“አለማመኔን እርዳው!”
“የብላቴናው አባት ጮኾ፦ ‘አምናለሁ! አለማመኔን እርዳው!’ አለ።”—ማርቆስ 9:24
1. አንድን አባት “አለማመኔን እርዳው” ብሎ እንዲጮህ ያደረገው ምን ነበር?
አንድ ጋኔን የያዘው ልጅ አባት በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቆሟል። ይህ ሰው ብላቴናው እንዲፈወስለት በጣም ጓጉቶ ነበር! የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ጋኔኑን ለማውጣት የሚያስችል እምነት አልነበራቸውም። አባትየው ግን “አምናለሁ! አለማመኔን እርዳው!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስ አምላክ በሰጠው ኃይል አማካኝነት ጋኔኑን አወጣለት። ይህን በማድረጉም ያለ ጥርጥር የልጁን አባት እምነት አጠንክሮታል።—ማርቆስ 9:14-29
2. እምነትን በሚመለከት ክርስቲያኖች የማያፍሩት በምን ሁለት መንገዶች ነው?
2 ማንኛውም የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ ተስፋ እንደነበረው እንደዚህ አባት “አምናለሁ!” ለማለት እፍረት አይሰማውም። አሿፊዎች የአምላክን ኃይል፣ የቃሉን እውነተኛነትና ሕላዌውንም ሳይቀር ይክዱ ይሆናል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን በይሖዋ አምላክ እምነት እንዳላቸው ያለማወላወል ያስታውቃሉ። ሆኖም በግል ጸሎታቸው ለሰማያዊ አባታቸው በሚናገሩበት ጊዜ እነዚህ ግለሰቦች “አለማመኔን እርዳው!” ብለው ይለምኑ ይሆናል። ይህንንም ልመና የሚያቀርቡት ምንም ፍርሐት ሳይሰማቸው ነው። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት እንኳን “እምነት ጨምርልን” ብለው እንደለመኑ ያውቃሉ።—ሉቃስ 17:5
3. ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ “እምነት” የሚለውን ቃል የተገለገለበት ሁኔታ ምን ልዩ ትርጉም አለው?
3 በተለይ ደግሞ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ እምነት ብዙ የሚናገሩት አላቸው። እንዲያውም የዮሐንስ ወንጌል በሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች ውስጥ ከተጠቀሱት ከ40 በመቶ ለሚበልጡ ጊዜያት ከ“እምነት” ጋር የተዛመዱ የተለያዩ የግሪክኛ ቃላትን ተጠቅሞአል። ዮሐንስ እምነት መኖሩ ብቻ በቂ ያለመሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። እምነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው። በ98 እዘአ አካባቢ ሲጽፍ በእምነት ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለማጥመድ የተዘረጋውን የክህደት መርዛማ መረብ ተመልክቷል። (ሥራ 20:28-30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3፤ 1 ዮሐንስ 2:18, 19) ስለዚህ እምነት ማሳየትና ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያስመሰክሩ ማስረጃዎችን ማቅረብ አስፈላጊ ነበር። አስቸጋሪ ጊዜ እየመጣ ነበር።
4. እምነት ላላቸው ሰዎች ምንም የማይቻል ነገር የሌለው ለምንድነው?
4 እምነት ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት ችግር እንዲቋቋሙ ያስችላቸዋል። ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል” እምነት ካለቻቸው የሚሳናቸው ነገር እንደማይኖር ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 17:20) በዚህ መንገድም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነውን የእምነት ኃይል ጐላ አድርጎ ገልጾአል። በመሆኑም ኢየሱስ ጐላ አድርጎ የገለጸው ሰዎች ሊሠሩት ስለሚችሉት ነገር ሳይሆን የአምላክ መንፈስ ወይም ፈጣን ኃይል ስለሚሠራው ነገር ነበር። በሱ ማለት በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ሰዎች ጥቃቅኗን መሰናክልና ችግር ተራራ አያደርጉትም። የአምላክ መንፈስ የሚሰጠውን ጥበብ በሥራ ላይ ማዋል ነገሮችን በተገቢው አስተያየት እንዲመለከቱ ይረዳቸዋል። አሳሳቢ ችግሮችም እንኳን ጽናት በሚሰጠው የአምላክ ኃይል ይጠወልጋሉ።—ማቴዎስ 21:21, 22፤ ማርቆስ 11:22-24፤ ሉቃስ 17:5, 6
እምነት እንዳይጠፋ መጸለይ
5-7. (ሀ) ኢየሱስ መታሰቢያውን ሲደነግግ ስለ እምነት ምን የማስጠንቀቂያ ቃላት ተነገረ? (ለ) የጴጥሮስ እምነት ወንድሞቹን ያጠነከረው እንዴት ነው?
