“በመንፈስ ቅዱስ ስም”
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19
1. አጥማቂው ዮሐንስ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በየትኛው አዲስ አዲስ አባባል ተጠቅሞአል?
በ29 እዘአ ላይ ዮሐንስ መጥምቁ በእሥራኤል ምድር ለመሲሑ መንገድ ለማዘጋጀት ተግቶ ይሠራ ነበር። በአገልግሎቱ ወቅትም ስለ መንፈስ ቅዱስ አንድ አዲስ ነገር አስታወቀ። በእርግጥ አይሁዳውያን ቀደም ብሎም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ መንፈስ የሚናገሩትን ያውቁ ነበር። ይሁንና ዮሐንስ “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ። ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን . . . በመንፈስ ቅዱስ . . . ያጠምቃችኋል” ብሎ ሲናገር ሲሰሙት ተገርመው ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 3:11) ‘በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ’ የሚለው አነጋገር አዲስ አነጋገር ነበር።
2. ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን የሚመለከት ምን አዲስ መግለጫ አስተዋወቀ?
2 የሚመጣው ሰው ኢየሱስ ነበር። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር እንጂ ማንንም በመንፈስ ቅዱስ አላጠመቀም። ከዚህም በላይ ከትንሣኤው በኋላ ስለ መንፈስ ቅዱስ አዲስ በሆነ ሌላ መንገድ ተናግሮአል። ለደቀመዛሙርቱ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀመዛሙርት አድርጓቸው” አላቸው። (ማቴዎስ 28:19) “በ. . . ስም” የሚለው አገላለጽ “የአንድን ነገር ወይም የአንድን ሰው ምንነት ወይም ማንነት ቦታና ደረጃ መገንዘብና መቀበል ማለት ነው።” አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አውቆና ተቀብሎ በውኃ መጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ ከመጠመቅ የሚለይ ነገር ነበር። ይህም አነጋገር መንፈስ ቅዱስን የሚመለከት አዲስ አነጋገር ነበር።
በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ
3, 4. (ሀ) የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የተፈጸመው መቼ ነበር? (ለ) በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ደቀመዛሙርት ከማጥመቅ ሌላ ምን ሌላ ተግባር ፈጽሞአል?
3 ኢየሱስ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅን በሚመለከት ለደቀመዛሙርቱ፦ “ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” ብሎአቸዋል። (ሥራ 1:5, 8) ከጥቂት ቀናት በኋላም ይህ የተስፋ ቃል ተፈጽሞላቸዋል። ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ ይህን የመጀመሪያውን በመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ በፈጸመበት ጊዜ 120 የሚያክሉት ደቀመዛሙርቱ በኢየሩሳሌም በአንድ ሰገነት (ፎቅ) ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። (ሥራ 2:1-4, 33) ይህስ ምን አይነት ውጤት አስከተለ? ደቀመዛሙርቱ የክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ክፍል ሆኑ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል” በማለት ገልጾአል። (1 ቆሮንቶስ 12:13) በዚሁ ጊዜ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ ተቀቡ። (ኤፌሶን 1:13, 14፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ ራእይ 20:6) መንፈስ ቅዱስ ለዚህ ወደፊት ለሚያገኙት ክብራማ ውርሻ እንደ ምልክት ወይም ማህተም ሆኖ አገልግሎአል። ነገር ግን ጉዳዩ በዚህ ብቻ አያበቃም። 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22
4 ኢየሱስ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ለኒቆዲሞስ- “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም። . . . ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 3:3, 5) አሁን ደግሞ ማለትም በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት 120 ደቀመዛሙርት ዳግም ልደት አግኝተዋል። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችና የክርስቶስ ወንድሞች ለመሆን ቻሉ። (ዮሐንስ 1:11-13፤ ሮሜ 8:14, 15) እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ሁሉ ከተአምራት የበለጠ የሚያስደንቁ ናቸው። ከዚህም በላይ በአንድ ወቅት እንደነበሩት ተአምራት ይኸኛው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሐዋርያት ሞት አላቆመም። ከዚህ ይልቅ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። በይሖዋ ምሥክሮች መሃል በመንፈስ የተጠመቁ የክርስቶስ አካል የመጨረሻ አባሎች መገኘታቸው በጣም ትልቅ መብት ነው። እነዚህ የክርስቶስ አካል የመጨረሻ አባሎችም መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ በማቅረብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ያገለግላሉ።—ማቴዎስ 24:45-47
“በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ”
5, 6. የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወደ ውኃ ጥምቀት የመራው እንዴት ነው?
