፈጠራቸው ቋንቋቸው በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎች እስከ ዛሬ ድረስ ቅርጽ እየያዙ መጥተዋል። በቋንቋ አካዳሚዎች መሠረት ዛሬ በመላዋ ምድር ላይ ወደ ሦስት ሺህ የሚያክሉ ቋንቋዎች ይነገራሉ።
5. ‘ወደ ንጹሕ ቋንቋ መለወጥ’ ምን ነገርን እንደሚጨምር ለመወሰን የምንችለው እንዴት ነው?
5 ታዲያ እነዚህን ሁሉ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሰዎች ‘ንጹሑን ልሳን’ ለመናገር የትውልድ ቋንቋቸውን መተውና አምላክ ለአዳም የሰጠውን የመጀመሪያ ቋንቋ መማር ይፈለግባቸዋልን? ትንቢቱ በተነገረበት ጊዜ የነበሩ ሁኔታዎች ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ይረዱናል።
የንጹሕ ቋንቋ አስፈላጊነት
6-8. (ሀ) የሶፎንያስ 3:9 ትንቢት ከመሰጠቱ በፊት በይሁዳ ውስጥ ምን ሃይማኖታዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? (ለ) በይሁዳ ዙሪያ በነበሩት ብሔራት ላይ ምን ዓይነት ዝንባሌ ተስፋፍቶ ነበር?
6 ከዚህ ጊዜ ቀደም ብሎ የይሁዳ መንግሥት ለበዓል የመሰዊያ አጸድ ባቆሙት፣ ምዋርት ባደረጉትና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ባስፋፉት በመጀመሪያ በምናሴ በኋላም በአሞን ተገዝቶ ነበር። (2 ነገሥት 21:1-6፤ 2 ዜና 33:21-23) በዚህም ምክንያት በአሞን ልጅና ወራሽ በኢዮስያስ የግዛት ዘመን ይሖዋ ነቢዩ ሶፎንያስን መለኮታዊው ፍርድ በምድሪቱ ላይ ቅጣት ሊያመጣ መሆኑን እንዲያስጠነቅቅ ኃላፊነት ሰጠው።—ሶፎንያስ 1:1, 2
7 አይሁዶች ከራሳቸው ታሪክና ከቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ እውነተኛው አምላክ መሆኑን ቢያውቁም እንኳ በበዓል አምልኮ ላይ በሚደረጉ የብልግና ሥነ ስርዓቶች ይካፈሉ ነበር። ለጸሐይና ለጨረቃ እንዲሁም ለዞዲያክ የከዋክብት ስብስቦች ይሰግዱ ነበር፤ ይህም በቀጥታ የአምላክን ሕግ ማፍረስ ነበር። (ዘዳግም 4:19፤ 2 ነገሥት 23:5) ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ እንደሆኑ አድርገው በመውሰድ፣ በይሖዋ እንደዚሁም ማልካም በሚባለው የውሸት አምላክ መሐላ በመማል ሃይማኖትን በመቀላቀል ድርጊት ይሳተፉ ነበር። የነበራቸው አስተሳሰብ “[ይሖዋ (አዓት)] መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም” የሚል ነበር። (ሶፎንያስ 1:4-6, 12) በይሁዳ ዙሪያ የነበሩት ብሔራትም ቢሆኑ ሁሉም ይሖዋንና ሕዝቡን በመቃወም የታወቁ ናቸው። ስለዚህ እነርሱም መለኮታዊ ፍትሕ ሲፈጸምባቸው ተራቸውን የሚጠብቁ ነበሩ።—ሶፎንያስ 2:4-15
8 ይሖዋ “አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ” የሚለውን ትንቢት ያስነገረው እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች እየተፈጸሙ በነበሩበት ጊዜ ነው። (ሶፎንያስ 3:9) ታዲያ ይህ ንጹሕ ልሳን ወይም ቋንቋ ምን ነበር?
