አምላክን በመሐሪነቱ ትመስለዋለህን?
“እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።”—ኤፌሶን 5:1 አዓት
1. ሌሎችን የመምሰሉ ጉዳይ ሁላችንንም ሊያሳስበን የሚገባን ለምንድን ነው?
በጥሩም ይሁን በመጥፎ ብዙ ሰዎች ሌሎችን ይከተላሉ። በዙሪያችን ያሉትና ጠባያቸውን የምንከተለው ሰዎች በእኛ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። በመንፈስ የተመራው የምሳሌ 13:20 ጸሐፊ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” ስለዚህ የአምላክ ቃል “በጎ የሆነውን እንጂ ክፉውን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው” ብሎ መናገሩ በጥሩ ምክንያት ነው።—3 ዮሐንስ 11
2. ማንን መምሰል ይገባናል? በምንስ መንገዶች?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አርአያቸውን ልንመስለው የምንችል ብዙ ወንዶችና ሴቶች አሉ። (1 ቆሮንቶስ 4:16፤ 11:1፤ ፊልጵስዩስ 3:17) ሆኖም ከሁሉ በላይ አርአያውን ልንመስለው የሚገባን አምላክ ነው። በኤፌሶን 4:31 እስከ 5:2 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ልናስወግዳቸው የሚገቡንን ባሕርዮችና ድርጊቶች ከገለጸ በኋላ ‘በነፃ ይቅር እየተባባልን እርስ በርሳችን ርኅሩሆች እንድንሆን’ አሳስቦናል። ይህም “እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” ወደሚለው ቁልፍ ማሳሰቢያ ይመራል።
3, 4. አምላክ ስለ ራሱ ምን መግለጫ ሰጥቷል? እርሱ ትክክለኛ አምላክ የመሆኑን ጉዳይ ልናስብበት የሚገባንስ ለምንድን ነው?
3 ልንመስላቸው የሚገቡን የአምላክ መንገዶችና ባሕርዮች ምንድን ናቸው? አምላክ ራሱን ለሙሴ በገለጸበት ጊዜ እንደታየው የእርሱን ባሕርይና ሥራዎች የሚያሳዩ ብዙ ገጽታዎች አሉ፦ “[ይሖዋ (አዓት)] መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ [ሳይቀጣ የማይቀር (አዓት)] የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው።”—ዘፀዓት 34:6, 7
4 ይሖዋ ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድ’ አምላክ ስለሆነ ይህንን የባሕርዩን ገጽታ በትክክል ማወቅና መምሰል ይገባናል። (መዝሙር 33:5፤ 37:28) እርሱ ፈጣሪ፣ እንዲሁም የሰው ዘር የበላይ ፈራጅና ሕግ ሰጪ ነው፤ ስለዚህ ለሁሉም ፍትሑን ይገልጣል። (ኢሳይያስ 33:22) ይህም በሕዝቦቹ በእስራኤል መካከልና በኋላም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍትሕ እንዲደረግ በጠየቀበትና ፍትሕ እንዲኖር ባደረገበት መንገድ በግልጽ ታይቷል።
መለኮታዊ ፍትሕ ሥራ ላይ ውሏል
5, 6. አምላክ ከእስራኤል ጋር በነበረው ግንኙነት ፍትሕ የታየው እንዴት ነው?