5 በ33 እዘአ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር የማለፍን በዓል ለመጨረሻ ጊዜ አከበረ። ከዚያም የአስቆሮቱን ይሁዳ ካስወጣ በኋላ እንደሚከተለው በማለት የመታሰቢያውን በዓል ደነገገ፦ “አባቴ እኔን እንደሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ . . . እሾማችኋለሁ። ስምዖን ሆይ እነሆ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ። እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለአንተ አማለድሁ። አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።”—ሉቃስ 22:28-32
6 ኢየሱስ የስምኦን ጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ጸልዮአል። ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ በመተማመን ኢየሱስን ፈጽሞ እንደማይክድ ቢናገርም ጥቂት ቆይቶ ወዲያውኑ ሦስት ጊዜ ክዶታል። (ሉቃስ 22:33, 34, 54-62) እንዲያውም በትንቢት እንደተነገረው እረኛው ሲመታ በጐቹ ተበታተኑ። (ዘካርያስ 13:7፤ ማርቆስ 14:27) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በፍርሃት ወጥመድ ከወደቀበት ሲያገግም መንፈሳዊ ወንድሞቹን አጽናንቷል። የእምነተ ቢሱን የይሁዳ አስቆሮቱን ቦታ የሚተካ ሰው የመምረጡን ጉዳይ ያነሣው እሱ ነበር። ጴጥሮስ በ33 እዘአ የጴንጠቆስጤ ዕለት የሐዋርያቱ ቃል አቀባይ በመሆን አይሁዳውያን የመንግሥቱ አባሎች እንዲሆኑ መንገድ በመክፈት ኢየሱስ የሰጠውን የመጀመሪያውን “ቁልፍ” ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 16:19፤ ሥራ 1:15 እስከ 2:41) ሰይጣን ሐዋርያትን እንደ ስንዴ እንዲያበጥራቸው ጠይቆ ነበር። አምላክ ግን እምነታቸው እንዳይጠፋ ጠብቋቸዋል።
7 ጴጥሮስ ኢየሱስ “እምነትህ እንዳይጠፋ ስለአንተ አማለድሁ” ሲል በሰማው ጊዜ እንዴት እንደተሰማው ገምት። እስቲ አስብ! የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ የጸለየው የሱ ጌታና መምህር ነበር። ደግሞም አልጠፋም ወይም አልተዳከመም። እንዲያውም በጴንጠቆስጤ ዕለት ጴጥሮስና ሌሎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በሰማያዊ ክብር ከክርስቶስ ጋር የኋላ ኋላ ተባባሪ ወራሾች ይሆኑ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ለመቀባት የመጀመሪያዎቹ ሆኑ። ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን መንፈስ ቅዱስ በነሱ ላይ ይሠራ ስለነበር ከምንጊዜውም የበለጠ ፍሬዎቹን እምነትንም ጭምር ማሳየት ችለው ነበር። “እምነት ጨምርልን” ብለው ላቀረቡት ልመና እንዴት ዓይነት ግሩም መልስ ነበር!—ሉቃስ 17:5፤ ገላትያ 3:2, 22-26፤ 5:22, 23
ወደፊት የሚመጡ ፈተናዎችን መቋቋም
8. ድርጅቱ የ1 ተሰሎንቄ 5:3ን ፍጻሜ በሚመለከት ምን ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ ነው የሰጠን?