5 በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚደረገው የውኃ ጥምቀትስ ምንድን ነው? በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት እነዚህ የመጀመሪያ ደቀመዛሙርት በውኃ አልተጠመቁም። ቀደም ሲል የዮሐንስን የውኃ ጥምቀት ተቀብለው ስለነበረና ያ ጥምቀትም በዚያ ወቅት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስለነበረ እንደገና መጠመቅ አላስፈለጋቸውም። ነገር ግን በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አዲሱን የውኃ ጥምቀት ተቀበሉ። ይህ የሆነው እንዴት ነበር?
6 የ120ዎቹ በመንፈስ መጠመቅ ብዙ ሰዎችን ሊስብ በቻለ ትልቅ ድምጽ ታጅቦ ነበር። በድምጹ የተሳቡት ሰዎች ደቀመዛሙርቱ በልሳኖች ማለትም በቦታው ለነበሩት ሰዎች በሚገባቸው የውጭ ቋንቋ ሲናገሩ በመስማታቸው ተገርመው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ ተአምር ከሙታን ተነስቶ በሰማይ በአምላክ ቀኝ ጐን የተቀመጠው ኢየሱስ የአምላክን መንፈስ እያፈሰሰ ለመሆኑ ማስረጃ እንደሆነ ገለጸ። ጴጥሮስ አድማጮቹን “እናንተ የሰቀላችሁትን ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእሥራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” በማለት አበረታታቸውና “ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት ንግግሩን ደመደመ። ለዚህም ጥሪ 3,000 የሚያህሉ ነፍሳት ምላሽ ሰጥተዋል።—ሥራ 2:36, 38, 41
7. (ሀ)በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት 3,000 ሰዎች በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁት በምን መንገድ ነበር?
7 እነዚህ 3,000 የሚያህሉ ሰዎች የተጠመቁት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም (ማለትም የአብን፣ የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን ማንነት እንዲሁም ሥልጣን ቦታና ደረጃ በመገንዘብ በመቀበል) ነው ሊባል ይችላል? አዎን፣ ጴጥሮስ በአብ ስም እንዲጠመቁ ባይነግራቸውም ሥጋዊ አይሁዳውያንና ለሱ የተወሰነው ሕዝብ አባሎች ስለነበሩ ቀደም ብለውም ይሖዋ ልዑል ጌታቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። ጴጥሮስ የነገራቸው “በወልድ ስም” እንዲጠመቁ ነበር። ስለዚህ ጥምቀታቸው ኢየሱስ ጌታና ክርስቶስ መሆኑን አውቀውና አምነው መቀበላቸውን ያመለክት ነበር። አሁን ደቀመዛሙርቱ ስለሆኑ ከዚያ በኋላ የኃጢአት ሥርየት የሚገኘው በኢየሱስ በኩል ብቻ መሆኑን ተቀብለዋል። በመጨረሻም የተጠመቁት የመንፈስ ቅዱስን ምንነት በመገንዘብና በመቀበል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን በነፃ ስጦታነት እንደሚቀበሉ ለተገባላቸው የተስፋ ቃል ምላሽ በመስጠት ነበር።
8. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከውኃ ጥምቀት ሌላ የተቀበሉት ምን ጥምቀት ነው? (ለ) ከ144,000 ሌላ በመንፈስ ቅዱስ ስም የውኃ ጥምቀት የሚቀበሉት እነማን ናቸው?
8 በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት በውኃ የተጠመቁት ሁሉ በሰማያዊ መንግሥት ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ ስላገኙ በመንፈስም ተጠምቀዋል። በራእይ መጽሐፍ መሠረት በመንፈስ የሚጠመቁት ሰዎች ቁጥር 144,000 ነው። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁና በመጨረሻም የመንግሥት ወራሾች በመሆን ‘የሚታተሙት’ ቁጥራቸው 144,000 ብቻ ነው። (ራእይ 7:4፤ 14:1) ይሁን እንጂ ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን አዳዲስ ደቀመዛሙርት ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ይጠመቃሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ታዲያ ለክርስቲያኖች በሙሉ የ“ታናሽ መንጋ”ም ሆነ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል ይሁኑ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቃቸው ምን ትርጉም ይኖረዋል? (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16) ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በክርስትና ዘመን የታዩትን አንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች እንመልከት።
የመንፈስ ፍሬ
9. ለክርስቲያኖች ሁሉ አስፈላጊ የሆነው የትኛው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው?
9 የመንፈስ ቅዱስ ዋና ተግባር በውስጣችን ክርስቲያናዊ ባሕርዮችን ማዳበር ነው። እውነት ነው ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት ኃጢአት መሥራታችን አይቀርም። (ሮሜ 7:21-23) ነገር ግን ከልብ ተጸጽተን ንስሐ ስንገባ ይሖዋ በክርስቶስ መስዋዕት አማካኝነት ይቅር ይለናል። (ማቴዎስ 12:31, 32፤ ሮሜ 7:24, 25፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ከዚህም በላይ ይሖዋ ኃጢአት ከመሥራት ዝንባሌያችን ጋር እንድንዋጋ ይፈልግብናል። መንፈስ ቅዱስም ይህን እንድናደርግ ይረዳናል። ጳውሎስ “በመንፈስ ተመላለሱ። የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” በማለት ተናግሯል። (ገላትያ 5:16) ጳውሎስ በመቀጠል መንፈስ በውስጣችን በጣም ጥሩ ባሕርያትን እንደሚያፈራ ገልጿል። “የመንፈስ ፍሬ ግን፣ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጐነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው” በማለት ጽፏል።—ገላትያ 5:22, 23
10. የመንፈስ ፍሬዎችስ በአንድ ክርስቲያን ውስጥ ሊያድጉ የሚችሉት እንዴት ነው?
10 ታዲያ መንፈስ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቶቹን ፍሬዎች እንዲያፈራ የሚያስችለው እንዴት ነው? ውስንና የተጠመቅን ክርስቲያኖች ስለሆንን ብቻ እንዲሁ ያለምንም ጥረት የሚሆን ነገር አይደለም። ተግተን መሥራትና ልባዊ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ባሕርያት ከሚያሳዩ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከዋልን፣ ወይም ከተሰበሰብን በተለይ ለማሳደግ የምንፈልጋቸውን ባሕርያት ለማፍራት እንድንችል መንፈሱን እንዲሰጠን አምላክን በጸሎት ከጠየቅን፣ መጥፎ ባልንጀርነትን ካስወገድንና ምክርና ጥሩ ምሳሌዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናን የመንፈስ ፍሬዎች በውስጣችን ያድጋሉ።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ገላትያ 5:24-26፤ ዕብራውያን 10:24, 25
በመንፈስ ቅዱስ መሾም
11. ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት በምን መንገድ ነው?
