‘መጠመቅ አለብኝን?’
በሕይወታችን ውስጥ ማድረግ ካለብን ውሳኔዎች ሁሉ አንዳቸውም ቢሆኑ ‘መጠመቅ አለብኝን?’ ከሚለው የበለጠ አስፈላጊነት የላቸውም። ይህ ውሳኔ የሚጠይቅ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዚህ ጥያቄ ረገድ የምናደርገው ውሳኔ በአሁኑ አኗኗራችን ላይ ብቻ ሳይሆን በዘላለማዊ ደኅንነታችን ላይ ቀጥተኛ ውጤት ስላለው ነው።
ይህ ጥያቄ ተደቅኖብሃልን? ምናልባት ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ለጥቂት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ቆይተህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ወላጆችህ ከሕፃንነትህ ጀምሮ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲያስተምሩህ ቆይተው ይሆናል። አሁን ምን ማድረግ እንደሚኖርብህ መወሰን ያለብህ ደረጃ ላይ ደርሰሃል። ትክክለኛውን ውሳኔ ለማድረግ እንድትችል ጥምቀት ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልልና መጠመቅ ያለበት እንዴት ያለ ሰው መሆኑን መረዳት ያስፈልግሃል።
ጥምቀት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
ጥምቀት ከጋብቻ ጋር ይመሳሰላል። ለአንድ ዓይነት ዝምድና ቃል ኪዳን የሚገባበት ሥነ ሥርዓት ነው። በጋብቻ ረገድ ተጋቢዎቹ ወንድና ሴት ቀደም ብለውም ቢሆን የተቀራረበ ዝምድና አዳብረዋል። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በግል የተስማሙበትን ወደ ጋብቻ ህብረት የመግባት ውሳኔ ለሕዝብ የሚያሳውቁበት ብቻ ነው። ጋብቻቸው ባልና ሚስቱ የሚደሰቱባቸውን አጋጣሚዎች የሚከፍትና ሊሸከሟቸው የሚገቧቸውን ኃላፊነቶች የሚያመጣ ነው።
ሁኔታው ከጥምቀት ጋር በጣም ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ ለእኛ ስላደረጋቸው ፍቅራዊ ነገሮች እንማራለን። እርሱ የሰጠን ሕይወታችንንና ሕይወታችንን ለማቆየት የሚያስፈልገንን ነገር ብቻ ሳይሆን እኛ ኃጢአተኞቹ የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር ዝምድና የምንመሠርትበትንና በገነት ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን መንገድ ይከፍትልን ዘንድ አንድያ ልጁንም ሰጥቶናል። ይህን ሁሉ በምናስብበት ጊዜ አንድ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ አንገፋፋምን?
ምንስ ልናደርግ እንችላለን? የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም [የመከራውን እንጨት አዓት] ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ይነግረናል። (ማቴዎስ 16:24) አዎ፣ አርአያውን ተከትለን የአባቱን የይሖዋን ፍላጎቶች በማገልገል የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ይህንን ለማድረግ ራሳችንን ‘መካድ’፣ ይኸውም የአምላክን ፈቃድ ከራሳችን ፈቃድ ለማስቀደም በፈቃደኝነት መወሰንን ይጠይቃል። ይህም ፈቃዱን ለማድረግ ሕይወታችንን ለእርሱ መስጠትን ወይም መወሰንን ያጠቃልላል። ይህን የፈቃደኝነትና የግል ውሳኔ ለማሳወቅ አንድ ሕዝባዊ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። ለአምላክ ያደረግነውን ውሳኔ በሕዝብ ፊት የምናሳይበት ሥነ ሥርዓት ጥምቀት ነው።
መጠመቅ ያለበት ማን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን ‘እንዲሄዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቁአቸው፣ ያዘዛቸውንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማሯቸው ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉአቸው’ አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በግልጽ እንደሚታየው ከሚጠመቁት ሰዎች የአእምሮና የልብ ብስለት ይፈለግባቸዋል። በአምላክ ቃል ላይ በሚያደርጉት የግል ጥናት አማካኝነት ከቀድሞ አኗኗራቸው ‘ንስሐ የመግባትንና የመመለስን’ አስፈላጊነት መገንዘብ መቻል አለባቸው። (ሥራ 3:19) ከዚያም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን እርሱ የሠራውን የወንጌላዊነት ሥራ የመሥራትን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው የጥምቀት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ነው።