5 አምላክ እስራኤልን እንደ ሕዝቡ አድርጎ በመረጠበት ጊዜ ‘ድምፁን በጥብቅ ይታዘዙ እንደሆነና ቃል ኪዳኑን ይጠብቁ እንደሆነ’ ጠይቋቸው ነበር። እነርሱም በሲና ተራራ ግርጌ ተሰብስበው “[ይሖዋ (አዓት)] ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መልሰው ነበር። (ዘፀዓት 19:3-8) ከባድ ኃላፊነት መቀበላቸው ነበር! አምላክ በመላእክት አማካኝነት እስራኤላውያን ለእርሱ የተወሰኑ ሕዝብ እንደ መሆናቸው ሊጠብቋቸው በኃላፊነት የተቀበሏቸውን 600 የሚያክሉ ሕጎች ሰጣቸው። አንድ ሰው ይህንን ሳያደርግ ቢቀር ምን ይደረጋል? አንድ የአምላክ ሕግ አዋቂ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፦ “በመላእክት የተነገረው የአምላክ ቃል ጥብቅ ነበር፤ እርሱን የመተላለፍና ያለ መታዘዝ ድርጊት ከፍትሕ ጋር የተዛመደ ቅጣትን የሚያስከትል ነበር።”—ዕብራውያን 2:2
6 አዎን፣ የማይታዘዝ እስራኤላዊ “ከፍትሕ ጋር የተዛመደ ቅጣት” ይደርስበት ነበር። ይህም ጉድለት ያለው ሰብዓዊ ፍትሕ ሳይሆን ከፈጣሪያችን የመጣ ፍትሕ ነው። አምላክ ሕግ ለሚያፈርሱ የተለያዩ ቅጣቶችን ደንግጎ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በጣም ከባድ የሆነው ቅጣት ‘መቆረጥ’ ወይም መገደል ነበር። ይህም የሚፈጸመው እንደ ጣዖት አምልኮ፣ ዝሙት፣ ከቅርብ የሥጋ ዘመድ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም፣ ከእንስሳ ጋር መገናኘት፣ ግብረ ሰዶም፣ ልጅን መስዋዕት ማድረግ፣ ነፍስ ግድያና በደም አላግባብ መጠቀም የመሳሰሉትን ከባድ ኃጢአቶች በሚሠሩ ሰዎች ላይ ነው። (ዘሌዋውያን 17:14፤ 18:6-17, 21-29) ከዚህም በላይ አውቆና ያለ ምንም ንስሐ የትኛውንም መለኮታዊ ሕግ የሚጥስ እስራኤላዊ ‘ይገደል’ ነበር። (ዘኁልቁ 4:15, 18፤ 15:30, 31) ይህ መለኮታዊ ፍትሕ በሚፈጸምበት ጊዜ እርምጃው የሚያስከትላቸው ውጤቶች ለኃጢአተኛ ዝርያዎቹ ጭምር ይተርፉ ነበር።
7. በጥንት የአምላክ ሕዝቦች መካከል ፍትሕ መደረጉ ያስከተላቸው አንዳንድ ውጤቶች ምንድን ናቸው?
7 እንደነዚህ ያሉት ቅጣቶች መለኮታዊውን ሕግ መጣስ ምን ያህል ከባድ ጉዳይ እንደሆነ አጥብቀው ያሳዩ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ልጅ ሰካራምና ሆዳም ከሆነ በበሰሉ ዳኞች ፊት መቅረብ ነበረበት። ልጁ አውቆ አጥፊ የሆነ፣ ንስሐ የማይገባ በደለኛ ሆኖ ካገኙት ወላጆቹም በእርሱ ላይ በሚከናወነው የሞት ፍርድ ተካፋዮች ይሆናሉ። (ዘዳግም 21:18-21) ወላጆች የሆንን ይህንን ማድረጉ ቀላል እንዳልነበረ ልንገምት እንችላለን። ሆኖም አምላክ በእውነተኛ አምላኪዎች መካከል ክፋት እንዳይስፋፋ ይህን ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ያውቃል። (ሕዝቅኤል 33:17-19) ይህ ዝግጅት የተደረገው “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው። እርሱ የፍትሕ መጓደል የሌለበት፤ ጻድቅና ቅን የሆነ ታማኝ አምላክ ነው” ሊባልለት የሚቻል አምላክ ነው።—ዘዳግም 32:4 አዓት
8. አምላክ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ባደረጋቸው ግንኙነቶች ፍትሕ የታየው እንዴት ነው?
8 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ አምላክ የእስራኤልን ብሔር ተወና የክርስቲያን ጉባኤን መረጠ። ይሁን እንጂ ይሖዋ አልተለወጠም። አሁንም ፍትሕን አጥብቆ ይዟል፤ “የሚያጠፋ እሳት” ተብሎም ሊገለጽ ተችሏል። (ዕብራውያን 12:29፤ ሉቃስ 18:7, 8) ስለዚህ እርሱ ኃጢአተኞችን በማስወገድ በመላው ጉባኤ ውስጥ አምላካዊ ፍርሃት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል አንድ ዝግጅት እንዲቀጥል አድርጓል። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች ኃጢአት ቢሠሩና ንስሐ ባይገቡ ይወገዳሉ።
9. ማስወገድ ሲባል ምን ማለት ነው? ለምንስ ዓላማ ያገለግላል?
