ደስተኛ እንድትሆን የሚያስፈልግህ ነገር ምንድን ነው?
በሕዝብ የተመረጡ የፖለቲካ ሰዎች የመረጣቸውን ሕዝብ ለማስደሰት የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። በሥራቸው ላይ መቆየታቸው የተመካውም ይህን በማድረጋቸው ነው። ሆኖም አንድ የዜና መጽሔት በፖላንድ ስለሚገኙ ‘የጠበቁትን ስላላገኙ እና ጥላቻ ስላደረባቸው መራጮች’ አትቷል።አንድ ጋዜጠኛ ዩናይትድ ስቴትስ “መደበኛውን የፖለቲካ ሥርዓት በጥርጣሬ በሚያይ” ኅብረተሰብ የተሞላች ናት በማለት አስረድቷል። ሌላው ጸሐፊ ደግሞ “በፈረንሳይ እያደገ ስለመጣው ፖለቲካዊ ግድየለሽነት” ይነገረናል። በመስፋፋት ላይ ያለው እንዲህ ዓይነቱ ግድየለሽነትና ሕዝባዊ ቅሬታ በእነዚህ ሦስት አገሮች ብቻ ተወስኖ የቀረ አለመሆኑ የፖለቲካ ሰዎች ሕዝቦችን ለማስደሰት የሚያደርጉት ጥረት እየከሸፈ መሆኑን ያሳያል።
የሃይማኖት መሪዎችም አሁን ባለው ሕይወትም እንኳ ባይሆን ወደፊት ስለሚገኝ ደስታ ተስፋ ይሰጣሉ። ይህን ተስፋ የሚሰጡት ሰዎች የማትሞት ወይም ወደ ሌላ ፍጡር ልትለወጥ የምትችል ነፍስ አለቻቸው የሚለውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ነው። ይህን ደግሞ ብዙዎች በተለያዩ ምክንቶች የማይቀበሉት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስም በግልጽ ይቃወመዋል። አብያተ ክርስቲያናት የሚሄድባቸው ስለሌለ ጭር ብለዋል፤ የአባላቱ ቁጥርም እየቀነሰ በመምጣት ላይ ነው። ይህም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደስተኛ ለመሆን አስፈላጊው ነገር ሃይማኖት ነው ብለው ማሰባቸውን እንዳቆሙ ያሳያል። — ከዘፍጥረት 2:7,17 እና ከሕዝቅኤል 18:4,20 ጋር አወዳድር።
አልጠግብ ባይ ብር ወዳዶች
በፖለቲካ ወይም በሃይማኖት ደስታ ማግኘት ካልተቻለ ታዲያ ደስታ ከየት ይገኛል? ምናልባት በንግዱ ዓለም ይገኝ ይሆን? የንግዱ ዓለምም ቢሆን ደስታን ላስገኝ እችላለሁ ባይ ነው። የንግዱ ዓለም በማስታወቂያዎቹ አማካኝነት በጣም ባማሩ ቃላት ለማሳመን ምክንያቱን ሲያቀርብ:- ደስታ የሚገኘው ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉትን ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች ሁሉ በማግኘት ነው በማለት ይለፍፋል።
በዚህ መንገድ ደስታን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ይመስላል። ከብዙ ዓመታት በፊት በጀርመን ካሉት ሁለት ቤተሰቦች ውስጥ አንዱ በከባድ የዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ሪፖርት ተደርጎ ነበር። ደ ሳይት የተባለው እውቅ የጀርመን ጋዜጣ “[ከእነዚህ ቤተሰቦች] ብዙዎቹ ከዕዳቸው ነፃ የመሆን ቅንጣት ያህል አጋጣሚ የላቸውም” ብሎ መተንበዩ አያስደንቅም። ቀጥሎም:- “ባንክ ከሚፈቅድላችሁ ገንዘብ በላይ በየጊዜው ማውጣት በጣም ቀላል ነው፤ አንገታችሁን ከዕዳ ሸምቀቆ ማውጣት ግን በጣም ከባድ ነው” በማለት አብራርቷል።
በኢንዱስትሪ በጣም በበለጸጉ ሌሎች አገሮችም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው ዩንቨርሲቲ ሶሽዎሎጂስት የሆኑት ዴቪድ ካፕሎቪትዝ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት ከ20 ሚልዮን እስከ 25 ሚልዮን የሚሆኑ ቤተሰቦች በከባድ ዕዳ ውስጥ እንደተዘፈቁ ገምተው ነበር። እርሳቸውም “ሰዎች በዕዳ ተውጠዋል፤ ይህም ሕይወታቸውን እያበላሸባቸው ነው” ብለዋል።
ይህ ደስታ ነው ሊባል አይቸልም። ሆኖም ሁለቱ (የፖለቲካውና የሃይማኖቱ) ዘርፎች ሊያስገኙት ያልቻሉትን ደስታ የንግዱ ዓለም ያስገኛል ብለን መጠበቅ ይኖርብናልን? ባለ ጠጋ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን በአንድ ወቅት እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር:- “ብርን የሚወድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። — መክብብ 5:10
ቁሳዊ ንብረቶችን በመሰብሰብ ደስታን ለማግኘት መፈለግ የህልም እንጀራ ነው። መብላቱ ያስደስትህ ይሆናል፤ እርካታና ጥጋብ ስለማታገኝ ግን ታዝናለህ።
ደስታ ሊገኝ ይችላል፤ ግን እንዴት?
ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን “ደስተኛው አምላክ” ሲል ጠርቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ደስተኛው አምላክ ሰዎችን በራሱ አምሳል በመፍጠር ደስተኛ የመሆን ችሎታንም ጨምሮ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 1:26) ይሁን እንጂ ሰዎች ደስተኛ መሆናቸው የተመካው አምላክን በማገልገላቸው ላይ መሆኑን መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ የተባረከ [ደስተኛ አዓት] ነው። (መዝሙር 144:15” የ1980 ትርጉም) በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በ110 ቦታዎች ላይ ከሚገኙት “ደስተኛ” እና “ደስታ” ከሚሉት ቃላት ጥቂቶቹን ብንመረምር ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ምንን እንደሚጨምርና እርሱን ማገልገላችን እንዴት እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝልን ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል።
የሚያስፈልጉንን መንፈሳዊ ነገሮች ማወቅ
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) የንግዱ ዓለም ምቾትና ውበት ያላቸውን ነገሮች መግዛት ደስተኛ ለመሆን በቂ ነው ብለን እንድናስብ በማድረግ ሊያስተን ይሞክራል። የንግዱ ዓለም ደስታ ማለት የቤት ውስጥ ኮምፒውተር፣ ቪድዮ ካሜራ፣ ስልክ፣ መኪና፣ ዘመናዊ የስፖርት ዕቃዎችና የፋሽን ልብሶች ሲኖሩን ነው ይለናል። የንግዱ ዓለም የማይነግረን ነገር ቢኖር በዓለም ላይ ያሉ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደስተኞች ለመሆን የግድ እነዚህ ቁሳቁሶች ያላስፈለጓቸው መሆኑን ነው። እነዚህ ቁሳቁሶች ኑሮን ይበልጥ ምቹና ቀላል ሊያደርጉት ቢችሉም ደስታን ለማግኘት ዋነኞቹ መሠረታዊ ነገሮች አይደሉም።
ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ሰዎች እንደ ጳውሎስ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ይላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ለምን እንደዚህ ይላሉ? ምክንያቱም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራን የሚያስፈልጉንን መንፈሳዊ ነገሮች ማሟላታችን ስለሆነ ነው። — ዮሐንስ 17:3
ገንዘብ ካለን ጥሩ ነገሮችን ገዝተን መደሰታችን ስህተት ነውን? ስህትተ ላይሆን ይችላል። ሆኖም ያየነውን ነገር ሁሉ ለማግኘት ወይም ገንዘብ ስላለን ብቻ አንድን ነገር ለመግዛት አለመሞከርን መልመዳችን መንፈሳዊነታችንን ያጠነክረዋል። እንዲህ ከሆነ ምንም እንኳ ከዓለማዊ መመዘኛዎች አንፃር ሲታይ የኢኮኖሚ ሁኔታው ጥሩ እንዳልነበረው እንደ ኢየሱስ ርካታና ደስታ ያልተለየን መሆን እንዴት እንደምንችል እንማራለን። (ማቴዎስ 8:20) እንዲሁም ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ ደስታ የሌለው መሆኑን መናገሩ አልነበረም:- “የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ።” — ፊልጵስዩስ 4:11,12
በይሖዋ መታመን
አንድ ሰው ለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ መሆኑ በአምላክ ለመታመን ፍላጎት ያለው መሆኑን ያሳያል። ንጉሥ ሰሎሞን “በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] የታመነ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” ብሎ እንደገለጸው ደስታ የሚያስገኘው ይህ ነው። — ምሳሌ 16:20
ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በአምላክ ላይ ከመታመን ይልቅ ባላቸው ገንዘብና ንብረት ይበልጥ መመካታቸው የምናየው ነገር አይደለምን? ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ከገንዘብ ይልቅ “በአምላክ እንታመናለን” የሚሉት ቃላት በዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ላይ መቀርጻቸው አለቦታው የገባ መመሪያ ነው።
ገንዘብ ሊገዛቸው ከሚችላቸው ጥሩ ነገሮች ሁሉ አንድም እንኳ ያልጎደለው ንጉሥ ሰሎሞን በቁሳዊ ንብረት መታመን ዘላቂ ደስታ እንደማያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። (መክብብ 5:12–15) በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ባንኩ በመክሰሩ ወይም የገንዘብ ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት ሊጠፋ ይችላል። ያለን ንብረትና ርስትም በከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊወድም ይችላል። የንብረት ዋስትና ውሎች የጠፋውን ገንዘብ በከፊል የሚተኩ ቢሆኑም የደረሰውን ስሜታዊ ጉዳት ለማካካስ ፈጽሞ አይችሉም። አክስዮኖችና ቦንዶች ድንገት በሚደርስ የገበያ ውድቀት ምክንያት ባንድ ሌሊት ዋጋ ሊያጡ ይችላሉ። ዛሬ ያለን ጥሩ ደሞዝ የሚከፈልበት ሥራ እንኳ በብዙ ምክንያቶች ነገ ሊታጣ ይችላል።