9. (ሀ) ንጹሑ ቋንቋ የዕብራይስጥ ቋንቋ ወይም የተጻፈው የአምላክ ቃል ብቻ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ንጹሕ ቋንቋ ምን ነበር? በዚህ ቋንቋ የሚናገሩትንስ ሰዎች አኗኗር የሚነካው እንዴት ነው?
9 የዕብራይስጥ ቋንቋ ነበርን? አልነበረም፤ ምክንያቱም ቀድሞውኑም የይሁዳ ሕዝብ የሚጠቀሙት በዚህ ቋንቋ ነበር። ቢሆንም የሚናገሩትና የሚያደርጉት ነገር በይሖዋ ዓይን ንጹሕና ቅን አልነበረም። ንጹሑ ቋንቋ በጽሑፍ ይገኝ የነበረው የአምላክ ቃል ብቻ አልነበረም። ይህም ቢሆን ነበራቸውና። እነርሱ ያስፈልጋቸው የነበረው ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት በትክክል መረዳት ነበር። ይህንንም በመንፈሱ አማካኝነት ሊሰጣቸው ይችል የነበረው ይሖዋ ብቻ ነው። ይህን ንጹሕ ቋንቋ መናገር ሲችሉ አስተሳሰባቸው፣ አነጋገራቸው፣ ጠባያቸው ሁሉ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን አምነው በመቀበላቸው ላይ የሚያተኩር ይሆናል። (ሶፎንያስ 2:3) ትምክህታቸውን በእርሱ ላይ ይጥላሉ፤ ለሉዓላዊነቱም ሙሉ ድጋፋቸውን ይሰጣሉ። ይህ በዛሬው ጊዜ እኛም ብንሆን ልዩ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ለምን?
ንጹሕ ቋንቋ የተሰጣቸው ሰዎች
10. የሶፎንያስ 3:9 ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ የደረሰው መቼ ነው?
10 ትንቢቱ በአንድ የተወሰነ ወቅት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በማመልከት ሶፎንያስ 3:9 እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ጊዜም ለአሕዛብ ሁሉ . . . ንጹሑን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።’ ይህ ጊዜ መቼ ነው? ቁጥር 8 ይሖዋ ‘የቁጣውን ትኩሳት በአሕዛብ ላይ ከማፍሰሱ’ በፊት ‘መንግሥታትን በሚያከማችበት’ ጊዜ ለምድር ትሑታን የንጹሑን ቋንቋ ለውጥ ይሰጣቸዋል በማለት መልሱን ይሰጠናል።
11. (ሀ) ከዘመናችን በፊት የሶፎንያስ 3:9 ትንቢት የተፈጸመባቸው ሁለት ጊዜያት የትኞቹ ነበሩ? (ለ) በዛሬው ጊዜ የትንቢቱ አፈጻጸም ልዩ የሚሆነው እንዴት ነው?
11 በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን ይኸውም የባቢሎን ሠራዊት ፍርዱን እንዲፈጽሙ ይሖዋ ከመፍቀዱ በፊት ብዙ ሰዎች የሐሰት አምልኮትን ትተው ይሖዋን ያገለግሉ ነበር። (2 ዜና 34:3-33) እንደገና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ከመጥፋትዋ በፊት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እውነት ካወቁ በኋላ እርሱን በአንድነት አገልግለዋል። በዚያን ጊዜም የይሖዋን ዓላማ ለማስፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረጋቸው ነገሮች ምክንያት የእውነት ቋንቋ በከፍተኛ ደረጃ ደርጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ የሶፎንያስ ትንቢት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተፈጸመ ያለው በእኛ ዘመን ነው። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ብሔራት ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን በአርማጌዶን ወደሚሆነው ጦርነት በመሰባሰብ ላይ ናቸው። (ራእይ 16:14, 16) ይህ መሰባሰብ መንግሥቱ በ1914 ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይሖዋ ትንቢቱን በመፈጸም በመላው ዓለም ላይ ለሚገኙ ሰዎች የንጹሕ ቋንቋ ለውጥ በመስጠት ላይ ያለውም በዚሁ ጊዜ ነው። ይህንን ቋንቋ መማሩ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ከመጪው ታላቅ መከራ በሕይወት ተርፈው የሚያልፉት ይህን ንጹሕ ቋንቋ የራሳቸው ቋንቋ ያደረጉት ብቻ ናቸው።—ኢዩኤል 2:32
12. (ሀ) በኢሳይያስ 6 ላይ የሚገኘው ራእይ ስለ ንጹሑ ቋንቋ ከተነገረው ትንቢት ጋር ምን ግንኙነት ይኖረዋል? (ለ) ቅቡዓን ቀሪዎች በይሖዋ አገልግሎት ተቀባይነት በማግኘት ለመቀጠል ከፈለጉ እርዳታ ያስፈልጋቸው የነበረው ለምንድን ነው?
