እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው
“አንተ ክርስቶስ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ።”—ማቴዎስ 16:16
1, 2. (ሀ) አንድ ሰው በምን ምክንያቶች ታላቅ ሊባል ይችላል? (ለ) በታሪክ ውስጥ ታላቅ የተባሉ ሰዎች እነማን ናቸው?
እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማን ይመስላችኋል? የአንድን ሰው ታላቅነት የምትመዝኑት በምኑ ነው? በወታደራዊ ስልት አዋቂነቱ ነው? በአእምሮ ችሎታው ወይም በአካላዊ ኃይሉ?
2 “ታላቅ” ተብለው የተጠሩ ብዙ ገዥዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ታላቁ ቂሮስና ታላቁ እስክንድር ይገኛሉ። ሻርለማይንም ገና በሕይወቱ እያለ “ታላቁ” ተብሎ ተጠርቶአል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በሕልውናቸውና በግርማቸው በሚገዙአቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
3. (ሀ) የአንድ ሰው ታላቅነት የሚመዘነው በምንድን ነው? (ለ) በዚህ መለኪያ መሠረት እስከዛሬ ድረስ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማን ነው?
3 የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤች ጂ ዌልስ የሰው ትልቅነት ስለሚለካበት መመዘኛ የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ከሃምሳ ዓመታት በፊት እንደሚከተለው በማለት ጽፈው ነበር። “አንድ የታሪክ ሊቅ የአንድን ግለሰብ ታላቅነት የሚመዝነው ‘እርሱ ካለፈ በኋላ የሚበቅል ምን ነገር ትቶአል? በሰዎች ላይ እርሱ ከሞተ በኋላም እንኳን ቢሆን ያልደበዘዘ አዲስ ዓይነት አመለካከትና አስተሳሰብ ትቶ አልፎአልን?’ ብሎ በመጠየቅ ነው።” ዌልስ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ በዚህ መለኪያ ሲመዘን “አንደኛ ቦታ የሚይዘው ኢየሱስ ነው” ብለዋል። በጣም ኃያል ገዥ የነበረው ናፖሊዮን ቦናፓርት እንኳን “ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል መገኘት ሳያስፈልገው ተገዥዎቹ የሆኑትን ሰዎች ለማዘዝና ለመግዛት ችሎአል” ብሎ ነበር።
4. (ሀ) ኢየሱስን በሚመለከት ምን የተለያዩ አመለካከቶች አሉ? (ለ) ክርስቲያን ያልሆኑ ታሪክ ፀሐፊዎች ለኢየሱስ ምን ዓይነት ቦታ ይሰጡታል?
4 ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ አፈ ታሪክ የወለደው ሰው እንጂ በታሪክ የታወቀ ሰው አይደለም ይላሉ። በሌላው በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ወደ ምድር መጣ በማለት ኢየሱስን እንደ አምላክ አድርገው የሚያመልኩት ሰዎች አሉ። ዌልስ ግን ስለ ኢየሱስ ሰብአዊ ሕልውና የሚገልጹትን ታሪካዊ ጭብጦች ብቻ መሠረት በማድረግ በሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። “ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ዝንባሌ የሌለው ታሪክ ፀሐፊ ለአንድ ቤሳ ቢስቲን ላልነበረው የናዝሬት መምህር ከፍተኛ ግምት ሳይሰጥ የሰው ልጅን ዕድገት በሐቀኝነት ሊገልጽ እንደማይችል መገንዘቡ ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነው። . . . እንደኔ ያለው ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ የማይጠራ ታሪክ ፀሐፊ እንኳን መላው የታሪክ ሥዕል በዚህ ታላቅ ሰው ሕይወትና ባሕርይ ላይ ያተኮረ መሆኑን ለመቀበል ይገደዳል።”
በእርግጥ ኢየሱስ የሚባል ሰው ኖሮ ያውቃልን?
5, 6. ኤች ጂ ዌልስና ዊል ዱራንት የተባሉት ታሪክ ፀሐፊዎች ኢየሱስ በታሪክ የታወቀ ሰው ስለመሆኑ ምን ብለዋል?
5 ይሁን እንጂ ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የፈለሰፉት የተረት ሰው ነው እንጂ ኢየሱስ የሚባል ሰው በሕይወት ኖሮ አያውቅም ቢሏችሁስ? እንደዚህ ላለው አነጋገር ምን መልስ ትሰጣላችሁ? ዌልስ ስለ ኢየሱስ “ማወቅ የምንፈልገውን ያህል ለማወቅ አልቻልንም” ቢሉም የሚከተለውን ጽፈዋል፦ “አራቱ ወንጌሎች . . . ስለአንድ የተወሰነ ሰው እርስ በርሱ የሚስማማ መግለጫ ይሰጡናል። በእርግጥ በሕይወት ስለኖረ ሰው እንደሚናገሩ ግልጽ ነው። ኢየሱስ የተባለ ሰው ኖሮ አያውቅም፣ ስለ ሕይወት ታሪኩ የተጻፈው ሁሉ የፈጠራ ታሪክ ነው ማለት አንድን የታሪክ ሰው የወንጌሎችን ታሪክ እውነት ናቸው ብሎ ቢቀበል ከሚያጋጥሙት የበለጡ ችግሮች ውስጥ ያስገባዋል።”
6 ከፍተኛ ከበሬታ ያተረፉት ዊል ዱራንት የተባሉት ታሪክ ፀሐፊም እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ ክርክር አቅርበዋል። ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ “ጥቂት ተራ ሰዎች በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ኃይልና ተወዳጅነት ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የሥነምግባር ደረጃ፣ ይህን የመሰለ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለመፈልሰፍ ከቻሉ በወንጌሎቹ ውስጥ ከተጻፉት ተአምራት በሙሉ የበለጠ እምነት የሚጠይቅ ትልቅ ተአምር ይሆናል።”
7, 8. ኢየሱስ የሰውን ልጅ ታሪክ የነካው ምን ያህል ነው?
7 ስለዚህ ለተጠራጣሪ ሰዎች “በምድር ላይ ኖሮ የማያውቅ ተረት የፈጠረው ሰው በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ይህን የሚያክል ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላልን?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ልታወያዩአቸው ትችላላችሁ። ታሪክ ጸሐፊ የዓለምን ታሪክ ሲዘግብ የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] ያደረጋቸው ነገሮች በታሪክ ላይ ያስከተሉት ውጤት በዓለማዊ አመለካከት ብቻ እንኳን ሲታይ ማንኛውም ሰው ካደረገው እጅግ የሚልቅ ነው። ዋነኞቹ የዓለም ሥልጣኔዎች የተከሰቱበት አዲስ ዘመን የጀመረው ከእርሱ ልደት በኋላ ነው።” እስቲ ነገሩን በጥሞና ተመልከቱት፦ የዓመታት ቁጥር እንኳን የሚቀመረው ኢየሱስ ተወልዶበታል ተብሎ ከሚታሰበው ዓመት ጀምሮ ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው “ከዚህ ዓመት በፊት ያሉት ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት ተብለው ሲጠሩ ከዚያ በኋላ ያሉት ዓመታት ደግሞ አኖ ዶሚኒ (በጌታ ዘመን) ተብለው ይጠራሉ።”
8 ኢየሱስ እጅግ ኃይለኛ በሆኑት ትምህርቶቹና በእነዚህ ትምህርቶች ላይ በተመሠረተው አኗኗሩ አማካኝነት በብዙ ሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሁለት ሺህ ዓመት ለሚያክል ዘመን ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። አንድ ፀሐፊ ጥሩ አድርጎ እንደገለጸው “በምድር ላይ የተነሱት ጦር ሠራዊቶችና የባሕር ኃይሎች በሙሉ፣ በምድር ላይ የነገሱ ነገሥታትና ምክር ቤቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቢጠቃለሉ የኢየሱስን ያህል የሰው ልጆችን ሕይወት አልለወጡም።” ይሁን እንጂ ተቺዎች “ስለ ኢየሱስ የሚታወቀው ነገር ሁሉ ተጽፎ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው። እርሱ በኖረበት ዘመን ስለእርሱ የተጻፈ ሌላ የታሪክ ማስረጃ አይገኝም” ይላሉ። ታዲያ ይህ አባባላቸው እውነት ነው?
9, 10. (ሀ) የቀድሞ ዘመን ዓለማዊ ታሪክ ፀሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ምን ብለዋል? (ለ) አንድ የታወቀ ኢንሳይክሎፔድያ የቀድሞ ታሪክ ፀሐፊዎች በሰጡት ምሥክርነት ላይ በመመርኮዝ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል?
9 የጥንት ዓለማዊ ታሪክ ፀሐፊዎች ብዙ አይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጽፈዋል። ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማዊ ታሪክ ፀሐፊ፣ ኮርኔልየስ ታሲተስ የሮማ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ኔሮ ‘የሮማን መቃጠል በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ’ ካለ በኋላ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጥ “[ክርስቲያን] የሚለው ስም ገዥው ጴንጤናዊ ጲላጦስ በጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ካስገደለው ክርስቶስ ከተባለ ሰው የተወሰደ ነው” ብሎአል። ስዌቶንየስና ታናሹ ፕሊኒ የተባሉት የዘመኑ የሮማ ታሪክ ፀሐፊዎችም ስለ ክርስቶስ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ታሪክ ፀሐፊ የነበረው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ክርስቲያን ደቀመዝሙር ስለነበረው ስለ ያዕቆብ አሟሟት የአይሁድ ጥንታዊ ታሪክ በተባለው መጽሐፉ ላይ ጽፎአል። ጆሴፈስ ተጨማሪ መግለጫ ሲሰጥ ያዕቆብ “ክርስቶስ የተባለው የኢየሱስ ወንድም ነበር” ብሎአል።
10 በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው በማለት ይደመድማል፦ “እነዚህ ነፃ የሆኑ የታሪክ ማስረጃዎች በጥንት ዘመናት የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳን ኢየሱስ በታሪክ የታወቀ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ ያረጋግጣሉ። ሰዎች የኢየሱስን ታሪካዊነት አለበቂ ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ መጠራጠር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመንና በሃያኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።”
ኢየሱስ ማን ነበር?
11. (ሀ) በመሠረቱ ስለ ኢየሱስ የሚተርከው ብቸኛ የሆነ የታሪካዊ መረጃ ምንጭ ምንድነው? (ለ) የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን ብለዋል?
11 ይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ የታወቁት ነገሮች ሁሉ ተመዝግበው የቆዩልን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተከታዮቹ ነው። የእነዚህ ፀሐፊዎች ትረካ በወንጌሎቹ ውስጥ ማለትም በሁለት ሐዋርያቱ በማቴዎስና በዮሐንስ እንዲሁም በሁለት ደቀመዛሙርቱ በማርቆስና በሉቃስ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት መጻሕፍት ውስጥ ነው። የእነዚህ ሰዎች ትረካ ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን ይገልጽልናል? ኢየሱስ ማን ነበር? የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ተከታዮችም ይህ ጥያቄ አሳስቦአቸው ነበር። ኢየሱስ በሞገድ የተናወጠውን ባሕር ገስጾ ጸጥ ሲያሰኝ በተመለከቱ ጊዜ በጣም ተደንቀው “ኧረ ለመሆኑ ይህ ማነው?” ብለው ነበር። ከዚያ ቆየት ብሎም በሌላ ጊዜ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እናንተስ እኔን ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠይቆ ነበር።—ማርቆስ 4:41፣ ማቴዎስ 16:15
12. ኢየሱስ እግዚአብሔር አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን?
12 እናንተስ ይህ ጥያቄ ቢቀርብላችሁ ምን ብላችሁ ትመልሱ ነበር? ኢየሱስ ማን ነበር? በሕዝበክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በሰው መልክ የመጣ፣ ሥጋ የለበሰ አምላክ ነው ይላሉ። ከኢየሱስ ጋር አዘውትረው ይሄዱ የነበሩት ሰዎች ግን ኢየሱስ አምላክ ነው ብለው አላመኑም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ክርስቶስ የሕያው አምላክ ልጅ” ነው ብሎ ጠርቶታል። (ማቴዎስ 16:16) የፈለጋችሁትን ያህል ስታገላብጡ ብትውሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ አምላክ ነኝ ያለበትን ቦታ ልታገኙ አትችሉም። ኢየሱስ ለአይሁዳውያን የተናገረው እርሱ “የአምላክ ልጅ” እንደሆነ ነው። አምላክ ነኝ አላለም።—ዮሐንስ 10:36
13. ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተለየ የሆነው እንዴት ነበር?
13 ኢየሱስ በማዕበል ይናወጥ በነበረ ባሕር ላይ በእግሩ ሲሄድ ደቀመዛሙርቱ በተመለከቱ ጊዜ እንደማንኛውም ተራ ሰው እንዳልሆነ ተገንዝበው ነበር። (ዮሐንስ 6:18-21) በጣም ልዩ የሆነ ሰው ነበር። ይህም የሆነው ቀደም ሲል መንፈሣዊ አካል ሆኖ፣ አዎ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው የመላእክት አለቃ ሆኖ ከአባቱ ጋር በሰማይ ይኖር ስለነበረ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ይሁዳ 9) አምላክ ሌሎች ነገሮችን ከመፍጠሩ በፊት የፈጠረው ኢየሱስን ነበር። (ቆላስይስ 1:15) ስለዚህ በጠፈር ውስጥ ያሉት ግዑዛን ነገሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው ዘመናት፣ ምናልባትም በቢልዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ኢየሱስ ከታላቁ ፈጣሪና ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ጋር በተቀራረበ ወዳጅነት አብሮ ይኖር ነበር።—ምሳሌ 8:22, 27-31፤ መክብብ 12:1
14. ኢየሱስ ሰው የሆነው እንዴት ነው?
14 ከዚያም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ አምላክ የልጁን ሕይወት ወደ አንዲት ሴት ማህፀን አዛወረው። በዚህ ዓይነት ኢየሱስ በተለመደው መንገድ ከሴት የተወለደ ሰብአዊ ልጅ ሆነ። (ገላትያ 4:4) ኢየሱስ በእናቱ በማርያም ማህፀን ውስጥ እያደገ በነበረበት ጊዜና ከተወለደም በኋላ በልጅነቱ ዘመን አምላክ ሰብዓዊ ወላጆቹ እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰዎች ጥገኛ ነበር። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሙሉ ሰው ሆነ። ከአምላክ ጋር በሰማይ ይኖር የነበረበትንም ዘመን ሙሉ በሙሉ እንዲያስታውስ ተደረገ። ይህም የሆነው ሲጠመቅ ‘ሰማያት በተከፈቱለት ጊዜ ነበር።’—ማቴዎስ 3:16፤ ዮሐንስ 8:23፣ 17:5
15. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሰው እንደነበረ እንዴት እናውቃለን?
15 በእርግጥም ኢየሱስ ልዩ ሰው ነበር። ቢሆንም አምላክ መጀመሪያ ፈጥሮ በኤደን ገነት ውስጥ ካስቀመጠው ከአዳም ጋር እኩል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ፣ የኋለኛው አዳም ደግሞ ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” በማለት ይገልጽልናል። ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” ተብሎ ተጠርቷል፤ ምክንያቱም እንደ መጀመሪያው አዳም ፍጹም ሰብዓዊ አካል ስለነበረ ነው። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ግን ከሙታን ተነስቶ መንፈሣዊ አካል በመሆን ከአባቱ ጋር በሰማይ መኖር ጀመረ።—1 ቆሮንቶስ 15:45
ስለአምላክ ለማወቅ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምንድነው?
16. (ሀ) ከኢየሱስ ጋር አብሮ ለመዋል መቻል ትልቅ መብት የሆነው ለምንድነው? (ለ) ኢየሱስን ማየት አምላክን ከማየት ጋር አንድ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድነው?
16 አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አብረውት ለመዋል በመቻላቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት እንዳገኙ ለአንድ አፍታ አስቡ! የይሖዋ አምላክ የቅርብ ባልንጀራ በመሆን በቢልዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖረ ሰው ሲናገር መስማት፣ የሚያደርገውን ማየት፣ እርሱን ማነጋገርና ከእርሱ ጋር አብሮ መሥራት ምን ያህል የሚያስደስት ነገር እንደሆነ ገምቱ! ኢየሱስ ታማኝ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የሰማያዊ አባቱን ምሳሌ ተከትሏል። እንዲያውም አባቱን የመሰለው ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስለነበረ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለሐዋርያቱ “እኔን ያየ አብን አይቷል” ለማለት ችሎ ነበር። (ዮሐንስ 14:9, 10) አዎ፣ ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ አጋጥሞት በነበረው በእያንዳንዱ ሁኔታ አባቱ የሆነው ሁሉን የሚችለው አምላክ በዚህ ምድር ላይ ቢኖር ኖር የሚያደርገውን አድርጎአል። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት ስናጠና አምላክ እንዴት ያለ ባሕርይ ያለው መሆኑን እየተማርን ነው ማለት ነው።
17. በመጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣ የነበረው “ኢየሱስ፣ ሕይወቱና አገልግሎቱ” የተባለው ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ለምን ዓላማ አገልግሎአል?
17 ለዚህም ዓላማ ሲባል “ኢየሱስ፣ አገልግሎቱና ሕይወቱ” የሚል ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ከሚያዝያ 1985 ጀምሮ እስከ ሰኔ 1991 ለስድስት ዓመታት መጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጣ ቆይቷል። ይህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ስለ ኢየሱስ የተሟላ ዕውቀት እንዲኖረን ከማስቻሉም በላይ ስለ ሰማያዊ አባቱ ስለ ይሖዋ አምላክ የበለጠ ዕውቀት እንድናገኝ አስችሎናል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎች ከወጡ በኋላ አንድ አቅኚ አገልጋይ አድናቆቱን ለመጠበቂያ ግንብ ማህበር ሲገልጽ “ወደ አብ ለመቅረብ ልጁን በይበልጥ ከማወቅ የተሻለ ምን መንገድ ሊኖር ይችላል!” ሲል ጽፎአል። እውነተኛ አባባል ነው። አብ ለሰዎች ያለው ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሁም ልበ ሠፊነቱ በልጁ ሕይወት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ታይቶአል።
18. የመንግሥቱ መልእክት አመንጪ ማን ነው? ኢየሱስስ ይህን ያሳወቀው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ለአባቱ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በመገዛቱ የተገለጸውንና ለአባቱ ያለውን ፍቅር ለማስተዋል መቻል በጣም ያስደስታል። ኢየሱስ ሊገድሉት ይፈልጉ ለነበሩ አይሁዳውያን “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች” አላደርግም ብሎአል።” (ዮሐንስ 8:28) ስለዚህ ኢየሱስ ይሰብክ የነበረው የመንግሥት መልእክት ከራሱ ያመነጨው አልነበረም። የመልእክቱ ምንጭና ባለቤት ይሖዋ አምላክ ነበር። ኢየሱስም ይህን ን ደጋግሞ ተናግሯል። “እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፣ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትዕዛዝ ሰጠኝ። . . . ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ” ብሎአል።—ዮሐንስ 12:49, 50
19. (ሀ) ኢየሱስ ያስተማረው ይሖዋ በሚያስተምርበት መንገድ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ኢየሱስ እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ሰው የሆነው ለምንድነው?
19 ይሁን እንጂ ኢየሱስ አባቱ የነገረውን በመናገርና በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። የተናገረውና ያስተማረው አባቱ ራሱ በሚናገርበት ወይም በሚያስተምርበት በዚያው መንገድ ነው። ከዚህም በላይ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነትና በተግባራቱ ሁሉ አባቱ እርሱን ያጋጠመው ሁኔታ ቢያጋጥመው ኖሮ የሚያደርገውን ያንኑን ነገር አድርጎአል። ኢየሱስ ይህን ሲያስረዳ “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም። ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። ” (ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ በማንኛውም መንገድ የአባቱ የይሖዋ አምላክ ፍጹም ነፀብራቅ ነበር። ስለዚህ በምድር ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። አዎ፤ በምድር ላይ የተነሱት ወታደራዊ ሠራዊቶችና የባሕር ኃይሎች፣ ነገሥታትና ፓርላማዎች አንድ ላይ ቢጣመሩ በሰው ልጅ ላይ ኢየሱስ ያስከተለውን ለውጥ ያህል ሊያስከትሉ አለመቻላቸው ሊያስደንቀን አይገባም። ስለዚህ የዚህን ታላቅ ሰው አኗኗርና ባሕርይ በትኩረት ማጥናታችን በጣም በጣም አስፈላጊ ነው።
የአምላክ ፍቅር በኢየሱስ ላይ ታይቶአል
20. ሐዋርያው ዮሐንስ አምላክ ፍቅር መሆኑን ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው?
20 የኢየሱስን አኗኗርና አገልግሎት በጥልቀትና በጥንቃቄ ስንመረምር ምን ለማወቅ እንችላለን? ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” ብሎአል። (ዮሐንስ 1:18) ቢሆንም ዮሐንስ በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ ፍጹም በሆነ እርግጠኝነት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሎአል። ዮሐንስ እንዲህ ለማለት የቻለው በኢየሱስ ላይ ከተመለከታቸው ሁኔታዎች ስለአምላክ ፍቅር ለማወቅ ስለቻለ ነበር።
21. ኢየሱስን በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው ያደረገው ምንድነው?
21 ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ርህሩህ፣ ደግ፣ ትሁትና ሰዎችን የሚያቀርብ ነበር። ደካሞችና ቅስማቸው የተሰበረ ሰዎች ከእርሱ ጋር ሲሆኑ አይከብዳቸውም ነበር። ሁሉም ዓይነት ሰዎች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ሕጻናትም ሆኑ ትልልቆች፣ ባለጠጎችም ሆኑ ድሆች፣ ባለሥልጣኖችም ሆኑ ኃጢአተኞች ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። በእርግጥም እስከዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው እንዲሆን ያስቻለው አባቱን በመምሰል ያሳየው ታላቅ ፍቅር ነው። ናፖሊዮን ቦናፓርት እንኳን የሚከተለውን እንዳለ ይነገርለታል፦ “እስክንድር፣ ቄሣር፣ ሻርላማይም ሆነ እኔ ሠፊ ግዛት ያላቸውን መንግሥታት ለማቋቋም ችለናል። ነገር ግን ያገኘነው ከፍተኛ ውጤት በምን ላይ የተመሠረተ ነበር? በኃይል ላይ የተመሠረተ ነበር። መንግሥቱን በፍቅር ላይ የመሠረተ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዛሬው ቀን እንኳን ለእርሱ ሲሉ ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ።”
22. የኢየሱስ ትምህርት ሥር ነቀል የነበረው እንዴት ነው?
22 ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች እስከዚያን ጊዜ ድረስ የነበረውን የተለመደውን አስተሳሰብ የሚገለብጡ ነበሩ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ክፉውን አትቃወሙ፣ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት።” “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁምን መርቁ።” “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴ 5:39, 44፣ 7:12) ሰው ሁሉ እነዚህን ዕጹብ ድንቅ ትምህርቶች በሥራ ላይ ቢያውል ኖሮ ዓለማችን ምን ያህል የተለየች በሆነች ነበር!
23. ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ለመንካትና መልካም እንዲያደርጉ ለመቀስቀስ ምን አድርጎአል?
23 የኢየሱስ ምሳሌዎች የሰዎችን ልብ የሚነኩና ከመጥፎ ነገር እንዲጠበቁና መልካም እንዲያደርጉ የሚያነሳሱ ነበሩ። አንድን የተጎዳ ሰው የራሱ ወገን የሆኑ ሃይማኖተኛ ሰዎች ትተውት ሲያልፉ አንድ የተናቀ ሳምራዊ የራሱ ወገን ያልሆነውን ሰው እንደረዳ ስለሚገልጸው ታሪክ ሳታውቁ አትቀሩም። አዛኝ፣ ርህሩህና ይቅር ባይ ስለሆነ ስለ አንድ አባትና ስለ አባካኝ ልጁ የሚገልጸው ምሳሌም አለ። የ60 ሚልዮን ዲናር ዕዳ ከተማረለት በኋላ የ100 ዲናር ዕዳ ሊከፍል ያልቻለውን ባሪያ ስላሳሰረው ባሪያ የሚገልጸው ምሳሌስ? ኢየሱስ ቀላል በሆኑ ምሳሌዎች አማካኝነት የራስ ወዳድነትና የስግብግብነት ድርጊቶች ጸያፍ መስለው እንዲታዩ፤ የፍቅርና የምህረት ድርጊቶች ደግሞ በጣም ማራኪ መስለው እንዲታዩ አድርጓል።—ማቴዎስ 18:23-35፣ ሉቃስ 10:30-37፣ 15:11-32
24. ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም የምንለው ለምንድነው?
24 ይሁን እንጂ በተለይ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይስብ የነበረውና በእነርሱም ላይ መልካም ለውጥ ለማምጣት ያስቻለው ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ መኖሩ ነበር። የሚሰብከውን ነገር በሥራ ያውል ነበር። የሌሎችን ጉድለት በትዕግሥት ያልፍ ነበር። ደቀመዛሙርቱ ከመካከላቸው ማናቸው ታላቅ እንደሚሆን ጭቅጭቅ ባነሱ ጊዜ በደግነት አረማቸው እንጂ በክፉ ቃል አልገሰጻቸውም። ራሱን ዝቅ አድርጎ አገለገላቸው። እግራቸውንም እንኳን አጠበ። (ማርቆስ 9:30-37፣ 10:35-45፣ ሉቃስ 22:24-27፣ ዮሐንስ 13:5) በመጨረሻም ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ልጅ ሲል ተሰቃይቶ ለመሞት ፈቃደኛ ሆነ። አላንዳች ጥርጥር እስከዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ኢየሱስ ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ኢየሱስ በእርግጥ የነበረና በታሪክ የታወቀ ሰው ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?
◻ ኢየሱስ ሰው እንደነበረ እንዴት እናውቃለን? ሆኖም ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የሚለየው እንዴት ነበር?
◻ ስለ ኢየሱስ ሕይወት ማጥናት ስለአምላክ ለመማር የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ስለ ኢየሱስ በማጥናት ስለ አምላክ ፍቅር ምን ልንማር እንችላለን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ሐዋርያት በመገረም “ይህ ማነው?” ብለዋል