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በይሖዋ የሚታመን ሰው ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠቱ ጥበብ መሆኑን ይገነዘባል:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ።” — ማቴዎስ 6:19,20
አንድ ሰው ዘወትር አትረፍርፎ በሚሰጠው ሁሉን በሚችለው አምላክ ከመታመን የበለጠ ታላቅ ደስታና የመተማመን ስሜት እንዲኖረው የሚያደርግ ሌላ ምን ነገር ሊኖር ይቸላል? — መዝሙር 94:14፤ ዕብራውያን 13:5,6
መለኮታዊ ተግሣጽን መቀበል
እውነተኛ ጓደኛ በፍቅር መንፈስ ተገፋፍቶ ቢመክረን እንዲሁም ቢገሥጸንም እንኳ እንቀበለዋለን። የአምላክ አገልጋይ ለነበረው ለኢዮብ ወዳጅ ነኝ ባይ የሆነ አንድ ሰው ራሱን በማጽደቅ “እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” ብሎ ኢዮብን ተናግሮት ነበር። ኤልፋዝ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት ያስተላለፈው ሐሳብ ትክክል ቢሆንም ኢዮብ ከባድ ኃጢአት እንደሠራ መናገሩ ስህተት ነበር። እንዴት ያለ ‘አድካሚ አጽናኝ ነው’! ምንም እንኳ ይሖዋ ቆይቶ ኢዮብን ቢገሥጸውም በፍቅራዊ መንገድ ስለሆነ ኢዮብ ተግሣጹን በትህትና ተቀብሏል፤ ይህም የበለጠ ደስታ እንዲያገኝ አድርጎታል። — ኢዮብ 5:17፤ 16:2፤ 42:6,10–17
በዛሬው ጊዜ ግን አምላክ ኢዮብን እንዳነጋገረው አገልጋዮቹን በቀጥታ አያነጋግርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚገሥጻቸው በቃሉና በመንፈስ በሚመራው ድርጅቱ አማካኝነት ነው። ሥጋዊ ጥቅሞችን የሚያሳድዱ ክርስቲያኖች ግን ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ድርጅት በምታዘጋጃቸው በሁሉም ስብሰባዎች ለመገኘት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ለማጥናት ጊዜው፣ ጥንካሬውና ዝንባሌውም አይኖራቸውም።
አምላክ የሚገሥጸው ሰው እንዲህ ዓይነቱን ተግሳጽ መቀበሉ በምሳሌ 3:11–18 መሠረት ጥበብን ማግኘቱ እንደሆነ ይገነዘባል። “ጥበብን የሚያግኝ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ እንቁም ትከብራለች፣ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፣ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፣ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኮዘባትም ሁሉ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።”
ንጹሕና ሰላም ወዳድ መሆን
ኢየሱስ ደስተኛ ሰዎች “ልበ ንጹሖች” እና “የሚያስተራርቁ [ሰላማውያን አዓት]” እንደሆኑ ተናግሮአል። (ማቴዎስ 5:8,9) ይሁን እንጂ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ የአኗኗር ዘይቤዎችን እንድንከተል በሚገፋፋው ዓለም ራስ ወዳድነትና ንጹሕ ያልሆኑ ምኞቶች በልባችን ውስጥ በቀላሉ ሥር ሊሰድዱ ይችላሉ። በመለኮታዊ ጥበብ ካልተመራን በስተቀር ከሌሎች ጋር ያለንን ሰላማዊ ዝምድና በሚያጠፋና አጠያያቂ በሆነ መንገድ ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ብልጽግና ለማግኘት በመፈለግ ልንስት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ያለምክንያት አይደለም:- “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” — 1 ጢሞቴዎስ 6:10
ገንዘብን መውደድ የርካታ ማጣት፣ የምስጋና ቢስነትና የስግብግብነት ስሜቶች በውስጣችን እንዲያድጉ የሚያደርገውን ራስን ከሌሎች በላይ ከፍ አድርጎ የመመልከትን ዝንባሌ ያስከትላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው የተሳሳተ መንፈስ በውስጣቸው እንዳያድግ ለመከላከል ገንዘብ ነክ የሆኑ ትልልቅ ውሳኔዎችን ከመወሰናቸው በፊት ራሳቸውን እንዲህ እያሉ ይጠይቃሉ:- በእርግጥ ያስፈልገኛልን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውድ የሆኑ ዕቃዎችን መግዛት ሳያስፈልጋቸው መኖር ከቻሉ እኔስ መግዛት ያስፈልገኛልን? ወይም ጊዜን የሚያሟጥጥና ከፍተኛ ደሞዝ ያለው ሥራ መሥራት ሳያስፈልጋቸው ከኖሩ እኔስ መሥራት ያስፈልገኛልን? ምናልባትም ገንዘቤንና ጊዜዬን ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በመደገፍ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ወይም ከእኔ ያነሰ ኑሮ ያላቸውን ሰዎች በመርዳት በተሻለ መንገድ ልጠቀምበት እችል ይሆንን?