12 ከዚህም ጋር በመስማማት ይሖዋ በኢሳይያስ ምዕራፍ ስድስት ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አስደናቂ ራእይ እንዲያስተውሉ የቅቡዓን አገልጋዮቹን የመረዳት ዓይኖች መክፈት የጀመረው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባለው ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር። (ኢሳ 6 ቁጥር 1-4) ይህ ራእይ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል ንጹሕ ከንፈር ሊኖረን እንደሚያስፈልግ ያጎላል። ይሖዋ በከፍተኛ ደረጃ ቅዱስ መሆኑንም ያሳያል። አገልጋዮቹም ቢሆኑ ይህንን ባሕርይ ማንጸባረቅ ያስፈልጋቸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) ሆኖም ቅቡዓን ቀሪዎች በዚህ በኩል እርዳታ አስፈልጓቸዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዓለም ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት በመጠኑ እንዲቆሽሹ ፈቅደው ነበር። “የይሖዋ ፍርሃት ንጹሕ” ወይም የጠራ ነው፤ ይሁን እንጂ የሰውና የሰው ድርጅቶች ፍርሃት ከንፈራቸው ላይ ተጽዕኖ በማድረግ የአምላክን ቃል በስፋት እንዳያውጁ ዝም አሰኝቷቸው ነበር። (መዝሙር 19:9) ከሕዝበ ክርስትና ጋር በነበራቸው ግንኙነት ምክንያት ቀሪዎቹ ገና በአንዳንድ ባሕሎችዋና ልማዶችዋ ቆሽሸው ነበር።
13, 14. (ሀ) ቀሪዎቹ ትክክለኛ ዝንባሌ ያሳዩት እንዴት ነበር? ይሖዋስ ምን እርምጃ ወሰደላቸው? (ለ) ይሖዋ ለቀሪዎቹ ንጹሑን ቋንቋ የሰጣቸው በምን መንገድ ነው?
13 ቀሪዎቹ የነበሩበትን ሁኔታ በመረዳት ልክ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብለው ነበር፦ “እኔም፦ ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፣ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን [ይሖዋን (አዓት)] ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ አልኩ።” (ኢሳይያስ 6:5) የነበሩበት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተገነዘቡ። በተሳሳተው መንገዳቸው በደካማነት ለመቀጠል ወይም በእምቢተኝነት የይሖዋን ተግሣጽ ላለመቀበል አልፈለጉም። በአንድ በኩል ለአምላክ መንግሥት ተራ የከንፈር አገልግሎት እየሰጡ በሌላው በኩል ደግሞ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን የአምላክ መንግሥት እንደሆነ አድርገው ድጋፋቸውን በመስጠት ይህን ካደረጉት ቄሶች ጋር አልተባበሩም።
14 እነዚህ ትሑት ቀሪዎች ንስሐ የመግባት ዝንባሌ በማሳየታቸው ምክንያት ይሖዋ በማይገባ ደግነቱ ከንፈራቸውን አነጻላቸው። ኢሳይያስ 6:6, 7 እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፣ በእጁም ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና፦ እነሆ፣ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።” የሰዎችን ልማዶችና ትምህርቶች እንደ እሳት የሚደመስሰው ከአምላክ ቃል የሚመጣው የሚያነጻ መልዕክት ነው። እርሱም ከልባቸው የሰውን ፍርሃት ነቅሎ በማውጣት በምትኩ በከንፈራቸው ይሖዋን ለማክበር የሚያስችል የሚቃጠል ቅንዓት አስገባ። በዚህ መንገድ ይሖዋ “አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሑን ልሳን [ቃል በቃል ንጹሕ ከንፈር] እመልስላቸዋለሁ” በማለት የገባውን ቃል ፈጽሞአል።—ሶፎንያስ 3:9
15. ይሖዋ ንጹሑን ቋንቋ ለእነርሱ ከሰጠበት ምክንያት ጋር በመስማማት ቀሪዎቹ እሺ የሚል ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?
