በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘት የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
በደቡብ አሜሪካ የምትኖረው ሮዛሪዮ ከኤልሳቤት ጋር ለብዙ ወራት መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና ነበር። ሮዛሪዮ ስለ አምላክ መንግሥትና ይህች መንግሥት ገነታዊ ሁኔታዎችን እንዴት በምድር ላይ እንደምታመጣ ማወቋ በጣም አስደስቷት ነበር። ይሁን እንጂ ኤልሳቤት በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ስትጋብዛት ግን አትመጣም። የጉባኤ ስብሰባዎች ሳትሄድ ቤቷ ሆና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በሥራ ላይ ማዋል የምትችል መስሎ ተሰምቷት ነበር። አንተስ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በእርግጥ ጠቃሚ ስለመሆናቸው አስበህ ታውቃለህን? አምላክ ሕዝቦቹ እንዲሰበሰቡ ዝግጅት ያደረገው ለምንድን ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች የተለዩ ስለነበሩ ትክክለኛ የሆነ ቅርርብ ማበጀቱ ለሕይወታቸው መዳን የግድ አስፈላጊ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንድ የጥንት ክርስቲያኖች ጉባኤ ‘በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ፣ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው ሆናችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ’ ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:15) በተለይ በይሁዳ የነበሩ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያቶች ነበሩባቸው። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የጻፈው ለእነሱ ነበር:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉት።” (ዕብራውያን 10:24, 25) አንድ ላይ በመሰብሰብ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የምንነቃቃው እንዴት ነው?
ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንደ ብረት “የሚሳሳሉት” እንዴት ነው?
“ማነቃቃት” ተብሎ የተተረጎመው ጳውሎስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ብረትን መሳል” ማለት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስለዋል” በማለት ክርስቲያኖች እንዴት እርስ በርሳቸው እንደሚሳሳሉ ያብራራል። (ምሳሌ 27:17፤ መክብብ 10:10) እኛ ዘወትር መሳል እንደሚያስፈልገው መሣሪያ ነን። ለይሖዋ ፍቅር ማሳየትና በእምነታችን ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ማለት ከዓለም የተለዩ መሆን ማለት ስለሆነ ዘወትር ከአብዛኛው ሰው የተለየ መንገድ መከተል አለብን ማለት ነው።
ዘወትር ከዓለም የተለየን ለመሆን የምናደርገው ጥረት ለመልካም ሥራ ያለንን ቅንዓት ሊያዶለድመው ይችላል። ነገር ግን ይሖዋን ከሚያፈቅሩ ሰዎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ እርስ በርሳችን እንሳሳላለን። ይህም ማለት ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንነቃቃለን። በሌላ በኩል ግን ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ይበልጥ ስለ ራሳችን ወደማሰብ እናዘነብላለን። ብቻችንን ስንሆን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ፣ የራስ ወዳድነት ወይም የሞኝነት አስተሳሰቦች ወደ አእምሮአችን ሊመጡ ይችላሉ። “መለየት የሚወድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1) ለዚህ ነው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ከተማ ለሚገኘው ጉባኤ “ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፣ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው” ሲል የጻፈው። — 1 ተሰሎንቄ 5:11
ሮዛሪዮ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማጥናቷን ከጨረሰችም በኋላ በጉባኤ ከመሰብሰብ ወደኋላ ትል ነበር። ስለዚህ ኤልሳቤት ከዚህ የበለጠ ልትረዳት ስላልቻለች እሷ ጋ መሄዷን አቆመች። ከተወሰኑ ወራት በኋላ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሮዛሪዮን ሄዶ ጎበኛትና “ምንም እንኳ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የሚበላው ጥሩ ምግብ እውጭ ቢያገኝም እቤት አንድ ላይ ባለመብላታቸው ሁሉም የቤተሰቡ አባል ምን የሚቀርበት ይመስልሻል?” ብሎ ጠየቃት። ሮዛሪዮም “ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ መጫወት ይቀርበታል” ስትል መለሰች። ነጥቡ ገባትና አዘውትራ ወደ ስብሰባዎች መምጣት ጀመረች። በጣም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘችው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ትገኛለች።
ሌሎች ሰዎች አንተ በምታምንባቸው ነገሮች እንደሚያምኑ እምነታቸውን ሲገልጹ መስማትና ይህ እምነት ሕይወታቸውን እንዴት እንደለወጠው ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው። ጳውሎስ ይህንን ከግሉ ተሞክሮ ያውቅ ነበር። በሮም ይገኝ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው።” (ሮሜ 1:11, 12) እንዲያውም ጳውሎስ ወደ ሮም ለመምጣት የቻለው ከዚያ ብዙ ዓመት ቆይቶ ነው። የመጣውም የሮማውያን እስረኛ ሆኖ ነው። ነገር ግን ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ከከተማዋ በእግራቸው ተጉዘው ሊቀበሏቸው ከሮም የመጡትን ወንድሞች ሲያይ “ጳውሎስ . . . እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።” — ሥራ 28:15
በአስጨናቂ ጊዜያት ላይ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት
ጳውሎስ በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን እንዳይተዉ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ነበር። “ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” ሲል አክሎ የተናገራቸው ቃላት ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው። (ዕብራውያን 10:25) የይሖዋ ምስክሮች 1914 የዚህ ዓለም የፍጻሜ ዘመን የሚጀምርበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆኑንና “እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች የሚጠፉበት ቀንና የፍርድ ቀን” መቅረቡን ከቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ ማስረጃዎችን ሳያቋርጡ ሲያመለክቱ ቆይተዋል። (2 ጴጥሮስ 3:7) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ በሚለው መሠረት የመጨረሻው ቀን ሲጀምር ዲያብሎስ ከሰማይ በተወረወረበት ጊዜ በጣም እንደተቆጣና “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ” እንደመጣ ይናገራል። (ራእይ 12:7–17) ስለዚህ በተለይ አሁን የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው። ከምንጊዜውም የበለጠ ከእምነት ጓደኞቻችን ጋር መሰብሰብ ያስፈልገናል። ስብሰባዎች የዲያብሎስን ጥቃቶች ለመመከትና እምነታችንንና ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማጠንከር ይረዱናል።
ለአምላክ ያለን ፍቅርና እምነት አንዴ ከተገነቡ ቋሚ ሆነው እንደሚቀጥሉት ግንቦች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ዘወትር ሲመገቡ እያደጉ እንደሚሄዱና ከተራቡ ደግሞ እንደሚጠወልጉና እንደሚሞቱት ሕይወት እንዳላቸው ነገሮች ናቸው። ለዚህም ነው ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማጠንከር ዘወትር መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርበው። ሁላችንም ይህ ዓይነቱ ምግብ ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ ከአምላክ ድርጅትና ድርጅቱ ካዘጋጃቸው ስብሰባዎች ውጭ ይህን ምግብ ከየት ልናገኝ እንችላለን? ከየትም ልናገኘው አንችልም። — ዘዳግም 32:2፤ ማቴዎስ 4:4፤ 5:3
ኢየሱስ ክርስቲያን ጉባኤን እንዴት እንደሚመግብ እንድናውቅ ሊረዳን የሚችል አንድ ጥያቄ አስቀምጧል። እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው” (ማቴዎስ 24:45, 46) ክርስቶስ በመጀመሪያ መቶ ዘመን ተከታዮቹን እንዲመግብ የሾመው ማንን ነበር? በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ተመልሶ ሲመጣ በተግባሩ የታመነ ሆኖ ሲመግብ ያገኘውስ ማንን ነው? ይህን ሁሉ መቶ ዘመን በሕይወት የኖረ ሰው እንደሌለ ግልጽ ነው። በቅድመ ክርስትና ዘመን የእስራኤል ሕዝብ የአምላክ አገልጋይ እንደነበረ ሁሉ ባሪያው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው ጉባኤ እንደሆነ ማስረጃው ይጠቁማል። (ኢሳይያስ 43:10) አዎ፣ ኢየሱስ በዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ አካል አማካኝነት መንፈሳዊ ምግባችንን ያቀርብልናል። ዛሬ ይህ አካል በየአካባቢው ባሉት የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ያስተላልፋል።
ኢየሱስ መንፈሳዊ ምግብ የሚያስተላልፍበት መሥመር በሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚከተለው ተደርጎ ተገልጿል:- “‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ወንዶችንም ስጦታ አድርጎ ሰጠ።’ . . . እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደ ሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፣ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” — ኤፌሶን 4:8, 11–13
እነዚህ ‘ስጦታ ተደርገው የተሰጡ ወንዶች’ ወንድሞችን የሚገነቡት በየአካባቢው ባሉት ጉባኤዎች ማለትም በስብሰባዎች ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንጾኪያ “ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው።” (ሥራ 15:32) ዛሬም በተመሳሳይ መንፈሳዊ ብቃት ባላቸው ወንዶች የሚቀርቡት ንግግሮች እምነታችን እንዳይጠወልግ ወይም እንዳይቀዘቅዝ በሚገባ ይመግቡታል።
ምንም እንኳ ገና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ባንጀምርም በአንዱ የጉባኤ አባል በሚደረግልን የግል እርዳታ አማካኝነት ጥሩ እድገት አድርገን ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው “ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም” በማለት የመጀመሪያዎቹን ትምህርቶች የሚያስተምራችሁ ሰው የሚያስፈልግበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:12) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ዘወትር ወተት እየተመገበ ሊቀር አይችልም። ክርስያቲያናዊ ስብሰባዎች ለአምላክ ያለንን ፍቅርና እምነት ሕያው አድርገው ለማቆየት እንዲሁም “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉን ተግባራዊ እርዳታ የሚሰጥ የማያቋርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ያቀርባሉ። (ሥራ 20:27) ይህም “ከወተት” የሚበልጥ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራችው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው” ይላል። (ዕብራውያን 5:14) በስብሰባዎች ላይ ምናልባትም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረታዊ ጥናት ክፍል ያልሆኑ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ይብራራሉ። ለምሳሌ ያህል በጣም አስፈላጊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥቅስ በጥቅስ ይጠናሉ እንዲሁም በአኗኗራችን እንዴት አምላክን ልንመስለው እንደምንችል ጥልቀት ያለው ውይይት ይደረጋል።
ከኋላህ እንዳለ ድምጽ የሆኑት የይሖዋ ማሳሰቢያዎች
በእነዚህ የጉባኤ ጥናቶች አማካኝነት ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደሚኖርብን ይሖዋ ዘወትር ያሳስበናል። እነዚህ ማሳሰቢያዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ ማሳሰቢያዎች ከሌሉ በቀላሉ ወደ ራስ ወዳድነት፣ ወደ ኩራትና ወደ ስግብግብነት እናዘነብላለን። ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው ማሳሰቢያዎች ከሌሎች ሰዎችና ከራሱ ከአምላክ ጋር የተሳካ ግንኙነት እንድናደርግ ይረዱናል። የመዝሙር 119:59 ጸሐፊ “ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፣ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ” ሲል ተናግሯል።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር ስንገኝ “አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ” የሚለውን በኢሳይያስ አማካኝነት የተነገረው የይሖዋ ትንቢት ሲፈጸም ትመለከታለህ። ይሖዋ እድገታችንን ይመለከታል፤ የተሳሳተ እርምጃ ከወሰድንም በፍቅር ያስተካክለናል። (ኢሳይያስ 30:20, 21፤ ገላትያ 6:1) ከዚህ የበለጠ እርዳታም እንኳን ይሰጠናል።
በጉባኤ አማካኝነት መንፈስ ቅዱስን መቀበል
ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በሕዝቦቹ ላይ በሚፈሰው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ማበረታቻ እናገኛለን። (1 ጴጥሮስ 4:14) ከዚህም በተጨማሪ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሾሙ ናቸው። (ሥራ 20:28) ይህ ከአምላክ የሚገኘው አንቀሳቃሽ ኃይል በአንድ ክርስቲያን ላይ ኃይለኛ ግፊት ያሳድራል። መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው” ይላል። (ገላትያ 5:22, 23) በተጨማሪም በአምላክ ድርጅት አማካኝነት የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ ለሚያፈቅሩት ሰዎች ወደፊት ምን እንዳስቀመጠላቸው ግልጽ የሆነ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል። ጳውሎስ የዚህ ሥርዓት ታላላቅ ሰዎች የአምላክን ዓላማ እንደማይረዱት ከገለጸ በኋላ “ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” ሲል ጽፏል። — 1 ቆሮንቶስ 2:8–10
ጉባኤ እምነት የሚያጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ከመስጠቱ በተጨማሪ በጉባኤው ዋና ተግባር ለመካፈል ለሚፈልጉ ስልጠና ይሰጣል። ያስ ምንድን ነው?
በጉባኤ አማካኝነት የሚሰጥ ስልጠና
የክርስቲያን ጉባኤ እንዲያው ሰዎች በመዝናናት የሚደሰቱበትና የተሻለ ኑሮ ለመኖር እርስ በርስ የሚበረታቱበት ማኅበራዊ ክበብ አይደለም። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ላሉት ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያደርስ ጉባኤን አዟል። (ሥራ 1:8፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ጉባኤው በ33 እዘአ በጴንጠቆስጤ ዕለት ከተመሠረተ ጀምሮ የሰባኪዎች ድርጅት ሆኖ ቆይቷል። (ሥራ 2:4) ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ለሰው ለመናገር ሞክረህ ነገር ግን ልታሳምነው ሳትችል የቀረህበት ጊዜ አለን? የጉባኤ ስብሰባዎች የማስተማር ጥበብ በተመለከተ በግል ስልጠና ይሰጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን በማጥናት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለማስረዳት የጋራ መሠረት እንዴት እንደምንመሠርትና ምክንያታዊ የሆነ ሐሳብ ለማቅረብ በቅዱሳን ጽሑፎች እንዴት እንደምንጠቀም እንማራለን። ጥያቄዎችንና ምሳሌዎችን በመጠቀም ሌሎች እንዴት ምክንያቱን እንዲያገናዝቡት እንደምናደርግ እንማራለን። እንዲህ ዓይነቱ ችሎታ ሌላ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማር በመርዳት የሚገኘውን በቃል የማይነገር ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።
በዚህ በሁከት በተሞላና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ ትክክለኛ መጠለያ ነው። ምንም እንኳ ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የተገነባ ቢሆንም ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት ቦታ ነው። ስለዚህ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ በመገኘት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው። . . . በዚያ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት እውነተኝነት አንተ ራስህ ተመልከት። — መዝሙር 133:1, 3