ጽናትን ማሳየት
ኢዮብ ጽናት እንዲያሳይ ከተገደደባቸው ፈተናዎች አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ነበር። (ኢዮብ 1:14–17) የእሱ ምሳሌ እንደሚያሳየው እያንዳንዱ የኑሮ ዘርፍ ጽናትን ይጠይቃል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በስደት መጽናት አስፈልጓቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ስህተት የሚገፋፋ ፈተናን፣ ሌሎቹ ደግሞ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት በማያስችሉ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሥር ያለውን ኑሮ መቋቋም አለባቸው። ሆኖም ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ ኢዮብን ጠቅሶ “የጸኑትን ብፁአን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን” ብሎ እንደጻፈው ሁሉ በማንኛውም ፈተና መጽናት ከይሖዋ ሽልማት የሚያስገኝ ይሆናል። — ያዕቆብ 5:11
የኢኮኖሚ ሁኔታዎቻችንን ለማሻሻል ሲባል መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ችላ ማለት ለጊዜው ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን በመጠኑ ሊያቃልልን ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ይህንን ማድረጋችን በአምላክ መንግሥት ሥር የኢኮኖሚ ችግር ለዘለቄታው እንደሚወገድ ያለንን አመለካከት ብሩህ አድርገን እንድንይዝ ሊረዳን ይችላልን? ልንለፋለትስ የሚገባው ጉዳይ ነውን? — 2 ቆሮንቶስ 4:18
አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስታ ማግኘት
ሰዎች ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ይሖዋ የሚሰጠውን ሐሳብ አንዳንድ ሰዎች በግልጽ ይቃወማሉ። ለዘለቄታው ጥቅም የሚያስገኘውንና ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር አቅልለው ስለሚመለከቱ አምላክ የሚሰጠውን ምክር ቢከተሉ አሁኑኑ በግል ጥቅም እንደሚያገኙ አይታያቸውም። በቁሳዊ ነገሮች መታመን ከንቱና ብስጭት የሚስከትል መሆኑን መገንዘብ ተስኗቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ እንዲህ ሲል በትክክል ጠይቋል:- “ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?” (መክብብ 5:11፤ በተጨማሪም መክብብ 2:4–11ን እና 7:12ን ተመልከት።) የሰው ፍላጎት ቶሎ ይለወጣል፤ እኛም ቢኖሩን ጥሩ ነው ብለን የገዛናቸው ነገሮች ከጊዜ በኋላ መኖራቸውንም እንረሳለን።
አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ ‘ከማን አንሼ’ የሚለው አስተሳሰብ በእሱም ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት በፍጹም አይፈቅድም። የሰው ሰውነቱ የሚለካው በማንነቱ እንጂ ባሉት ነገሮች እንዳልሆነ ያውቃል። እውነተኛ ደስታ እንዲያገኝ የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን ስለመሆናቸው በአእምሮው ውስጥ ጥርጣሬ አያድርበትም። ከይሖዋ ጋር ባለው ጥሩ ዝምድና ይደሰታል፤ በይሖዋ አገልግሎትም ሥራ የበዛለት በመሆን ይቀጥላል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቁሳዊ ነግሮች ብቻቸውን ዘላቂ ደስታ ሊያስገኙ በፍጹም አይችሉም
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው’ ይላል