ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ወንጌላውያን መሆን አለባቸው
“የወንጌላዊነትን [ወይም የሚስዮናዊነትን] ሥራ ፈጽም።”—2 ጢሞቴዎስ 4:5 አዓት የግርጌ ማስታወሻ
1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በወንጌላውያን የተሰበከው የምሥራች ምን ነበር?
በዛሬው ጊዜ ወንጌላዊ መሆን ምን ማለት ነው? አንተስ ወንጌላዊ ነህን? “ወንጌላዊ” የሚለው ቃል የመጣው “የምሥራቹ ሰባኪ” የሚል ትርጉም ካለው ኤውአግሊስቴስ የተባለ የግሪክኛ ቃል ነው። የክርስቲያን ጉባኤ በ33 እዘአ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ክርስቲያናዊው ምሥራች የአምላክን የመዳን መንገድ አጉልቶ የገለጸ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ ግዛቱን በሰው ልጆች ለመጀመር በመጨረሻው ዘመን እንደሚመለስ አስታውቋል።—ማቴዎስ 25:31, 32፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1፤ ዕብራውያን 10:12, 13
2. (ሀ) የምሥራቹ የያዘው ፍሬ ነገር በዘመናችን የዳበረው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ባሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ላይ የተጣለው ግዴታ ምንድን ነው?
2 ከ1914 ወዲህ ኢየሱስ ስለመመለሱና ስለማይታይ መገኘቱ የተናገረው ምልክት በመፈጸም ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች ታይተዋል። (ማቴዎስ 24:3-13, 33) አሁንም እንደገና ምሥራቹ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” የሚለውን መግለጫ ሊጨምር ችሏል። (ሉቃስ 21:7, 31; ማርቆስ 1:14, 15) በእርግጥም በማቴዎስ 24:14 ላይ የተመዘገበው “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” የሚለው የኢየሱስ ትንቢት በታላቅ ሁኔታ የሚፈጸምበት ጊዜ መጥቷል። ስለዚህ ዛሬ ወንጌላዊነት የተቋቋመችውን የአምላክ መንግሥትና ይህችም መንግሥት በቅርቡ ለታዛዥ ሰዎች የምታመጣላቸውን በረከቶች በቅንዓት ማስታወቅን ይጨምራል። ሁሉም ክርስቲያኖች ይህን ሥራ እንዲሠሩና ‘ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ታዘዋል።”—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ራእይ 22:17
3. (ሀ) “ወንጌላዊ” የሚለው ቃል ምን ተጨማሪ ትርጉም አለው? (ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1, ገጽ 770፣ 2ኛው አምድ አንቀጽ 2ን ተመልከቱ።) (ለ) ይህስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሳል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “ወንጌላዊነት” የሚለውን ቃል ምሥራቹን ስብከት በአጠቃላይ ለማመልከት ከመጠቀሙ በተጨማሪ የምሥራቹ ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች ለመስበክ ሲሉ የተወለዱበትን አካባቢ ትተው የሚሄዱ ሰዎችን ለማመልከት ልዩ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ፊልጶስ፣ ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ የመሳሰሉ ብዙ ሚስዮናዊ ወንጌላውያን ነበሩ። (ሥራ 21:8፤ ኤፌሶን 4:11) ይሁን እንጂ ከ1914 ወዲህ ስላለው ልዩ የሆነ ዘመናችንስ ምን ሊባል ይቻላል? በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢና በሚስዮናዊነት የወንጌላዊነቱን ሥራ ለመፈጸም ራሳቸውን አቅርበዋልን?
ከ1919 ወዲህ የተገኘው እድገት
4, 5. ከ1914 በኋላ በነበሩት ዓመታት ለወንጌላዊነት ሥራ የነበሩት አጋጣሚዎች ምን ነበሩ?
4 የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በ1918 ሲያበቃ የአምላክ አገልጋዮች ከከሐዲዎች፣ ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ከፖለቲካዊ ጓደኞቻቸው እየጨመረ የሚሄድ ስደት አጋጠማቸው። እንዲያውም ሰኔ 1918 በዩናይትድ ስቴትስ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ይመሩ የነበሩት ወንድሞች የሐሰት ክስ ቀርቦባቸው የ20 ዓመት እሥራት በተፈረደባቸው ጊዜ እውነተኛው ክርስቲያናዊ የወንጌላዊነት ሥራ ተቋርጦ ነበር ለማለት ይቻላል። የአምላክ ጠላቶች የምሥራቹን ስብከት ሥራ ለማቆም ተሳካላቸውን?