11 ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ሲናገር “በገዛ ልጁ ደም የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት የመንፈስ ቅዱስን ሌላ ተግባር አስታውቋል። (ሥራ 20:28 (አዓት)) አዎን የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው። ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት በምን መንገድ ነው? የሚሾሙት ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ማሟላት ስላለባቸው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9) እነዚህን ብቃቶች ሊያዳብሩ የሚችሉት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ብቻ ነው። በተጨማሪም የሽማግሌዎች አካል አንድ ሰው አዲስ ሽማግሌ እንዲሆን በሚያጩበት ጊዜ ግለሰቡ ብቃቶቹን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማስተዋል የመንፈስ ቅዱስን መሪነት ለማግኘት ይጸልያል። በመጨረሻም ሹመቱ የሚጸድቀው በመንፈስ በተቀባው ታማኝና ልባም ባሪያ ተቆጣጣሪነት ነው።
መንፈስ ቅዱስ ይምራችሁ
12. መንፈሱ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ሊያነሣሣን የሚችለው እንዴት ነው?
12 ክርስቲያኖች ቅዱሳን ጽሑፎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን ይገነዘባሉ። ስለዚህ በቅድመ ክርስትና ዘመን ይኖሩ የነበሩ የይሖዋ ምስክሮች ያደርጉት እንደነበረው ከቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መንፈስ ያለበት ጥበብ ለማግኘት አጥብቀው ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 2:1-9) ቅዱሳን ጽሑፎቹን ያነቧቸዋል፣ ያሰላስሏቸዋል፣ ሕይወታቸውንም እንዲመሩላቸው ያደርጋሉ። (መዝሙር 1:1-3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመሆኑም “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንዲመረምሩ” በመንፈስ ይታገዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:10, 13፤ 3:19) መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን ከሚያከናውናቸው አስፈላጊ ተግባራት አንዱ የአምላክን አገልጋዮች በዚህ መንገድ መምራት ነው።
13, 14. በጉባኤው ውስጥ የነበሩ ችግሮችን ለማስወገድ ኢየሱስ የተጠቀመው በምን ነበር? ዛሬስ እንደዚያው የሚያደርገው እንዴት ነው?
13 በተጨማሪም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ በትንሹ እስያ ለነበሩ ሰባት ጉባኤዎች መልእክቶችን ልኮ ነበር። (ራእይ ምዕራፍ 2 እና 3) በመልእክቶቹም ውስጥ ጉባኤዎቹን እንደሚመራቸውና የነበሩበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ተመልክቶ እንደነበረ ገልጾአል። በእምነት ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ጉባኤዎች እንዳሉም ተመልክቶአል። በሌሎቹ ጉባኤዎች ውስጥ ደግሞ ሽማግሌዎቹ መንጋው በመናፍቅነት፣ በብልግናና በለዘብተኝነት እንዲበላሽ ፈቅደዋል። የሰርዴስ ጉባኤ ከጥቂት ታማኝ ነፍሳት በቀር በመንፈሳዊ ሙት ሆኖ ነበር። (ራእይ 3:1, 4) ኢየሱስ እነዚህን ችግሮች ያስተካከለው እንዴት ነበር? በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነበር። ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች ምክር ሲሰጥ ለእያንዳንዱ ጉባኤ የላከውን መልእክት የደመደመው “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት ወይም ለጉባኤዎች የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” በሚለው ቃል ነበር።—ራእይ 2:7, 11, 17, 29፤ 3:6, 13, 22
14 ኢየሱስ ዛሬም ቢሆን ጉባኤዎችን ይመረምራል። ችግሮች እንዳሉ በሚመለከትበት ጊዜም ችግሮቹን የሚፈታው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። መንፈሱ መጽሐፍ ቅዱስ በምናነብበት ጊዜ ችግሮቹን ለይተን እንድናውቅና እንድንቋቋም ይረዳናል። እርዳታው በመንፈስ በተቀባው ታማኝና ልባም ባሪያ በታተሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በኩልም ሊመጣ ይችላል። ወይም ደግሞ እርዳታው በጉባኤው ውስጥ በመንፈስ ከተሾሙ ሽማግሌዎች ዘንድ ሊመጣ ይችላል። ያም ሆነ ይህ ምክሩ ለግለሰቦች የተሰጠም ይሁን ለመላው ጉባኤ “መንፈስ የሚለውን (የሚናገረውን) ጆሮ ያለው ይስማ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እንቀበላለንን?
መንፈሱና የስብከቱ ሥራ
15. የስብከቱን ሥራ በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ ለኢየሱስ ምን አድርጎለት ነበር?
15 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ናዝሬት በነበረው ምኩራብ ሲሰብክ ሌላውን የመንፈስ ተግባር አመልክቷል። ታሪኩ፦ “መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ [የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ በእኔ ላይ ነው። ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና። ለታሠሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነፃ አወጣ ዘንድ . . . ልኮኛል። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር” ይለናል። (ሉቃስ 4:17, 18, 21፤ ኢሳይያስ 61:1, 2) አዎን ኢየሱስ ወንጌልን ለመስበክ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ነበር።
16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን መንፈስ ቅዱስ በምሥራቹ ስብከት ሥራ ሙሉ በሙሉ ይካፈል የነበረው እንዴት ነበር?
16 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ተከታዮቹ ታላቅ የስብከት ዘመቻ እንደሚያካሂዱ ትንቢት ተናግሮ ነበር። “ለአሕዛብም ሁሉ የምሥራቹ መሰበክ ይኖርበታል” ብሎአል። (ማርቆስ 13:10 አዓት) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ሲሆን በዚያም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ያበረከተው የሥራ ድርሻ የሚደነቅ ነበር። ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንዲሰብክ የመራው መንፈስ ቅዱስ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስን ወደ ቆርኔሌዎስ እንዲሄድ መርቶታል። ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያት ሆነው ከአንጾኪያ እንዲላኩ የመራውም መንፈስ ቅዱስ ነበር። በኋላም ጳውሎስ በእስያና በቢታንያ ለመስበክ በፈለገ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ዓይነት መንገድ እንዳይሰብክ ከልክሎታል። አምላክ የምሥክርነቱ ሥራ ወደ አውሮፓ እንዲስፋፋ ፈልጎ ነበር።—ሥራ 8:29፤ 10:19፤ 13:2፤ 16:6, 7
17. ዛሬ መንፈስ ቅዱስ በስብከቱ ሥራ የሚካፈለው እንዴት ነው?
17 ዛሬም መንፈስ ቅዱስ በስብከቱ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ይካፈላል። በኢሳይያስ 61:1, 2 ተጨማሪ ፍጻሜ መሠረት የኢየሱስ ወንድሞች እንዲሰብኩ የይሖዋ መንፈስ ቀብቷቸዋል። እነዚህ ቅቡዓን የማርቆስ 13:10ን ትንቢት ለመጨረሻ ጊዜ ለመፈጸም በእጅግ ብዙ ሰዎች እየታገዙ የምሥራቹን ቃል በቃል “ለአሕዛብ ሁሉ” ሰብከዋል። (ራእይ 7:9) መንፈስ ሁሉንም በዚህ ሥራ ይደግፋቸዋል። እንደመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚሰበክባቸውን ቀበሌዎች ወይም ክልሎች ይከፍታል፣ የሥራውንም አጠቃላይ እርምጃ ይመራል። ግለሰቦች የፍርሐት ስሜታቸውን እንዲቋቋሙና የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በመርዳት ያጠነክራቸዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ ብሏል፦ “ለእነርሱና ለአሕዛብም ምሥክር እንዲሆን ስለእኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። አሳልፈው ሲሰጧችሁ . . . እንዴት ወይም ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።”—ማቴዎስ 10:18-20
18, 19. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሕይወትን ውኃ እንዲወስዱ በመጋበዙ ሥራ መንፈስ ቅዱስ ከሙሽራዋ ጋር የሚተባበረው በምን መንገድ ነው?
18 መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በስብከቱ ሥራ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ያለውን ተሳትፎ ጠበቅ አድርጎ ገልጾአል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና’ ይላሉ። የሚሰማም ‘ና’ ይበል። የተጠማም ይምጣ። የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” ብሎአል። (ራእይ 22:17) አሁንም በምድር ላይ በሚገኙት የ144,000 ቀሪዎች እንደራሴነት የምትወከለው ሙሽራ ሰዎች ሁሉ የሕይወትን ውኃ እንዲወስዱ ግብዣዋን እያቀረበች ነው። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስም ‘ና’ የሚል መሆኑን አስተውሉ። ግን ‘ና’ የሚለው በምን መንገድ ነው?
19 በዛሬው ጊዜ በሌሎች በጐች እጅግ ብዙ ሰዎች አጋዥነት በሙሽራይቱ ክፍል እየተሰበከ ያለው መልእክት በመንፈስ ቅዱስ ቀጥተኛ መሪነት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ስለሆነ ነው። ይኸው መንፈስ የሙሽራይቱ ክፍል የሆኑት ሰዎች በመንፈስ የተጻፈውን የአምላክ ቃል እንዲረዱና ለሌሎችም እንዲያስረዱ ልባቸውንና አእምሮአቸውን ከፍቶላቸዋል። አዳዲስ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በመሆን የተጠመቁት ሰዎችም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ማለትም በነፃ በመውሰድ ይደሰታሉ። ሌሎችንም “ና” በማለት ከመንፈሱና ከሙሽራይቱ ጋር በመተባበራቸው በጣም ይደሰታሉ። ዛሬ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎች ከመንፈሱ ጋር በዚህ ሥራ ይካፈላሉ።
ከጥምቀታችን ዓላማ ጋር ተስማምተን መኖር
20, 21. በመንፈስ ቅዱስ ስም ከተቀበልነው ጥምቀት ዓላማ ጋር ተስማምተን መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ጥምቀትስ እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
20 በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የመንፈስ ቅዱስን ምንነት እንደተገነዘብንና በይሖዋ ዓላማዎች ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አምነን እንደተቀበልን የሚያሳይ በሕዝብ ፊት የሚደረግ መግለጫ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቃችን በይሖዋ ሕዝብ መሃል መንፈሱ እንዳይሠራ የሚከለክል ምንም ነገር ባለማድረግ ከመንፈሱ ጋር የምንተባበር መሆናችንን ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ታማኝና ልባም ባሪያን ለይተን በማወቅ ከዚህ ባሪያ ጋር እንተባበራለን። በጉባኤው ውስጥ ካለው የሽማግሌዎች ዝግጅት ጋርም እንተባበራለን። (ዕብራውያን 13:7, 17፤ 1 ጴጥሮስ 5:1-4) የምንኖረው በስጋዊ ጥበብ ሳይሆን በመንፈሳዊ ጥበብ ስለሆነ ባሕርያችን ይበልጥ ክርስቶስን የሚመስል እንዲሆን መንፈሱ እንዲቀርጽልን እንፈቅድለታለን። (ሮሜ 13:14) ጥሪውን ሊቀበሉ ለሚችሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ና” በማለት ከመንፈሱና ከሙሽራይቱ ጋር በሙሉ ልብ እንተባበራለን።
21 እንግዲያውስ ‘በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ’ በጣም ከባድ ነገር ነው። ሆኖም ብዙ በረከቶችን ያስገኝልናል። በዚህ መንገድ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ ከልብ እንመኛለን። ይሖዋን በማገልገልና ‘በመንፈስ በመቃጠል’ ሁላችንም ከዚህ ጥምቀት ትርጉም ጋር ተስማምተን የምንኖር እንሁን።—ሮሜ 12:11
ስለ መንፈስ ቅዱስ ምን ታስታውሳለህ?
◻ በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ይሠራ የነበረው እንዴት ነው?
◻ የመንፈስን ፍሬዎች ልናፈራ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት በምን መንገድ ነው?
◻ ኢየሱስ በጉባኤ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለማስወገድ በመንፈስ ቅዱስ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
◻ መንፈሱ በስብከቱ ሥራ የተዋጠው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ የሰበከው ጥምቀት በአብና በመንፈስ ቅዱስ ስም ጭምር የተደረገ ነበር
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንፈሱ በምሥራቹ ስብከት ሥራ ይካፈላል