15 ስለዚህ ዘመናዊ የኢሳይያስ ክፍል የሆኑት በኢሳይያስ 6:8 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ፦ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ብሎ ሲጠይቅ ድምፁን ሲሰሙ በደስታ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት ምላሽ ሰጡ። ለሕዝብ የሚደረገውን አገልግሎት መጀመሩ ለሁሉም ቀላል አልነበረም። ቢሆንም አምላክ የስሙ ሕዝብ አድርጎ እንዲጠቀምባቸው ፈለጉ። መንፈሱም አጠነከራቸው። ቁጥራቸውም እያደገ ሄደ።
16. (ሀ) የቀሪዎቹ ስብከት ምን ያልተጠበቁ ውጤቶችን አስከተለ? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ንጹሑን ቋንቋ እየተናገሩ ለመሆናቸው ማስረጃ የሚያቀርቡት እንዴት ነው?
16 እያደርም ስብከታቸው ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያፈራ መሆኑ በግልጽ መታየት ጀመረ። በእነርሱ በኩል ይሖዋ አንድ ሌላ ቡድን ንጹሑን ልሳን እንዲማር በማድረግ ላይ ነበር። (ኢሳይያስ 55:5) እነዚህ ሰዎች የሰማያዊ ሕይወት ተካፋይ አልነበሩም፤ ይሁን እንጂ የመንግሥቱ ወራሽ ለሆኑት ቀሪዎች ጓደኞች መሆናቸውንና ከእነርሱም ጋር የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎች በመሆን ጎን ለጎን ቆመው ማገልገሉን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። እነርሱም ቀስ በቀስ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” እየወጡ ባሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እስከመሆን በቁጥር አድገዋል። ከአፋቸው የሚወጣው ንግግር ከየትኞቹም የዓለም ከፋፋይ ኃይሎች ጋር የሚያስቆጥራቸው ዓይነት አይደለም። ተስፋቸውን በማንኛውም ሰው ወይም ሰብዓዊ ድርጅት ላይ አልጣሉም። ከዚህ ይልቅ “በታላቅ ድምፅ እየጮኹ፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” ይላሉ።—ራእይ 7:9, 10
ቋንቋውን መማር ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል?
17. ንጹሑን ቋንቋ በደንብ መማራችንና በእርሱ ለመጠቀም ያለንን ችሎታ ማሻሻላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ከይሖዋ ድርጅት ጋር ግንኙነት ከመሠረትን ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ቢሆነንም የንጹሕ ቋንቋ እውቀታችንን ለማሻሻልና በእርሱም በጥሩ ችሎታ ለመጠቀም ብዙ ልናደርገው የምንችለው ነገር አለ። ለዚህ ሲባል ጥረት ማድረጋችንም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይህ ለእውነት ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ስለሆነ ነው።
18, 19. (ሀ) ከመጀመሪያው ጀምሮ ለእውነት ጠንካራ ፍቅርን መኮትኮት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) ይህንንስ ፍቅር ማሳደጋችንን መቀጠል አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
18 በመጀመሪያ ላይ እንደዚህ ያለው ፍቅር አንድን ሰው የተጠቀሱለትን ጥቅሶች ለመረዳት እንዲችል አእምሮውንና ልቡን ለመክፈት ይረዳዋል፤ ወደ ይሖዋ እንዲቀርብና ድርጅቱን እንዲያደንቅም ያንቀሳቅሰዋል። ስለዚህ ከሐሰት ሃይማኖት እግር ብረት ለመላቀቅ የሚረዳው ቁልፍ ነገር የእውነት ፍቅር ነው። አንዳንድ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ፤ ሆኖም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ከተያያዙ ከአንዳንድ ነገሮችና ልቅ ከሆነው የአኗኗር ዘይቤው በፍጹም ለመላቀቅ አይፈልጉም። ለምን? በ2 ተሰሎንቄ 2:10 ላይ እንደተገለጸው “ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር” አይቀበሉም። እንደዚህ ያለውን ፍቅር መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
19 አንድ ጊዜ እውነትን ከያዝን በኋላ ያንን ፍቅር መኮትኮታችን ለመንፈሳዊ እድገታችን አንዱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ይሖዋ እውነትን እንደ አንድ “ቋንቋ” አድርጎ እንደሚጠቅሰው አስታውሱ። አንድ ሰው አዲስ ቋንቋ ሲማር የመነጋገሪያ ቃላት እውቀቱን ለማሳደግ፣ ቃሎችን በትክክል ለመጥራት፣ የሰዋሰው ዝርዝሮችን ለማወቅና የመሳሰሉትን ለማድረግ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ለአዲሱ ቋንቋና እርሱን ለሚናገሩት ሰዎች ያለው ፍቅር እድገት እንዲያደርግ ይረዳዋል። በጥቂት ወራት ውስጥ ቋንቋውን መናገር ይችል ይሆናል፣ ይሁን እንጂ እንደ ትውልድ ቋንቋው አድርጎ ለመናገር ትጋት የተሞላበት የብዙ ዓመታት ጥረት ያስፈልገዋል። ንጹሑን ልሳን ጠንቅቆ ለማወቅም ይህን የመሰለ ጥረት ያስፈልጋል።
20. (ሀ) ንጹሑን ልሳን በእርግጥም ንጹሕ የሚያደርገው ምንድን ነው? (ለ) በየግላችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
20 አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው ቋንቋ ንጹሕ ነው መባሉ በተለይ ተገቢ ነው። ይህም እውነት የሆነው በሰዋሰው ጥሩ ሆኖ ስለተቀነባበረ ሳይሆን በስነ ምግባርና በመንፈሳዊ በኩል ንጹሕ ስለሆነ ነው። በዚህ ቋንቋ ላይ ለመዋሸት፣ ለማታለል ወይም ለተንኮለኛ ምላስ ቦታ የለም። ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ሁልጊዜ እውነትን መናገር ይገባቸዋል። (ሶፎንያስ 3:13፤ ኤፌሶን 4:25) ንግግራቸውም የጾታ ስነምግባርን በተመለከተ ይሖዋ ያወጣቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ማንጸባረቅ ይኖርበታል። (ኤፌሶን 5:3, 4) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ነገር ርኩስ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርጉናል። (ራእይ 18:2-4) የአማልክቶችዋም ምስል ‘የገሙ ጣዖቶች’ ተብለው ተጠርተዋል። (ኤርምያስ 50:2 አዓት) ንጹሑን ቋንቋ የተማሩ ሁሉ የሐሰት አምልኮት ክፍል የሆኑ ነገሮችን ማስወገድ፣ ትምህርቶቹን መተው፣ ከሚያከብሯቸው በዓሎች መላቀቅና ከንግግራቸውም የተሳሳተ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቁ አነጋገሮችን ማስወገድ የሚገባቸው በተገቢ ምክንያት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በራእይ 16:13-16 ላይ ብሔራት የአምላክን መንግሥት በመቃወም እንዲሰበሰቡ የሚገፋፋቸው በአጋንንት አነሳሽነት የተነገረ ፕሮፓጋንዳ ርኩስ እንደሆነ ተገልጾልናል። ስለዚህ ከእነዚህ ርኩስ ነገሮች ውስጥ አንዱም እንኳ አነጋገራችንን እንዳይበክለው ነቅተን መጠበቅ ያስፈልገናል።
21. በንጹሑ ቋንቋ ውስጥ ከመነጋገሪያ ቃላት በተጨማሪ ምን ሌላ አለ?