5 በመጋቢት ወር 1919 ድንገት ሳይታሰብ የማኅበሩ ባለሥልጣኖች ከእሥራት ተለቀቁ። በኋላም ለእሥራት ካበቃቸው የሐሰት ክስ ነፃ መሆናቸው ተረጋገጠላቸው። እነዚህ አዲስ ነፃነት ያገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት ተባባሪ ወራሾች በመሆን ወደ ሰማያዊ ሽልማታቸው ከመሰብሰባቸው በፊት ብዙ የሚሠሩት ሥራ እንደሚቀር ተገነዘቡ።—ሮሜ 8:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ 4:18
6. የወንጌላዊነቱ ሥራ ከ1919 እና ከ1939 ወዲህ ዕድገት ያሳየው እንዴት ነው?
6 በ1919 የምሥራቹን በማስፋፋት ሥራ እንደሚካፈሉ ሪፖርት ያደርጉ የነበሩት ሰዎች ቁጥር ከ4,000 የሚያንስ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ሃያ ዓመታት በርካታ ሰዎች ለሚስዮናዊ ወንጌላዊነት ሥራ ራሳቸውን አቀረቡና አንዳንዶቹ ወደ አፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ አገሮች ተላኩ። ከሃያ ዓመት የመንግሥት ስብከት በኋላ ማለትም በ1939 የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር አድጎ ከ73,000 በላይ ሆነ። ብዙ ስደት በነበረበት ሁኔታ የተገኘው ይህ ከፍተኛ ጭማሪ የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ከደረሰው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው።—ሥራ 6:7፤ 8:4, 14-17፤ 11:19-21
7. በ47 እና በ1939 እዘአ የክርስቲያን ወንጌላዊነትን ሥራ በሚመለከት ምን ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር?
7 ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ የነበሩት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙት እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የፕሮቴስታንት አገሮች ነበር። እንዲያውም ከ73,000 የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ከአውስትራሊያ፣ ከብሪታኒያ፣ ከካናዳ፣ ከኒውዚላንድና ከዩናይትድ ስቴትስ የተውጣጡ ነበሩ። በ47 እዘአ አካባቢ እንደተደረገው ወንጌላውያን እምብዛም ባልተሰበከባቸው የዓለም አገሮች ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማበረታታት አንድ ነገር አስፈልጎ ነበር።
8. እስከ 1992 የጊልያድ ትምህርት ቤት ያከናወናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
8 የጦርነት ጊዜ እገዳዎችና ስደቶች የይሖዋ ኃያል መንፈስ አገልጋዮቹን ለበለጠ መስፋፋት እንዲዘጋጁ ከማንቀሳቀስ ሊያግዱ አልቻሉም። በ1943 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጧጧፈበት ወቅት የአምላክ ድርጅት የምሥራቹን ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ በሠፊው ለማሠራጨት በማሰብ የጊልያድን የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አቋቋመ። ይህ ትምህርት ቤት እስከ መጋቢት 1992 ባለው ጊዜ 6,517 ሚስዮናውያን ወደ 171 የተለያዩ አገሮች ልኮአል። በተጨማሪም በውጭ አገሮች ያሉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፎችን ለሚያስተዳድሩ ወንዶች ማሠልጠኛ ተሰጥቷል። እስከ 1992 ድረስ 97 ከሚሆኑት የቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪዎች መካከል 75ቱ በጊልያድ የሠለጠኑ ናቸው።
9. በወንጌላዊነቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ዕድገት ድርሻቸውን ያበረከቱት የትኞቹ የማሠልጠኛ ፕሮግራሞች ናቸው?