9 ማስወገድ ምን ነገሮችን ይጨምራል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ ችግር መፍትሔ ካገኘበት አንድ መንገድ በተግባር ላይ የዋለ ትምህርት እናገኛለን። በቆሮንቶስ ጉባኤ ይገኝ የነበረ አንድ ክርስቲያን ከአባቱ ሚስት ጋር የብልግና ድርጊት ፈጽሞ ንስሐ አልገባም ነበር፤ ስለዚህ ጳውሎስ ከጉባኤ እንዲወገድ መመሪያ ሰጠ። ይህ የተደረገው የአምላክን ሕዝብ ንጽሕና ለመጠበቅ ሲባል ነው፤ ምክንያቱም ‘ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።’ ይህንን ሰው ማስወገዱ አምላክም ሆነ ሕዝቡ ከስድብ እንዲጠበቁ ያደርጋል። ከባድ የሆነው የማስወገድ ቅጣት ሊያስደነግጠውና በእርሱም ሆነ በጉባኤው ውስጥ ተገቢ የሆነ የአምላክ ፍርሃት ያሳድራል።—1 ቆሮንቶስ 5:1-13፤ ከዘዳግም 17:2, 12, 13 ጋር አወዳድር
10. የአምላክ አገልጋዮች አንድ ሰው በሚወገድበት ጊዜ ምን ማድረግ አለባቸው?
10 መለኮታዊው ትዕዛዝ አንድ ክፉ የሆነ ሰው ሲወገድ ክርስቲያኖች ‘ከእርሱ ጋር መተባበር እንደሌለባቸውና እንደዚህ ካለው ሰው ጋር መብል እንኳ መብላት እንደማይገባቸው’ ያዛል።a ስለዚህ እርሱ የአምላክን ሕግ ከሚያከብሩትና በሕጉም መሠረት ለመመላለስ ከሚፈልጉት ታማኞች ጋር ማኅበራዊውን ኑሮ ከሚጨምረው ዝምድና ተቋርጧል። ምናልባት አንዳንዶቹ በአንድ ቤት ውስጥ የማይኖሩ ከቅርብ ቤተሰብ ውጭ ያሉ ዘመዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም በሙሴ ሕግ ሥር ለነበሩትና ክፉውን ልጃቸውን ለመግደል ተካፋይ ለሚሆኑት ዕብራውያን ወላጆች ቀላል እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬም ላሉት ዘመዶች ቀላል ላይሆንላቸው ይችላል። ቢሆንም የአምላክ ትዕዛዝ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ውገዳው ትክክለኛ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 5:1, 6-8, 11፤ ቲቶ 3:10, 11፤ 2 ዮሐንስ 9-11፤ መጠበቂያ ግንብ 9-102 ገጽ 14-17፤ 8-109 ገጽ 17-20 ተመልከት።
11. ከውገዳ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የአምላክ ባሕርይ ገጽታዎች ሊገለጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ሆኖም አምላካችን ፍትሕ ያለው ብቻ ሳይሆን “ምሕረቱ የበዛ፣ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል” አምላክ መሆኑንም አስታውስ። (ዘኁልቁ 14:18) አንድ የተወገደ ሰው መለኮታዊውን ይቅርታ ለማግኘት በመፈለግ ንስሐ ሊገባ እንደሚችል ቃሉ ያሳያል። ከዚያስ በኋላ? ተሞክሮ ያላቸው የበላይ ተመልካቾች ወደ መወገድ ላደረሰው ኃጢአት የንስሐ ማስረጃ አቅርቦ እንደሆነና እንዳልሆነ በጸሎትና በጥንቃቄ ለመወሰን ከእርሱ ጋር ይገናኛሉ። (ከሥራ 26:20 ጋር አወዳድር) ንስሐ ገብቶ ከሆነ 2 ቆሮንቶስ 2:6-11 እንዳመለከተው በቆሮንቶስ ጉባኤ ለነበረው ሰው እንደተደረገው ወደ ጉባኤው እንደገና ሊመለስ ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ የተወገዱ ሰዎች ከአምላክ ጉባኤ ለብዙ ዓመታት ርቀት ስለቆዩ ለእነርሱ ሊደረግ የሚቻል ነገር ይኖራልን?