21 የምንማረው ነገር ቋንቋ ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ እንደዚህ ሲባል ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የይሖዋ ሕዝቦች የሚጠቀሙባቸውን አነጋገሮች ይማራሉ ማለት ብቻ አይደለም። የድምፅ ቃና፣ የፊት አገላለጽና የሰውነት እንቅስቃሴም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ነገሮች በቃላት ብቻ የማይገለጹትን መልዕክቶች ያስተላልፋሉ። በውስጣችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን በትክክል ያንጸባርቃሉ። የኃጢአተኛ ሥጋ ሥራ የሆኑትን ቅንዓትን፣ ምቀኝነትንና ቁጣን ከሥራቸው ነቅለን አውጥተን መሆኑንና አለመሆኑን ሊያሳዩ ይችላሉ። የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ምንም ነገር ሳያግደው ሲሠራ ፍሬው ከሌሎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ይገለጣል።—ገላትያ 5:19-23፤ ኤፌሶን 4:31, 32
22. ንጹሑን ቋንቋ በደንብ ስናውቅ የምናደርገውን ውሳኔ የሚነካው እንዴት ነው?
22 አዲስ ቋንቋ የሚማር ማንኛውም ሰው በራሱ የትውልድ ቋንቋ እየተረጎመ ሳይሆን በአዲሱ ቋንቋ ማሰብ በሚጀምርበት ጊዜ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያውቃል። እኛም በተመሳሳይ እውነትን ስናጠና፣ በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ልናውለው ከልባችን ጥረት ስናደርግና ዘወትር ለሌሎች ስናካፍለው ሁሉንም ነገር ከእውነት ጋር እያዛመድን እያሰብን እንዳለን ቀስ በቀስ እየተገነዘብን እንሄዳለን። ዘላለም የድሮውን ከአዲሱ ጋር እያወዳደርን ምርጫ ለማድረግ ትግል አናደርግም። በትንንሽ ነገሮችም እንኳ ቢሆን አስፈላጊውን መመሪያ ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ስርዓቶች ወደ አእምሮአችን ይመጣሉ።—ምሳሌ 4:1-12
23. የትውልድ ቋንቋቸው ምንም ይሁን ምን በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ንጹሑን ቋንቋ እንደሚናገሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?
23 ሰው የሚናገራቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቋንቋዎች መኖራቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ ንጹሑ ቋንቋ በእነዚህ ሁሉ ሊነገር ይችላል። የይሖዋ ምስክሮች እንደ አንድ በመሆን በመላው ምድር ላይ ለአፍቃሪው ፈጣሪያችን ክብር የሚያመጣውን የሕዝብ ምስክርነት ጐን ለጐን ቆመው ሲያገለግሉ በንጹሑ ቋንቋ በደንብ ይጠቀሙበታል።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የንግግር ስጦታ ምን ነገርን ይጨምራል?
◻ ንጹሑ ልሳን ወይም ቋንቋ ምንድን ነው?
◻ ሶፎንያስ 3:9 የተፈጸመው ለእነማን ነው?
◻ ንጹሑን ቋንቋ በእርግጥ እንደምናፈቅር ማስረጃ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጹሑን ቋንቋ የሚያውቁት ሰዎች ለሌሎች ያሳውቁታል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትውልድ ቋንቋቸው ምንም ዓይነት ቢሆን በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ንጹሑን ቋንቋ ይናገራሉ