9 ከጊልያድ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ሌሎች የማሠልጠኛ ፕሮግራሞችም የይሖዋን ሕዝቦች የወንጌላዊነት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሻሽሉ አስታጥቀዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል ቲኦክራቲካዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት በምድር ዙሪያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይካሄዳል። ይህ ዝግጅትና ሳምንታዊው የአገልግሎት ስብሰባ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥት አስፋፊዎች በሕዝባዊ አገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አሠልጥኗል። በተጨማሪም ሽማግሌዎችና ዲያቆናት እያደጉ ለሚሄዱት ጉባኤዎች የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ እንዲችሉ ጠቃሚ ማሠልጠኛ የሚሰጠው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት አለ። የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን በስብከት ሥራቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። በቅርቡም የአገልግሎት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በብዙ አገሮች ተካሂዶ ያላገቡ ዲያቆናትና ሽማግሌዎች ዘመናዊ ጢሞቴዎሶች እንዲሆኑ ረድቶአል።
10. በአምላክ ድርጅት አማካኝነት የተሰጡት ግሩም ማሠልጠኛዎች ውጤት ምን ሆነ? (በሣጥኑ ያለውን መረጃ ጨምሩ።)
10 ይህ ሁሉ ማሠልጠኛ ምን ውጤት አስገኘ? በ1991 በ212 አገሮች በትጋት የሚሠሩ ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ከፍተኛ ቁጥር ሊገኝ ችሎአል። ይሁን እንጂ በ1939 ከነበረው ሁኔታ በተለየ መንገድ ከእነዚህ ምሥክሮች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት እንግሊዝኛ እምብዛም ከማይነገርባቸው ከካቶሊክ፣ ከኦርቶዶክስ፣ ክርስቲያን ካልሆኑ ወይም ከሌሎች አገሮች የተገኙ ናቸው።—“ከ1939 ወዲህ የተገኘ ዕድገት” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ።
ጥሩ ውጤት ያገኙት ለምንድን ነው?
11. ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልጋይነት ላገኘው የተሳካ ውጤት ያመሰገነው ማንን ነው?
11 የይሖዋ ምሥክሮች ላገኙት ዕድገት የሚያመሰግኑት ራሳቸውን አይደለም። በዚህ ፈንታ ሥራቸውን የሚመለከቱት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል በገለጸው መንገድ ነው፦ “አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ [ይሖዋ አዓት] እንደሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። . . . የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምሠራ ነንና።”—1 ቆሮንቶስ 3:5-7, 9
12. (ሀ) የአምላክ ቃል የወንጌላዊነቱ ሥራ የተሳካ ውጤት እንዲያስገኝ በማድረግ ረገድ ያለው ድርሻ ምንድን ነው? (ለ) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ሆኖ የተሾመው ማን ነው? ለእርሱ ራስነት ራሳችንን እንደምናስገዛ የምናሳይበት አንዱ ትልቅ መንገድ ምንድን ነው?
12 የይሖዋ ምሥክሮች ያገኙት ከፍተኛ ዕድገት በአምላክ በረከት የተገኘ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ሥራው የአምላክ ሥራ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን ሐቅ በመገንዘብ የአምላክን ቃል ለማጥናት ጥረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። በወንጌላዊነት ሥራቸው ላይ የሚናገሩት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) በወንጌላዊነት ሥራ ጥሩ ውጤት የሚያገኙበት ሌላው ምክንያት አምላክ የጉባኤው ራስ አድርጎ ለሾመው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ዕውቅና ስለሚሰጡ ነው። (ኤፌሶን 5:23) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አድርጎ ከሾማቸው ጋር በመተባበር ኢየሱስ የጉባኤው ራስ መሆኑን እንደተገነዘቡ አሳይተዋል። ሐዋርያትና ሌሎች የኢየሩሳሌም ጉባኤ ሽማግሌዎች የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን አስተዳደር አካል አባላት ነበሩ። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሆኖ ይህንን የጎለመሱ ክርስቲያኖች ቡድን ለአከራካሪ ጉዳዮች እልባትና ለወንጌላዊነቱ ሥራ አመራር ለመስጠት ተጠቅሞበታል። ጳውሎስ ከዚህ መለኮታዊ ዝግጅት ጋር በቅንዓት መተባበሩ ለጎበኛቸው ጉባኤዎች ሁሉ ጭማሪ አስገኝቷል። (ሥራ 16:4, 5፤ ገላትያ 2:9) ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቲያን ወንጌላውያን የአምላክን ቃል አጥብቀው በመያዝና ከአስተዳደር አካሉ ከሚመጡ አመራሮች ጋር በቅንዓት በመተባበር በአገልግሎታቸው ውጤት እንደሚያገኙ እርግጠኞች ናቸው።—ቲቶ 1:9፤ ዕብራውያን 13:17
ሌሎች እንደሚበልጡ አድርጎ መቁጠር
13, 14. (ሀ) በፊልጵስዩስ 2:1-4 ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) በወንጌላዊነቱ ሥራ ስንካፈል ይህን ምክር ማስታወስ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ ለእውነት ፈላጊዎች ልባዊ ፍቅር አሳይቷል፣ የበላይነት ወይም የዘረኝነት ዝንባሌ አላሳየም። በዚህም ምክንያት የእምነት ባልደረቦቹን ‘ሌሎች የበላይ እንደሆኑ እንዲቆጥሩ’ ሊመክር ችሎአል።—ፊልጵስዩስ 2:1-4
14 ዛሬም በዚሁ ዓይነት እውነተኛ ክርስቲያን ወንጌላውያን ከተለያዩ ጎሣዎችና አስተዳደግ ከመጡ ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ራሳቸውን ከፍ የማድረግ ዝንባሌ አያሳዩም። አፍሪካ ውስጥ በሚስዮናዊነት እንዲሠሩ ከተመደቡት ከአሜሪካ ከመጡ የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ እንደተናገረው፦ “ከእነርሱ እንደማንበልጥ በደንብ አውቃለሁ። ምናልባት ከእነርሱ የበለጠ ገንዘብና መደበኛ የሚባለው ትምህርት ይኖረን ይሆናል፣ ነገር ግን እነርሱ [የአካባቢው ሕዝብ] ከእኛ የሚበልጡ ባሕርዮች አሏቸው።”
15. በውጭ አገር እንዲሰብኩ የተመደቡ ሰዎች ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑ ሰዎች እውነተኛ አክብሮት ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 በእርግጥም የምሥራቹን ለምናካፍላቸው ሰዎች እውነተኛ አክብሮት በማሳየት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዲቀበሉ ቀላል እናደርግላቸዋለን። አንድ ሚስዮናዊ ወንጌል ሰባኪ እንዲረዳቸው ከተመደበባቸው ሰዎች ጋር መኖሩ የሚያስደስተው መሆኑን ማሳየቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ያለፉትን 38 ዓመታት በአፍሪካ ያሳለፈ አንድ ጥሩ ውጤት ያገኘ ሚስዮናዊ “ይህ አገሬ እንደሆነና በተመደብንበት ጉባኤ ያሉት ደግሞ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደሆኑ ከአንጀቴ ይሰማኛል። ለዕረፍት ወደ አገሬ ወደ ካናዳ በተመለስኩ ጊዜ በእውነት በአገሬ እንዳለሁ ሆኖ አልተሰማኝም። ካናዳ በቆየሁበት የመጨረሻ ሳምንት ወደ ምድብ ቦታዬ ለመመለስ እቁነጠነጥ ነበር። ሁልጊዜም የሚሰማኝ እንደዚሁ ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼና ለወንድሞቼና ለእህቶቼ እንደገና መመለሴ ምን ያህል ደስ እንዳለኝ ስነግራቸው ከእነርሱ ጋር ለመሆን ፍላጎት ያለኝ መሆኔን በመገንዘባቸው ተደስተዋል” በማለት ገልጿል።—1 ተሰሎንቄ 2:8
16, 17. (ሀ) ብዙ ሚስዮናውያንና የአካባቢው ወንጌላውያን በአገልግሎታቸው ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ሲሉ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቀብለዋል? (ለ) አንድ ሚስዮናዊ በተመደበበት አካባቢ ቋንቋ በመናገሩ ምክንያት ምን ተሞክሮ አጋጥሞታል?