ሚዛኑ እንዲስተካከል በፍትሕ ላይ ምሕረት ይጨመራል
12, 13. አምላክን መምሰላችን ፍትሑን በማንፀባረቅ መወሰን የሌለበት ለምንድን ነው?
12 ቀደም ሲል የተመለከትነው በዘፀዓት 34:6, 7 ላይ እንደተጠቀሰው በተለይ ከአምላክ ባሕርዮች አንድ ገጽታ ጋር ግንኙነት ያለውን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ ከአምላክ ፍትህ የበለጠ ነገርን ያመለክታል፤ ስለዚህ እርሱን ለመምሰል የሚፈልጉት ፍትሕን በማስፈጸሙ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ አይሆኑም። በሰለሞን የተገነባውን ቤተ መቅደስ ሞዴል የምትሠራ ቢሆን የምታጠናው ከአምዶቹ አንዱን ብቻ ነውን? (1 ነገሥት 7:15-22) እንደዚያ አታደርግም ምክንያቱም ይህ ብቻውን ስለ ቤተ መቅደሱ ሁኔታና ሥራ ሚዛናዊ የሆነ ሥዕል አይሰጥህም። በተመሳሳይ እኛም አምላክን ለመምሰል ከፈለግን እርሱ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል” እንደመሆኑ እንደነዚህ ያሉትን ሌሎች መንገዶቹንና ባሕርዮቹን መቅዳት ያስፈልገናል።
13 ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት እንደምንመለከተው ምሕረትና ይቅር ባይነት መሠረታዊ የሆኑ የአምላክ ባሕርያት ናቸው። የፍትሕ አምላክ በተደጋጋሚ ላጠፉት ጥፋት ሳይቀጣቸው አላለፈም፤ ቢሆንም በቂ የሆነ ምሕረትና ይቅር ባይነት አሳይቷቸዋል። “ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፣ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን። [ይሖዋ (አዓት)] መሐሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀስፍም፣ ለዘላለምም አይቆጣም።” (መዝሙር 103:7-9፤ 106:43-46) አዎን፣ ባለፉት አያሌ መቶ ዓመታት ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች መለስ ብሎ መመልከቱ እነዚህ ቃላት ትክክል መሆናቸውን ያረጋግጣል።—መዝሙር 86:15፤ 145:8, 9፤ ሚክያስ 7:18, 19
14. ኢየሱስ የአምላክን የምሕረት ጠባይ እንደተከተለ ያሳየው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ “[የአምላክ] የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ስለሆነ ይቅር ለማለት ተመሳሳይ የሆነ ምሕረትና ፈቃደኝነት እንደሚያሳይ ልንጠብቅ እንችላለን። (ዕብራውያን 1:3) ለሌሎች ሰዎች ያደረጋቸው ነገሮች እንዳሳዩት ይህንን አድርጎአል። (ማቴዎስ 20:30-34) በተጨማሪም በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ በምናነባቸው እርሱ በተናገራቸው ቃላት ምሕረትን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። በዚያ ላይ የሚገኙት ሦስት ምሳሌዎች ኢየሱስ ይሖዋን እንደሚመስል ያሳያሉ፤ ለእኛም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ይሰጡናል።
ስለ ጠፋው መጨነቅ
15, 16. ኢየሱስ በሉቃስ 15 ላይ የሚገኙትን ምሳሌዎች እንዲናገር ያነሳሳው ምንድን ነው?
