የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የናይጄሪያ ተማሪዎች ስለ ታማኝነታቸው ተባረኩ
ሐዋርያው ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ሲል ጽፎአል። (ሮሜ 12:18) በናይጄሪያ የሚኖሩ ተማሪ የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ምክር በስደትም ጊዜ ቢሆን በሥራ ላይ አውለዋል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ባርኳቸዋል።
◻ የይሖዋ ምሥክሮችን በጣም የሚጠላ አንድ አስተማሪ ነበር። በአንድ የጠዋት ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ሁሉ ወደ ፊት እንዲመጡ ጠራቸውና የብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ አዘዛቸው። እነርሱም ከአምላክ ሌላ ምንም ነገር ለማምለክ እንደማይፈልጉ ገለጹና አንዘምርም አሉ። ከዚያም አስተማሪው ሁሉንም ወደ ውጪ ወሰዳቸውና ሳር እንዲያጭዱ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ የቀሩት ተማሪዎች በክፍላቸው ውስጥ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር።
አንድ በዕድሜ የጎለመሰ ምሥክር የይሖዋ ምሥክሮችን የገለልተኝነት አቋም ለማብራራት ትምህርት ቤት የተባለውን ብሮሹር ይዞ ወደ አስተማሪው ሔደ። ነገር ግን አስተማሪው ስለጉዳዩ ለመወያየት ወይም ብሮሹሩን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም የልጆቹን ቅጣት ይበልጥ አባሰው።
ወጣት ምስክሮቹ በተሰጣቸው ቅጣት ጸንተው ቆሙ። አስተማሪው በማይኖርበትም ጊዜ እንኳን ሣሩን ያጭዱ ነበር። አንድ ቀን አስተማሪው ተደብቆ ሲመለከታቸው የመንግስቱን መዝሙሮች እየዘመሩ ሣር ያጭዱ ነበር። እሱም በዚህ ጠባያቸው በጣም በመደነቁ ስለ አቋማቸው በአድናቆት በመግለጽ ወደ ክፍል መለሳቸው። ውጤቱስ ምን ሆነ? አሁን አስተማሪው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ነው።
በእርግጥም እነዚህ ተማሪዎች ለይሖዋና ለሥርዓቱ ታማኝ በመሆናቸው ተባርከዋል።—ምሳሌ 10:22
◻ ሩትና ጓደኞችዋም “የዓለም ክፍል አይደሉም” ለሚለው የይሖዋ ሥርዓት ታማኝ በመሆናቸው ተባርከዋል። (ዮሐንስ 17:16 አዓት) የ18 ዓመቷ ሩት የዘወትር አቅኚነት አገልግሎት የጀመረችው በ12 ዓመቷ ነበር። እሷና ሌሎች ምሥክሮች የብሔራዊ መዝሙር ለመዘመር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ስደት ደርሶባቸው ነበር። አንዲት አስተማሪ የልጃገረዶቹን ወላጆች ለማነጋገር ጠየቀች። እነርሱም ትምህርት ቤት በሚለው ብሮሹር በመጠቀም ካነጋገሩአት በኋላ አስተማሪዋ በተሰጣት ማብራሪያ ረካች። ከዚያ በኋላ ተማሪዎቹን አላስቸገረቻቸውም።
ይሁን እንጂ አንድ ቀን አንዲት ህንዳዊ አስተማሪ ይህች ልጃገረድ የብሔራዊ መዝሙር አልዘምርም ባለች ጊዜ በክፍል ተማሪዎቿ ፊት እየሰደበች ቀጣቻት። ልጅቷም እምነቷን በድፍረት አስረዳች። አስተማሪዋም የትምህርት ቤቱን ዲሬክተር እንድታነጋግር ይዛት ሄደች። እዚያም በደረሱ ጊዜ ምክትል ዲሬክተሯም በቢሮው ውስጥ ነበረች። ዲሬክተሯና ምክትል ዲሬክተሯ ጉዳዩን ሲሰሙ ከት ብለው ሳቁ። ዋናዋ ዲሬክተር ወደ አስተማሪዋ ዞር ብላ “ወይዘሮ፣ በነዚህ ልጃገረዶች ራስሽን አታስጨንቂ። ብትገድያቸው እንኳን መዝሙሩን አይዘምሩልሽም። ስለ እነርሱ ሰምተሽ አታውቂም?” አለቻት። እሷና ረዳቷ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምነትና ጉብዝና ተነጋገሩ። ዲሬክተሯ በልጃገረዲቱ ላይ በደረሰው ችግር በጣም ማዘንዋን ገለጠችላት። ከዚያም በመጨመር “በእምነትሽና በሥራሽ ግፊበት። ሃይማኖታችሁንና በውጪም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ የምታሳዩትን የድፍረት አቋም አደንቃለሁ” አለቻት። ቀደም ብላ የተቃወመቻትም አስተማሪ ምሥክሯን ይቅርታ በመጠየቅ ምሥክሮቹ የሚወስዱትን የገለልተኝነት አቋም እንደተረዳች ተናገረች።
እነዚህ ልጆች ለምስል ወድቀው በመስገድ ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ያላፈረሱትን የሶስቱን ዕብራውያንና እንዲሁም ወደ ይሖዋ መጸለይ አልተውም ያለውን የዳንኤልን ምሳሌ ተከትለዋል። ይሖዋም ለአምላክ የጽድቅ ሕጎች ባላቸው ታማኝነት ባርኳቸዋል።—ዳንኤል ምዕራፍ 3 እና 6