16 አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው የውጭ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች የሚኖሩበት ክልል ሲያገኙ ቋንቋውን ለመማር ጥረት ያደርጋሉ። ይህን በማድረጋቸው ሌሎች ከእነርሱ እንደሚበልጡ መቁጠራቸውን አሳይተዋል። አንድ ሚስዮናዊ “ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአፍሪካውያንና አውሮፓዊ ዝርያ ባላቸው ሰዎች መካከል ያለመተማመን መንፈስ ይታያል። ሆኖም የአካባቢውን ቋንቋ መናገር ይህን ያለመተማመን ስሜት ቶሎ ያስወግደዋል” በማለት ተናግሯል። የምሥራቹን የምናካፍላቸውን ሰዎች ቋንቋ መናገር ልባቸውን ለመንካት የሚረዳ ከፍተኛ መሣሪያ ነው። ይህም ጠንክሮ መሥራትንና በትሕትና መጽናትን ይጠይቃል። በአንድ የእስያ አገር የተመደበ ሚስዮናዊ እንደገለጸው፦ “ሁልጊዜ እየተሳሳታችሁና በተሳሳታችሁ ቁጥር እየተሳቀባችሁ መናገር ፈታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል። ሁሉንም መተዉ የተሻለ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል።” ይሁን እንጂ ይህ ሚስዮናዊ ለአምላክና ለጎረቤቱ ያለው ፍቅር እንዲጸና ረድቶታል።—ማርቆስ 12:30, 31
17 አንድ የውጭ አገር ሰው የምሥራቹን በራሳቸው ቋንቋ ሊያካፍላቸው በሚጥርበት ጊዜ የሚያዳምጡት ሰዎች ልብ እንደሚነካ መረዳት አዳጋች አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ በረከቶችን ያስገኛል። አፍሪካዊት አገር በሆነችው በሌሶቶ ያለች አንዲት አሜሪካዊት ሚስዮናዊ ለአንዲት በስጋጃ ሱቅ ለምትሠራ ሴት የሌሶቶ ቋንቋ በሆነው በሴሱቱ ቋንቋ ትናገር ነበር። ከሌላ የአፍሪካ አገር የመጣ የመንግሥት ሚኒስቴር በአካባቢው ሲዘዋወር ነበርና ጭውውቱን ሰማ። ወደ እርሷ መጣና ሲያመሰግናት ለእርሱም በራሱ ቋንቋ ተናገረችው። “ስዋሂልኛም ስለምታውቂ [ወደ አገሬ] መጥተሽ በሕዝባችን መካከል ለምን አትሠሪም?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም በጥበብ “እርሱስ ጥሩ ነበር። ነገር ግን የይሖዋ ምሥክር ነኝ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአገራችሁ ሥራችን ታግዷል” ብላ መለሰችለት። እርሱም “ሁላችንም ሥራችሁን የምንቃወም እንዳይመስልሽ። አብዛኞቻችን የይሖዋ ምሥክሮችን እንደግፋለን። ምናልባት አንድ ቀን በሕዝባችን መካከል በነፃነት ማስተማር ትችሉ ይሆናል” ብሎ መለሰ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህች ሚስዮናዊት የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ አገር የአምልኮ ነፃነት እንደተሰጣቸው ስትሰማ በጣም ተደሰተች።
የራስን መብት ለመተው ፈቃደኛ መሆን
18, 19. (ሀ) ጳውሎስ ጌታው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የጣረው በምን ትልቅ መንገድ ነው? (ለ) የምሥራቹን ለምናካፍላቸው ሰዎች ምንም ዓይነት የማሰናከያ ምክንያት ከማድረግ የመራቅን አስፈላጊነት ለማሳየት (በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሰውን ወይም የራስህን) አንድ ተሞክሮ ተናገር።
18 ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሎ በጻፈ ጊዜ “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ” ያለው ሌሎችን ከማሰናከል የመቆጠብን አስፈላጊነት ለመግለጽ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 10:31-33፤ 11:1