15 እነዚህ ምሳሌዎች አምላክ ለኃጢአተኞች በምሕረት እንደሚያስብላቸው ይመሰክራሉ፤ ይህ እኛም ልንቀዳው የሚገባን እርስ በርስ የሚስማማ ድርጊት ነው። እስቲ ምሳሌው የተነገረበትን ሁኔታ እንመልከት፦ “ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ [ወደ ኢየሱስ] ይቀርቡ ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎችም፦ ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጎራጎሩ።”—ሉቃስ 15:1, 2
16 በዚህ ቦታ ላይ የነበሩት በሙሉ አይሁዶች ነበሩ። ፈሪሳውያንና ጻፎች ሕጋዊ ጽድቅ ሊባል በሚቻለው ከሙሴ ሕግ ጋር በትክክል ተስማምተን እንሄዳለን በሚለው አቋማቸው ይኩራሩ ነበር። ሆኖም አምላክ እንደዚህ ባለው ራስን በራስ የማጽደቅ ድርጊት አልተስማማም። (ሉቃስ 16:15) እዚህ ላይ የተጠቀሱት ቀራጮች ለሮም ቀረጥ ይሰበስቡ የነበሩ አይሁዶች ናቸው። ብዙዎቹ ወገኖቻቸው ከሆኑት አይሁዶች ከመጠን ያለፈ ገንዘብ ይጠይቁ ስለነበር የተጠላ ቡድን ነበሩ። (ሉቃስ 19:2, 8) ከስነ ምግባር ውጭ የሆነ ኑሮ የሚኖሩትንና ጋለሞታዎችን ከሚጨምሩት “ኃጢአተኞች” የሚመደቡ ነበሩ። (ሉቃስ 5:27-32፤ ማቴዎስ 21:32) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያጉረመረሙበትን የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦
17. በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኘው የኢየሱስ የመጀመሪያ ምሳሌ ምንድን ነው?
17 “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፣ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ፦ የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።” ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ሥዕላዊ ምሳሌውን ለመረዳት ይችላሉ፤ ምክንያቱም በጎችና የበግ እረኞች በአካባቢው ይገኙ ነበር። እረኛው ስለተጨነቀ 99ኙን በጎች በተሰማሩበት ቦታ ትቶ የተቅበዘበዘውን ሊፈልግ ሄደ። እስከሚያገኘውም ድረስ ሳያቋርጥ ፍለጋ በማድረግ ፍርሃት ያደረበትን በግ በርህራሄ ተሸክሞ ወደ መንጋው መለሰው።—ሉቃስ 15:4-7
18. በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ በሚገኘው በሁለተኛው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ ጎልቶ እንደተገለጸው ለደስታ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
18 ኢየሱስ ቀጥሎ ሁለተኛውን ምሳሌ ተናገረ፦ “ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፣ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጎረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ፦ የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” (ሉቃስ 15:8-10) ድሪም ለአንድ ሠራተኛ የአንድ ሙሉ ቀን ደሞዝ የሚያክል ነበር። ሴትየዋ የጠፋባት ሳንቲም በውርሻ ያገኘችው ሀብት ወይም ለጌጥ እንዲያገለግል ሆኖ የተሠራ ዕቃ ይሆናል። ዕቃው ሲጠፋባትም ገንዘብዋን ለማግኘት ጠንክራ ፈለገች፤ ሲገኝም እርስዋና ጓደኞችዋ የሆኑት ሴቶች አብረው ተደሰቱ። ታዲያ ይህ ስለ አምላክ ምን ይነግረናል?
ሰማያዊ ደስታ—በምን ምክንያት?
19, 20. በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ የመጀመሪያ ሁለት ምሳሌዎች በቅድሚያ ስለ ማን የተነገሩ ናቸው? ምንስ ማዕከላዊ ነጥብ ይዘዋል?