8 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በቅርቡ “ሰላምና ደህንነት!” የሚል ጩኸት ወይም አዋጅ እንሰማለን። (1 ተሰሎንቄ 5:3) ይህስ እምነታችንን ፈተና ላይ ይጥለው ይሆን? አዎን መንግሥታት ሰላምን ለማምጣት የተሳካላቸው ይመስለንና ከጥበቃችን የመወሰድ አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል። ነገር ግን ሰላምን ለማምጣት ይሖዋ አምላክ ማንኛውንም የዚህ ዓለም ወኪል እንደማይጠቀም ካወቅን በዚያ የሰላም አዋጅ ነጋሪዎች መንፈስ አንካፈልም። ይሖዋ እውነተኛ ሰላምን የሚያመጣበት የራሱ መንገድ አለው። ያም በኢየሱስ ክርስቶስ በምትተዳደረው በራሱ መንግሥት አማካኝነት ብቻ ነው። ስለዚህ መንግሥታት ሰላምን ለማምጣት የቱንም ያህል ይሳካላቸው የሚያገኙት ውጤት ቅጽበታዊና ለሽፋን ያህል ብቻ ነው። በዚህ ረገድ እንድንጠነቀቅ እኛን ለመርዳት “ታማኝና ልባም ባሪያ” የይሖዋ አገልጋዮች የዚህ አሮጌ ሥርዓት መንግሥታት በሚያውጁት የ“ሰላምና ደህንነት” አስመሳይ አዋጅ እንዳንዘናጋ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ማቅረቡን ይቀጥላል።—ማቴዎስ 24:45-47
9. የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ድፍረትና እምነት የሚጠይቅብን ለምንድነው?
9 የ“ሰላምና ደህንነት” አዋጅ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ለሚመጣው “ድንገተኛ ጥፋት” ምልክት ነው። (ራእይ 17:1-6፤ 18:4, 5) ይህ ራሱ የክርስቲያን እምነትን ይፈትናል። የሐሰት ሃይማኖት ሲፈራርስ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነት ጸንተው ይቆሙ ይሆን? እንዴታ! ለብዙ ሰዎች ያልተጠበቀና የማይገባ የሚሆነው ይህ ጥፋት በሰው የሚደረግ አይደለም። ይህ በእርግጥ የሐሰት ሃይማኖት ሙልጭ አድርጋ የሰደበችውን የይሖዋን ስም የሚያስቀድስ የይሖዋ ፍርድ መሆኑን ሕዝቦች ማወቅ አለባቸው። ነገር ግን ሕዝቦች የሚነግራቸው ሰው ሳይኖር እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ከይሖዋ ምሥክሮች በቀር ሌላ ማን ሊነግራቸውስ ይታሰባል?—ከሕዝቅኤል 35:14, 15ና ከሮሜ 10:13-15 ጋር አወዳድር።
10. ጐግ በይሖዋ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እምነት ፈታኝ የሚሆነው ለምንድነው?
10 የይሖዋ ቅቡዓን ምሥክሮችና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ባልንጀሮቻቸው በታላቂቱ ባቢሎን ላይና በቀረውም የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ላይ ሊፈጸም ቀርቦ ስላለው የይሖዋ ፍርድ ለሌሎች ለመናገር የሚያስፈልገው ድፍረት ነበራቸው፣ አላቸውም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን የተዋረደ ደረጃውን በሚያመለክተው የማጐግ ጐግ ሚናው በአምላክ ሕዝቦች ላይ ያልተቆጠበ ጥቃት ለማድረስ ምድራዊ ሠራዊቱን ይመራል። የይሖዋ ምሥክሮችን ለመጠበቅ መለኰታዊ ኃይል ጣልቃ ሊገባ ስለመቻሉ እምነት ይፈተናል። ነገር ግን የአምላክ ቃል እንደተነበየው ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያድን እምነት ሊኖረን ይችላል።—ሕዝቅኤል 38:16፤ 39:18-23
11, 12. (ሀ) በውሃ መጥለቅለቅ ወቅት ለኖህና ለቤተሰቡ መዳንን ያረጋገጠላቸው ምንድነው? (ለ) በታላቁ መከራ ወቅት ስለምን ነገር መጨነቅ አያስፈልገንም?
11 ዛሬ አምላክ ሕዝቡን በ“ታላቁ መከራ” ወቅት እንዴት አድርጎ እንደሚጠብቃቸው በትክክል አናውቅም። ይሁን እንጂ ይህ የመጠበቅና የመከላከል ኃይሉን እንድንጠራጠር ምክንያት አይሆንም። (ማቴዎስ 24:21, 22) በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ሁኔታ ኖህና ቤተሰቡ በውሃ መጥለቅለቅ ወቅት የነበሩበትን ሁኔታ ይመስላል። በመርከቧ ውስጥ ተዘግተው የጥፋቱ ውሃ በዙሪያቸው ሲዥጐደጐድ በዚህ የመለኰታዊ ኃይል መግለጫ ተደንቀውና ከልብ ጸልየው መሆን አለበት። “መርከቡ በእርግጥ የጥፋት ኃይሎቹን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ነበረውን?” መጥለቅለቁ እስኪያልፍ ድረስ የሚበቃ በቂ ምግብ አለንን? ከዚያ በኋላስ በምድር ላይ የሚኖረውን የተለወጠ ሁኔታ ለማቋቋም እንችላለንን?” ብለው ራሳቸውን እየጠየቁ እንደተጨነቁ ቅዱስ ጽሑፉ አያመለክትም። ከጊዜ በኋላ የደረሱት ነገሮች እንዲህ ዓይነቶቹ ጭንቀቶች መሠረት የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
12 ኖህና ቤተሰቡ መዳናቸውን ለማረጋገጥ እምነታቸውን በሥራ መግለጽ ነበረባቸው። ይህም ማለት የአምላክን መመሪያና የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተል ማለት ነበር። በታላቁ መከራ ወቅትም የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተልና በድርጅቱ በኩል የሚያስተላልፍልንን የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ አስፈላጊ ይሆናል። እንዲህ ካደረግን መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጐቶቻችን የሚሟሉልን እንዴት ይሆን? በዕድሜ ለገፉና ልዩ እንክብካቤ ወይም አያያዝ ለሚያስፈልጋቸው ምን ዝግጅት ይደረጋል? ይሖዋ ከጥፋት ተርፈን ወደ አዲሱ ዓለም እንድንገባ የሚያስችለን እንዴት ነው?” እያልን ለመጨነቅና ለመጠየቅ ምክንያት አይኖረንም። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ በጠንካራ እምነት ማንኛውንም ነገር ሁሉን ማድረግ በሚችለው በአምላክ እጅ ይተዉታል።—ከማቴዎስ 6:25-33 ጋር አወዳድር።
13. ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የአብርሃም ዓይነት እምነት የሚያስፈልገን ለምንድነው?
13 አንዴ ታላቁ መከራ ከጀመረ በአምላክ ያለን እምነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠነክር አያጠራጥርም። ከሁሉ በላይ ይሖዋ አደርጋለሁ ብሎ የተናገረውን ነገር እየፈጸመው እንዳለ ልናይ ነው። ፍርዱን ሲፈጽም በገዛ ዓይኖቻችን ልናይ ነው! ነገር ግን አምላክ ክፉዎችን በሚያጠፋበት ጊዜ ሕዝቡን እንደሚያድን እኛ በግላችን እምነት ይኖረን ይሆን? “የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ እንደሚፈርድ” እና ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር እንደማያጠፋ እምነት እንደነበረው እንደ አብርሃም እንሆን ይሆን?—ዘፍጥረት 18:23, 25
14. እምነታችንን እንድንመረምርና ልናጠነክረው ጥረት እንድናደርግ ሊያደርጉን የሚገቡ ምን ጥያቄዎች ናቸው?
14 አሁኑኑ እምነታችንን መገንባታችን በጣም አስፈላጊ ነው። በጣም ቅርብ በሆነው በዚህ የነገሮች ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ “ለቅዱስ ኑሮና ለአምላክ ያደሩ ለመሆን ተግባሮች” መንፈስ ቅዱስ እንዲገፋፋን እንፍቀድለት። (2 ጴጥሮስ 3:11-14) እንዲህ ካደረግን በታላቁ መከራ ወቅት “የይሖዋን ጥበቃ ለማግኘት ዋስትና አለኝን? በአገልግሎቱ የበለጠ ልሠራ እችል ነበርን? “አዲሱን ሰው” ለመልበስ በእርግጥ ጥረት አድርጌአለሁን? ይሖዋ በአዲስ ዓለም እንድኖር የሚፈልገኝ ዓይነት ሰው ነኝን?” እያልን ይህን በመሰሉ ዕረፍት የሚነሱ ጥያቄዎች አንረበሽም። እንዲህ ዓይነቶቹ አሳሳቢ ጥያቄዎች እምነታችንን እንድንመረምርና አሁኑኑ እንድናጠነክረው ጥረት እንድናደርግ ሊያደርጉን ይገባል!—ቆላስይስ 3:8-10
ደህና የሚያደርገን እምነት
15. ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች አንዳንዴ ምን ብሏቸው ነበር? ይህስ የዘመናችንን የእምነት ፈውስ የማይደግፈው ለምንድነው?
15 ኢየሱስ አካላዊ የመፈወስ ሥራዎቹን እምነት ላላቸው ሰዎች ብቻ አልወሰነም። (ዮሐንስ 5:5-9, 13) ስለዚህ የሱ ሥራ የእምነት ፈውስ ለሚባለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ መሠረተ ትምህርት ምንም ድጋፍ አይሰጥም። እውነት ነው ኢየሱስ አንዳንዴ የፈወሳቸውን ሰዎች “እምነትህ አድኖሃል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 9:22፤ ማርቆስ 5:34፤ 10:52፤ ሉቃስ 8:48፤ 17:19፤ 18:42) ነገር ግን እንዲህ ሲል እነዚያ በበሽታ የተጠቁ ሰዎች በኢየሱስ የመፈወስ ችሎታ እምነት ባይኖራቸው ኖሮ መጀመሪያውኑ ለመፈወስ ብለው ወደሱ የማይመጡ የመሆናቸውን ግልጽ እውነት ማመልከቱ ብቻ ነበር።
16. ኢየሱስ ዛሬ እየመራ ያለው ምን የመፈወስ ፕሮግራም ነው?
16 በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈሳዊ ፈውስ ፕሮግራም እየመራ ያለ ሲሆን ከ4,000,000 በላይ የሆኑ ግለሰቦችም ከዚህ ፕሮግራም ለመጠቀም ራሳቸውን አዘጋጅተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናቸው መጠን ምንም እንኳን አካላዊ ድካም ቢኖርባቸውም መንፈሳዊ ጤንነት እያገኙ ነው። ከመካከላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ሲሆን እነሱም “የማይታየውን ዘላለማዊ ነገር ይመለከታሉ።” (2 ቆሮንቶስ 4:16-18፤ 5:6, 7) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም በአምላክ አዲስ ዓለም የሚሆነውን አስደናቂ አካላዊ ፈውስ ተስፋ ያደርጋሉ።
17, 18. በራእይ 22:1, 2 ላይ ምን የይሖዋ ዝግጅት ነው የተገለጸው? ከእሱስ ለመጠቀም እምነት የሚያስፈልገን እንዴት ነው?
17 ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ 22:1, 2 ላይ አምላክ ለዘላለማዊ ሕይወት ያደረገውን ዝግጅት በእነዚህ ቃላት አመልክቷል፦ “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበር። የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።” “የሕይወት ውሃ” የአምላክን የእውነት ቃልና ታዛዥ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳንና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የዘላለም ሕይወት የሚያሰጥበትን የይሖዋን ዝግጅት ይጨምራል። (ኤፌሶን 5:26፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በምድር ላይ ሳሉ የኢየሱስ 144,000 ቅቡዓን ተከታዮች በኢየሱስ በኩል የአምላክን የሕይወት ዝግጅት ይጠጣሉ፤ “የጽድቅ ዛፎች” ተብለውም ይጠራሉ። (ኢሳይያስ 61:1-3፤ ራእይ 14:1-5) በምድር ላይ ብዙ መንፈሳዊ ፍሬ አፍርተዋል። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በሰማይ ትንሣኤ የሚያገኙ እንደ መሆናቸው መጠን ከኃጢአትና ከሞት ለሕዝብ መፈወሻ” የሚያገለግለውን የቤዛውን ዝግጅት በማደሉ ሥራ ይካፈላሉ።
18 በእነዚህ የአምላክ ዝግጅቶች ላይ ያለን እምነት ጠንካራ በሆነ መጠን ከእነዚህ ዝግጅቶች ለመካፈል የሚሰጠንን የመንፈሱን አመራሮች ለመከተል ፈቃደኛነታችን ከፍተኛ ይሆናል። አንድ ሰው በክርስቶስ እምነት ባሳየና መንፈሳዊ እድገት ባደረገ መጠን ደግሞ አካላዊ ፍጽምና ያገኛል። አንድ ሰው ዋና ዋና ሕመሞቹ በተዓምራዊ መንገድ ቢፈወሱም ወደ ፍጽምና እየቀረበ የሚመጣው ትክክል የሆነውን ነገር እያደረገ ሲሄድ ነው። በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ለፈውስ ከሚቀርበው የአምላክ ዝግጅትም አዘውትሮ ይካፈላል። ስለዚህ እምነት በአካላዊ ወይም በሥጋዊ መንገድ መፈወሳችንና ፍጹም መሆናችን ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል።
“በእምነት አድኗችኋል”
19. በእምነት ጸንቶ መኖር አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
19 የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክ አዲስ ዓለም መጀመር የአሁኑን ክፉ ዓለም ጨለማ ለዘላለም እስኪያስወግድ ድረስ በእምነት ጸንተው መቆም በጣም ያስፈልጋቸዋል። “እምነት የሌላቸው ሰዎች” “በእሣትና በድኝ ወደሚቃጠል ባሕር” ማለት ወደ ሁለተኛው ሞት ይገባሉ። ይህም እጅግ ቢዘገይ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ ከሚሆነው የመጨረሻ ፈተና በኋላ ይፈጸማል። (ራእይ 20:6-10፤ 21:8) እምነት በማሳየት የሚቀጥሉትና ከጥፋት ተርፈው ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች ዕጣ እንዴት የተባረከ ነው!
20. በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ 1 ቆሮንቶስ 13:13 ልዩ ትርጉም የሚኖረው እንዴት ነው?
20 ያኔ እነዚህ በ1 ቆሮንቶስ 13:13 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ልዩ ትርጉም ይኖራቸዋል፦ “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።” ከዚያ በኋላ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለው ትንቢታዊ ተስፋ አንድ ቀን እውን ይሆናል ወይም ይፈጸማል በሚል ተስፋ ማመን አያስፈልገንም። የሆነ ወይም የተፈጸመ ነገር ይሆናል። ታማኝ ወይም ፍጹም አቋም ጠባቂዎች በመሆን በይሖዋ ተስፋ በማድረግ እንቀጥላለን፤ በሱና በልጁ እምነት ይኖረናል። የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ያመጡ በመሆናቸውም እናፈቅራቸዋለን። ከዚህም በላይ ለመዳናችን ያለን ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ ምሥጋና ከአምላክ ጋር ለዘላለም ዓለም በማይበጠስ ለአምላክ የማደር ፍቅር ያስተሳስረናል።—1 ጴጥሮስ 1:8, 9
21. “በእምነት እንድንድን” እኛ ዛሬ ምን ማድረግ አለብን?
21 ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት እምነታችንን ለማጠንከር ድንቅ ዝግጅቶች አድርጎልናል። በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። በአምላክ ሕዝቦች ስብሰባ አዘውትረህ ተገኝ፤ ተሳተፍም። (ዕብራውያን 10:24, 25) ቃሉንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በትጋት አጥና። መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ይሖዋን ለምነው። (ሉቃስ 11:13) በጉባኤ ውስጥ በትሕትና የሚመሩትን በእምነታቸው ምሰላቸው። (ዕብራውያን 13:7) ዓለማዊ ተፈታታኝ ግፊቶችን ተቋቋም። (ማቴዎስ 6:9, 13) አዎን፣ ከይሖዋ ጋር ያለህን የግል ዝምድናም በምትችለው በማንኛውም መንገድ አጥብቀው። ከሁሉም በላይ እምነት በማሳየት ቀጥል። ከዚያም ጳውሎስ በኤፌሶን 2:8 ላይ “ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና። ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” ብሎ እንደተናገረው ይሖዋን ከሚያስደስቱትና ደህንነትን ከሚጠብቁት መካከል ልትሆን ትችላለህ።
መልስህ ምንድነው?
◻ ምን የእምነት ፈተና ነው ወደፊት የሚጠብቀን?
◻ በምን ሁለት መንገዶች ነው እምነታችን የሚጠብቀን?
◻ በ1 ጴጥሮስ 1:9 መሠረት እምነታችንን መጠበቅ ያለብን እስከመቼ ነው?
◻ እምነታችንን የምናጠናክርባቸው ምን ዝግጅቶች አሉልን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ልጁን እንደፈወሰለት አባት የበለጠ እምነት የመያዙ አስፈላጊነት ይሰማሃልን?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከታላቁ መከራ” ለመዳን ኖኅና ቤተሰቡ እንደነበራቸው ዓይነት እምነት እንዲኖረን ያስፈልጋል