19 እንደ ጳውሎስ ለሚሰብኩላቸው ሰዎች ጥቅም ሲሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች የሆኑ ወንጌላውያን ብዙ በረከት ያጭዳሉ። ለምሳሌ ያህል በአንድ የአፍሪካ አገር ሚስዮናውያን የሆኑ ባልና ሚስት የጋብቻ በዓላቸውን ለማክበር ወደ አንድ በአካባቢው የሚገኝ ሆቴል እራት ለመብላት ሄዱ። የአልኮል መጠጦችን በመጠኑ መጠጣት በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘ ባለመሆኑ በመጀመሪያ ወይን ለመግዛት አስበው ነበር። (መዝሙር 104:15) ሆኖም እነዚህ ባልና ሚስት ምናልባት የአካባቢውን ሰዎች ያስቀይም ይሆናል ብለው በማሰብ አልኮል ላለመግዛት ወሰኑ። ባልዬው የሚከተለውን ታሪክ ይነግረናል፦ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከዚያ ሆቴል ወጥቤት ኃላፊ ጋር ተገናኘንና ከእርሱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን። ብዙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ‘ራት ለመብላት ወደ ሆቴሉ የመጣችሁበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ? ሁላችንም ከወጥ ቤቱ በር በስተ ኋላ ሆነን እንመለከታችሁ ነበር። አያችሁ፣ የቤተ ክርስቲያን ሚስዮናውያን መጠጣት ኃጢአት ነው ብለው ይነግሩናል። ወደ ሆቴሉ ሲመጡ ግን በብዛት ወይን አዝዘው ይጠጣሉ። እናንተም አልኮል ካዘዛችሁ ልትሰብኩ ስትመጡ አንሰማችሁም ብለን ወስነን ነበር’ ብሎ ነገረን።” ዛሬ ያ የወጥ ቤት ኃላፊና በሆቴሉ የሚሠሩ ሌሎች ሰዎች የተጠመቁ ምሥክሮች ሆነዋል።
አሁንም ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ
20. ቀናተኛ ወንጌላውያን ሆነን መጽናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙዎች እየጨበጡት ያሉትስ የትኛውን አስደሳች መብት ነው?
20 የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየቀረበ ሲመጣ የምሥራቹን ለመስማት የሚናፍቁ ገና ብዙ ሰዎች አሉ፣ ስለዚህ ከምን ጊዜውም የበለጠ እያንዳንዱ ክርስቲያን ታማኝ ወንጌላዊ በመሆን መጽናት አለበት። (ማቴዎስ 24:13) ታዲያ እንደ ፊልጶስ፣ ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ልዩ በሆነ መንገድ ወንጌላዊ በመሆን በዚህ ሥራ ያለህን ድርሻ ልታሰፋ ትችላለህን? ብዙዎች በአቅኚነት ሥራ በመካፈልና ይበልጥ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ለማገልገል ራሳቸውን በማቅረብ ከእነዚህ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሚስዮናዊ ወንጌላውያን ጋር የሚመሳሰል ነገር እየሠሩ ነው።
21. ለይሖዋ ሕዝቦች “ሥራ የሞላበት ሠፊ በር” የተከፈተላቸው በምን መንገድ ነው?
21 በቅርቡ ከዚህ በፊት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶባቸው በነበሩ በአፍሪካ፣ በእስያና በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ሠፊ የወንጌላዊነት መስኮች እየተከፈቱ ነው። ለሐዋርያው ጳውሎስ እንዳጋጠመው ሁሉ ለይሖዋ ሕዝቦችም “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶላቸዋል።” (1 ቆሮንቶስ 16:9) በቅርቡ የአፍሪካ አገር ወደ ሆነችው ወደ ሞዛምቢክ የደረሱ ሚስዮናዊ ወንጌላውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ለማስጠናት ጊዜ ሊበቃቸው አልቻለም። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በዚያ አገር የካቲት 11, 1991 ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘቱ ምንኛ ደስተኞች ልንሆን እንችላለን!
22. የአካባቢያችን የአገልግሎት ክልል በደንብ የተሰበከበት ሆነም አልሆነ ሁላችንም ምን ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን?
22 የአምልኮ ነፃነት በነበረባቸው አገሮችም ወንድሞቻችን የማያቋርጥ ጭማሪ እያገኙ ነው። አዎ፣ የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ አሁንም ገና የሚሠራ “ብዙ የጌታ ሥራ” አለ። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይህም በመሆኑ እያንዳንዳችን ‘አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ በመፈጸም የወንጌላዊነትን ሥራ ስንሠራ’ የቀረውን ጊዜ በጥበብ መጠቀማችንን እንቀጥል።—2 ጢሞቴዎስ 4:5፤ ኤፌሶን 5:15, 16
ልታብራሩ ትችላላችሁን?
◻ወንጌላዊ ምንድን ነው?
◻ የምሥራቹ የያዘው መልእክት ከ1914 ወዲህ የዳበረው እንዴት ነው?