19 እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ከሁለት ወራት አካባቢ በፊት ራሱን ለበጎቹ ነፍሱን የሚሰጥ “መልካም እረኛ” እንደሆነ ባስታወቀው በኢየሱስ ላይ ለተሰነዘረ ትችት መልስ የተሰጡ ነበሩ። (ዮሐንስ 10:11-15) ቢሆንም ምሳሌዎቹ በተለይ ስለ ኢየሱስ የተነገሩ ብቻ አልነበሩም። ጻፎችና ፈሪሳውያን መማር የሚያስፈልጓቸው ትምህርቶች በአምላክ አስተሳሰብና መንገዶች ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ በሰማይ ደስታ ይሆናል ሲል ተናገረ። እነዚህ ሃይማኖተኞች ይሖዋን እንደሚያገለግሉ ይናገሩ እንጂ እርሱን አይመስሉም ነበር። በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ የተከተላቸው የምህረት መንገዶች የአባቱን ፈቃድ የሚያንጸባርቁ ነበሩ።—ሉቃስ 18:10-14፤ ዮሐንስ 8:28, 29፤ 12:47-50፤ 14:7-11
20 ከመቶዎቹ ውስጥ አንዱ ለደስታ ምክንያት ከሆነ ከአሥሩ ሳንቲሞች አንዱ የበለጠ ለደስታ ምክንያት ይሆናል። ዛሬም ቢሆን ሴትየዋ ገንዘብዋን በማግኘትዋ የተሰማትን ዓይነት ስሜት ለማየት እንችላለን! እዚህም ቢሆን ትምህርቱ የሚያተኩረው “አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በመግባቱ” በሰማይ “የአምላክ መላእክት” ከይሖዋ ጋር በመደሰታቸው ላይ ነው። “ንስሐ ሲገባ” የሚለውን በመጨረሻ ላይ የተጠቀሰውን ቃል ልብ በል። እነዚህ ምሳሌዎች ንስሐ ስለሚገቡ ኃጢአተኞች የሚገልጹ ናቸው። ሁለቱም ምሳሌዎች ኃጢአተኞች ንስሐ በመግባታቸው መደሰቱ ተገቢ መሆኑን አጥብቀው እንደገለጹ ለመመልከት ትችላለህ።
21. በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ ከሚገኙት የኢየሱስ ምሳሌዎች ምን ትምህርት ማግኘት ይገባናል?
21 እነዚህ ላይ ላዩን ከሕጉ ጋር ስምምነት እንዳላቸው ሆኖ የሚሰማቸው የተጣመሙ የሃይማኖት መሪዎች አምላክ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ . . . አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” መሆኑን ረስተው ነበር። (ዘፀዓት 34:6, 7) ይህንን የአምላክ መንገዶችና ባሕርይ ገጽታ ምሳሌ ቢከተሉ ኖሮ ኢየሱስ ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች ያሳየውን ምሕረት ያደንቁ ነበር። እኛስ እንዴት ነን? ትምህርቱን ወደ ልባችን በማስገባት በሥራ ላይ እናውለዋለንን? እስቲ ሦስተኛውን የኢየሱስ ምሳሌ እንመልከት።
ንስሐና ምሕረት በተግባር ሲታይ
22. ኢየሱስ በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ የሰጠው ሦስተኛ ምሳሌው በአጭር ምንድን ነው?
22 ይህ ምሳሌ በተለምዶ የአባካኙ ወይም የኰብላዩ ልጅ ምሳሌ ተብሎ ይጠራል። ሆኖም ስታነበው አንዳንዶች ለምን የአባት ፍቅር ምሳሌ አድርገው እንደሚመለከቱት ታያለህ። ምሳሌው በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለ አንድ ታናሽ ልጅ የሚደርሰውን ውርሻ ከአባቱ ስለመውሰዱ ይናገራል። (ከዘዳግም 21:17 ጋር አወዳድር) ይህ ልጅ ሩቅ አገር ሄዶ ገንዘቡን ሁሉ በማይረቡ ነገሮች አባክኖ ጨረሰ። በኋላም የእሪያ ጥበቃ ሥራ ተቀጠረ፣ እንዲያውም የእሪያዎቹን ምግብ እስኪመኝ ድረስ ተቸገረ። በመጨረሻም ወደ አእምሮው ተመለሰና ለአባቱ እንደ ተራ ሠራተኛ ተቀጥሮ ለመሥራት ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ። ወደ ቤቱ ሲቀርብ አባቱ በጥሩ ሁኔታ ተቀበለው፣ ድግስም ደገሰ። በቤት ሥራውን እየሠራ ቀርቶ የነበረው ታላቅ ወንድሙ ግን በተደረገው ምሕረት ተቆጣ። ነገር ግን አባትየው ሞታ የነበረው ልጅ አሁን ሕያው በመሆኑ መደሰት እንደሚገባቸው ተናገረ።—ሉቃስ 15:11-32
23. ስለ አባካኙ ልጅ ከተነገረው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል?