በመንፈሳዊ ዕድገትህ ወደዚህ ደረጃ ደርሰሃልን? አምላክን ለማገልገል ትመኛለህን? ከሆነ በሥራ ምዕራፍ 8 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በጸሎት አስብበት። ስለ መሢሑ የሚገልጹት ትንቢቶች በተብራሩለት ጊዜ አእምሮውንና ልቡን መረመረና “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ። በግልጽ እንደሚታየው የሚከለክለው ምንም ነገር አልነበረም፤ ስለዚህም ተጠመቀ።—ሥራ 8:26-38
በአሁኑ ጊዜም ብዙዎች “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” እያሉ ይጠይቃሉ። በዚህም ምክንያት በ1991 300,945 የሚሆኑ ራሳቸውን የወሰኑ አዲሶች ተጠምቀዋል። ይህም ለሁሉም የይሖዋ ሕዝብ ታላቅ ደስታ አምጥቷል፤ በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎችም ሌሎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ዕድገት እንዲያደርጉና ለጥምቀት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እንዲያሟሉ ለመርዳት ደስ ይላቸዋል።
ይሁን እንጂ አንተ ለመጠመቅ ስትጠይቅ በጉባኤህ ያሉት ሽማግሌዎች እንድትቆይ ሐሳብ ሊሰጡህ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ገና ትንሽ ልጅ ከሆንክ ወላጆችህ እንድትቆይ ሐሳብ ሊያቀርቡልህ ይችላሉ። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? ተስፋ አትቁረጥ። ከልዑሉ አምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት በጣም ከባድ ጉዳይ እንደሆነ አስታውስ። ከፍተኛ የሆኑ የሥነ ምግባር ደረጃዎች መሟላትና መጠበቅ አለባቸው። ስለዚህ የሚቀርብልህን ሐሳብ ተቀብለህ በሙሉ ልብህ ሥራበት። እንድትቆይ የተሰጠው ምክንያት ሙሉ በሙሉ ካልገባህ ዓይነ አፋር ሳትሆን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ እስኪገባህ ድረስ ጠይቅ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የመጠመቅን አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ ሊያመነቱ ወይም እነርሱ እንደሚሉት ሊፈሩ ይችላሉ። አንተስ ከእነርሱ አንዱ ነህን? በእርግጥ ሕይወትህን መወሰንንና መጠመቅን የምታዘገይበት ግልጽ ምክንያቶች ሊኖሩህ ይችላሉ። ነገር ግን ብቃቱን ብታሟላም የምትፈራ ከሆነ ራስህን “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” ብለህ ብትጠይቅ መልካም ነው። ሁኔታህን በጸሎት መርምርና ይሖዋ ከእርሱ ጋር የግል ዝምድና እንድትመሠርት ለሚያቀርብልህ ጥሪ ምላሽ ላለመስጠት የሚያዘገይህ በቂ ምክንያት እንዳለህ ተመልከት።
‘ገና ልጅ ነኝ’
ወጣት ከሆንክ ምናልባት ‘ገና ልጅ ነኝ’ እያልክ ታስብ ይሆናል። ወጣቶች ለክርስቲያን ወላጆቻቸው ታዛዦችና ተገዥዎች እስከሆኑና ቅዱሳን ጽሑፎችን በተቻላቸው መጠን በሥራ ላይ እስካዋሏቸው ድረስ ይሖዋ “የተቀደሱ” እንደሆኑ አድርጎ እንደሚያያቸው ትምክህት ሊኖራቸው ይችላል። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለጻድቅ ወላጆች የሚሰጠው ድጋፍ በእነርሱ ሥር ለሚተዳደሩ ልጆችም እንደሚደርስ ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የልጆች ጥገኝነት መቼ እንደሚያበቃ የዕድሜ ገደብ አይሰጠንም። ስለዚህ ክርስቲያን ወጣቶች ‘መጠመቅ አለብኝን?’ የሚለውን ጥያቄ በጥሞና ሊያስቡበት ያስፈልጋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶችን ‘በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ’ ያበረታታቸዋል። (መክብብ 12:1) በዚህ ረገድ “ገና ብላቴና ሳለ በይሖዋ ፊት ያገለግል የነበረው” የወጣቱ የሳሙኤል ምሳሌ አለን። ከሕፃንነቱ ጀምሮ እናቱና ሴት አያቱ ያስተማሩትን እውነት ወደ ልቡ ያስገባው የጢሞቴዎስ ምሳሌም አለ።—1 ሳሙኤል 2:18፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች ወይም ትንንሽ ልጆች ይሖዋን ለማገልገል ሕይወታቸውን ወስነዋል። በተመሳሳይም የ15 ዓመቱ አኬፉሳ በአገልግሎት ስብሰባ ላይ የተሰጠ አንድ ክፍል ለመጠመቅ ውሳኔ እንዲያደርግ እንደረዳው ተናግሯል። አዩሚ አስር ዓመት ሲሆናት ተጠመቀች። ይሖዋን በእርግጥ ስለምትወደው ልታገለግለው ፈለገች። አሁን 13 ዓመቷ ነው። የእሷ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ይሖዋን በመውደዷ በ12 ዓመቷ ስትጠመቅ የማየት ተሞክሮም አግኝታለች። የአዩሚ ታናሽ ወንድም ሂካሩም በአስር ዓመቱ ተጠምቋል። “አንዳንዶች ገና ልጅ ነህ ብለው ነበር። ይሖዋ ግን እንዴት እንደሚሰማኝ ያውቃል። ባለኝ ሁሉ እሱን ለማገልገል ሕይወቴን ለይሖዋ አንዴ ከወሰንኩ በኋላ ለመጠመቅ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ” በማለት ያስታውሳል።
ከአንዲት ወጣት እህት ተሞክሮ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የወላጆች ምሳሌነትም ወሳኝነት አለው። ይህችን ወጣት እናቷ ለእርሷ፣ ለወንድሟና ለእህቷ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳታስጠናቸው አባቷ ከልክሎ ነበር። ይመታቸውና መጻሕፍቶቻቸውን ያቃጥልባቸው ነበር። ልጆቹ ግን በእናታቸው ጽናትና እምነት ምክንያት ይሖዋን የማገልገልን አስፈላጊነት ሊገነዘቡ ቻሉ። ይህች ወጣት ልጃገረድ በ13 ዓመት ዕድሜዋ ስትጠመቅ ታናሽ ወንድሟና እህቷ ደግሞ ምሳሌነቷን ተከትለዋል።
‘በጣም አርጅቻለሁ’
መዝሙራዊው “ሽማግሌዎችና ልጆች የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ስም ያመስግኑ” ብሏል። (መዝሙር 148:12, 13) አዎ፣ ያረጁ ሰዎችም ከይሖዋ ጎን የመሰለፍን አስፈላጊነት መገንዘብ አለባቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ የሸመገሉ ሰዎች ለውጥ ከማድረግ ወደ መራቅ ያዘነብላሉ። “በስተርጅና ሙሽርና” እንደሚባለው ላረጀ ሰው አዲስ ነገር ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለው ያስባሉ። ይሖዋ ለታማኙ አብርሃም “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ” ብሎ ሲነግረው የ75 ዓመት ዕድሜ ያለው ሽማግሌ እንደነበር አስታውሱ። (ሥራ 7:3፤ ዘፍጥረት 12:1, 4) ሙሴ “አሁንም ና፣ ሕዝቤን የእሥራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ” ብሎ ይሖዋ ሲያዝዘው የ80 ዓመት ዕድሜ ሽማግሌ ነበር። (ዘጸአት 3:10) እነዚህ ሰዎችና ሌሎችም ይሖዋ ፍቅራቸውንና ለእርሱ መወሰናቸውን እንዲያሳዩ በጠየቃቸው ጊዜ በቆየው አኗኗራቸው የተደላደሉ ነበሩ። ለይሖዋ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት አላመነቱም።
በዛሬው ጊዜስ? ሼዙሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመጀመሩ በፊት ለ78 ዓመት ቡድሂስት ሆኖ የኖረ ሽማግሌ ነበር። ቤተሰቡ በገዛ ቤቱ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያጠና እስከ መከልከል ድረስ ተቃወሙት። ከአንድ ዓመት ብቻ በኋላ ራሱን ለይሖዋ የመወሰንን አስፈላጊነት ተገነዘበና ተጠመቀ። ለውጡን ያደረገው ለምን ነበር? “ለብዙ ዓመታት በሐሰት ሃይማኖት ስታለል ቆይቻለሁ፣ ስለዚህ እውነቱን ከይሖዋ መቀበሌን ልቀጥልበት እፈልጋለሁ” ብሏል።
‘ጥምቀት ያድናችኋል’
ጊዜው እያለቀ ነው። የሰዎች ሕይወት፣ የራስህም ሕይወት ጭምር በአደጋ ላይ ነው። ራስህን ለይሖዋ የመወሰንንና ይህንኑም ውሳኔህን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት የምታደርገውን ውሳኔ በጥሞና ልታስብበት የሚገባ አጣዳፊ ነገር ነው። ይህንንም ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጥምቀት . . . አሁን ያድነናል” በማለት አጥብቆ ገልጾታል። በተጨማሪም “የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፣” (ሰውየው ለጥምቀት ከመብቃቱ በፊት ቀደም ብሎ የሰውነቱን እድፍ አስወግዶአልና) “ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ” በማለት አስረድቷል።—1 ጴጥሮስ 3:21
የተጠመቀው ደቀ መዝሙር የይሖዋን መሥፈርቶች በማሟላት በጎ ሕሊና ይኖረዋል። ይሖዋን በማገልገል የቻለውን ሁሉ በማድረግ የአእምሮ ሰላምና እርካታ ያገኛል። (ያዕቆብ 1:25) ከሁሉ በላይ በሚመጣው አዲስ ሥርዓት ከይሖዋ ማለቂያ የሌላቸው በረከቶችን እንደሚያገኝ በእርግጠኝነት ተስፋ ሊያደርግ ይችላል። አንተም ‘መጠመቅ አለብኝን?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ስትሰጥ ይህን ዕጣ እንድታገኝ እንመኛለን።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳሙኤል በይሖዋ ፊት ያገለግል የነበረው ገና ብላቴና ሳለ ጀምሮ ነበር
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ በይሖዋ ሲታዘዝ ዕድሜው 80 ዓመት ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ የተጠመቁ ወጣቶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በአምላክ አዲስ ሥርዓት ማለቂያ የሌላቸው በረከቶችን እንደሚቀበሉ ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