◻ የወንጌላዊነቱ ሥራ ከ1919 ወዲህ እያደገ የመጣው እንዴት ነው?
◻ ለዚህ የወንጌላዊነት ሥራ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከ1939 ወዲህ የተደረገ መስፋፋት
በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን ከተላኩባቸው ሦስት አህጉሮች የተውጣጡ ምሳሌዎችን ተመልከቱ። በ1939 ምዕራብ አፍሪካ ሪፖርቱ የሚያደርጉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች 636 ብቻ ነበሩ። እስከ 1991 ድረስ ይህ ቁጥር በ12 የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ከ200,000 በላይ ወደመሆን አድጓል። ሚስዮናውያን በደቡብ አሜሪካ አገሮችም ለተገኘው ከፍተኛ ዕድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አንዷ ብራዚል ስትሆን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በ1939 ከነበረበት ከ114 ተነስቶ በሚያዝያ ወር 1992 335,039 ደርሶአል። በእስያ አገሮችም ከሚስዮናውያን መድረስ በኋላ ተመሳሳይ ዕድገት ተገኝቶአል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓን የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ይሰደዱ ነበር፤ ሥራቸውም ሊቋረጥ ተቃርቦ ነበር። ከዚያ በኋላ በ1949 ሥራውን እንደገና ለማደራጀት እንዲረዱ 13 ሚስዮናውያን ተላኩ። በዚያ የአገልግሎት ዓመት በመላው ጃፓን ሪፖርት ያደረጉት ከአሥር ያነሱ የአገሩ ተወላጆች የሆኑ አስፋፊዎች ነበሩ። በሚያዚያ 1992 ግን የአስፋፊዎች ጠቅላላ ቁጥር 167,370 ደርሶአል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሕዝበ ክርስትናና የቋንቋ ችግር
አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን የውጭ አገር ቋንቋ ለመማር ልባዊ ጥረት አድርገዋል፣ ብዙዎቹ ግን የአካባቢው ሕዝብ የእነርሱን የአውሮፓ ቋንቋ እንዲናገር ይጠብቁ ነበር። ጂኦፍሬይ ሙርሃውስ ሚስዮናውያን በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፦
“ችግሩ ያገሩን ቋንቋ መማር በሚስዮናውያኑ ዘንድ የሚታየው ቅዱሳን ጽሑፎችን ከመተርጎሚያ መንገድ የበለጠ ጥቅም እንዳለው ተደርጎ አልነበረም። አንድ ሚስዮናዊ ለተመደበበት አገር ተወላጅ በሁለት ሰዎች መካከል ጥልቅ የሆነ መግባባትን ሊያስገኝ በሚችል ርቱዕ አንደበት በራሱ ቋንቋ እንዲነግረው ለማድረግ በግለሰቦችም ሆነ ግለሰቦቹን በሚያሠሯቸው ማኅበሮች የተደረገው ጥረት እምብዛም ነበር። እያንዳንዱ ሚስዮናዊ በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ አንዳንድ ቃላት ይማር ይሆናል። ከዚያ አልፎ ግን የሐሳብ ልውውጥ የሚደረገው አፍሪካዊው ተወላጅ ራሱን ለእንግሊዛዊው እንግዳው አስተሳሰብ ማስገዛት አለበት ከሚል አመለካከት በመነጨ የፒጅን እንግሊዝኛ ተብሎ በሚጠራ ቀላል አነጋገር ነበር። ይህም ሌላው የዘር የበላይነት ማሳያ መንገድ ነበር።
በ1922 በሎንደን የሚገኘው የሩቅ ምሥራቅና የአፍሪካ ጥናት በቋንቋ ችግር ላይ አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር። ዘገባው “እኛ እንደሚመስለን ሚስዮናውያን የአገሬውን ቋንቋ በመናገር ረገድ የደረሱበት የችሎታ መጠን . . . በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ከዚያም አልፎ በአደገኛ ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ነው።”
የመጠበቂያ ግንብ ሚስዮናውያን ምንጊዜም የተመደቡበትን አካባቢ ቋንቋ መማር ግዴታቸው እንደሆነ ይቆጥራሉ። በሚስዮናዊ መስካቸው ሊሳካላቸው የቻለውም በዚህ ምክንያት ነው።