23 አንዳንድ ጻፎችና ፈሪሳውያን እንደ ታናሹ ልጅ ከተመሰሉት ኃጢአተኞች አንጻር ሲታዩ እነርሱ ከታላቁ ልጅ ጋር እንደሚመሳሰሉ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም የምሳሌውን ቁልፍ ነጥብ ተረድተው ነበርን? እኛስ? ምሳሌው የመሐሪውን ሰማያዊ አባታችንን አንድ ከፍተኛ ባሕርይ ይኸውም ኃጢአተኛው በሚያሳየው ልባዊ ንስሐና ለውጥ መሠረት ይቅር ለማለት ያለውን ፈቃደኝነት ያጎላል። ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ተቀባይነት ማግኘታቸው አድማጮች የደስታ ምላሽ እንዲሰጡ ገፋፍቷቸው መሆን ይኖርበታል። አምላክ ነገሮችን የሚያየውና የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። እርሱን የሚመስሉትም እንደዚሁ ማድረግ ይገባቸዋል።—ኢሳይያስ 1:16, 17፤ 55:6, 7
24, 25. የትኞቹን የአምላክ መንገዶች ለመከተል መፈለግ ይኖርብናል?
24 በግልጽ እንደሚታየው የአምላክ መንገዶች ሁሉ የሚታወቁት በፍትሑ ነው፤ ስለዚህ ይሖዋን ለመምሰል የሚፈልጉት ሁሉ ፍትሕን ከፍ አድርገው መመልከትና መከተል አለባቸው። ሆኖም አምላካችን ረቂቅ ወይም ግትር በሆነ ፍትሕ ብቻ የሚሠራ አይደለም። ምሕረቱና ፍቅሩ ታላቅ ነው። ይህንንም እውነተኛ ንስሐ ተመልክቶ ይቅር ለማለት ባለው ፈቃደኝነት አሳይቶታል። ስለዚህ ጳውሎስ ይቅር ባይ መሆናችንን አምላክን ከመምሰላችን ጋር አያይዞ መግለጹ ተገቢ ነው፦ “እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። እንግዲህ እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን [የምትመስሉ (አዓት)] ሁኑ። . . . በፍቅር ተመላለሱ።”—ኤፌሶን 4:32 እስከ 5:2
25 እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋን ፍትሕ እንዲሁም ምሕረቱንና ይቅር ለማለት ያለውን ፈቃደኛነት ለመቅዳት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲሞክሩ ቆይተዋል። እርሱን የበለጠ እያወቅነው በሄድን መጠን በእነዚህ ነገሮች እርሱን ለመምሰል የምናደርገው ሙከራ በይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ታዲያ ይህንን አሁን በቅርቡ የኃጢአት መንገድ በመከተሉ ምክንያት ከባድ ተግሣጽ በተሰጠው ሰው ላይ እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን? እስቲ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ማስወገድ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ አንድ ቡድን በአንድ ወቅት ጥሩ አቋም ካላቸው አባሎች ጋር የነበረውን የአባልነት መብት በሚክድበት ጊዜ የሚወሰድ እርምጃ ነው። . . . ማስወገድ በክርስቲያን ዘመን አንድ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ አንድን በደለኛ ከቅዱስ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት፣ ከጉባኤው አምልኮና ምናልባትም ከማንኛውም ዓይነት ማኅበራዊ ግንኙነት የሚያግድበት እርምጃ ነው።”—ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳክሎፔዲያ
ምን ነገሮችን ተምረሃል?
◻ በእስራኤል ጉባኤ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የአምላክ ፍትሕ የተገለጸው እንዴት ነው?
◻ ከፍትሑ በተጨማሪ የአምላክን ምሕረት መከተል የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ በሉቃስ ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኙት ሦስት ምሳሌዎች እንዲነገሩ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? ለእኛስ ምን ትምህርት ሊሰጡን ይገባል?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሲና ተራራ ፊት የሚገኘው የኤር-ራሃ ሜዳ (በግራ በኩል የሚገኘው አካባቢ)
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian